March 22, 2018

ከደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ህብረት ለአንድ አማራ ድርጅት የተሰጠ የድጋፍ መግለጫ
ለአንድ አማራ ድርጅት፤
ከደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ህብረት የተሰጠ የድጋፈ መግለጫ።
በደቡብ ኢትዮጵያ አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች ከሁሉም የሀገራችን ህዝቦች ጋራ በመሆን ሀገርን ከውስጥና ከውጭ አደጋዎች
ለማዳን እና ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ ከፍተኛ መስዋዕትነት ከፍለዋል፡፡ የሀገራችን ህዝብ ለዘመናት ዘርፈብዙና መራር ትግልን ቢታገልም በሀገር ደረጃ የሚመጥነዉን የፖለቲካ ስርዓት መመስረት ሳይቻል ቀርቷል።
ለዘመናት በበርካታ ትዉልዶች እና ህዝቦች ሲገነባ የቆየዉ የአብሮነት፤ የመተሳሰብ እና የመከባበር መስተጋብሮች በፍጥነት በህወሃት ገዥ ቡድን በማፈራረስ የህዝብን ህልዉና አደጋላይ ጥሏል፡፡ በዚህ የወያኔ መሰሪ እና ጠባብ አስተሳሰብ ምክንያት እንደ ሌሎች ህዝቦች ሁሉ የአማራዉ ህዝብ የሞት፤ የእስራት፤ የንብረት ዝርፊያ፤ የስደትና የጉስቁልና ገፈት ቀማሽ ሆኗል። የ ኢትዮጵያ ህዝቦች ለመብታቸዉና ለነጻነታቸዉ የሚደረጉትን ትግል በብሄራዊ ደረጃ ለማቀናጀት እና በብቃት ለመምራት ይቻል ዘንድ የአንድ አማራ የፖለቲካ ድርጅት መመስረት ተገቢ ብቻ ሳይሆን አስፈላጊ ከመሆኑም በተጨማሪ ያልተደራጀ ህዝብ ራንሱን እና አከባቢዉን ከጥቃት መከላከል አይችልም ብለን እናምናለን። ዛሬ በኢትዮጵያና በሕዝቦችዋ ላይ በወያኔ የተደቀነው አደጋ ተድራጅተው ካልተንቀሳቀሱ በስተቀረ የህዝቦች አብሮ የመኖር ህልውና እጅግ የከፋና አስጊ ደረጃ ላይ ደርሷል።
የአማራ ሕዝብ ኢትዮጵያን በመገንባቱና በመጠበቁ ተግባር እንደሌሎቹ ህዝቦች ሁሉ የጎላ ታሪካዊ ድርሻ አለው። በመሆኑም አሁን ያለዉ ትውልድ በመደራጀት የራሱን ጠንካራ ሥራ በመስራት አገራዊ አደራና ታሪካዊ ሀላፊነቱን በብቃት መወጣት አለበት። በዚህም መሰረት የአማራው ሕዝብ በሚገባዉ መጠን ድርጅታዊ አቅም ፍጥሮ ራሱን ከጥቃት መከላከል ስለሚኖርበት ከሁሉም የሃገሪቱ ህዝቦች ጋራ በመሆን ኢትዮጵያን ከወያኔ አደገኛ የጥፋት ተልእኮ ለመግታት እንዲሁም ሀገሪቱን ከመፈራረሰ ለመታደግ እና ወደፊት የሚፈጠረዉን ዴሞክራሳያዊ ስርዓት ለመመስረት ይቻል ዘንድ “አንድ አማራ” ድርጅት የአማራዉን ህዝብ የማስተባበርና የማታገል ሚና የመጫወት ትልቅ አስተዋጽዖ ማበርከት እንደሚችል ሙሉ እምነት አለን።
በአንድ አማራ ድርጅት ምሥረታ ጉባኤ ላይ እንድንገኝ መጋበዛችሁን ከማመሰገንን በተጨማሪም ወደ ፊት በጋራ ለሚደረጉ ዘርፈ ብዙ ሀገራዊ የፖለቲካ ሥራዎች ላይ የጋራ ዉጤት በደማቁ ለማስመዝገብ የአረንጓዴ ኮከቦች ህብረት ከአንድ አማራ ደርጅት ጋራ በቅርበትና በመደጋገፍ አስፈላጊዉን ትብብር ለማድረግ የትግል አጋርነቱን ያርጋግጣል ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!
