በሞያሌ በግፍ ስለ ተጨፈጨፉት ወገኖቻችን

የተሰጠ የኃዘን መግለጫ ።

የሚያጽናናኝ ነፍሴንም የሚያበረታት ከእኔ ርቋልና ስለዚህ አለቅሳለሁ ዓይኔ ዓይኔ ውኃ ያፈስሳል ጠላት በርትቶአልና ልጆቼ ጠፍተዋል ሰቆቃ ኤር 116

ይህ ጩኸት የኢትዮጵያ የእየለቱ ጩኸት ሁኖ ሲቀጥል ዓመታት ተቈጠሩ ። ያለፈውን የወገኖቻችን እልቂት ሰምተን እንባችን በወጉ ሳንጠርግ አሁንም በየቀኑ ከሚፈሰው የንጹሐን ደም ባለፈ በሰላማዊ መንገድ በሥራ ቦታቸው ያሉ ወገኖቻችንን በጅምላ ጨፍጭፎ በስሕትት ነው እያለ  የሚንቅና  የሚቀልድ  አካል ልባችንን አድምቶታል ። ይህ ተግባር አንድ አገር እመራለሁ ከሚል አካል ይቅርና በሰው ደረጃ ከሚንቀሳቀስ ጤናማ አእምሮ የሚከናወን ድርጊት አይደለም ።

ኤርምያስ በነበረበት ዘመን መከራና ስቃይ ለሚደርስበት ሕዝብ የጮኸው የኃዘን ጩኸት ፣ ዛሬም በኢትዮያ ምድር የሚጮኽ ጩኸት ነው ። ነቢዩ የሕዝቡን መከራ እያየ ዝም ማለት አቅቶት ይህንን የመከራ እሮሮ አንጎራጎረ ። እኛም ዛሬ በባዕድ ምድር ሁነን የወገኖቻችንን እልቂት ስንሰማ የመረረ ኃዘን ውስጥ ሁንን ነው ይህን አጭር የልብ ስብራታችንን የሚገልጥ መግለጫ ያወጣነው ።

ጉዳዩን አሳዛኝ የሚያደርገው ደግሞ “በስሕተት ነው” የሚለው ቀልድ ነው ።  አንድ የታጠቀ ኃይል በጦር ሜዳ እንደ ተሰለፈ ሠራዊት ይህን ያህል ሰው ለመግደል እንዴት ሊሳሳት ይችላል ? ይህ ከሆነ አእምሮው የተነካ ሰው መሆን አለበት ፣ በሠለጠነው ዓለም እንዲህ የሚያደርግ ሰው አእምሮው የተነካ ይባላል ። በመሆኑም እንደዚህ ዓይነት ሰው ማኅበረሰቡን እንዳይጎዳ ወደ ጥብቅ የእሥር ወይም የጥበቃ ቦታ ይገባል ። መሣሪያ ከእጁ እንዳይገኝ ጥንቃቄ ይደረጋል ። በኢትዮጵያ አእምሯቸው የተነካው የሚባሉት ታዘው የተኮሱት ሳይሆኑ ፣ አዛዦቹና ሰው እንዲገድሉ ሥልጣን የሚሰጠውን “የአስቸኳይ ጊዜ” የተባለውን የጥፋት አዋጅ ያወጡት ግለሰቦች ናቸው ። መሣሪያቸውንና የሚገለገሉበትን አዋጅ መነጠቅ ያለባቸው እነሱ ናቸው ።

አሁን በኢትዮጵያ በሕወኃት የሚመራ ሥርዓት ፥ በሥልጣን ወዳድነት የአዕምሮ መቃወስ የገጠማቸው ግለሰቦች የተጠራቀሙበት ስለ ሆነ ለአገርና ለሕዝብ አደጋ ነው ። ስለሆነም መታሰር ያለበት ይህ ሥርዓት ነው ።

ሥር ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ሳይሆን በሥልጣን አጣለሁ በሽታ የተያዘ ፥ ከጤናማ ሰው አእምሮ ውጭ እንደ አውሬ የሚያስቡ የግለሰቦች ስብስብ እንጂ መንግሥትን በመንግሥትነት ሊመራ የሚችል ሥርዐት አይደለም ።

ይህን የምንልበት ምክንያት ሰውን ያህል ፍጡር ትንፋሽን የሚቈጣጠር አዋጅ አውጥቶ ዘወትር ሰዎችን እያስገደለ “በስህተት ነው” የሚለው አባባል ተቀባይነት ሊያግኝ የሚችለው የእእምሮ ጤና በጎደላቸው ሰዎች ዘንድ ብቻ መሆን አለበት እንጂ ፤ በትክክለኛና በጤናማ አእምሮ የሚያስብ ማኅበረ ሰብ ይህን የዕብዶች ሥርዓት አይቀበልም ። እንዲያውም ሊያውግዘው ይገባል ።

