March 23, 2018

ፕ/ር መስፍን በመጋቢት 2010 ‘በዘሃበሻ’ ድህረ ገፅ ላይ ‘የአማራ ጉዳይ’ በሚል ዕርእስ ስር የፃፉትን ማየት ችያለሁ::

ለመንደርደሪያ ያግዘን ዘንድ:-

1. ፕ/ር መስፍን በፕ/ር እንድሪያስ እሸቴ በተዘጋጀውና “ነቢዩ” መለስ ዜናዊንና ዶ/ር መኮንን ቢሻውን ባሣተፈው የቴሌቪዥን ውይይት ቀርበው ሲከራከሩ አማራ የሚባል ዘር አለምኖሩን አፅኖት ሠጥተው ሲያስረዱ ነበር:: ይህ አቋማቸው ኢትዮጵያን በዘር እንደ ጣሊያን ከፋፍለው ለመግዛት ኢትዮጵያን ለወረሩት ወያኔዎች ብርቱ ምላሽ ነው በሚል ከደገፉት ግለሰቦች መካከል አንዱ ነኝ::

2. ፕ/ር መስፍን ከትንሽ ጊዜ በሁዋላ አሜሪካን ሃገር ከቪ.ኦ.ኤ አማርኛ ፕሮግራም ክፍል ባልደረባ አቶ አሉላ ጋር ሲወያዩ፤ ጋዜጠኛ አሉላ “አሁንም አማራ የለም በሚለው አቋሞ እንደፀኑ ነው ወይ?” ብሎ ሲጠይቃቸው ፕ/ር መስፍን “አይ እዚህ አሜሪካ ውስጥ እንደማየው አሁን እየተፈጠረ ነው” ሲሉ መመለሳቸውን አስታውሳለሁ::

ለኔ ይህ “አማራ የለም” የሚለው አቋማቸው በኢትዮጵያዊነት ላይ ያለውን አንደምታ ተገንዝበው በቅን ልቦና የሚናገሩ አድርጌም እወስድ ነበር::
በእርግጥ አማራነትን አጉልቶ ያወጣው የአማራ ብሄረተኝነትም አይደለም:: አማራነትም ኢትዮጵያዊነት ነው:: የአማራ ብሄረተኝነት እንዲፈጠር ምክንያት የሆነው ህወሃትና ኦነግ ናቸው:: የአማራ ብሄረተኝነት ለመፈጠር የቻለው በአቀናውና በመሠረተው ሃገር ሁለተኛ ዜጋ ሆኖ የዘር ማፅዳት (ethnic cleansing & genocide) እኩይ ተግባር የተፈፀመበትና እየተፈፀመበት ያለ አማራ በመኖሩ ነው:: በአማራው ላይ ልክ እንደ ጣሊያን አማራ ብለው የፈረጁት የማህበረሠብ ክፍልን ለማጥፋት በተግባር መሠለፋቸውና ማጥቃት መቀጠላቸውም ነው:: ልክ እንደ ጣሊያን፣ ህወሃትና ኦነግም “በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምን አማርኛን የሚናገር ሁሉ አማራ ነው” ከሚል ማጠቃለያ ላይ ደርሠው በበደኖ፣ በአርባጉጉ፣ ጉራፈርዳ ወ.ዘ.ተ ለእንግልት፣ ለመከራ፣ ለመሰደድና ለሞት ያበቁትም መሆኑ ገሃድ ነው::

አማራ ተብሎ የተፈረጀና አማራ ሆኖ በአማራነቱ የሚደርስበትን የዘር ማፅዳት ወንጀልና እናት ሃገሩን ኢትዮጵያን ከመፍረስ ለመታደግና ለመከላከል የተሰለፈ አማራ የተሰኘ ህዝብ በእርግጥ ለመኖሩ ፕ/ር መስፍንን ለምስክርነት መጥራት የሚያስፈልገው ጉዳይ አይመስለኝም:: “አማራ አይደለህም” ብሎ አማራውን መሞገትዎን ትተው ጣሊያንንና ወያኔን አማራ ብለው የፈረጁትን ህዝብ ማንነት ቢጠይቁ ቀላል ምላሽ ባገኙ ነበር:: አዎ አማርኛን የሚናገር በአማርኛ ስር የተካተተ፣ ባህሉና ስነልቦናዊ አመለካከቱ የዳበረ ከዘርና ከጎሣ የላቀ (Supranational ethnic) ብቸኛው ብሔር አማራ የተሠኘ አለ:: ይህ ብሔር ከብዙ የኢትዮጵያ ቋንቋ ተናጋሪዎች በጋራ እሴት ላይ የሚያስተሣስር አማራ በእርግጥ አለ:: አማራ የለም ካልን ኢትዮጵያም አለመኖሯን አብረን መቀበል ይኖርብናል::

የፕ/ር መስፍን ተልዕኮ ምንድን ነው?
ይህንን ጥያቄ በጥያቄ መልክ ማስቀመጥ እፈልጋለሁ::
1. በዚህ እጅግ ፈታኝ የሆነ ፓለቲካዊ ክንውንና ምስቅልቅል ባለበት ወቅትና ሃገሪቷ ፓለቲካዊ አጣብቂኝ ውስጥ ባለችበት ፈታኝ ሠዐት ፕ/ር መስፍን ለምን እየደጋገሙ ይህን የአማራን አለመኖር ጉዳይ እየደጋገሙ ያነሣሉ?

