የኢትዮጵያ ሕዝብ ጥያቄ ከሞላ ጎደል ተቀራራቢ እየሆነ መጥቷል። ምንም እንኳን ከበደሉ የተነሳ ለየት ያለ ምላሽ የሚያስፈልገው ህዝብ ቢኖርም። ነገር ግን ችግሩ የቱንም ያህል ቢገዝፍ አሁን ያለውን ያህል የፖለቲካ ፓርቲ ቁጥር እንዲኖር የሚጋብዝ አይደለም።

ወያኔ በሚለው እንኳን ብንሄድ 88 በላይ “ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች” ባሉበት ሀገር ከ100 የማያንስ የፖለቲካ ፓርቲ የትኛውን መብትና ጥቅም ሊያስከብር ነው?

የእስካሁኑስ ይሁን ፣ወያኔ በሞትና ህይወት መካከል ሆኖ እያጣጣረ፣ ሕዝቡ የወያኔን የልዩነት ፖለቲካ ሸፍጥ ተረድቶ ደምህ ደሜ ነው እየተባባለ ባለበት ወቅት፣ ጅምር ቢሆንም በተበታተነ መንገድ የሚታገሉ በብሔር ማንነት ላይ አተኩረው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ ድርጅቶችና ሚዲያዎች ተቀራርበው ለመስራት ጥረቶች በሚያደርጉበት ወሳኝ ሰአት ሌላ የፖለቲካ ፓርቲ ምስረታ የአበባ ጉንጉን ይዛችሁ ኑ ብሎ መጥራት ዓላማው ምንድን ነው?

ሀገር ቤት ያሉትን ፓርቲዎች ቢቻል ወደ አንድ ካልሆነ ደግሞ ወደ ሁለትና ሶስት ማጠቃለል ሲገባ “የኢትዮጵያዊያን ሀገር አቀፍ ንቅናቄ” ብለው ከተፍ አሉ።

በውጪ ደግሞ “አንድ አማራ” የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ ለመመስረት በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ከተጋባዥ ፓርቲዎች ደብዳቤ እየተመለከትን ነው። የመጀመሪያው ይሁን ግድ የለም። ሁለተኛው ላይ ግን የግል አስተያየቴን መስጠት እፈልጋለሁ።

1ኛ. አንድ አማራ ሆኖ ሁሉንም አማራ የሚያቅፍ ስብስብ ለመፍጠር የተነሱ ሰዎች በቅርብ ጊዜ ኢትዮጵያዊ ንቅናቄ እንዲፈጠር ውስን የፖለቲካ ፓርቲዎችን አግባብተው ገለልተኛ መስለው ለመታየት ይሞክሩ የነበሩ ግለሰቦች ናቸው። እና ዛሬ ምን ተገኝቶ ነው ከአንድ ኢትዮጵያ ወደ አንድ አማራ እመር ብለው ጉብ ያሉት?

2ኛ. የአንድ አማራ መስራቾች በአንድ ኢትዮጵያ የሚያምኑ የነበሩ ሲሆን በድንገት የአሰላለፍ ለውጥ አድርገው ወደ መንደር ሲወርዱ የሀገር አድን ንቅናቄው አባል ጓዶቻቸው ምን ሊሆኑ ነው?

2.1. አንድ ኦሮሞ፣ አንድ ሲዳሞ፣ አንድ አፋር ወዘተ ብለው ይመጣሉ ወይስ

2.2. ያኔ የሀገር አድን ንቅናቄው ሲመሰረት አማራ ለምን አልተወከለም ሲባል በቅርብ ቀን አማራን የሚወክል ፓርቲ መስርተን እናቀርባለን ባሉት መሰረት አንድ አማራ የሚባለውን ፓርቲ ይዘው ወደ ሀገር አድን ንቅናቄው ይገባሉ?

3ኛ. ምስረታው የአንድ አማራ ድርጅት ነው ተጋባዦች ደግሞ የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ግንባር፣ የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህብረት እንዲሁም የጋምቤላ ህዝብ ንቅናቄ ናቸው። እናም እነኚሁ ድርጅቶች ግብዣችሁ ደርሶናል በስብሰባው ላይም እንገኛለን ሲሉ ደብዳቤ ፅፈዋል። የአይጥ ምስክሯ ድንቢጥ ይሉሃል ይኼ ነው። አንድ አማራ የሚባል የፖለቲካ ፓርቲ ልትመሰርት በአማራ ስም የተደራጁ የፖለቲካም ሆነ የማህበረሰብ ድርጅቶችን፣ ሚዲያዎችን፣ የለውጥ አራማጆችንና ፍላጎት ያላቸውን አማራዎች ሳትጋብዝ ቡና አጣጭዎችህን ደብዳቤ እያፃፍህ መደስኮር ትርፉ ትዝብት ነው።

18 የሚሆኑ በአማራ ጥቅምና ፍላጎት ዙሪያ የሚሰሩ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የማህበረሰብ ድርጅቶች፣ ሚዲያዎችና የለውጥ አራማጆች ልዩነታቸውን ( ኢጓቸውን ብለው ይሻላል መሰለኝ) አጥብበው በጋራ ለመስራት በተስማሙበት ወቅት አንድ አማራ ብሎ ድርጅት ማቋቋም ፋይዳው ምንድን ነው? ይልቁን እነዚህን አካላት ቀርቦና አቅርቦ የተዛነፈውን እያስተካከሉ፣ የበሰበሰውን ደግሞ ቆርጠው እየጣሉ ከ18ቱ ውስጥ አንድ አማራን የሚወክል ድርጅት መመስረት አይቀልም ወይ?

በአንድ በኩል የአማራን ጥቅም አስከብራለሁ ብሎ የሚሰራው ወገን በሌላ አንፃር ደግሞ በአንዴ ከአንድ ኢትዮጵያ ወደ አንድ አማራ የተፈጠፈጠው ቡድን በሚያደርጉት ልፊያ ያ ምስኪን የአማራ ህዝብ የወያኔ ቀንበር ይከብድበታል። አማራው የፓርቲ ቁጥር አይደለም ችግሩ ከሴራ፣ ከሸፍጥ፣ ከስሌት የፀዳ ግፉን፣ ብሶቱንና የተደቀነበትን አደጋ ተረድቶ ታግሎ የሚያታግለው ግለሰብና ድርጅት እንጂ።

ሁለት ዝሆኖች ቢጣሉ የሚጎዳው ሳሩ ነው።

Getaneh Genanew እንደዘገበው