መጋቢት 9 ቀን፤ 2010 ዓ/ም
ከጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር የተሰጠ መግለጫ
ሃገራችን ኢትዮጵያን ለ27 አመት በዘር ከፋፍሎ አስጨንቆ እየገዛ ያለው የወያኔ ቡድን በአገሪቱና በህዝቡ ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ ፈጽሟል። አሁንም ህዝቡን እንደጠላት ሃይል ጅምላ ጭፍጨፋውን አጠናክሮ ቀጥሎበታል። በዚህ በያዝነው ሳምንት በሞያሌ የተፈፀመው ጭፍጨፋ የወያኔ ተደጋጋሚ ሕዝብን በፍርሃት ዓለም ጠርንፎ እየቀጠቀጡ የመግዛት አላማና ፖሊሲ እንጂ የጥቂት ወታደሮች የአንድ ቀን ስህተት ነው ብለን አናምንም። ባለፉት ጥቂት ሳምንታት ብቻ ሰላማዊ ወጣቶችን በወልድያ፣ በመርሳ፣ በአምቦ፣ በሃማረሳ፣ በለቀምቴ፤በሃርር አሁን ደግሞ በሞያሌ ሰላማዊ ዜጎች በግፍ ተጨፍጭፈዋል። ወያኔዎች ይህን ዘግናኝ ጭፍጨፋ እያካሄዱ ያሉት በገበያ ቦታዎችና በሃይማኖት በዓላት ታጣቂዎችን በማሰማራት ህዝቡን በማሸበር ነው። ይህን የወያኔ እኩይ ተግባር የጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር በጥብቅ እያወገዘ ገዳይ ወታደሮቻቸውና አዛዦቻቸው ለፍርድ የሚቀርቡበት ቀን ሩቅ እንደማይሆን ያረጋግጣል። ገዳዮችና ተባባሪዎቻቸው ከወንጀላቸው ሊያመልጡም አይችሉም። የአካባቢው ህበረተሰብም የወንጀለኞችንና ተባባሪዎቻቸን ማንነትና አድራሻቸውን መረጃ በማቀበል እንድትተባበሩን እናሳውቃለን።
ህወሃት የሚመራው የወንበዴ ቡድን በቅርቡ ለይስሙላ ባሳወጀው የአስቸኩአይ ጊዜ አዋጅ ሁለት ሶስተኛ የፓርላማ ድምፅ አልሞላለት ብሎ እንደልማዱ ሲያጭበርብር በራሱ አፈ ጉባኤ አባዱላ ገመዳ የቁጥር መደመርና መቀነስ በአደባባይ ሲዋሽና ሲውጀለጀል ከዚያም ሲጨንቀው ይቅርታ ሲዘላብድ ተስተዉሏል። ህዝቡ ወሸታቸውን በማህበራዊ መገናኛ መሳለጫ ሲያደርጋቸው በቀጥታ የተላለፈውን ድምጽ ቆጠራ ሽምጥጥ አድርገው በሰአታት ውስጥ 395 ነው እንጂ 346 ያልነው ተሳስተን ነው ብለው ለማስተባበል በየመድረኩ ሲወሽክቱ ተስተውለዋል። ወያኔዎች ሕዝቡን በሃሰት በማታለል፣ህጋዊ ለመምሰል ሞክረዋል ይሁን እንጂ ይህኛው እንደበፊቱ አልተሳካላቸውም።
በሃሰት ጸደቀ የተባለውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በመጠቀም በአገሪቱ፤ በተለይ በኦሮሞና በአማራ ክልል ብለው በሚጠሩት ህዝብ ላይ ጦርነት አውጀውበታል። ወደ ሰላሳ የሚጠጉ ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያንና ሌሎችን ቋንቋ የሚናገሩ በዚህ ገዳይ ህወሃት ቡድን ተገድለዋል። በሌላ በኩል ዘመቻዉን ወደ አማራ ክልላቸው በማዞር ይሄ መንግስት ነኝ ባይ የህወሃት ወንበዴዎች ቡድን በአሁኑ ሰዓት አማራውን ትጥቅ ማስፈታት በሚል በተለይ በጎጃምና በጎንደር ሰላማዊ አርሶ አደር ዜጎችን በከባድ መሳርያ ሳይቀር እየታገዘ ጭፍጨፋውን ቀጥሏል። ባሳለፍነው ሳምንት በጎጃም ዱርቤቴ አቶ ደርበው አየለ የተባሉ አዛውንትን ትጥቅ ለማስፈታት የተንቀሳቀሱት የባንዳ ሃይሎች በጀግናው አርበኛ ደርቤ አንድ በአንድ ድባቅ ቢመቱም ሃይሉን እያጠናከረ በሌሎች አካባቢዎች ላይ ዘመቻውን ቀጥሎበታል። በዚህ ረገድ በተለይ የህዝቡን ትግል የምትደግፉ የብአዴን ካድሬዎችና ከውጭ ሆናችሁ ትግሉን የምታግዙ ሃይሎች ለህብረተሰቡ መረጃውን እየተከታተላችሁ በማቀበል የወያኔን ዘመቻ እንድታከሽፉ አደራ እንላለን። በዚህ ቀውጢ ቀን ህዝቡን የሚያስገድሉ ባንዳ ተላላኪዎችንም ማንነትና ሃላፊነታቸውን መረጃ በማቀበል እንድትተባበሩን እንሳስባለን።
