በጥፋት ኃይሎች አማራን የማጥፋት ጽንፈኛ ዓላማና አቋም የተነሣ ከፍተኛ የህልውና አደጋ በተጋረጠበት በአማራ ሕዝብ ጉዳይ ላይ ያገባናል የሚሉ ሁሉ በአንድነት ለመሥራት መስማማታቸው በጣም ቢዘገይም አልመሸምና በጣም ደስ የሚያሰኝ ጉዳይ ነው ትልቅም ስኬት ነው፡፡ እንኳን ደስ ያለን! ማለት እፈልጋለሁ፡፡ አስቀድሜ ይህ እንዲሆን ሳያሰልሱ የደከሙትን ወገኖች በእጅጉ ማመስገን እወዳለሁ፡፡

ስምምነት ላይ የደረሱት የአማራ ድርጅቶች መሪዎች ግንዛቤ ሊወስዱ የሚገባቸው ጉዳይ ቢኖር ከምንጊዜውም በላይ አሁን በወያኔ ዓይን ውስጥ መሆናቹህን ነው፡፡ እንኳንና ይሄ አንድነት ተፈጥሮ ይቅርና አማራ በማንነቱ የመደራጀት እንቅስቃሴ ውስጥ መግባቱ በታወቀ ጊዜ እንኳ የአማራ ሕዝብን የትግል አቅጣጫ ለማሳት ወያኔ በሰርጎገቦቹ በኩል ምን ያህል ጥረት ሲያደርግ እንደቆየ በግልጽ የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ይህ እመርታ ሲመዘገብ ደግሞ ወያኔ ምን ያህል ዓይኑ ደም እንደሚለብስና በአንድነት የትግል ኃይሉ ላይ ፈተና ለመጋረጥ፣ ለማደናቀፍ፣ ለማፍረስ እንቅልፍ እንደማይተኛ መታወቅ ይኖርበታ፡፡ ሰርጎ በመግባት፣ መሪዎችን በጥቅም በመግዛት ወይም በማስፈራራት ድርጅቶችን ማፈራረስ ወያኔ የተካነበት የክፋት ሥራው ነው፡፡ በመሆኑም በተቻለ መጠን አንዱ የሌላውን ሰው እያንዳንዷን እንቅስቃሴ ያለአንዳች መዘናጋት በንቃትና በጥንቃቄ መከታተል አስፈላጊ መሆኑ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ድርጅቱ የእያንዳንዱን ኃላፊ የኋላ ታሪክ፣ የትውልድ ሥፍራና ማንነት አብጠርጥሮና አጣርቶ የሚያውቅበት አሠራር ሊኖር ይገባል፡፡

ሌላው ፈተና ሊሆንባቸው የሚችለው ነገር ደግሞ ይህ በእጅጉ ሲፈለግ የኖረ አንድነት ተፈጥሯልና ወደፊት በእርግጠኝነት በምቹ ሁኔታው ተስበው የሚመጡ በርካታ የአማራ ልኂቃን ይኖራሉ፡፡ በዚህ ጊዜ መሥራች አባላቱ በሜሪት (በችሎታ፣ በአቅም ብቃት) ላይ የተመሠረተ የአመራር ቦታ አያያዝን በጸጋ ተቀብለው ሁኔታውን አዎንታዊ በሆነ መንገድ ያስተናግዱታል ወይስ በግል ጥቅም ታውረው ቦታ ላለመልቀቅ ይተናነቃሉ??? የሚለው ነው፡፡ በነገራችን ላይ ይሄ ችግር ከና ከወዲሁ አንድነቱን ለመፍጠር በተደረገው ድርድር ወቅትም ጎልቶ የታየ ችግር ነው፡፡

ሰዎቹ መከረኛ አሳረኛ ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን የሚያስቀድሙ ከሆኑና ለዚህ መከረኛና አሳረኛ ሕዝባቸው እስከሞት ድረስ የታመኑና እራሳቸውን የሰጡ ከሆኑ ያለጥርጥር እንኳን የተሻለ ብቃትና ችሎታ ያላቸው ወገኖቻቸው መጥተውላቸው ይቅርና እራሳቸው ሔደው እያመጡ የሚያስተናግዱ የሚያሳትፉ ይሆናሉ፡፡ የሥልጣንና የዝና ጥመኞች ከሆኑና ይሄንን ሕዝባዊ ትግል የግል ጥቅማቸውን ምኞታቸውን ፍላጎታቸውን ለማስጠበቂያነት ለማሳኪያነት ለመጠቀም ያቆበቆቡ ከሆኑ ደግሞ ቦታውን የተሻለ አቅም ብቃት ችሎታ ላለው ሰው እንዲለቁ ሲጠየቁ ሌላ ምክንያት እየፈጠሩ አንድነቱን ለማፍረስ የሚጥሩ መሆናቸው የማይቀር ነው፡፡

