ከአራቱ የሸዋ ዞኖች ህዝብ (5,947,455) ከግማሽ በላይ የሚሆነው ማለትም 3,384,569 የሚኖረው አዲስ አበባ ነው። አዲስ አበባ የሃገሪቱ ዋና ከተማ፣ የፖለቲካና ኢኮኖሚ ባህላዊና ምሁራዊ በረከቶች አስተሳሰቦች የሚቀረፁበት፣ የሚፋጩበትና የሚወቀሩበትና የሚወሰኑበት ማዕከል ናት።
ሀ). የአዲስ አበባ ህዝብ ዝምታ ምንጩ ምንድነው?
በተደጋጋሚ ጊዜ እንደምንሰማውና እንደምናነበው የአዲስ አበባ ህዝብ የህዝባዊ እምቢተኝነቱ አለመሳተፉ ፖለቲከኞቻችንን ማስከፋቱን ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ በድፍን ከመውቀስ በፊት የዝምታውን ምክንያት ነቅሶ ማውጣቱ ይበጃል።
የአዲስ አበባ ህዝብ ኢትዮጵያዊ ነው። እንደማንኛውም የኢትዮጵያ ህዝብ የወያኔያዊው አፓርታይድ ስርዓት ተጠቂም ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ የሚመጥነው ፖለቲካ አላገኘም። ፓለቲካዊ ማበረታቻ አልቀረበለትም። የላቀ አስተሳሰብና ፈጠራ የሚከውን ህዝብን በ19ኛው ክፍለ ዘመን ኋላ ቀር ፖለቲካ ለመንዳትም አይቻልም። የአዲስ አበባ ህዝብ ያልጣመው፣ የማይጥመውና ሊጥመውም የማይችል የጎሣ ፖሊቲካና የወያኔ መርዘኛ “የጎሣ ፌደራሊዝም” ርዕዮት ነው። ለሚደርሱበት ፖሊቲካዊ ጭቆና፣ ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛና ማህበራዊ እንግልት ምክንያቱ ይህ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ከአመፅ መንደሩና ርቆ የሚታየው የህወሃት-ወያኔ አፓርታይዳዊና ብሄራዊ ግፍና በደል ተጠቂ ባለመሆኑም ሣይሆን ከበፊቱ የስርዓት ለውጥ የቀሰመው ልምድ የህወሃት-ወያኔ አፓርታይዳዊ ግፍና በደል በሌላ ቡድን የግፍና በደል ስርዓት አለመተካቱን ማረጋገጥ ስለሚፈልግ ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ የወያኔ ተጠቂና መብትና ነፃነቱ እንደሌሎቹ ወንድሞቹ ኢትዮጵያውያን በወያኔ የተገፈፈ ነው። ‘የትም ፍጪው፤ ዱቄቱን አምጪው’ በሚል ፖለቲካዊ ዘይቤ መካተትና መዘወርን ስላልፈለገም ነው። የአዲስ አበባ ህዝብ ከአመፅ መንደሩ ያራቀው የህወሃት-ወያኔ አፓርታይዳዊና አረመኔያዊ ግፍና በደል ስርዓት የሆነውን መርዘኛ “የጎሣ ፌደራሊዝም” አሽከርካሪውን በመቀየር መኪናውን እንዳለ እንጠቀምበታለን የሚለው የጎሣ ፖለቲከኞች ፌዝ ነው። የህዝብን አብሮና ተሳስቦ የመኖር ባህላዊ እሴትን የሚርደውን፣ ህዝብን በጎሣ ከፋፍሎና የህዝብን አንድነት በመበተን በልዩነት ቅርንጫፍ ላይ የሚንጠላጠለውን “የጎሣ ፌደራሊዝም” አድሶ ለመጠቀም የጎሣ ፖለቲከኞች ሙጥኝ ማለታቸው ነው። በጎሣ ፖለቲከኞችና እነርሱን እሹሩሩ የሚሉ ሌሎች ፖለቲከኞች የአዲስ አበባ ህዝብ የከተማውን ስያሜ ከመቀየር እስከ ማባረር የሚያስፈራሩትን፣ በቆረቆረውና ባለማው ከተማ መጤና ሠፋሪ በሚሉ ቅፅሎች የሚያጣጥሉትን፣ ጉሮሮውን በአቅርቦት ማዕቀብ እንዘጋለን እያሉ በሚዘፍኑበትና መብቱን ለመግፈፍ በቋመጡ ህልመኞች የተሳሳተ ፖለቲካዊ ዕይታ ሣቢያም ነው።
ለ). የአዲስ አበባ ህዝብ የፖለቲካዊው አመፅ እንዴት ሊሣተፍ ይችላል?
