ከበቀለ ደገፋ Bekeledegefa5@gmail.com

ባለፉት 27 የህወሃት አገዛዝ አመታት በፈጣን የቁልቁለት መንገድ እየተንደረደርንና ብዙ መልካም የለውጥ አጋጣሚዎች እየመከኑ አሁን ከምንገኝበት የመከራ አረንቋ ውስጥ ገብተናል። የልማትና የዲሞክራሲው ችግር እንደተጠበቀ ሆኖ እንደ ሀገር የመቀጠል ህልውናችንም አደጋ ውስጥ ወድቋል። በአንድ በኩል የተስፋ ጭላንጭሎችና ተስፋን በማጥፋት የሚኖር ስርአት ፤ በሌላ በኩል ሀገርን የማዳን ከፍተኛ የህዝብ እንቅስቅሴና ይህንን የሚመራ ሀይል አለመኖር ተደቅነው ስርአቱ ከከተተን አረንቋ የመውጣትና የመስጠም አስጨናቂ ግርታ ውስጥ እንገኛለን።

የችግሩ መሰረታዊ ምንጭ

እንደሚታወቀው የዲሞክራሲ እጦትም ሆነ አምባገነናዊ ስርአቶች ለኛ ብርቃችን አይደሉም። ይልቁንም ይህ ስርአት የደቀነብን ታሪካዊ አደጋ የህልውናና እንደሀገር የመኖርና ያለመኖር ነው። መፍትሄ ማምጣት ከተፈለገም ችግሩን ከምንጩ መረዳት ይጠይቃል። ለተጋረጠብን የህልውና አደጋ የዳረገን በአንዳንድ የ1960ዎቹ ተራማጅ ነን ባይ አብዮተኞች ተጠንስሶ በህወሃት እውን የሆነው የዘር ፓለቲካ መሆኑ በተግባር እየታየ ያለ ሀቅ ይመስለኛል። እነዋለልኝ ሳይረዱ የኮረጁትን ሰልቫጅ የዘር ፓለቲካ ለኢትዮጵያ ይሆናታል ብለው ካስተዋወቁበት ጊዜ ጀምሮ በማንነት መብትና ጥያቄ ስም እየታመስን እንገኛለን። መለስና ህወሀት ደግሞ ይህንን ሀገር በታኝ አስተሳሰብ በህገመንግስት ነድፈው ፣ በመዋቅር አደራጅተው ፣ በፓሊሲና በጉልበት ተግባራዊ ለማደረግ 27 አመታት ለፍተው እዚህ አድርሰውናል።

የተጋረጠብን ታሪካዊ አደጋ ምንጭ የዘር ፓለቲካን መሰረት ያደረገው ይህ ስርአት ነው። ያለንበትን ሁኔታ የበለጠ የከፋ የሚያደርገው ግን ይህ አስተሳሰብና አካሄድ ከዚህ በላይ ከተገፋ ሊያስከትል የሚችለው ሀገራዊ ጉዳትና መዘዝ በንድፈ ሀሳብ ደረጃ ሳይሆን በተግባር ግልጽ እየሆነ መምጣቱ ነው። አሁን የእሳቱ ወላፈን እያቃጠለንና ጭሱም እያፈነን ነው። ከዚህ በላይ ቢቀጥል ሁላችንንም እንደሚያጠፋን በተጨባጭ እያረጋገጥን ነው።

የገዢው ቡድን ምላሽ

የዘር ፓለቲካ፥ ምናልባትም ለሌሎች ሀገሮች ትምህርት በሚሆን መልኩ፥ በኢትዮጵያ ምድር ሊሰራ የማይችልና በተጨባጭ ተፈትሾ የወደቀ ፕሮጀችት መሆኑን እያየን ነው። ይህ የዘር ፓለቲካ ሀገራችንን ገፍቶ ገደል አፋፍ ላይ እንዳደረሳት የኢትዮጵያ ህዝብም ሆነ አንዳንድ የራሱ የገዢው ቡድን ባለስልጣናት ጭምር የተገነዘቡት ሀቅ ሆኗል። ለዚህም ይመስላል በተለይ ጥቂት የኦህዴድ አመራሮች በወሬ ደረጃም ቢሆን ፈጥነው የትርክት ለውጥ ያደረጉትና የህዝብ ቅቡልነትን እያካበቱ የመጡት። በተቃራኒው በሚጠበቅ ሁኔታ ህወሃት ይህንን አደጋ የመረዳት ከፍተኛ ችግር ውስጥ እየተጨማለቀ ይገኛል። ፍላጎት ማጣት ብቻ ሳይሆን ሁኔታዎችን የመረዳትና እራሳቸው ይደግፈናል ለሚሉት ህዝብ እንኳን የሚበጅ መፍትሄ የማየት አቅም ማጣት እየተጫወተባቸው ነው።