ወያኔ በህዝባዊ ማእበል ሲወጠር እስረኞችን በመፍታት ተራምጅ ለመምሰል ቢስተዋልም ስይጣናዊ ስራውን እንደገና አጠናክሮ ጀምሮታል። ወያኔ የሚመራው ቡድን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያስፈለገበት ምክንያት ህግ ለማስከበር ነው ቢልም ሃቁ ግን የራሱን ህገ-መንግስታዊ ስርአቱን ሙሉ በሙሉ በሚባል መልኩ ወታደራዊ ያደርገበት መሆኑን አሳይቷል። አስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የህዝቡን መሰረታዊ መብት ከማገዱም በላይ የራሱን ድርጅት በተለይ ያገለግሉት የነበሩትን ብአዴንና ኦህዴድ አባላትና አመራሮችን በቁጥጥር ስር ለማዋል ታልሞና ታቅዶ በጥናት የተደረገ መሆኑን እናምናለን። ለዚህም ማሳያው ባሰለፍነው ሳምንት በኦሮሞ ክልል በተደረገው ህዝባዊ ተቃዎሞ የኦህዴድ አመራሮችን ጨምሮ ማሰሩ ነው። የክልሉ ባለስልጣናትም ጭፍጨፋውን ማውገዝ እንኳን አልቻሉም። ይህ የወያኔ አደገኛና መሰሪ አካሄድ የኢህአዴግ አጋር ድርጅቶችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮ የአገዛዝ ቀንበሩን ለማስቀጠል የታለመ ነው ብለን እናምናለን። ስለሆነም ህዝቡን የምትወክሉ ካድሬዎች በተለይ የክልሎች ታጣቂዎችና ፖሊስ ሃይል አባላት ሚናችሁን ለይታችሁ ሳይመሽባችሁ ትግሉን በይፋ እንድትቀላቀሉ እንሳስባለን። ከህዝቡ ወግናችሁ ሴራውን ለማክሸፍ ጥረት ካላደረጋችሁ ወያኔ አንድ በአንድ እያሳደደች እንደምትጨርሳችሁ የማይቀር ሃቅ ነው።
ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ፦እንደ ጥንቱ በአንድነት ታግለህ ጠላትህን ወያኔን በአስቸኳይ ማውረድ ይጠበቅብሃል። የኢትዮጵያ ሕዝብ በፍርሃት እንደማይገዛ ታሪካችን ህያው ምስክር ነው።አትዮጵያውያን በፍጹም በፍርሃት አይገዙም። የወያኔ የመውደቂያው ጊዜ ይረዝም ይሆናል እንጂ መውደቁ አይቀረም ስለዚህ መውደቁ ይፋጠን ዘንድ ህዝቡ በአንድ ላይ ተባብሮ እንዲታገል ጥርያችንን እናስተላልፋለን።
ጀግናው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ፣ በተቻለህ መንገድ ሁሉ ይሄ መንግስት ተብየው በሕዝባዊ ስርዓት እንዲተካ ታገል። መንግስት ነኝ የሚለው ጉጅሌ ገዢ ቡድን ምንም አይነት ህጋዊ መሰረት ስለሌለው ለተላላኪዎቻቸውና ለባንዶች አትታዘዝላቸው፤ትጥቅህንም ለወያኔ አትፍታ። አማራ ሆነህ ትጥቅህን ፈታህ ማለት ቢለዋ በአንገትህ እንደመሳል ነው። በወያኔ በከንቱ ደማቸው ለፈሰሰው ንፁሃን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ነፍስ ይማር እያልን፤ለቤተሰቦቻቸዉ መጽናናትን እንመኛለን።
የህዝብ ትግል ያሸንፋል! ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር !!
የኢትዮጵያ ሕዝብ ተዋዶና ተስማምቶ ለዘለዓለም ይኑር!!
ጎጃም ዓለምአቀፍ ትብብር፣ መጋቢት 9፣ 2010 ዓ/ም
Gojjam Global Alliance
