ዘንድሮ መካሄድ የሚገባው የአካባቢና የሁለቱ ከተማ አስተዳደሮች ምርጫ በተመለከተ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ ነው

ዘንድሮ መካሄድ በሚገባው የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደሮችና የአካባቢ ምርጫን በተመለከተ የመንግሥት ውሳኔ እየተጠበቀ መሆኑ ታወቀ፡፡

ምርጫው መካሄድ የነበረበት በሚያዝያ ወር 2010 ዓ.ም. የነበረ ቢሆንም፣ በአገሪቱ ወቅታዊ የፖለቲካ ቀውስ ምክንያት ምርጫውን በወቅቱ ማከናወን አይቻልም ተብሏል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ዝግጅት አጠናቋል፡፡ ቦርዱ የመንግሥትን ውሳኔ እየጠበቀ ነው፤›› ሲሉ የቦርዱ ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ወንድሙ ጎላ ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በ2005 ዓ.ም. እና ከዚያ በፊት የነበረው የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች ምርጫ በሚያዝያ ወር የተካሄደ ሲሆን፣ የሁለቱም ከተማ አስተዳደሮች ቻርተር ድንጋጌዎች ‹‹የምክር ቤቱ አባላት በየአምስት ዓመቱ በከተሞቹ ነዋሪዎች ይመረጣሉ›› ይላሉ፡፡ በዚህም መሠረት የዘንድሮው ምርጫ መካሄድ የነበረበት በሚያዝያ ወር ነበር፡፡

ይሁን እንጂ በወቅታዊ የአገሪቱ የፖለቲካ ቀውሶች፣ እንዲሁም ይህንን ተከትሎ ለስድስት ወራት በታወጀው የአስቸኳይ አዋጅ ሳቢያ ምርጫው እንዴትና መቼ ማከናወን እንደሚቻል አልታወቀም፡፡

የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የካቲት 9 ቀን 2010 መታወጁና ለስድስት ወራት የሚቆይ መሆኑ፣ እንዲሁም በይዘቱ በሕገ መንግሥቱ የተረጋገጡ ፖለቲካዊና ሰብዓዊ መብቶች በሙሉ እንዲገደቡ አድርጓል፡፡

ይህ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያጥር ወይም እንዲራዘም የሚደረግ ካልሆነ በስተቀር፣ በነሐሴ 2010 ዓ.ም. ነው የሚጠናቀቀው፡፡ በመሆኑም ዘንድሮ የሚጠበቀውን ምርጫ ከነሐሴ ወር በኋላ ካልሆነ ለማካሄድ አዳጋች ነው፡፡

በጉዳዩ ላይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው አቶ ወንድሙ ቦርዱ የመንግሥትን ውሳኔ እየጠበቀ እንደሚገኝ ነገር ግን በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ውስጥ ምርጫን ማካሄድ እንዴት እንደሚቻል የመንግሥት ውሳኔ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡ ቦርዱ ሙሉ ለሙሉ ለምርጫው እንደተዘጋጀ ተናግረው ክረምቱ የማያስቸግር ከሆነም በክረምቱ ወቅት ማካሄድ ይቻላል ብለዋል፡፡