March 14, 2018

የነዳጅ ምርቶች እንዳይንቀሳቀሱ ለማድረግ ትላንት የተጀመረው አድማ ዛሬም ቀጥሎ ዋለ፡፡ አድማው በዛሬው ዕለት ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ ሲውል፣ ነዳጅ አመላላሽ ቦቴ መኪኖች እንቅስቃሴያቸው ተገትቶ ተስተውሏል፡፡ በሞያሌ ከተማ ቦረና ዞን ውስጥ በአጋዚ ጦር የተፈጸመውን ጭፍጨፋ ተከትሎ፣ የተጠራው ይኸው አድማ፣ በህግ ሽፋን ግድያ እየተፈጸመበት የሚገኘውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅም ይቃወማል፡፡ አድማው ከመጋቢት 4 እስከ መጋቢት 10 ቀን 2010 ድረስ እንደመጠራቱ፣ ከዚህ በኋላም በተከታታይ ቀናት ተተግብሮ ይውላል፡፡

ዛሬ ለሁለተኛ ቀን ቀጥሎ የዋለውን የነዳጅ ምርቶችን እንቅስቃሴ የማገድ አድማ ተከትሎ በመላ ሀገሪቱ ከፍተኛ የነዳጅ እጥረት ተከስቶ ተስተውሏል፡፡ በአድማው የተነሳ አዲስ አበባን ጨምሮ ሌሎች የክልል ከተሞች የነዳጅ እጥረት ያጋጠማቸው ሲሆን፤ መኪኖች ነደጃ ፍለጋ ወዲያ ወዲህ ሲንከራተቱም ተስተውለዋል፡፡ በተለይ በዋና ከተማዋ አዲስ አበባ የሚገኙ የነዳጅ ማደያዎች በረዣዥም የመኪና ሰልፎች መጨናነቃቸውን የሚጠቁመት መረጃዎች፤ ማደያዎቹ ነዳጅ በማጣታቸው የተሽከርካሪዎችን ሰልፍ ሲበትኑ እንደነበር መረጃዎቹ ያክላሉ፡፡

በአንዳንድ ማደያዎች የተገኘችውን ጥቂት ነዳጅ ለመቀራመት የመኪና ግፍያ እና እሽቅድድም ሲደረግ ማየታቸውን የዓይን እማኞች ተናግረዋል፡፡ በአዲስ አበባ አብዛኞቹ ማደያዎች ለመጠባበቂያ ብለው አስቀምጠውት የነበረው ነዳጅ በአድማው የተነሳ በፍጥነት በማለቁ፣ የነዳጅ እጥረቱ በሚቀጥሉት ቀናት ተባብሶ ሊቀጥል እንደሚችል ተነግሯል፡፡ የነዳጅ ምርቶችን ከሱዳን እና ጅቡቲ ወደ ሀገር ቤት የሚያመላልሱ ቦቴ መኪኖች ቀደም ሲል በተላለፈላቸው መመሪያ መሰረት በዛሬው ዕለትም ምንም ዓይነት የመኪና አንቅስቃሴ ሳያደርጉ መዋላቸውን መረጃዎች ይገልጻሉ፡፡.

የአድማውን መመሪያ በመተላለፍ ለመንቀሳቀስ የሞከሩ አንዳንድ ነዳጅ ጫኝ ከባድ መኪኖች፣ የህዝባዊ ትግሉ ባለቤት በሆነው የህብረተሰብ ክፍል የማስጠንቀቂያ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ከመረጃዎች ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ በኦሮሚያ ክልል እየተካሄደ ያለውን ህዝባዊ ተቃውሞ በማስተባበር እና የትግል አቅጣጫ በማስቀመጥ ትልቅ አስተዋጽዖ እያደረገ የሚገኘው ቄሮ፣ አድማው እስከመጪው ሰኞ ድረስ እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡ በቄሮ የተጠራው ይኸው አድማ፣ በአገዛዙ ላይ የኢኮኖሚ እና የፖለቲካ ኪሳራ እያስከተለ እንደሚገኝ የታወቀ ሲሆን፤ አድማው የተጠራው ለአንድ ሳምንት መሆኑ ደግሞ፣ በቀጣይ በአገዛዙ ላይ የሚደርሰውን የፖለቲካ ጫና እጥፍ ድርብ እንደሚያደርገው ተገልጿል፡፡

BBN news March 14, 2018