ስቶክሆልም (March 11, 2018)
ከሃያስድስት አመት በኋላ ህዝቡ ጭቆናን መሸከም አቅቶት ለወያኔ አልገዛም ባይነቱን በግልጽ እያሳየ የሚገኝበት ወቅት ላይ ደርሰናል። የሥርአቱ ቁንጮዎችና ከሥርአቱ ጋራ በጥቅም የተሳሰሩ ግለሰቦች ካልሆኑ በስተቀር ዛሬ በኢቲዮጵያ ውስጥ በአንድ ብሄር የበላይነት መገዛት በቃኝ ያላለና ያልተመረረ የህብረተስብ ክፍል አለ ለማለት ያስቸግራል፤ ይጠቅሙኛል ብሎ ያደራጃቸው የዘውግ ድርጅቶች እንኳን ሳይቀሩ በወያኔ ላይ እያመጹ ነው፤ የወያኔም እድሜ ወደማለቂያው የተቃረበ ይመስላል፤ ባጠቃላይ አገሪቱ በመስቀለኛ መንገድ ላይ ትገኛለች፤ ወይ ወደ ሲኦል ወይ ወደ ገነት አሊያም መድረሻውን ወደማናውቀው ቦታ የሚያመራ መንገድ ልትጓዝ ትችላለች። ስለሆነም ብዙ ጥያቄዎች በብዙ ሰው ጭንቅላት ውስጥ በመንገዋለል ላይ ነው፤ ከጥያቄዎቹ ውስጥ አንዱ ከወያኔ በኋላ መምጣት ያለበት ሥርአት ምን መሆን አለበት የሚለው ሆኗል። ጥያቄው አስቀድሞም በጭላንጭል የሚታይም ቢሆንም አሁን ግን ኢትዮጵያ ከወያኔ በኋላ የምትከተለው ሥርአት ምን መሆን አለበት ፤ አሃዳዊ ወይስ ፌደራላዊ የሚሉ አስተሳሰቦች ከምንጊዜውም በበለጠ ሁኔታ ወደፊት እየገፉ ብቅ ማለት ጀምረዋል። ከፊሉ በጥያቄው ላይ ከወዲሁ ተነጋግረን እንወስን ሲል ከፊሉ ደግሞ የህዝብ ምርጫ ተደርጎ የኢቲዮጵያ ህዝብ የሚወስነው ይሆናል የሚል ነው። ስምምነት ላይ የሚደረሰው ከህዝብ ምርጫም በኋላ ሆነ በፊት ውይይቱን ግን ከወዲሁ ከመጀመር የሚያግደው ነገር ያለ አይመስለኝም። እሸቱ ጮሌ የፌዴራል ሥርአትን አስመልክቶ ተናገረ እንደተባለው መከፈት ያልነበረበት ሳጥን (pandora box) ነው የተከፈተው፤ የተከፈተው ግን ከሃያ ስድት ዓመት በፊት መሆኑን አንዘንጋ ።
እንደልማድ ሆኖ ፌዴራላዊ ሥርአት የሚለው አነጋገር ለብዙ ዘመን በሰውም አፍ፤ በብዙሃንና በማህበራዊ መገናኛውችም፤ በህዝባዊ ውይይቶችም ላይ እይተደጋገመ ስለተነገረና ህገመንግስቱም ”የኢቲዮጲያ ፊዴራል ዲምፖክራሳዊ ረፑብሊክ ህግ ”ተብሎ ስለተሰየመ ፤ብዙዎቻችን እንዳውም ሁላችንም በሚባል ደረጃ የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ሥርአት እያልን ነው የምንናገርውም የምንጽፈውም። ሃቁ ግን በኢትዮጲያ ያለው የአስተዳደር ሥርአት ዘውጋዊ የፌዴራል ሥርአት (ethnic federalism) መሆኑና ትክክለኛውም መጠሪያው ይሄ መሆን እንዳለበት ነው፤ ይሄ ደግሞ ከብዙዎቻችን የተደበቀ አዲስ ነገር አይደለም። እኔም ይህን ጽሁፍ እንዳቀርብ ያነሳሳኝ በዚህ ጥያቄ ላይ አዲስ ሃሳብ አቀርባለሁ ከሚል አስተያየት በመነሳት ሳይሆን፤ አውቀንም ሆነ ሳናውቅ በኢቲዮጲያ ያለውን ሥርአት ዘውጋዊ የፊዴራል አስተዳደር ብሎ አለምጥራቱ ትልቅ ስህተት መስሎ ስለሚሰማኝ ነው። የዘውግ ፌደራላዊ አስተዳደር የሚያስከትለውን መዘዝ አውቆ ከወዲሁ ውይይት መክፈትና በጥያቄውም ዙሪያ ቢቻል አንድ አይነት ስምምነት ላይ መድረስ፤ ባይቻል ግን ልይነቶችን በሚገባ ለህዝብ ማሳወቅ ተገቢ ነው ብዬ ስለማምን ነው። የዚህ ጽሁፍ አላማም በኢትዮጵያ ያለው አስተዳደር ዘውጋዊ የፌዴራል ሥርአት መሆኑን ማሳየት፤ ሥርአቱ እንዴት መሻሻል እንደሚችል ሃሳብ ማቅረብ፤ ካልተሻሻለም የሚያመጣውን መዘዝ ለማሳየት መሞከር፤ በመጨረሻም ለውይይት መነሻ ሃሳብ እንዲሆን በመመኝትም ነው። የፌዴራላዊ ሥርአት የሚመረጥና የሚቀጥል ከሆነ የማሻሻያ ሃሳብ ለማቅረብ የተደረገ ሙከራ እንጂ አሃዳዊ አገዛዝን በማሳነስ ከአማራጭነት ለማውጣት በመፈለግ አይደለም።