2. የሌሎች ጎሣዎችን ለምሣሌ ትግራይ፣ ሱማሌ፣ ኦሮሞ የሚባሉትን የመኖር አለመኖር ጉዳይ መናገርና ወይም መፃፍ ለምን አልደፈሩም? ለምንስ አልፈለጉም?

3. “ሮም ውስጥ ስትኖር ሮማውያንን ምሠል” በሚለው እሳቤ በዚህ በጎሣ ፓለቲካ በታመሠ ሃገር ኢትዮጵያዊነቱን ሣይክድና በኢትዮጵያዊንቱ ሣይደራደር ለመብቱና ለማንነቱ ይህ አማራ ብለው ፈርጀው በጠላትነት የሚጠቃው አማራ መደራጀቱ ለምን አስቆጣቸው? በዚህ መልክ ነገር ግን ለአፍራሽ ግብ የተደራጁ ሌሎች ሃይሎችን እሹሩሩ እያሉ በአማራ ላይ መንጠላጠልንስ ለምን መረጡ?

4. ፕ/ር መስፍንና ሌሎች 44 የዩኒቨርስቲ መምህራንን “ነፍጠኛ አማሮች” በሚል ሽፋን ወያኔ ሳያባርር፤ ተባራሪ መምህራኑ ጀርመናውያን ነበሩ እንዴ?

5. ፕ/ሮ መስፍን “አማራ የለም” ካሉን ‘አማራ ነን’ ለሚሉና አማራ ለሆኑ ሁሉ ያወጡላቸው አዲስ መጠሪያ ይኖራቸው ይሆን?

ለማጠቃለል ያህል ፕ/ሮ መስፍን ይህን ደጋግመው የሚያነሱት ጉዳይ ወቅቱን ያልመጠነ ብቻ ሣይሆን ከመሠሪነትና ከግል ጥላቻ ጋር የተቆራኘ ልዩ ደባም ይመስለኛል:: ጠላቶቹም ይሁኑ እራሱ ‘አማራ ነኝ’ የሚል የማህበረሠብ ክፍል ‘አንተ የለህም:: ይህ ያንተ ስም አይደለም” ብለው ዳቦ ሣይቆርሱ የዳቦ ስም ሊያወጡለት የሚፈልጉት ለምን እንደሆነ ቢገባን መልካም ነበር:: የኢትዮጵያ ህዝብ ትግሉ ከከሃዲው ወያኔ ጋር እንጂ ከስያሜ ጋር አይደለም::

ጣሊያንና ወያኔ “ኢትዮጵያን ለመቆጣጠርና ቀጥሎም በዘላቂነት ለመግዛት የምንችለው አማራንና የተዋህዶ ኦርቶዶክስ ሃይማኖቱን አከርካሪ መምታት ስንችል ነው” ብለውናል:: ፕ/ሮ መስፍን “አማራ የሚባል ነገር የለም” የሚሉን በአማራነቱ ግፍና በደል እያስተናገደ ያለውንና ጣሊያኖች ለይተው፤ ወያኔዎች እየለዩ የሚያጠቁት ህዝብ ነው::

ፕ/ሮ መስፍን! አማራና የአማራ ልጆች አዎን “አማራ ነን ጥንትም አሁንም አለን” እያሉዎት ነው::
ይህን ብዬ በዚህም ላብቃ:-

ፕ/ር መስፍን፡ “አማራ የሚባል የለም” – መለስ ዜናዊ፡ “አማራ አለ”

የትግራይ ወያኔ አዲስ አበባን ተቆጣጥሮ ስልጣን በማየ ማግስት ፕሮፌሰር መስፍን ወልደማሪያም ወደ ቤተመንግስት ጎራ ብለው ከወዳጃቸው ከአቶ መለስ ዜናዊ ጋር ያደጓትን አጠር ያለች ውይይት ይመልከቷት።

“Practice the pause. Pause before judging. Pause before assuming. Pause before accusing. Pause whenever you’re about to react harshly and you’ll avoid doing and saying things you’ll later regret.”

Lori Deschene

(American Author)

 

https://www.youtube.com/watch?v=HmNFAHe8R3I