ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅ

የመለስ የነብስ አባት ፕ/ር ኤፍሬም ይስሀቅ ሰሞኑን ደግሞ ብቅ ብለዋል፡፡ መለስ ባይኖርም ድርጅቱን ህውኃትን ለመታደግ፡፡ አስር አመት እንዲህ ሩቅ ሆኖ በምርጫ 97 ማግሥት የፈጸሙት የተረሳ መስሎአቸው ይሆን ወይንስ የእምነት ነገር የዓላማ ጉዳይ ሆኖባቸው አይኔን በጨው ብለው መዝለቃቸው፡፡  በማናቸውም አለማዊ ነገሮቸ ተደልሎ ወይንም ፈርቶ እውነትን ለመናገር የማይደፍር ሰው ሽማግሌ ሆኖ በአስታራቂነት ሊሰልፍ፣ ስለ እርቅና ፍቅር ሰላምና መቻቻል  በአደባባይ ሊደሰኩር የሞራል ብቃት አይኖረውም ፡፡ በአለባበሳቸውም ሆነ በአነጋገራቸው ፈጣሪን አማኝ የሚመስሉት ፕ/ር ኤፍሬም ግን እርሳቸው ብቻ የሚያውቁት እውነት ከግለሰብ ህይወት ጋር በተቆራኘበትና መናገራቸው ወሳኝ በሆነበት ወቅት( ብርቱካን ዳግም በታሰረችበት) አንድ መለስን ፈርተው ለመናገር ሳይደፍሩ ቀሩ፡፡  አንድ ቀን እናገራለሁ እንዳሉም እዚህ ደረሱ ፡፡  

ፕ/ር ኤፍሬም የቅንጅት አመራሮችን አስፈቱ ተብሎ ለሙገሳና ሽልማት በበቁበት ጉዳይ አንድም ዋሽተዋል፣ሁለትም ሀቅ ደብቀዋል፡፡ ሽማግሌ ዋሽቶ ያስታርቃል የሚል ሀገራዊ ብሂል ቢኖርም በዚህ መልክ የተፈጸ እርቅ አንዱን ጠቅሞ ሌላኛውን ሊጎዳ ከሆነ ከዚህ አልፎ የተደበቀው የእርቁ ሂደትና እንዴትነት በአንደኛው ሰው ህይወት ላይ አደጋ ሲደቅን  አስታራቂዎቹ ፈጥነው የለም የሆነው እንዲህ ነው የተፈጸመው በዚህ ሂደትና መልክ ነው ሊሉ ማንም ሳይሆን የራሳቸው ህሊና ያስገድዳቸዋል፡፡ ፕ/ር ኤፍሬም ግን ይህን ማድረግ አልቻሉም፡፡ አልቻሉም ብቻ ሳይሆን በአቶ መለስ ሞት ማግስት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቆይታ ነገሩ እንዴት እንደተወጠነ በምን ሁኔታ እንደተጓዘና ከፍጻሜ እንደደረሰ ከራሳቸው ቃል ጋር በሚቃረን ሁኔታ ዋሽተዋል፡፡ ሰዎች ለምን አትናገርም ይሉኛል አንድ ቀን እናገራሉ በማለትም የተደበቀ ምሥጢር እንዳለ አመላክተውን ያ አንድ ቀን ግን እስከ ዛሬም አልከሰት ብሎ ርሳቸው ግን ለሌላ ተመሳሳይ ህውኃት አድን ዘመቻ ሰሞኑን ተከስተዋል፡፡

ጉዳዩ ሰፊ በመሆኑ በራሱ አንድ መጽኃፍ የሚወጣው ነው፡፡ስለሆነም ዋሽተዋል ሀቅ ደብቀዋል ያልኩትን በአጭሩ ለማሳየት ማስረጃ ላቅርብ፡፡አቶ መለስ የምርጫ 97ን ውጤት በጠመንጃ ቀልብሰው አሸናፊዎቹን ሰብሰበው ቢያስሩም እፎይ ብለው መተኛት አልቻሉም፡፡ እንደውም የውጪውም የውስጡም ተቃውሞ, የደጋፊዎቻቸው ማእቀብ ወዘተ ያልገመቱት ሳይሆንባቸው አልቀረም፡፡ ከዚህ ተገላግለው የኢትዮጵያ ምሊኒየም የተባለውን በአል ለገጽታ ግንባታ ለማዋል አቅደው ትያትር ሲጽፉ ፕ/ር ኤፍሬምን በመሪ ተዋናይነት መረጡ፡፡ በእውነቱ ከደራሲና አዘጋጁ ፍላጎት አንጻር ፕ/ር ኤፍሬም የተሰጣቸውን ገጸ ባህርይ በሚገባ ከውነዋል ማለት ይቻላል፡፡ ከአሜሪካ አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት ከቤተ መንግስት ቃሊቲ እየተመላለሱ ሲላቸው መጽኃፍ ቅዱስ እየጠቀሱ ሲላቸውም እያለቀሱ በሚገባ ተውነዋል፡፡