ዘውጋዊ የፈዴራል ሥርአትን አይነተኛ የሚያደርገው በማንነት (በብሄር) ላይ ብቻ የተመሰረተ የጆግራፊ ክልል ሲገነባ፤ ብሄሮችም በተገነባው ክልል ውስጥ እራስን በራስ የማስተዳደር መብት ሲኖራቸው ነው። በርግጥ ለብዙዎቻችን የፌዴራል ሥርአቱ ዘውጋዊ መሆኑ ግልጽ ሊሆን ይችላል። ኢንተርኔት ውስጥ እንኳን ገብተን ዘውጋዊ ፌደራሊዝም ብለን ስንፈልግ (search) ከምናገኝቸው ሶስትና አራት አገሮች ውስጥ (ኔፓል፤ፓኪስታን፤ደቡብ ሱዳን) አንዷና በዘውጋዊ ፌዴራል አስተዳደር እንደተምሳሌት በመወሰድ አስቀድማ ብቅ የምትለው ሃገር ኢትዮጵያ ናት፤ የኢትዮጵያ ዘውጋዊ ፌዴራል ሥርአት ዓለም ያወቀው ፀሃይ የሞቀው ነው ማለት ነው። ይህም ሆኖ ግን ብሄር ተኮር ሆኖ የተገነባው የክልሎች አወቃቀር (የዘውጋዊ ሥርአቱ ምሰሶ) ይሻሻል ሲባል ብዙ ስምምነት አላይም፤ አንዳንዶቹ እንዳውም ህገመንግስቱ በሚገባ ስራ ላይ አለመዋሉ ነው እንጂ ”ሳይሸራረፍ” ስራ ላይ ቢውል ምንም እንከን የለበትም ይላሉ። በግሌ በህገ መንግስቱም ውስጥ የማልስማማባቸው ነግሮች ቢኖሩም፤ ለጊዜው ግን ትኩረቴ የሥርአቱን ዘውጋዊነት በማሳየት ላይ ብቻ ይወሰናል።
ዘውጋዊ የፌዴራል ሥርአት በብዙ እጁ ጎጂና አገር አፍራሽ እንደሆነ ነው የሚነገርለት፤ ታላላቅ የፖሊቲካ ተንታኞችና የፖሊቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎችም የሚጋሩት አስተሳሰብ ነው። ከፖሊቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎች ውስጥ ሊያም አንደርሰንና (Liam Anderson august 2014)i ሮደር (Roeder may 2009)ii የአስተሳሰቡ አራማጆች ናቸው። ለአብነት ያህል ይህን አስተሳሰብ የሚያጠናክር ነው ተብሎ የሚነገርለትን የሮደርን የዳሰሳ (empirical) ጥናት
2
እንመልከት፤ እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር ከ 1901 – 2009 ድረስ ባለው ጊዜ ውስጥ (መቶ ስምንት ዓመት) የነበሩ ሥርአቶችን በሁለት ጎራ ከፍሎ የተካሄደ ጥናት ነው። 1. በዘውጋዊ የፈዴራላዊ ሥርአት ይተዳደሩ የነበሩትንና በተጨማሪም በፌዴራል ሥርአት ሳይሆን ግን ብሄር ተኮር በሆነ (ethnic) የአውቶኖሚ አስተዳደር ይተዳደሩ የነበሩትን በአንድ ጎራ (ጎራ አንድ) ስበሰበ 2. በሌላ በኩል ደግሞ ዘውጋዊ ባልሆነ የፌዴራል ሥርአት ይተዳደሩ የነበሩትንና በተጨማሪም በሌላም ሥርአት ስር የሚተዳደሩ ሆነው ግን ብሄርተኛ አስተዳደር የሌላቸውን በሌላ ጎራ (ጎራ ሁለት) ሰበሰበ
የጥናቱም ውጤት በሁለቱ ጎራዎች መሃል የሚታየውን ልዩነት አስገራሚ እንዲሆን አድሮጎታል፤ ጎራ አንድ ውስጥ የሚገኙ አስተዳደሮች በመገነጣጠል ሲታመሱ በጎራ ሁለት ውስጥ በሚገኙ አስተዳደሮች ውስጥ አንድም የመገንጠል ሁኔታ አልከሰተም። በጎራ አንድ ከ 18 ዘውጋዊ የፌዴራ አስተዳደር ውስጥ አስራ አራቱ (14) ማለት 78 % ውድቀት ሲደርስባቸው፤ በ 19 ብሄርተኛ የአውቶኖሚ አስተዳደር ከነበራቸው ውስጥ ደግሞ 12 (63%) ውድቀት ደርሶባቸዋል፤ ሮደር ውድቀት የሚለው መገንጠልን ነው።
ጥናቱ በዘውጋዌ የፌዴራል ሥርአትም ሆነ ሌላም ፌዴራላዊ ሳይሆን ግን ዘር ተኮር ላይ በተመሰረተ ራስ ገዝ ባለው አስተዳደር (autonomi) ውስጥ የሚኖረውን ችግር ነው ለማሳየት የሞከረው። እንዲህ አይነቱ ችግር እንዳይከሰት ሰዎች የተለያዩ የመፍትሄ ሃሳቦችን ያቀርባሉ፤ እንደ አማራጭ ሆኖ የሚቀርበው አንዱ የአሃዳዊ አስተዳደር ነው። ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ እንደ ኢቲዮጵያ ብዙ ብሄሮች በሚኖሩበት አገር ያለው ዘውጋዊ የፊዴራል አስተዳደር እንዲሻሻልና የመገነጣጠሉም አደጋ እንዲቀረፍ/እንዲያንስ ከተፈለገ ትልልቅ የህዝብ ብዛት ያላቸውን ህዝቦች/ብሄሮች በአንድ የጆግራፊ ክልል ውስጥ እንዳይኖሩ ማድረግ የሚል ነው። የፖሊቲካ ሳይንስ ተመራማሪዎችም እንደ አንድ አማራጭ አድርገው የሚያቀርቡት ”አስታራቂዊ ሃሳብ” ይህንኑ አስተሳሰብ የሚያጠናክር ነውiii፤ ተመራማሪዎቹም እንደተምሳሌት አድርገው ከሚያቀርቧችውም ሶስት አገሮች ውስጥ አንዷህንድ ናት። በዚህ ጽሁፉ ላይ ትኩረት በመስጠት ለውይይት ከማቀርበው ሃሳቦች አንዱ በህንድ ውስጥ የሂንዲ ቋንቋ ተናጋሪዎች የሚገኙባቸው ስቴቶችን (ክልሎችን) የተመለከተ ይሆናል። የሂንዲ ቋንቋ ተናጋሪ ስቴቶችን ተሞክሮ በጥሞና መመልከቱ ፤ ዘውጋዊው የፌዴራላው አስተዳደሩን ለማሻሻል በሚደረገው ውይይት ላይ ግብአት ይኖረዋል የሚል ግምት አለኝ። ኦሮሞውና አማራው ትልቅ የህዝብ ብዛት ስላላቸው (65%) ክልል የመሸንሸኑ ሃሳብ ሊተገበር ይችላል ብዬ የምገምተውም በነኚህ ክልሎች ውስጥ ነው፤ ምናልባትም ትልቅ የቆዳ ስፋት ስላለው የሶማሌን ክልልንም ሊያካትት ይችል ይሆናል። የህንድን ተምሳሌነት ጋባዥ (inviting) የሚያደርገው፤ ህንድ ብዙ የተለያዩ ህዝቦች መኖሪያ በመሆኗ በዚህም ደረጃ ከኢቲዮጵያ ጋር ብዙ ተመሳሳይነት ስለሚኖራት ነው። ሃሳቡን ተግባራዊ ለማድረግ የሚቻለው አገራዊ አጀንዳ ይዞ የሚንቀስቅስ ጠንካራ አመራር ሲኖር፤ በህዝቦችም መሃል ስምምነት ላይ ሲደረስ ነው።
ስለሆነም የዚህ ጽሁፍ አንዱ አላማ በህንድ ውስጥ የሂንዲ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ስቴቶችን ተሞክሮ ወደፊት በማምጣት ውይይት ከፋች ሊሆን የሚችል ሃሳብ ለማቅረብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ፌዴራላዊ ሥርአትን ተግባራዊ ለማድረግና አስተማማኝ ሆኖ እንዲቀጥል የዲሞክራሲን ባህል ማዳበርና ጠንካራ የዲሞክራሲ ተቋማትንም ማጠናከር አስፈላጊ ስለሆነ ፤ አስፈላጊነቱንም ለመረዳት የስዊስንና የህንድን ተሞክሮ አስመልክቶ በእነኚህ አገሮች ላይ የታየውን ስኬትና ክፍተት ማቅረብ ይሆናል ፤ ስዊስም እንደህንድ የፌዴራላዊ ሥርአትን የምትከተል ከመሆኗም በተጨማሪ ብዙም ባይሆን የተለያዩ ህዝቦች የሚገኙባት አገር ስለሆነች ተሞክሮዋ ጥሩ ግንዛቤ ሊያስጨብጥ ይችላል የሚል ግምት አለኝ። በመጨረሻም የአሃዳዊ ሥርአትም ቢሆን መብትን በተመለከተ ረጅም እርቀት የሚሄድ አውቶኖሚ እንደሚሰጥ ለማሳየት የስፔንን ተሞክሮ በጥቂቱ ማሳየት ይሆናል፤ በሥርአቱም ውስጥ ሊከሰት የሚችለውን ችግር በመጠኑም ቢሆን ይቀርባል።
ባለፈው ጽሁፌ በኢቲዮሜዲያ ላይ የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦችም መብታቸው ተጠብቆ በአንድ ስቴት/ክልል ውስጥ አብረው ለመኖር የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚኖር አሳይቼ ነበር። እንደምሳሌም ግሪሶን ካንቶን/ክልል (Grison canton) ተብላ በምትጠራው የስዊስ ክልል ውስጥ የሶስት ቋንቁዋ ተናጋሪዎች (ጀርመንኛ፤ ጣልያንኛና ሮማንሽ)፤ ቋንቋቸውም የተለያየ ባህላቸውም ተከብሮ በእኩል ደረጃ እንደሚኖሩ ማሳየት ነበር። ይሄን አይነቱ ውይይት በዚህ ጽሁፍ ላይ አይደረግም፤ ባለመደረጉም ውይይቱን ያልተሟላ ሊያደርገው ይችል ይሆናል፤ ይሁን እንጂ ጉድለቱንም እየተገነዘብኩ ነው በዚህ ጽሁፍ ይሄን አይነቱን ውይይት የማላደርገው።
የህንድ ስቴቶች (ክልሎች)
የዛሬዋ ህንድ ሃያ ዘጠኝ የፌደራል ስቴቶችና (ክልሎች) ሰባት ዩኒዮን ቴሪቶሪዎች (union territories) በጠቅላላው ሰላሳ ስድስት ስቴቶችና ዩኒዮን ቴሪቶሪዎች ያካተተች የፌደራል አገር ነች። ስቴቶቹ የተዋቀሩበት አንዱ መርህ ቋንቋን ተክትሎ በሄደ መስመር ላይ የተዘረጋ መሆኑ ነው፤ በዚህ ደረጃ ከኢትዮጵያው ዘውጋዊ የፌደራል ሥርአት ጋር ተመሳሳይነት ይኖረዋል። ይሁን እንጂ ህንድ ብዙ ህዝቦችን ያቀፈ ትልቅ ብሄር ባንድ የጆግራፊ ክልል አብሮ እንዲኖ ሳይሆን ፤ ከአንድ
3
