ይህችን አነስተኛ ጽሁፍ እንዳዘጋጅ ያነሳሳኝ እንደወትሮየ የሀገራችንና የህዝባችንን ውሎ አዳር እንደሚያስጨንቀው ማንኛውም ኢትዮጵያዊ አዲስ ነገር ካለ ብየ ሳፈላልግ „የአማራ ፖለቲካ ሃይሎችን ወደ አንድነት ለማምጣት የተደረገ ጥረት ሂደትና ውጤቱ!“ በሚል ርእስ በጥረት አድራጊዎቹ ተጽፋ በዘ- ሐበሻ ድህረ ገጽ የወጣችውን ጽሑፍ በማንበቤ ነው።

ከሁሉ በማስቀደም አገራችን ውስጥ እየተካሔድ ያለው እጅግ በጣም አስቸጋሪና ውጤቱን ለመተንበይ ማንም ያልቻለው ሁኔታ እንቅልፍ ነስቷቸው የተበታተነውን ሀይል አስተባብሮ ትግሉን አቅጣጫ ለማስያዝ ሲሉ በቅንነት ለት ተቅን ለሚለፉ ወገኖቼ ሻለቃ ዳዊት ወልደጎርጊስ፣ ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻውና ለአቶ ኃይለገብርኤል አያሌው ልግፍና ለመከራ በተዳረገው ሕዝባችን ስም ምስጋ ለማቅረብ እወዳለሁ።

የወያኔ ሕወሓት መንግሥት በተቃዋሚ ድርጅቶች ብዛት የሚወገድ ቢሆን ኖሮ ሃያሰባት ዓመት ሊገዛ ይቅርና አንዱንም የሥልጣን ጊዜ ባላጠናቀቀ ነበር። ይህንን ሀቅ ተገንዝቦ ሁሉም ተቃዋሚ ድርጅት እንኳን ባይሆን የተወስኑ ድርጅቶች ለሀገርና ለሕዝብ ሲሉ ተሰባስበው አገር ቤት እየተካሄደ ያለውን ትግል በጋራ ለመደገፍ አለመቻል በትውልድና በታሪክ የሚያስጠይቅ ትልቅ ወንጀል ነው።

ለመሆኑ እነኚህ ከኢትዮጵያ ውጭ የተቋቋሙና የሚቋቋሙ የፖሌቲካ ድርጅቶች ዓላማ አገር ቤት እንዳሉት የፖሌቲካ ስልጣን ይዞ ፕሮግራማቸውን ለመተግበር ከሆነ ችግሩ የሚጀምረው ገና ከአመሰራረቱ ነው ። ምክንያቱም ድርጅቶችን የሚመሰርቱ ግለሰቦችም ሆኑ በአባልነት የሚሰባሰቡ( የሚመለመሉ አላልኩም ምክንያቱም በምንም ይሁን በምን ተጠራርቶ መሰባሰብ እንጂ ጥናት ተደርጎ ምልመላ ባለመኖሩ ነው) ስዎች ነዋሪነታቸው ከሀገር ውጭ በመሆኑ ህዝቡን አንቅቶ አደራጅቶና ትግሉን መርቶ ለሥልጣን መብቃት የማይቻል በመሆኑ ነው። ይህንን ስል ከኢትዮጵያ ውጭ ያሉ የፖሌቲካም ሆነ የሲቪክ ማህበራት በሀገር ውስጥ በሚካሄደው ሕዝባዊ  ትግል ሚና የላቸውም እያልኩኝ አይደለሁም። አንድ የእግር ኳስ ቡድን እንደ ቀላል ምሳሌ ብንወስድ የተጫዋቹ የጋራ ዓላማ ተጋጣሚውን ማሸነፍ ሲሆን እያንዳንዱ ተጫዋች በተመደበበት ቦታ ተሰልፎ የግል ችሎታውን በመጠቀም ተቀባብሎ በቡድን ከተጫወት ዓላማው ግቡን ይመታል ነገር ግን የፈለገው ችሎታ ኖሮ ግለኝነት የሚያጠቃው ከሆነ ውጤት አልባ ነው የሚሆነው።

አሁን ሀገራችንና ሕዝባችን ያሉበት ሁኔት እንደ እግር ኳሱ ቀላል ቢሆን ኖሮ ኳስ ድቡልቡል ነች ብለን እናልፈው ነበር ነገር ግን የኛ ፍጹም የተለየ የመኖርና ያለመኖር ጥያቄ ነው። ታዲያ ከአንዱ (ከመኖር ) በቀር ሌላኛውን (አለመኖርን) መምረጥ እንደማንችል እያወቅን በተግባራችን ወደማይመረጠው ስናጋድል ይታያል።ከሁሉ በላይ ችግሩን ሳንረዳው ቀርተን ወይንም መፍትሄው ጠፍቶን ቢሆን ኖሮ ባላስደነቀን ነበር። ችግሩ ከላይ ለመግለጽ ዮሞከርኩት ምርጫ የለሹ መኖር አለመኖር ነው። መፍትሔውም አማራጭ የለለው አንድነት ብቻ ነው። ዓላማውን የማያውቅ ፤ መሬት ላይ ያለውን ችግር የማይረዳ ፤ የመፍትሔው አካል ለመሆን የማይፈልግ ፤ በኪሱ ዘውድና ወንበር ይዞ የሚዞር ድርጅትም ሆነ ግለሰብ በግልጽ ሊወቀስና ሊወገዝ ይገባል። ማንም በሕዝብና በሃገር ስም እንዲነግድ መፍቀድ አያስፈልግም ። ስለሆነም  የአማራ ፖለቲካ ሃይሎችን ወደ አንድነት ለማምጣት ጥረት  ያደረጉ ውገኖቻችን ስለ ሂደቱና ውጤቱ በሰጡት ማብራሪያ ማወቅ ለሚፈልግ የተሟላ መረጃ ስላለን መስጠት እንችላለን ብሎ ከማለፍ ይልቅ የተሳታፊ ድርጅቶችን ዝርዝርና ከተሳታፊዎች የቀረበን ሃሳብ ለመመለስና ለመከራከር ባለመፈለግ ስብሰባውን እረግጠው በመውጣት እራሳቸውን ከሂደቱ ያገለሉ እነ ማን እንደሆኑ ለሀገሩና ለወገኑ የሚቆረቆር ዜጋ ሁሉ የማወቅ መብት አለውና እንደምታሳውቁን ተስፋ አለኝ ። ጠቃሚነቱ እርስ በርስ ጣት ለመጠቋቆም ሳይሆን ድርጅቶቹን የሚደግፉ ግለሰቦች ድርጅታቸው በስማቸው የሚፈጽመውን እንዲያቁና ሌላውም ግንዛቤ እንዲኖረው ይረዳልና ነው ።

ኢትዮጵያ በልጆቿ መስዋእትነት አንድነቷ ተጠብቆ ለዘለዓለም ትኑር