ለዚህም ሳይሆን አይቀርም አርብሀምሌ 1 3/ 1999 ዓም በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ሲነበብ የዋለው መግለጫ / / ኤፍሬም ይስሀቅና ከሀገር ሽማግሌዎች ተብሎ የተገለጸው፡፡ በወቅቱ የሁሉም ሰው ትኩረት የእስሮቹ ከቃሊቲ መውጣት ላይ ስለነበረ  እነዚህ መሰል ጉዳዩች ልብ አልተባሉም እንጂ ፕሮፌሰሩና ሌሎቹ ሽማግሌዎች ሁለት የተለያየ አካላት ተደርገው መገለጻቸው በራሱ የሚያመላክተው ነገር ነበረው፡፡

ክውሸቶቹ ከብዙ በጥቂቱ፡(በአቶ መለስ ሞት ማግሥት ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር በባደረጉትቃለ ምልልስ ከተናገሩት)

1ቅንጅቶቹ ባለመስማማታቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄደ

ከላይ በገለጽኩት  ሀምሌ 13/1999 ዓም በወጣው መግለጫቸው  የሀገር ችግር ለመፍታት ፍቱን መድሀኒቱ ባእዳን ሳይሆኑ የሀገር ተወላጆች መሆናቸውን ያመንን እኛ የሀገር ሽማግሌዎች ከመንኛውም ፖለቲካዊ ኃይማኖታዊ አድሎና ጫና ነጻ በሆነ መንፈስ በራስ ተነሳሽነትና በጋለ የሀገር ፍቅር ስሜት ተነሳስተን ምርጫ 97 ተከትሎ በሀገራችን በተፈጠው አለመግባባት ችግሩ ሰላማዊ እልባት አንዲያገኝ በሀገራዊ ወግ መሰረት መፍትሄ ለማፈላለግ 18 ወራት ጥረት ስናደርግ ቆይተናል፡፡በማለት ሂደቱ የፈጀውን ግዜ ገልጸዋል፡፡

እንደ ሰሞነኛዋ የአባዱላ ክስተት የማስላት ችግር ካላገጠመን በስተቀር እስረኞቹ ከተፈቱበት ወደ ኋላ ሄዶ ሲቆጠር ሽምግልናው የተጀመረው የካቲት 1998 ዓም መሆኑን እናገኛለን፡፡ ሂደቱን የተከታተለ ሁሉ እንደሚያስታውሰው ደግሞ ክስ የተመሰረተው ታኀሣሥ 7/98 ነው፡፡ በመሆኑም  ቅንጅቶች ባለመስማማታቸው ጉዳዩ ወደ ፍርድ ቤት ሄደ የሚለው ያገጠጠ ውሸት ከፕ/ር ኤፍሬም የሚጠበቅ አልነበረም ፡፡

2- ከዚያ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ‹‹ጉዳዩ ከእጄ ወጥቷል፤ ፍርድ ቤት በያዘው ጉዳይ ጣልቃ አልገባም፤›› አሉኝ፡” ብለዋል ፕ/ር በዛው ቃለ ምልልሳቸው፡፡ ይሄ እውነት ቢሆን ኖሮ ሽምግልናው መጀመር የነበረበት ፍርድ ቤቱ የእድሜ ልክ እስር ፍርዱን ከሰጠበት ሀምሌ 9/1999 በኋላ ነበር፡፡ ነገር ግን ፕ/ር በመግለጫቸው አንደገለጹት ጉዳዩ አስቀድሞ በአስራ ስምንት ወራት ሂደት ያበቃ ስለነበር ሀምሌ 9 የተፈረደባቸው እስረኞች ከቃሊቲ የወጡት በአራተኛው ቀን ሀምሌ 13 ነው፡፡ ፕ/ር ይህን ሲናገሩ ርሳቸው ባይጽፉትም ቢያንስ ሳያዩት አይቀርምና መግለጫው ላይ የሰፈረውን ማስታወስ ነበረባቸው፡፡ አንደ ፕ/ር ኤፍሬም የሪርተር ጋዜጣ ገለጻ ከሆነ ሽምግልናው ተጀምሮ የተጠናቀቀው በአራት ቀናት ውስጥ ነው ማለት ነው፡፡ ሌላው ቢቀር 18 ወራት በፈጀ የሀገር ባህል ወግ መሰረት የሚለውን መግለጫቸውን እንደምን ሊዘነጉት በቁ፡፡