የአዲስ አበባ ህዝብን በህዝባዊው ተጋድሎ እንዲሳተፍ ከተፈለገና አልሳተፍም አለ ብለን በጅምላ ከማውገዛችን በፊት የሚከተሉት ሁኔታዎችን ማሟላቱ ብልህነት ነው።
1. ለጋራ ትግል የጋራ አላማና አርማ ቀዳሚው ነው። የጋራ ዓላማው ኢትዮጵያዊነት፤ ዓርማውም የኢትዮጵያ ባንዲራ ሲሆን
2. ’የራስን ዕድል በራስ መወሰን’ የተሰኘውን ኋላ ቀርና ጊዜ ያለፈበትን ወያኔያዊ “የጎሣ ፌደራሊዝም” መርሆ ‘የኢትዮጵያን ዲሞክራሲያዊ መፃኢ ዕድል በዲሞክራሲያዊና ፍትሃዊ ምርጫ መወሰን’ በሚል ዘመናዊ ስልት መቃኘት ሲቻል
3. የኢትዮጵያ የግዛት አንድነትን የማይደራደር ፖለቲካዊ ንድፍ ሲቀመርና በትግሉ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የሚዳሰስና የሚጨበት ሲሆን
4. የተቀናጅ ወያኔያዊ ጥቃትን የሚገታ ወይም የሚቀንስ ሁሉን አቀፍ የተቀናበረ የጋራ የትግል ታክቲክና ስልት በማዕከል መንደፍ ሲቻል
5. የመከራችን ምንጭ የሆነውን “የጎሣ ፌደራሊዝም” በመሻር በምትኩ የህግ የበላይነት የሚሰፍንበትን፣ ነፃነትና መብት የሚከበርበትን ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ማስፈን፤ ከዘር፣ ከጎሣና ከሃይማኖት ተፅኖ ነፃ የሆነ በህዝባዊ ተሳትፎ ላይ የተመሰረተና በዲሞክራሲያዊ አብላጫ ድምፅ የሚተገበር ዲሞክራሲያዊ ህዝባዊ ምርጫ በመደረጉ ላይ የጋራ መግባባት ሲፈጠር
ከዚህ ውጭ ለማን፣ ለምንና ከማን ጋር ሆኖ ማንን ህዝቡ እንደሚታገል ግልፅ ባልሆነበት መንገድ በድፍኑ የአዲስ አበባ ህዝብን መውቀሱ ፍትሃዊ አይደለም። የጎሣ ፓለቲከኞች በአርማቸው ስር “ህዝባቸን” የሚሉትን አካል ለይተው ሃገራዊ ሣይሆን ጎጣዊ የአመፅ ጥሪ አልተሳተፍክም ብሎ ማብጠልጠል አንድም አለማወቅ ሌላም ፓለቲካዊ ጅልነት ነው። የተንሻፈፈ ፖለቲካዊ አመለካከትና በድብቅ የተከወነ ነገር ግን ግልፅ ሆኖ በራሱ ለራሱ በሚናገር ፖለቲካዊ መጋረጃ ስር ተደብቀን የምናቀርበው የፖለቲካዊ ትግል ግብዣ እንኳን ተጋባዡን ጋባዡን አያረካም። ግልፅነት የሌለው ፖለቲካ፤ የፖለቲካ አመንዝራነትና ፖለቲካዊ ቁማርም ነው።
የጋራ ኑሮ እንጂ የጋራ ሞት የለንም። ወያኔን በሌላ ወያኔያዊ ግን በተለየ ስያሜ ሣይሆን ወያኔን በህዝባዊ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ለመተካት ብቸኛ አማራጩ ህብረት ብቻ ነው። ህብረትንም ለመፍጠር ዓላማን ማቀናጀት፤ ህብረቱንና ፖለቲካዊ ዓላማውን፣ ገድሉንና ድሉን ህብረ – ብሄራዊና ኢትዮጵያዊ ማድረግ ብልህነትና የወያኔን የሽፍታ ቡድን ማሸነፍና የግፍ ዘመኑን ማሣጠር ነው።
ወያኔ የሚወድመው በተባበረ ህዝባዊ ትግል ብቻ ነው። የተባበረን የሽፍታ ወራሪ ቡድን በምንፈጥረው ህብረት መመከት ይቀለናል።
ኢትዮጵያዊያን ኢትዮጵያዊ ህብረትን መፍጠር ካልቻልን ባርነትን መቀበላችንና መቀጠሉንም መስማማታችን ነው። የወያኔን የግፍና የደም ጠላ ስንጎነጭ መኖር ነው።
የአዲስ አበባ ህዝብ ያልጣመው፣ የማይጥመውና ሊጥመውም የማይችል የጎሣ ፖሊቲካና የወያኔ መርዘኛ “የጎሣ ፌደራሊዝም” ርዕዮት ነው። ምርጫውም ኢትዮጵያዊነት ብቻ ነው።