አብዛኞቹ የህወሃት ባለስልጣናት ጊዜውን የሚዋጅ መንገድ ለመከተል አዕምሯዊ ብቃት ላይ የሚገኙ አይመስልም። አንዳዶቹ ደግሞ መለስ የቀረጸው የዘር ፓለቲካ ፕሮጀክት ከፈጣሪ የመጣ ቃል ይመስል ከራሳቸውም ህይወት በላይ አግዝፈው ያዩታል። የሰው ልጅ ከፕሮጀክት በላይ መሆኑን ፣ የፓለቲካ ድርጅት የአመለካከት ለውጥ እንደሚያደርግ እንዲሁም ህገመንግስት ሊሻሻል ወይም ሊለወጥ የሚችል ነገር መሆኑን የሚገነዘቡ ሰዎች አይደሉም። አሁን ያለው የዘር ፕሮጀክት ከተከለሰ አብረው የሚያልቅላቸውና ባለራእዩ መሪያቸውም የሚያዝንባቸው ይመስላቸዋል።

ሌሎቹ የህወሃት ሰዎችና ደጋፊዎቻቸው ደግሞ ለ27 አመታት በዘረፉት ሀብትና ባካበቱት ስልጣን አዕምሯቸው ተደፍኖ ማን አባቱ ይነካናል በሚል እብሪት ተወጥረዋል። እንዲያውም ጥቂቶቹ ካስፈለገ እንገነጠላለን የሚል አስተሳሰቡ ከላሸቀ የመንደር ጎረምሳ ጭንቅላት የሚመጣ አይነት አስተያየት በመስጠት ላይ ናቸው። የአስቸኳይ ጊዜ አውጁ ታዲይ የዚህ የህወሃት መበስበስ መገለጫና ውጤት ነው።
በህዝብ ትግልና በኦህዴድ ተራማጆች ታንቆ በሺዎች የሚቆጠሩ እስረኞችን የለቀቀው ህወሃት (ከእስር ያልተለቀቁት ለቁጥር ይታክታሉ) አሁንም የአፈጻጸም ችግር ነው እንጂ የዘር ፓለቲካችን እንከን የለውም ይላል። ለዚህም መፍትሄ ብሎ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ አሁንም እያደባና ሁኔታዎችን እያመቻቸ ጉልበቱን አጠናክሮ ለመቆም ያስባል። በሌላ በኩል ችግሩን ቢገነዘብም ተመጣጣኝ መፍትሄ ለማሰብ የአቅም ችግር ያለበት ድርጅት እንደሆነ አይተናል።

የመፍትሄ አቅጣጫ

ሀገራችን አሁን ካለችበት ምጥ ውጤቱ ባማረ መልኩ እንድትገላገል የሁላችንም ርብርብር እንደሚያስፈልጋት አጠያያቂ ጉዳይ አይደለም። በመጀመሪያ ደረጃ አሁን እየታየ ያለውን የለውጥ እንቅስቃሴ በማፋፋም ትልቁን ሚና እየተጫወተ ያለው ህዝቡ ራሱ ነው። ህዝቡ የህይወት ዋጋ ጭምር እየከፈለ ህወሃትን እንዲያፈገፍግ አድርጎታል። በህዝቡ ግፊት እንጂ ወያኔ እስረኞችን የመፍታት ሃሳብ እንዳልነበረው አፈታታቸው ላይ ሳይቀር ያሳይ በነበረው ማንገራገርና ውዥንብር መገንዘብ ይቻላል። አሁንም ህዝቡ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሚል የተደቀነበትን ፍጹም አፈና በተለያየ ዘዴ ሰብሮ ህወሃትን ራቁቱን ማስቀረት ይኖርበታል። ሰሞኑን በኦሮሚያ ክልል የተደረገው የ3ቀናት የስራ ማቆም አድማ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተብዬው ቀልድ መሆኑንና ህዝባችን ከቁብ እንደማይቆጥረው በተግባር አሳይቷል። ይህቺን የህወሃት የመጨረሻ ካርድ የኢትዮጵያ ህዝብ ነጥቆ ማክሸፍ ከቻለ፥ ህወሃት ራቁቱን ይቀራል። ምናልባት የዛን ጊዜ ስለድርድርና እርቅ አስፈላጊነት ይገነዘብ ይሆናል።

በሁለተኛ ደረጃ እውነተኛ የተቃዋሚ ፓርቲዎች ህዝቡን አቅጣጫ በማሳየትና ወጥ የሆነ እንቅስቃሴ እንዲያደርግ በማገዝ ከፍተኛ ሚና መጫወት የሚጠበቅባቸው ጊዜ አሁን ነው። በተለይም እንደ አርበኞች ግንቦት ሰባት ያሉ ህብረ ብሄራዊና ቆርጠው እስከ ትጥቅ ትግል ድረስ ለማድረግ የወሰኑ ድርጅቶች ይሄንን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማክሸፍ ረገድ ላቅ ያለ ሚና መጫወት ያለባቸው ይመስለኛል። በዚህ ወቅት የድርሻውንና የአቅሙን ማድረግ ያልቻለ ድርጅት ነገ መሬት ሲስተካከል እጁን ታጥቦ ለስልጣን ቢመጣ ያስተዛዝባል።

ኢትዮጵያዊ ሚዲያዎችም ከፍተኛ ድርሻ አላቸው ብዬ አምናለሁ። በአሁኑ ወቅት ሀገራችንና ህዝባችንን የሚታደግልን ብቸኛው መፍትሄ ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነት መሆኑ ግልጽ እየሆነ መጥቷል። ኢትዮጵያዊነት