(ዳዊት ከበደ ወየሳ እንደዘገበው) የኢትዮጵያ ደቡብ ጠረፍ ላይ በምትገኘው የሞያሌ ከተማ፤ ቅዳሜ እለት የደረሰው ግድያ እጅግ ሰቅጣጭ ነበር። የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ምክንያት በማድረግ፤ በተለይ በኦሮሚያ ክልል የተሰማሩ የመከላከያ ሰራዊት አባላት እየፈጸሙ ካሉት በደሎች መካከል ሰላማዊውን ህዝብ ያለምንም ምክንያት መግደል አደኛው ተልዕኮ ሆኗል። እንዲህ አይነቱ ግድያ ለሚቀጥሉት ስድስት ወራት፤ በህግ ሽፋን… በየትኛውም የአገሪቱ ክፍል ሊፈጸም እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ፤ ብዙዎች ይህንን የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ መቃወማቸው የሚታወስ ነው።
በህዝቡ ዘንድ የተፈራው እየደረሰ ነው። በኦሮሚያ የተሰማሩት ደም የጠማቸው የሰራዊቱ አባላት የጅምላ ግድያቸውን በሞያሌ ከተማ ፈጽመዋል። የሞያሌ ጎዳና በወጣቶች ደም ታጥባለች። ይህ የሆነው ደግሞ፤ ምንም አይነት ረብሻ ባልተደረገበት ሁኔታ ውስጥ መሆኑ ብዙዎችን አሳዝኗል። የአይን ምስክሮች እንደገለጹት ከሆነ፤ ሰራዊቱን ሊያናድድ ወይም ግድያውን ሊያስፈጽም የሚችል ምንም አይነት ምክንያት አልነበረም።
ቅዳሜ እለት በሞያሌ ምንም አይነት ሰላማዊ ሰልፍ አልተደረገም፤ መንገድ አልተዘጋም፤ ምንም ረብሻ አልነበረም። ነገር ግን በአንድ ካፌ በረንዳ ላይ ወጣቶች እንደወትሯቸው ሰብሰብ ብለው ቡና እየጠጡ የሚያወሩ ወጣቶች ላይ ተኩስ ተከፈተ። የመከላከያ ሰራዊት አባላቱ እነዚህ ወጣቶች ላይ በማነጣጠር መተኮስ እና መግደል ጀመሩ። የሞያሌ ከተማ በተኩስ እሩምታ ተሸበረች። ከተኩሱ ለማምለጥ የሚሮጡ ወጣቶች ጭምር፤ ከጀርባቸው በተተኮሰ ጥይት ተገደሉ፤ ብዙዎችም ቆሰሉ።
የዚያኑ ቀን ብዙ ወጣቶች ኬላውን ተሻግረው ወደ ኬንያ መግባት ጀመሩ። በመቀጠል የከተማዋ መብራት እንዲጠፋ ተደረገ። ምሽቱን 9 ሰዎች እና በርካታ ሰዎች በጥይት መቁሰላቸው በኦሮሚያ ቴሌቪዥን ተነገረ። ለሟቾቹም መጽናናትን እንደሚመኙ ተገለጸ። ዛሬ ጠዋት ደግሞ
የኦሮሚያ ምክትል ፕሬዘዳንት ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ግድያውን የፈጸሙት አምስት የመከላከያ ሰራዊት አባላት እና በሞያሌ የተሰማራውን ሻለቃ የሚመራው ወታደራዊ መኮንን፤ ትጥቃቸውን እንዲፈቱ ተደርጎ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጸዋል። አያይዘውም “እነዚህ የሰራዊቱ አባላት ለፍርድ ይቀርባሉ” ብለዋል።
የአስቸኳይ ግዜውን አዋጅ በፓርላማ ለማስጸደቅ፤ የውሸት ቁጥር ሰጥተው “2/3ኛ ሞልቷል” ያሉት አባዱላ፤ ምሽቱን “ስቆጥር ተሳስቼ ነው።” ብለው ነበር። በሚገርም ሁኔታ በዛሬው እለት የኢህአዴግ ቃል አቀባዮች፤ “ግድያው የተፈጸመው በስህተት ነው!” ሲሉ መግለጫ መስጠታቸው የሚያሳፍር ክስተት ሆኖ አልፏል።
ከአስቸኳይ ግዜ አዋጁ ቀደም ብሎ፤ የኦሮሚያ ፕሬዘዳንት የሆኑት አቶ ለማ መገርሳ፤ የኦሮሚያ ፖሊስ ሰራዊት የህዝቡን ደህንነት ለመከላከል የሚያደርገውን ጥረት አድንቀው፤ ፖሊስ ከህዝቡ ጎን እንዲቆም ጥሪ ማድረጋቸው የሚታወስ ነው። አሁንም የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን ሽፋን በማድረግ፤ በየትኛውም የአገሪቱ ክልል፤ እንደዚህ አይነት አስከፊ በደል እና ግፍ የሚፈጽሙ የሰራዊቱ አባላት ላይ እርምጃ መወሰዱ የኢህአዴግ ደጋፊዎችን የሚያናድደውን ያህል፤ ሌሎች ደግሞ እርምጃው አግባብ መሆኑን ይስማሙበታል።

