March 22, 2018
መስከረም አበራ
ፕሮፌሰር መስፍን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ብቅ ብቅ እያለ ስላለው የአማራ ብሄርተኝነት እንቅስቃሴ ጉዳይ “የአማራ ጉዳይ እንቆቅልሽ እየሆነ ነው፤” ሲሉ በጀመሩት እና እኔም በምስማማበት ሃሳብ ጀምረው “ከዚህ በላይ የተጠቀሱት ሦስት ሊቃውንት እንደሚያስረዱት አማራ የአንድ ጎሣ ስም አይደለም አማርኛ ቋንቋ የአማራ የሚባል ጎሣ ነው” ሲሉ ደንገር አድርገውኝ የቋጩትን አጭር ፅሁፍ አነበብኩት፡፡ ብዙ ጥያቄዎችን አጫረብኝ፡፡በጉዳዩ ላይ እንደሚመለሱበት ስለገለፁ ሲመለሱ ቢነሷቸው የምፈልጋቸውን፣በፅሁፋቸው ያልተገለፁልኝን ሃሳቦች ከአክብሮት ጋር ማንሳት ወደድኩ፡፡
ፕ/ሮ መስፍን የአማራን ትርጉም የተለያዩ ፀሃፍትን ጠቅሰው ዘርረው የደረሱበት መደምደሚያ አማራ የሚባል ጎሳ እንደሌለ፣ወይም አማራ የአንድ የተለየ ጎሳ መጠሪያ እንዳልሆነ ነው፡፡ እዚህ ላይ ነው ጥያቄየ የሚጀምረው፡፡ የአንድ ነገር የቀድሞ ስያሜ ሁልጊዜ የፀና ተመሳሳይ ትርጉም ይኖረዋል ወይ? ለምሳሌ የቦታ ስም የነበረ ነገር ከጊዜ ብዛት እና በተለያዩ ማህራዊ ተለዋዋጮች (variables) ምክንያት ተለውጦ የትምህርት ስም ሊሆን ይችላል፡፡ ለምሳሌ “Ethics” የሚለው የጥናት መስክ ቀድሞ በግሪክ “Ethos” ከሚለው የቦታ ስም ተነስቶ ከጊዜ ብዛት የተለያዩ የትርጉም እና የሆሄ(spelling) ለውጥ ተደርጎበት ፍፁም ልዩ ትርጉም ይዞ ይገኛል፡፡የጥንት ሱመሪያዊያን የሚፅፉበት ከጭቃ የተሰራ መፃፊያ ስሙ ታብሌት ይባል ነበር፡፡ የዘመኑ ታብሌት ከመምጣቱ በፊት የኖሩ ባለመዝገበ ቃላትም ታብሌትን ከጭቃ የተሰራ መፃፊያ ብለው ከመተርጎም ውጭ ሌላ አማራጭ የላቸውም፡፡ ይህ ማለት ግን ዛሬ ያለው ታብሌትም ትርጉሙ ያነው ማለት አይደለም!
በተመሳሳይ እነ ከሳቴ ብርሃን አማራ የሚለውን ቃል ለአንድ ጎሳ የተሰጠ ማንነት አድርገው አልተረጎሙትም ነገር ግን በኋላ የመጣው መለስ ዜናዊ ደግሞ ከዚህ በተቃራኒው አማራ ለሚለው ቃል የራሱን ትርጉም ሰጥቶ እንዲህ የሚባል ማንነት አላቸው ያላቸውን ሰዎች ወደ ገደል አስወረወረ፣ ድንኳን ነቅሎ አሰደደ፣ በሃገር ዳርቻ እንደ ክፉ ጭራቅ አድርጎ ስሎ የሃገሩ ልጆች ወንድሞቹ ሁሉ እንደጠላት እንዲያዩት፣ እንመራሃለን ያሉት ሁሉ እንዲሰድቡት አደረገ፡፡ የመለስ ስርዓት ተቃዋሚ ነን ያሉ ፓርቲዎች ሳይቀሩ ጉዞዋቸው ይሰምር ዘንድ አማራውን ከመሪነት ቦታ ገለል ማድረግን እንደብልሃት ተያዙት፡፡
በአሁኑ ሰዓት አማራ ተብሎ በመፈረጁ መከራውን ለሚያየው ህዝብ ትርጉም ሰጭው(በዚህ ወቅት የውይይት አጀንዳ ተደርጎ መነሳት ያለበት) የንቡረ እድ ኤርሚያስ ትርጉም ነው የመለስ ዜናዊ ትርጉም??? የመለስ ዜናዊ ትርጉም ያመጣው አደጋ በተተረጎሙበት አማራነት ከመደራጀ ሌላ የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ተቋም በሌለባት በአሁኗ የኢትዮጵያ ሁኔታ ሌላ መፍትሄው ምንድን ነው ብለው ያስባሉ ??? የጎሳ ድርጅት የሚያቋቁም ሁሉ እንጀራ ለመብላት ነው ብሎ መፈረጅስ እስዎን ከመሰለ አስተማሪ ጋር እንዴት ብሎ ይሄዳል?? እርግጥ ነው ብዙዎቹ የጎሳ ፖለቲከኞች እርስዎ እንዳሉት አይነት አላማ ያላቸው እንደሆኑ በተለያየ አጋጣሚ መረዳት ይቻላል፡፡ ሆኖም የምር ለህዝብ አስበው፣በሃገራችን የዲሞክራሲ እና የሰብአዊ መብት ማስጠበቂያ ተቋማት ድምጥማጣቸው ከመጥፋቱ የተነሳ፣ የዘመኑን ችግር በዘመኑ መንገድ ለመታገል አስበው እንጅ ኢትዮጵያዊነታቸውን በዘረኝነት ተክተው፣ወያኔ የሚከተለውን አይነት ዘረኝነት ለማጧጧፍ ሳይሆን በቅንነት አማራነት የማያስገድልበት፣ያማስገልልባት ኢትዮጵያዊነትን ለማምጣት የሚሰሩም አይጠፉምና ሁሉን በጅምላ መፈረጅ አግባብ አይመስለኝም፡፡