በላይ በሆኑ ክልሎች ተሸንሽኖ እንዲኖር ስለምታደርግ ዘውጋዊነቷ እዚህ ላይ ያከትማል፤ ከዚህም የተነሳ አንዳንድ የፖሊቲካ ተመራማሪዎች የህንድን ፌደራላዊ አስተዳደር ”ዘውጋዊ የወስን ፌዴራሊዝም ” (ethnoterritorial federalism) የሚል ስያሜ ይሰጡታል። ዩኒዮን ቴሪቶሪዎች በመባል የሚታወቁት ቦታዎች ደግሞ እንደሌሎቹ ስቴቶች የራሳቸው መንግስት የሌላቸው፤ በማከላዊ መንግስት ስር የሚተዳደሩ ናቸው፤ አስተዳዳሪ ወይም ገዢ የሚሾምላቸውም የህንድ ፕሬዚዳንት ነው።
በህንድ ውስጥ በብዙ መቶ የሚቆጠሩ ቋንቋዎች ይነገራሉ፤ ከነኚህ መሃል ሂንዲ በጣም ትልቁ ነው፤ 40 % ለሚሆነው የህንድ ህዝብ የመጀመሪያው ቋንቋው ሲሆን ከ 60 % በላይ የሚሆነውም የህንድ ህዝብ ቋንቋውን ይናገራል። ከሂንዲ ቀጥሎ የሚነገሩ ቋንቋዎች በጣም ዝቅተኛ ቁጥር ያላቸው ናቸው፤ ለአብነት ያህል በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው የቤንጋሊ ቋንቋ ተናጋሪ 8% ብቻ ነው። ከጠቅላላው የህንድ ህዝብ ሂንዲ ተናጋሪው አንድ ሶስተኛ ሲሆን፤ በቆዳ ስፋትም እሩቡን የህንድን አገር ይሸፍናል፤ በጆግራፊ አቀማምጡም በስሜኑና በመካከለኛው የህንድ መልክአ ምድር ላይ ባንድ የጆግራፊ አካባቢ ውስጥ ይገኛል። ይሁን እንጂ ይህ ህዝብ አንድ ቋንቋ ተናጋሪ ስለሆነና በአንድ የጆግራፊ መልክአ ምድር ላይ ስለሚገኝ ባንድ ስቴት (ክልል) ውስጥ እንዲኖር አልተደረገም፤ በዘጠኝ ክልሎች (ስቴቶች) ተሽንሽኖ ነው የሚገኘው፤ በዘጠኙም ክልሎች ውስጥ የሚነገረው ቋንቋ ሂንዲ ሲሆን፤ ሶስት ተጨማሪ ትንንሽ ቋንቋዎችም በክልል ውስጥ መገልገያ (official) ሆነው ከሂንዲ ቋንቋ ጋራ አብረው ይነገራሉ ፤ እነሱም ኡርዱ (በሶስቱ ስቴቶች)፤ እንግሊዝኛና (በሁለቱ ስቴቶች) ፑንጃቢ (ባንዱ ስቴት) ናቸው። መሸንሸኑ የሂንዲ ተናጋሪዎችን በቋንቋቸው ከመጠቀምና ቋንቋቸውንም ከማሳደግ አላገዳቸውም። ይልቁንም መሸንሸኑ አንድ ብዙ ቁጥር ያለው ህዝብ በአንድ ትልቅ የጆግራፊ ክልል ውስጥ አንድ ላይ በመኖሩ ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ቀርፎታል ተብሎ ነው የሚታመነው።
የህንድ ፌዴራል ስቴቶች አወቃቀር የተጀመረው ህንድ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ነጻ በወጣች ማግስት ቢሆንም፤ ዛሬ በሚታየው መልኩ ተሻሽሎ እንዲዋቀር የተደረገው በ 1956 ነው፤ አወቃቀሩም የቋንቋን መስመር ተክትሎ የሄደ ነበር። በአወቃቀሩ ላይ በየጊዜው ማሻሻያ እየተደረገበት እስከ 2000 ዓም ድረስ ቀጥሏል፤ አወቃቀሩ ቋንቋን ታሳቢ አድርጎ የቀጠለ ቢሆንም በይበልጥ ግን ያገሪቱን አንድነትና ሰላምን ባስቀደመ መመሪያ ላይ የተመሰረተ እንዲሆን ተደርጓል። መመሪያውንም በመከተል እንደ አውሮፕያውያን አቆጣጠር በ 2000 ዓም በተደረገው አወቃቀር በሂንዲ ስቴቶች ውስጥ ተጨማሪ የሆኑ ሶስት ስቴቶች (Chhattisgarh, Uttaranchal, Jharkhand) ተፈጥረዋል፤ በፊት ስድስት የነበሩትን የሂንዲ ስቴቶችን በመሸንሸን የተፈጠሩ (የተዋቀሩ) ናቸው፤ የሂንዲንም ስቴቶች ቁጥሩ ወደ ዘጠኝ አድርሶታል። የህንድ ፌደራላዊ ሥርአት የዜግነትን መብትና አገራዊ አንድነት ቢያስቀድምም የብሄሮችን መብትም እያከበረ ሚዛናዊ በሆነ ሁኔታ ይራመዳል። የህገመንግስቱ መግቢያም (preamble) ”እኛ የህንድ ህዝብ” ብሎ ይጀምርና ”የዜጎችን መብት ማስከበር፤ የግለሰብን ክብርና የህገሪቷን አንድነት ማረጋገጥ …. ” በማለት ይቀጥላል።
የኢቲዮጵያ ሁኔታ