ስለዚህ እንዲህ ዓይነት ችግሮች እንዳይፈጠሩ ለመከላከል ከወዲሁ የመተዳደሪያ ደንብ በመቅረጽ ሥልጣን ወይም የአመራር ቦታ የሚያዘው በጊዜ በተገደበ ተርም (የሥራ ጊዜ) እና በምርጫ መሆኑን መደንገግና ለዚህ ሕግና ደንብ ፍጹም ታማኝ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡ በሥልጣን ላይ ኖሩም አልኖሩ ልዩነት በማይታይበት ቁርጠኝነት እልህና ጽናት ለመታገል የቆረጡ መሆን ይኖርባቸዋል፡፡

ሌላው ይፋ መደረግና በግልጽ መታወቅ የሚገባው ዐቢይ ጉዳይ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለጽኩት የዚህ በአንድነት የቆመው የአማራ ሕዝብ የነጻነት ኃይል ዋናው ዓላማና ግብ እንደ ወያኔና ሌሎች ጠባብና ዘውገኛ ቡድኖች ጠባብና ዘውገኛ ቡድን ሆኖ ታግሎ ሥልጣን በመያዝ አማራን ኢፍትሐዊ በሆነ መንገድ ተጠቃሚ ለማድረግ ሳይሆን በጥፋት ኃይሎች አረመኔያዊ የዘር ማጥፋትና ማጽዳት ዘመቻና እርምጃ ዘሩ እየጠፋ ያለውን የአማራን ሕዝብ ከፈጽሞ ጥፋት ታድጎ ህልውናውን ለመታደግ ለማስቀጠል አንዱ ሲሆን፡፡

ሌላው ደግሞ እጅግ ኋላ ቀርና አደገኛ የሆነውን እንዲህ በመሆኑም በሠለጠነው ዓለም የማይሠራበትን፣ የተጣለውን፣ የተከለከለውን በተፈጥሮው ፀረ ዲሞክራሲ (መስፍነ ሕዝብ) እና ፀረ ሰብአዊ መብት የሆነውን የጎሳ ወይም የዘውግ ፖለቲካን (እምነተ አሥተዳደር) ከሀገራችን አጥፍቶ ወይም አስወግዶ የሀገራችንን ፖለቲካ ልክ እንደሠለጠኑትና አስተማማኝ ሰላምና መረጋጋት ማስፈን እንደቻሉት ሀገራት ዜጎች በዘራቸው ማን መሆናቸው ግምት ውስጥ ሳይገባ በዜግነታቸው ዕኩል ታይተው በችሎታቸው ብቻ በሚመዘኑበት አስተሳሰብ ላይ፣ በዜጎች ሰብአዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶች ላይ ብቻ እንዲመሠረት ለማድረግ መሆኑ በግልጽ መታወቅና በይፋ መነገር ይኖርበታል፡፡

ይሄ መደረጉ የጥፋት ኃይሎች ይሄንን የአማራ ድርጅት ለማስጠላትና መንገዱም ላይ እንቅፋት ለማስቀመጥ የሚነዙትን ስም ማጥፋት ለማምከን ይረዳል፡፡ ጽሑፌን ሳልቋጭ አንድ ማስገንዘብ የምፈልገው ነገር ቢኖር የዚህ የአማራ የአንድነት ኃይል መለያ አርማ (ሎጎ) ሲቀረጽ የአማራን ታሪክ ማንነት ሊያንጸባርቅ በሚችል ሁኔታ መቀረጽ እንዳለበት ማሳሰብ እወዳለሁ፡፡ ለምሳሌ አክሱምና ሰንደቃችን መረሳት አይኖርባቸውም፡፡ የቀረውን ነገር በአማራ ትግል ዙሪያ ከጻፏቸው ጽሑፎች አሟሉ፡፡ ዳይ እንግዲህ አማራ ወደ ማዕበላዊና መብረቃዊ ትግልህ!!!

ድል ለአማራ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!

ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው

amsalugkidan@gmail.com