
የኢትዮጵያውያን አገር አቀፍ ንቅናቄ መሥራቾችና የቀድሞ ሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች እነ አቶ ይልቃል ጌትነት (ኢንጂነር)፣ ስለአዲሱ ፓርቲያቸው የምሥረታ ውይይት መጋቢት 8 ቀን 2010 ዓ.ም. አደረጉ፡፡
የምሥረታ ውይይቱ የተደረገው አፍንጮ በር በሚገኘውና የመድረክ ጽሕፈት ቤት በነበረው በኦሮሞ ፌዴራሊስት ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጽሕፈት ቤት ሲሆን፣ ስለንቅናቄው መመሥረት አስፈላጊነት አቶ ይልቃል ለተገኙ አባላትና ተጋባዥ እንግዶች ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
አዲስ ፓርቲ መመሥረት ያስፈለጋቸው ሌሎች ፓርቲዎችን ለመወዳደር ሳይሆን፣ ከአገዛዝ ወደ ዴሞክራሲ ለሚያደርጉት ትግል ኢትዮጵያውያንን ያካተተ አገር አቀፍ ንቅናቄ ለመፍጠር መሆኑን አቶ ይልቃል ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡
ፓርቲው ሁሉን አቀፍ የሆነና ቀደም ብሎ ከነበረባቸው ችግሮች ልምድ በመውሰድ፣ የተሻለ አደረጃጀት ለመፍጠር መሆኑንም አክለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ችግር ብዙና ውስብስብ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ይልቃል፣ ከችግሩ ለመላቀቅ የፖለቲካ ማሻሻያ መደረግ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡ በኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ የተፈጠረው ፈርጀ ብዙ ውጥንቅጥ የፖለቲካና የአመራር ችግር፣ በአስቸኳይ መፈታት እንዳለበትም ጠቁመዋል፡፡
በሽብር ተግባር ወንጀል ተፈርዶባቸው የነበሩትና መንግሥት በይቅርታ የፈታቸው አቶ ዮናታን ተስፋዬና አቶ ብርሃኑ ተክለ ያሬድን ጨምሮ በርካታ ሰዎች መገኘታቸውን የገለጹት አቶ ይልቃል፣ በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ያለውን ዘርፈ ብዙ ችግር ተባብሮና አንድ ሆኖ መፍታት ጊዜ የሚሰጠው ጉዳይ አለመሆኑን ገልጸዋል፡፡
ፓርቲው ለምሥረታ የሚያበቃውን የአባላት ቁጥር ከደቡብ፣ ከኦሮሚያና ከአማራ ክልሎች፣ እንዲሁም ከድሬዳዋና ከአዲስ አበባ ከተማ አስተደደሮች 95 በመቶ ማግኘቱን አስረድተዋል፡፡
በቤኒሻንጉል ጉምዝና በሶማሌ ክልሎችም ፊርማ ማሰባሰብ መጀመራቸውንም አክለው፣ መጋቢት 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የምሥረታ ጉባዔ እንደሚያደርጉ አስታውቀዋል፡፡
