የዓለም ባንክ የ600 ሚሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ አፀደቀ
  • በአንድ ሳምንት አንድ ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ገንዘብ ለኢትዮጵያ ፈቅዷል

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ መንግሥት 600 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታና ብድር ሰጠ፡፡ የብድሩ ስምምነቱን የዓለም ባንክ የኢትዮጵያ፣ የሱዳንና የደቡብ ሱዳን ዋና ዳይሬክተር ሚስ ካሮሊን ተርክ፣ ከገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስትሩ አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ማክሰኞ መጋቢት 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ተፈራርመዋል፡፡

በባንኩ ከተፈቀደው ገንዘብ ውስጥ 127 ሚሊዮን ዶላር በብድር፣ 273 ሚሊዮን ዶላር በዕርዳታ እንደሚለቀቅ ይጠበቃል፡፡ 200 ሚሊዮን ብር ለከተሞች መሠረተ ልማትና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ የሚውል ብድር ነው ተብሏል፡፡ ይህ ገንዘብ ለ117 ከተሞች መሠረተ ልማትና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ የሚውል መሆኑን፣ በከተሞች እያደገና እየተስፋፋ የመጣውን ሕዝብ የኑሮ ደረጃ ለማሻሻል ይረዳል ተብሏል፡፡

የተመደበው ገንዘብ ከመጋቢት 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለቀጣዮቹ አምስት ዓመታት ተግባራዊ ለሚደረጉ ፕሮጀክቶች የሚውል እንደሆነ፣ የዓለም ባንክ ከ1998 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮጵያ ከተሞችን የልማት እንቅስቃሴዎች ሲደግፍ መቆየቱ ተገልጿል፡፡

በፊርማ ሥነ ሥርዓቱ ወቅት የተገኙት የከተማ ልማትና ቤቶች ሚኒስትር አምባቸው መኮንን (ዶ/ር) ለጋዜጠኞች እንደገለጹት፣ የከተሞች መሠረተ ልማትና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ግንባታ የተጀመረው በአሥር ከተሞች ነበር፡፡ ቀስ በቀስ ወደ 44 ከተሞች የተዳረሰው ፕሮግራሙ፣ በአሁኑ ወቅት 117 ከተሞች አካቷል፡፡፡

የፕሮግራሙ ዋነኛ ትኩረት ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ማስመዝገብ በሚችሉ ፕሮጀክቶች ላይ ነው፡፡ በተለይም ከተሞች ፅዱና አረንጓዴ እንዲሆኑ፣ የቱሪስት መስህብነትን እንዲላበሱና የግብይት ማዕከላት እንዲሆኑ፣ የተሻለ መሠረተ ልማት እንዲያጎለብቱ፣ ቋሚ የፋይናንስ ገቢ እንዲያገኙ የሚያደርጉ ሥራዎች በፕሮግራሙ ዋና ዋናዎቹ የሚተኮርባቸው ሥራዎች እንደሚሆኑ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡

ከጥቂት ቀናት በፊት ለአገር አቀፉ የኤሌክትሪክ ኃይል ማስፋፊያ ፕሮግራም የሚውል የ375 ሚሊዮን ዶላር ብድር ባንኩ መፍቀዱ አይዘነጋም፡፡ ይህም በአንድ ሳምንት ጊዜ ውስጥ ከ975 ሚሊዮን ዶላር በላይ ብድርና ዕርዳታ ለኢትዮጵያ በመፍቀድ፣ ባንኩ በየጊዜው በኢትዮጵያ እያካሄደ የሚገኘውን ኢንቨስትመንት ከፍተኛ እንዲሆን እያደረገው መምጣቱን ያሳየበት ወቅት ሆኗል፡፡

የዓለም ባንክ ከስድስት ወራት በፊት ይፋ ባደረገው መረጃ በግማሽ ዓመት ውስጥ ከ1.8 ቢሊዮን ዶላር በላይ ብድር በመፍቀድ ከፍተኛውን የገንዘብ መጠን እንዳቀረበ መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ባለፈው ዓመት መጨረሻ ለትምህርት ሚኒስቴር የ300 ሚሊዮን ዶላር ዕርዳታ ከማድረጉ በተጨማሪ፣ ለእንስሳትና ዓሣ ሀብት ሚኒስቴር የ170 ሚሊዮን ዶላር ብድር መስጠቱም አይዘነጋም፡፡

የዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ ቃል ከገባው አሥር ቢሊዮን ዶላር ብድርና ዕርዳታ ውስጥ፣ እስካለፈው ወር ከአራት ቢሊዮን ዶላር በላይ መልቀቁን አስታውቋል፡፡

Source     –   Ethiopian Reporter