ያገራችን ህገመንግስት በመግቢያው ላይ እኛ የኢትዮጲያ ብሄሮች፤ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ብሎ ነው የሚጀምረው፤ እንደ ህንድ ህገመንግስት የግለሰብንና የዜግነትን መብት በማስቀደም አይጀምርም፤ በተግባር እየታየ ያለውም የሰዎች ዜግነት ሳይሆን ማንነታቸው ነው ቅድሚያ ቦታ የሚይዘው፤ የህንድ መንግስት ትልልቅ ክልሎችን ሲሸነሽን ወያኔ በስልጣን ዘመኑ ከሰሜን ጎንደር፣ ከሰሜን ወሎና ከአፋርም መሬት በመውሰድ የትግሬን ክልል አሳብጦታል፤ መሸንሸን ያስፈልጋቸዋል የሚባሉትንም ክልሎች እንዳይሸነሸኑ አድርጓል፤ የወያኔ አገዛዝ እያደረገ ያለው የህንድ ፌዴራላዊ አስተዳደር የሚያደርገውን የሚጻረር ይመስላል፤ ኢቲዮጵያንም የዘውግ ፌዴራላዊ አስተዳደር ከሚከተሉ ጥቂት አገሮች ተርታ እንድትሰለፍ አድርጓታል።
የዛሬ ሃያ ሰባት ዓመት ተወልዶ ያደገ ሰው ዛሬ ጎልማሳ ሆኗል፤ የብሄርን ጥያቄ አንግበው ከታገሉ ህዝቦች ውስጥ በዚህ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኘው ጎልማሳም ከዘውጋዊው የፌዴራላዊ አስተዳደር ሌላ አስተዳደር አያውቅም፤ የብሄርን መብት በተመለከተም ሥርአቱ ትልቅ መሻሻል አድርጎለታል፤ በክፉም ሆነ በደግ መብቱ በስራ ሲተረጎም በአይኑ እያየ በጆሮው እየሰማ ነው ያደገው፤ ይሄ ትውልድ ይህን መብት ለማጣት አይፈልግም። አንደተባለው ወደፊት ኢቲዮጵያ ወስጥ መመስረት ያለበት ሥርአት ፌዴራላዊ አስተዳደር ወይስ አሃዳዊ ስርአት የሚል አማራጭ ለህዝበ ምርጫ ቢቀርብ ፤ የብሄርን ጥያቄ አንግበው የታገሉት ህዝቦች ፌዴራላዊ ሥርአትን ይመርጣሉ ብሎ መተንበዩ አዳጋች አይመለኝም። ነገር ግን የሚመረጠው ፌዴራልዊ ሥርአት ምን አይነት ነው ሊሆን የሚችለው? ዘውጋዊ የፌዴራል ሥርአትን ማስቀጠል? ይሄን ለመተንበይ አስቸጋሪ ይመስለኛል፤ በጥያቄው ዙሪያ ውይይት ስለማይደረግ ያለው አስተሳሰብ ወዴት እንደሚያመራ የሚያሳይ ”ኮምፓስ” ለማግኘት አስቸጋሪ ነው።
ወያኔ ዘዴንም ጉልበትንም በመጠቀም እሱ በሰፋው በዘር ከረጢት ውስጥ የኢቲዮጵያን ህዝብ ታፍኖ እንዲኖር ከማድረጉም በላይ ብሄር ተኮር የሆነ የዘውግ ፖሊቲካ እንዲጦዝና አገራዊ አጀንዳም እንዲደበዝዝ አድርጎታል። የዘር መጠሪያን ያነገቡ ድርጅቶች መበራከታቸውና የክልል አስተሳሰብ ከሃገራዊ አስተሳሰብ በላይ ከፍ እያለ መምጣቱን ለተገነዘበ ዜጋ ነገሩ ሊያሳስበው ይገባል። ከሁሉም በኩል የጦዘው ብሄርተኝነት መድረሻው የት ነው? ክልሎችን ይዞ ሌላ
4
አገር ለመፍጠር? ሁኔታው ሚዛናኑን ጠብቆ ካልተጓዘ የመገነጣጠሉ አደጋ እውን ሊሆን ይችላል፤ ከብሄርተኝነቱ ጋር አገራዊ አጀንዳ ያላቸው ህብረ ብሄራዊ የሆኑ ድርጅቶች ተጠናክረው አለመውጣታቸው ሁኔታውን የበለጠ አሳሳቢ ያደርገዋል። በርግጥ ያማራውና የኦሮሞው ህዝብ መቀራረብ የብርሃን ጭላንጭል እያሳየ ነው፤ የኢቲዮጵያም ህዝብ የፍራቻውን ግምብ ሰብሮ ወጥቷል ፤ በየቦታው የሚታየው የትግል መንፈስም ጠንካራ ሆኗል፤ የህሊና እስረኞችም እየተፈቱ ነው፤ ወያኔም በሚገባ ተዳክሟል፤ ሌላም ብዙ ድሎችን መቁጠር ይቻላል። በተለይ በአዲሱ ትውልድ እየተመራ ያለው የኦሮሞ ህዝብ ዴሞክራሳዊ ድርጅት (ኦህዴድ) በኢቲዮጵያዊነትና በኢቲዮጵያ አንድነት ላይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የሚያራምደው አቋም የሚያበረታታ ከመሆኑም በላይ፤ በቅርቡ ደግሞ ኦህዴድ እንደድርጅት የአሰቸኳይ ጊዜ አዋጁ እንዳይጸድቅ ያሳየው ታሪካዊ ተቃውሞ የሚያኮራና ትልቅ ተስፋ ሰጪ ነው። ሆኖም አሁንም ዋስትና የሚሰጥ አስተማማኝ ሁኔታ ባለመኖሩ እቺ አገር ወዴት እንደምትሄድ ማወቅ አይቻልም፤ ከወደቀችም ተሰብራ መነሳቷን አናውቅም፤ ወያኔም ወድቃ እንዳትነሳ የሚፈልግ ይመስላል፤ አለበለዛ በዚህ ሁኔታ ውስጥ ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅን ምን አመጣው፤ ለችግሩ መፍትሄ ፈላጊ ባለመሆኑ እንዳውም ሁኔታውን ለማባባስና ሥርአቱንም ለማስቀጠል ፍላጎት እንዳለው ነው የምረዳው።
ዘውጋዊው ፌዴራላዊ አስተዳደር ስለተሻሻለ ችግሮች ይወገዳሉ ወይ?