የፕ/ር ውሸት በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ እስረኞቹ ከቃሊቲ የወጡት በተፈረደባቸው አራተኛ ቀን መሆኑን ማስታወስ ተስኖአቸው እስከሚፈረድባቸው ጠበቅን፡ ብለዋል፡፡ ይሄ በዚሁይብቃኝና ለሁለተኛው ትንሽ ማስረጃ፡፡

ፕ/ር ኤፍሬም ለአመታት የደበቁት ሀቅ ምን ይሆን፤

በዛው ቃለ ምልልስ ላይ “አንድ መግለጽ የማልፈልገው ነገር አለ፡፡ ወደፊት የምናገረውና ጠቃሚ የሆነ ነገር አለ፡፡ ብዙ ጊዜ የቅንጅት ሰዎች ‹‹ለምን አትናገርም?›› የሚሉት፡፡”በማለት የደበቁት ሀቅ ጠቃሚ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አንድ ነገር ጠቃ የሚሆነው በወቅቱ ሲሆን ነው፡፡ አቶ መለስ ብርቱካን በሀገር ሽምግልና ወግ መሰረት ይቅርታ ጠይቄ መፈታቴን አልክድም በማለቷ እንዴት ተደፈርኩ ብለው እንደ ወንበዴ ከመንገድ አሳፍነው ማሰራቸው አላንስ ብሎ ሽምግልና ብሎ ነገር አልነበረም እስከሚል ክህደት ዘልቀው በመገናኛ ብዙኃን ሲደነፉ ምስጥር ያሉትን ለመናገር ወኔ ቢያጥራቸው በመግለጫቸው የገለጹትን ተንተርሰው ሽምግልናማ ነበር እንደውም 18 ወራት የፈጀ ብለው መናገር አለመቻላቸው ያከበርናቸውን ያህል አንድንንቃቸው የወደድናቸውን ያህል እንድንጠላቸው ያደረገ የትናንት ድርጊት ነው፡፡

ወደፊት የምናገረው ጠቃሚ ነገር አለ ካሉ በኋላም መለስ ሞቶ እንኳን በዝምታቸው መቀጠላቸው ነገሩ ምን ያህል ከባድ ቢሆን ነው የሚል ጥርጣሬ የሚያጭር ነው፡፡ በስመ የሀገር ሽማግሌዎች ዋና  ተወናይ የነበሩት እርሳቸው ብቻ ነበሩና የቤተ መንግሥቱን ደጅ መርገጥ ከመለስም ጋር መነጋገር የሚችሉት ሁለቱ በግል የሸረቡት ጠሀይ ሊሞቀው ሀገር ሊያውቀው የማይገባ ሴራ ነበር ይሆን?

ፕ/ር አንደኛ እድሜአቸው ገፍቷል፡፡ሁለተኛ ፈጣሪን አማኝ ነኝ ይላሉ፡፡ እነዚህ ሁለቱም በአውነት መንገድ የሚያስኬዱ እንጂ ከእውነት ጋር ሆድና ጀርባ ለመሆን የሚፈቅዱ አይደሉም፡፡ አለማዊውን ህይወት አስንቀው ለመንፈሳዊው እንዲያደሉ እንጂ በአለማዊ ነገር  እንዲታለሉም እንዲደለሉም የሚገፋፉ አይደሉም፡፡በፍርሀትም ሆነ በምን ቸገረኝነት አለያም ወዳጅን ባለማስከፋት ስሜት እውነትን በሀሰት ለመለወጥ የሚፈቅዱም አይደሉም፡፡ ፕ/ር ጋር ግን መሆን አልቻለም፡፡

እናም ክቡር ፕ/ር ኤፍሬም ለመታመን ሆኖ መገኘት እንደሚያሻ ለእርስዎ መነገር ያለበት አይመስለኝም፡፡ ስለሆነም ዛሬ ሊያደርጉት ለሚያስቡት አመኔታ ለማግኘት ትናንት የዋሹትን ያጥሩ የደበቁትን ሀቅ ይናገሩ፡፡ ሞት ደግሞ አይቀሬ ነው፡፡