 

 

 

ከሁለት ሰው በላይ በአንድ ቦታ ላይ መቆምና መሄድ አትችሉም የሚለውን አዋጅ ያወጅኩት ለሕዝብ ነጻነት ስል ነው የሚለው አባባል በተጨባጩ ዓለም ላይ ፈጽሞ ተቀባይነት የለውም ። በዚህ አዋጅ መሠረት በትዳር የሚኖሩ ጥንዶች ከትዳር ጓደኛቸው ጋር መሄድ አይችሉም ፥ ሁለት ልጆች ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸውን ትምህርት ቤት ለማድረስ ሁለት ጊዜ መመላለስ አለባቸው ፣ አባት ወይም እናት ከሁለቱ ልጆቻቸው ጋር ሲሄዱ ቢገኙ አዋጁን ጥሳችኋል ተብለው ሊገደሉ ወይም ተደብድበው ሊታሰሩ ይችላሉ። ምክንያቱም ሕጉ ይህን አዋጅ የሚያስከብሩት አካላት የፈለጉትን እንዲያደርጉ ይፈቅድላቸዋልና ነው ።

እነዚህ ወታደሮችም ይህን የመግደል አዋጅ ተጠቅመው ነው ንጹሐን ወገኖቻችንን በጥይት ጨፍጭፈዋል ።  በመሆኑም ነፍሰ ገዳዮች መባል ያለባቸው ወታደሮቹ ሳይሆኑ አዋጁን ያወጀው አካል ነው። መታሰርና መሣሪያውን መቀማት ያለበትም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት እያሉ የሚቀልዱበት ወያኔ የሚመራው ሥርዓትና መንግሥት ነው ። ስለዚህ በሞቱ ወገኖቻችን መሪር ኀዘናችንን እየገለጥን ፣ የሕወኃት የጦር አዛዦችና ባለ ሥልጣኖቹ ለፍርድ እዲቀርቡ ፥ በአውስትራልያ ሀገረ ስብከት ስም እንጠይቃለን ።

በሀገር ውስጥም ሆነ በዓለም ዙሪያ የምትኖር ኢትዮጵያዊ ወገናችን ሆይ ! የትኛውንም ቋንቋ የምትናገር ፥ በየትኛውም ነገድ የምትጠራ ፥ በየትኛውም ሃይማኖት የምታመልክ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ዛሬ በሞያሌና በሌላውም የኦሮሞኛ ተናጋሪ ወገኖቻችን እየፈሰሰ ያለው ደም ያንተ ደም ነው ። ሞታቸው ሞትህ ነው ፣ ስደታቸው ስደትህ ነው ፣ እየተንገላታ ያለው የአንተ አካል መሆኑን እወቅ ። መቃብር የገባው የአንተ የራስህ አካል ነው ። ስለዚህ ዛሬ አንተ ስላልሞትክ ለነገ ዋስትና ያለህ አይምሰለህ ። ነገ ጧት ስትወጣ ከአንድ ጓደኛህ ጋር ስትገናኝና ሁለት ሁናችሁ ትምህርት ቤት ወይም ሥራ እንዲሁም ገበያ ልሂድ ብትል አንተም ሞያሌ እንደ ሞቱት ወገኖችህ ትሞታለህ ፥ እነርሱም አንተን ናቸው ፥ አንተም እነርሱን ነህ ።

ስለዚህ ይህን የኢትዮጵያን ሕዝብ በማያቋርጥ ኀዘን ውስጥ እንዲገባ ያደረግ ሥርዐት ለአንዴና ለመጨረሻ እንዲያበቃ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ እንዲተባበር ፣ የተሰደዱት በያሉበት እርዳታ እንዲያገኙ እንድታደርጉ በግፍ በተጨፈጨፉት ወጎኖቻችን ስም ጥሪ እናቀርባለን ።

የሞቱትን ነፍሳቸውን እንዲምር ለወገኖቻቸውና እንዲሁም ለመላ የኢትዮጵያ ሕዝብ ብርታትን ጽንአትን ኅብረትን እንዲሰጥ ወደ አምላክችን እንጸልያለን ። የፖለቲካ መሪዎች ፥ የሰብአዊ መብት ተከራካሪዎች ፥ ኢትዮጵያውያን የፖለቲካ አቀንቃኞች ሁሉ የሕዝባቸውን መከራ ለማሳጠር ሲሉ እንዲተበባበሩና ይህን ሰላማዊ የሕዝብ ትግል ከዳር እንዲያደርሱ በቤተ ክርስቲያን ስም በታላቅ ጩኸት ጥሪ እናቀርባለን ።

አባ ጴጥሮስ

የአውስትራልያና የኒውዝላንድ ሊቀ ጳጳስ ።

ሜልቦርን አውስትራልያ