ዘውጋዊ አስተዳደር የሚያስከትለውን ችግር ለመቅረፍ የውይይት ሃሳብ ሊሆን ይችላል በሚል አስተሳሰብ ከመመራት ሌላ ችግሩ በቀላሉ ይፈታል የሚል ቅዠት የለኝም፤ ወደፊትም ውይይቱን ሊያዳብሩ ይችላሉ የሚባሉ ሃሳቦች ሺ ጊዜ ገምቢ ሆነው ቢቀርቡም ፍጹም የሆነ መፍትሄ ላይ ሊያደርሱ ይችላሉ ብዬ አላምንም። ይሄ ደግሞ ሰዎች የሃሳብ ደሃ በመሆናቸው ሳይሆን ፌዴራላዊ አስተዳደር በራሱ የሚፈጥረው ችግር ስለሚኖር ነው፤ የዲሞክራሲ ባህል ሽታውም በማይታወቅበት እንደ ኢቲዮጵያ ባሉ አገሮች ላይ ችግሩ እጥፍ ድርብ ነው የሚሆነው። የዲሞክራሲ ባህል ደግሞ ምሁሮቻችን ስለዲሞክራሲ ስለሚጽፉና ስለምያንበለብሉ የሚዳብር አይደለም፤ ዲሞክራሲያዊ በሆነ ሥርአት ውስጥ ህዝቦች ለብዙ ዘመን ከኖሩ በኋላ የሚያዳብሩት ነው፤ በቤተሰብ ውስጥ ከሚሰጥ አስተዳደግ ጀምሮ በትምህርት ቤትና የቀን ተቀን ህይወትም ውስጥ በሚገኝ ትምህርትና ልምድ ላይ ተመስርቶ የሚዳብር ባህል ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ ማንኛውም ዲሞክራሲን መሰረት ያደረገ ሥርአት አስተማማኝ በሆነ መንገድ እንዲራመድ የዲሞክራሲ ተቋሞች መኖርም አስፈላጊ ነው። በኛ አገር ባህሉም የለም ተቋሞቹም የሉም፤ ሁለት ባላዎች ወይም ሁለቱ ምሰሶዎች ተብለው የሚጠሩት ነገሮች የሉም ።
ሥርአቱን ለማሻሻል ፍላጎት ቢኖርም የደሞክራሲ ባህልና የመቆጣጠሪያ ተቋማት (ሁለቱ ምሰሶዎች) በሌሉበት አገር ችግሩን የተወሳሰበ እንደሚያደርገው ለመገንዘብ አያዳግትም። ሁለቱም ምሰሶዎች ጠንካራሮች ናቸው በሚባሉበት አገሮች ውስጥም እንኳን ቢሆን ሥርአቱን ፍጹም ማድረግ ቀላል አይሆንም፤ የሲዊትዘርላንድና የህንድን ተሞክሮ ማየት ይቻላል። ሁለቱም የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች የሚኖሩባቸውና በፌዴራላዊ ሥርአት የሚተዳደሩ አገሮች ናቸው፤ የስዊትዘርላንድ ተሞክሮ ስኬታማ ሲባል የህንዱ ግን እንደ ስዊስ ስኬታማ ሊሆን አልቻለም። ስኬታማ ነው የሚባለው የስዊስ ሥርአትም ቢሆን ችግር ያጋጠመው ጊዜ ነበር፤ ችግሩ የተከሰተው ለተወሰነ ጊዜም ቢሆን በሥርአቱ ላይ የታሪክ ጠባሳ ጥሎ ነው ያለፈው።
በስዊዘርላንድ የፌዴራል ሥርአት ውስጥ ሃያ ስድስት ስቴቶች/ክልሎች (cantons) ይገኛሉ፤ አራት የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ህዝቦችም አብረው ይኖራሉ። ክልሎችም ራሳቸውን በማስተዳደር በኩል ትልቅ ነጻነት አላቸው፤ በተለይ ታክስ በመጣልና ገቢውንም በማስተዳደር ረገድ አውሮፓ ውስጥ ካሉ የፌዴራል አገሮች ጋራ ሲነጻጸር የጎላ መብት እንዳላቸው ነው የሚነገረው፤ የስዊስ ክልሎች ከሚሰበስቡት የታክስ ገቢ ውስጥ 25% የሚሆነውን ሲያስተዳድሩ፤ የጀርመን ስቴቶች/ክልሎች (länder) 0,7% ፤ የኦስትሪያ ስቴቶች/ክልሎች (länder) 0,6% የሆነውን ብቻ ነው ሊያስተዳድሩ የሚችሉት። የውጪ ኢንቬስትመንት ለመሳብም የስዊስ ክልሎች የታክስ ተመናቸውን በመቀያየር በመካከላቸው ፉክክር ያደርጋሉ፤ በክልሎች መሃልም ሆነ በክልሎችና በፌዴራሉ መሃልም አለመግባባት ቢፈጠር በፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድቤት ታይቶ ውሳኔ ይሰጥበታል፤ ህዝቡም የፌዴራል አወቃቀሩ ላይ ደስተኛ እንደሆነ ነው በየጊዜው የሚደረጉ ጥናቶች (surveys) የሚያሳዩት፤ በውጪው ዓለምም ቢሆን ስዊስ የዲሞክራሲ ባህላቸውን ካዳበሩ፤ ሰላምንና መረጋጋት ካሰፈኑ አገሮች መሃል በቅድሚያ እንደተምሳሌ የምትታይ አገር ናት። እንደዚህም ሆኖ ዛሬ ጁራ ተብላ የምትጠራው ሃያ ስድስተኛው የስዊስ ካንቶን (ክልል) ከበርን ካንቶን ለመገንጠል በተነሳችበት ጊዜ አለመረጋጋት ተፈጥሮ በህዝቦች መሃል ግጭት ተቀስቀሶ ነበር፤ በተለይ የጁራ ነጻ አውጪ ድርጅት በመባል የሚጠራው ቡድን ያካሂድ በነበረው አመጻዊ ትግል የተነሳ ባንድ ወቅት ግጭቱን የከረረ አድርጎት ነበር፤ በመጨረሻም ችግሩ በህዝባዊ ምርጫ ሊፈታ ችሏል። ለመገንጠል መነሳቱም እንደ ዋና ምክንያት ሆኖ የሚነገረው የፕሮተስታንትና የካቶሊክ እምነት ተከታዮች መሃል በተፈጠረ አለመግባባት ነበር።
ሕንድ በፌዴራል አስተዳደሯ ውስጥ በሚኖሩ የተለያዩ ህዝቦችና የሃይማኖት ተከታዮች መሃል ሊፈጠሩ የሚችሉ ግጭቶችን ለማስወገድ በምታደርገው ጥረትና ባሳየቺው የፖሊቲካ ቆራጥነት የምትደነቅ አገር ሆናለች፤ በብዙ መቶ
5
በሚቆጠር የተለያየ ቋንቋ የሚናገሩ ህዝቦች ባሉበት አገር ውስጥ በፌዴራላዊ አስተዳደር መመራቷ በጅቷታልም የሚሉ ብዙ የፖሊቲካ ተንታኞች አሉ። ሆኖም አሁንም ቢሆን ግጭቶች ጊዜውን እየጠበቁ ብቅ ጥልቅ ማለታቸውን አላቆሙም፤ ሲኮች ሃይማኖታቸውና ቋንቋቸው (ፑንጃቢ) የሚገባውን እውቅና አላገኘም በመባሉ ምክኒያት ከሰባዎቹ ጀምሮ እስከዘጠናዎቹ ድረሥ ያልተቋረጠ ህዝባዊ አመጽ አካሂደዋል፤ የህንድ ጠቅላይ ሚንስተር የነበረችው የኢንዲራ ጋንዲን ሞት ተክትሎ በሲኮች ላይ ትልቅ ጭፍጨፋ ተደርጓል፤ በየጊዜው በሂንዱ ሃይማኖት ተከታዮችና በሙስሊምች መሃል የሚከሰተው ግጭት አሁንም መቋጫ አላገኘም፤ በሲክና በሂንዱ መሃል ፑንጃብ ስቴት ውስጥ አልፎ አልፎ ግጭቶች ይታያሉ፤ ይሄ ሁሉ የሚያሳየው አሁንም ድረስ የህንድ ፌዴራላዊ አስተዳደር ችግሩን ሙሉ በሙሉ እንዳልፈታው ነው። እንደ ስዊስም ባይሆን ህንድም ውስጥ ጠንካራ የሆኑ የዲሞክራሲ ተቋሞቶች አሉ፤ እንድሚመስለኝ በሁለቱ አገሮች መሃል ያለው ዋናው ልዩነት የዲሞክራሲን ባህል በተመለከት ነው፤ የስዊሱ በላቀ ደረጃ የሚገኝ ነው።
የተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ የሆኑ ህዝቦች በሚገኙበት አገር የሚኖረውን ችግር ለመፍታት የተሞከረው የፌዴራላዊ አስተዳደርን በሚከተሉ አገሮች ብቻ አይደለም፤ አሃዳዊ ሥርአትንም በሚከተሉ አገሮችም ላይ ሙከራ ይደረጋል፤ ከነኚህም መሃል አንደኛዋ ስፔይን ናት። ስፔይን አስራ ሰባት የሆኑ የራስ ገዝ (autonomi) ያላቸው ግዛቶችን ያቀፈች፤ ግዛቶቹም የራሳቸውን ፕሬዚደንት በቀጥታ መርጠው እንዲተዳደሩ ያደረገች አገር ናት። ከአስራሰባቱ ግዛቶች ውስጥ በተለይ ባስክ፤ ካታላን፤ጋልዝ (Basque: Catalan: Galician) ተብለው የሚጠሩት ግዛቶች የራሳቸው ቋንቋ ያላቸው፤ ቋንቋቸውም በየግዛታቸው ውስጥ ክስፓኒሽ ቋንቋ ጋር የመገልገያ (official) ቋንቋ ሆኖ ይነገራል። ስፔይን ከፍርንሲስኮ ፍራንኮ ፋሺሽታዊ ሥርአት (1939-1975) ተላቃ ዲሞክራሲን እንደገና መገንባት የጀመረችበት ዘመን አጭር ቢመስልም የዲሞክራሲ ተቋሞቿ ከማንኛውም የአውሮጳ አገር የሚያንስ አይደለም። ይሁን እንጂ ባስኮች የመገንጠልን ጥያቄ ይዘው በመነሳታቸው በስፔይንና በባስኮች መሃል ደም አፋስሽ ሆኖ ለሃምሳ ሁለት አመት የቀጠለ ውጊያ (1959- 2011) ተደርጓል፤ አንዳንድ ሰዎችም ”ባውሮፓ የታየ ረጅሙ ጦርነት ይሉታል“ ። ሌላው በቅርቡ (october 2017) ካታላንን ከስፔይን ለመገንጠል የተደረገው ህዝባዊ ምርጫ ነው። የስፔይን ማእከላዊ መንግስት በህገመንግስቱ ላይ የተካተተውንና ስፔይን የማትከፋፈል አገር መሆኗን የሚገልጸውን አንቀጽ አነቃንቆ ምርጫውን ሻረው።
ለካታላን የመገንጠል ፍላጎት እንደ አንድ ምክኒያት ሆኖ የሚነገረው ካታላን ከምታገኘው የታክስ ገቢዋ ላይ ተወስዶ ለሌሎች ገቢያቸው አነስተኛ ለሆኑ ግዛቶች መሰጠቱ ነው፤ ካታላን ለማእክላዊ መንግስት የምትከፍለውና ማእከላዊ መንግስት ደግሞ ለካታላን የሚሰጠው ገንዘብ አይመጣጠንም የሚል ነበር። ይህ አይነቱ አሰራር በፊዴራልም ሆነ በአሃዳዊ ሥርአት በሚተዳደሩ አገሮች ውስጥ ያለ ነው፤ በስቴቶች/በግዛቶች መሃል ያለውን የሃብት/የኑሮ መራራቅ ለማጥበብ ሲባል ገቢያቸው ከፍተኛ ከሆኑት ተወስዶ ዝቅተኝ ገቢ ላላቸው የሚሰጥ የገንዘብ ዱገማ ነው። ለአብነት ያህል ሃብታም ስቴቶች/ግዛቶች ናቸው፤ ገቢያቸውም ለሌሎች ስቴቶች ይተርፋል (net contributors) ከሚባሉት መሃል ባቫሪያና ሃምበርግ (ከጀርመን)፤ ጄኔቫንና ዙይሪክን (ከስዊስ)፤ ሎምባርዲያን (ከጣሊያን)፤ደቡብ ምስራቅ እንግሊዝን መጥቀስ ይቻላል። እነኚህ ሃብታም ስቴቶች/ግዛቶች ሌሎች መለስተኛ ገቢ ያላቸውን ስቴቶች/ግዛቶች መርዳታቻውን ተደስተውበት በጭብጨባ ይቀበሉታል ማለት ግን አይቻልም፤ በምኖርበትም አገር በተለምዶ ይህ አይነቱ የገንዘብ ዱገማ ”የሮቢንሁድ” ታክስ በመባል ይታውቃል።
መደምደሚያ
ባለፉት ሃያ ሰባት አመት በአገሪቱ ውስት የተሰራው ስራ ዘውጋዊው የፌዴራልን ሥርአት ስር የሰደደ እንዲሆን አድርጎታል፤ የብሄርን ጥያቄ ይዘው ይታገሉ ከነበሩ ብሄሮች መሃል የሚገኘውና ዛሬ ጎልማሳ እድሜ ላይ የደረሰው ትውልድ ከዘውጋዊ የፌዴራል ሥርአት ሌላ አያዋቅም፤ በመጠኑም ቢሆን መብቱን በተመለከተ ያገኘው ጥቅም ስላለ ሥርአቱን ይደግፋል፤ በሥርአቱ ላይ ያለው ግንዝቤ ግን በጣም ጠባብ ነው። እንኳን የኢቲዮጵያ ገበሬ ቀርቶ የዘመኑንም ትምህርት ቀምስናል የምንለውም ቢሆን በፌዴራላዊ አስተዳደር ላይ አብዛኞቻችን ያለን እውቀት እምብዛም ነው፤ በተለይ በአሃዳዊ ሥርአት ውስጥ የምንኖረው። ሃቁ ይህ ከሆነ ስለፌዴራላዊ አስተዳደር ምንነት (ዘውጋዊውንም ጨምሮ) የሚደረገው ውይይት ከወዲሁ መጀመር አለበት፤ ሃያ ስድት አመት የፈጀውን የወያኔን ዘውጋዊ ሥርአት በተወሰነ የጊዜ ገደብ ውስጥ በሚደረግ ውይይት መቋቋም አይቻልም፤ በቂ ግንዛቤ ለማስጨበጥ ውይይቱ ካሁኑ ቢጀመር የሚበጅ ይመስለኛል። በተለይ በጥያቄው ዙሪያ ምርምር ያደረጋችሁ ምሁራኖች ብቅ እንድትሉ የሚፈለግበት ግዜው አሁን ነው፤ በቅርቡ በሚደረገው የቪዥን ኢትዮጵያ አምስተኛ ኮንፈርንስ ላይም ብቅ እንደምትሉ ተስፋ አደርጋለሁ።
ወያኔም ዘውጋዊውን የፌዴራል ሥርአት አሻሽላለሁ ብሎ የማሻሻያ ሃስብ ይዞ ሊቀርብ ይችል ይሆናል። ሆኖም ግን የበላይነቱን የሚያሳጣው ሃሳብ ይዞ ይቀርባል የሚል እምነት የለኝም። ኢህአዴግ እንደጊዜውና እንደሁኔታው በሚለዋወጥ ”የጨዋታ ህግ” በወያኔ ዳኝነት የሚመራ ድርጅት ነው፤ የዲሞክራሲ መርሆችን የማይከተልና እውነተኛ አገር አቀፍ የሆኑ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲዎችም እንዳይፈጠሩ ያደረገ ነው። በኢህአዴግ አሰራር አንድ የጋምቤላ ወይም ከአራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች ውጪ የሆነ ሰው ምንም ብሩህ ፖሊቲከኛ ቢሆንም ጠቅላይ ሚንስተር፤ የውጪ ጉዳይ
6
ሚንስተር ወዘተ የመሆን እድሉ ባዶ ነው። በኢህዴግ ስር የተሰበሰቡ ድርጅቶች እውነተኛ አገራዊ አጀንዳ ያለው ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ ሊፈጥሩ የሚችሉት እንደድርጅት ሳይሆን በግለሰብ ወይም በቡድን ሆነው ከተቀሩት ብሄር ከሚመጡ ግለሰቦችና ቡድኖች ጋራ አንድ አገራዊ በሆነ የፖሊቲካ ፕሮግራም ላይ ስምምነት ከደረሱ በኋላ ነው፤ በዚህ አይነት በሚፈጠር ፓርቲ ውስጥ ከማንኛውም ብሄር/ብሄረሰብ የሚመጣ ግለሰብ በከፍተኛ የሚንስተር ወንበር ላይ የመቀመጥ እድሉ ባዶ አይሆንም። ወደፊት ፌዴራላዊውን ሥርአት እናሻሽል የሚል ስምምነት ላይ ቢደረስም ኢህአዴግ እንደ ህብረ ብሄራዊ ፓርቲ የሚያደርገው የፖሊቲካ ጨዋታ መወገድና በሌላ መተካት ይኖርበታል፤ በየክልሉ ያሉ አራቱ የብሄር ድርጅቶች የሚኖራቸው መብት ግን እንደተጠበቀ ሆኖ መቀጠል ይችላል፤ ውይይትም ሆነ የሽግግር መንግስት በመመስረቱ ሂደትም ላይ ሚና ሊኖራቸው ይገባል።
ምርጫው ፌዴራላዊም ሆነ አሃዳዊ ሥርአት ሁሉም የራሱ የሆነ ችግር አለው፤ የዲሞክራሲ ባህላችንም ሆነ የዲሞክራሲ ተቋሞቻችን ያልዳበሩ በመሆናቸው ችግሮቻችንን የባሰ ውስብስብ ያደርጉታል፤ የዲሞክራሲ ባህላቸውና የዲሞክራሲ ተቋሞቻቸው በላቀ ደረጃ ላይ በሚገኙ አገሮችም ውስጥም ችግሩ ኖሯል ይኖራልም፤ ቀላልና አፋጣኝ መፍትሄ ማግኘት አይቻልም።
የግርጌ ማስታወሻ
i Ethnofederalism: The Worst Form of Institutional Arrangement…? L Anderson – International Security, 2014 – MIT Pres Volume 39 | Issue 1 | Summer 2014 p.165-204
ii Philip G. Roeder, “Ethnofederalism and the Mismanagement of Conflicting Nationalism,” Regional and Federal Studies, Vol. 19, No. 2 (May 2009), pp. 203- 219;
iii Liam D. Anderson (2013). Federal Solutions to Ethnic Problems: Accommodating Diversity. Routledge. ISBN 978-0-415-78161-9.
