March 23, 2018
“አማራ የሚባል ብሔር የለም” በሚል የተከበሩ ፕ/ር መስፍን ወልደማርያም አንድ አጭር ጽሁፍ በነቆራ መልክ (mean spirited piece) አሰራጭተው ተመልክቻለው። ፕ/ር መስፍን አማራ የሚባል ብሔር የለም በማለት የሚያቀርቧቸው ማስረጃዎች በኔ እምነት ውሃ የማያነሱ ናቸው።

የጎሳ፣ የብሔር ወይንም የዘውግ ፖለቲካ ለሀገር ጠንቅ መሆኑን ለማሳየት ሲባል አንድን ብሔር “የለህም” ብሎ ሙግት ውስጥ መግባት አስፈላጊ አይመስለኝም። ባለፉት 27 ዓመታት የአማራ ህዝብ በወያኔ እና ግብረአበሮቹ የጥላቻ ጦርነት ተከፍቶበት ኑሮው የገሃነብ እንዲሆን ተደርጓል፣ በሀገሩ ኢትዮጵያ ባይተዋር ተደርጎ ጭፍጨፋ እየተፈጸመበት ይገኛል።
ኢትዮጵያዊ መሰረታቸውን ሳይለቁ አማራ በመሆናቸው ብቻ እየተሰነዘረባቸው ያለውን ጥቃት ለመመከትና ለዘለቄታውም በአማራ ህዝብ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለማስቆም ዜጎች በብሔራቸው አማራ ስም ተደራጅተው የህወሃትን የዘውግ አገዛዝ እድሜ ለማሳጠር ትግላቸውን ከተቀረው ኢትዮጵያዊ ወገናቸው ጋር ቢያቀናጁ ጥቅም እንጂ ጉዳት አይኖረውም። በነጻነት ቀንዲልነት ሲታወሱ የሚኖሩት ፕ/ር አስራት ወልደየስ በአማራ ስም ድርጅት መስርተው በተቀሳቀሱበት ወቅት ከፍተኛ ህዝባዊ ድጋፍ ያገኙትም ያለምክንያት አልነበረም።
ከላይ የጠቀስኩትን ምክንያታዊነት መሰረት በማድረግ አንጋፋ ኢትዮጵያውያን የተበታተኑትን የአማራ ድርጅቶች ወደ አንድ ለማምጣትና አንድ ጠንካራ የአማራን ህዝብ ብሎም መላውን የኢትዮጵያ ህዝብን ሊታደግ የሚችል ድርጅት ለመገንባት (መሰረት ለመጣል) ነገ መጋቢት 14/2010 (March 24, 2018) “የአንድ አማራ ህብረት መስራች ጉባኤ” በዋሽንግተን ዲሲ ተጠርቷል። ይህ ሊበረታታ ይገባዋል።
የአማራው ብሔር በአንድነት መቆም የህወሃትን አገዛዝ እድሜ እንደሚያሳጥር የገባቸው በተለያዩ ብሔሮች ስም የሚንቀሳቀሱ ድርጅቶች ለዚህ “የአንድ አማራ ህብረት መስራች ጉባኤ” ድጋፋቸውን እየገለጹ መሆኑም የሚያበረታታ ነው። የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝብ ሕብረት እና ጋምቤላ ክልላዊ ንቅናቄ፣ የኦሮሞ ዲሞክራሲያዊ ግንባር ንቅናቄ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ አረንጓዴ ኮከቦች ህብረት ንቅናቄ፣ የአፋር ህዝብ ፓርቲ ድጋፋቸውን ከገለጹት ውስጥ ጥቂቶቹ ናቸው።
በማህበራዊ ድረ-ገጾች ላይ በአማራ ስም እንደ አሸን የፈሉትና እራሳቸውን ለማስተዋወቅ ልክ ህወሃት እና ግብረአበሮቹ እንዳደረጉት ሕብረ-ብሔር ኢትዮጵያዊ ድርጅቶችን በጠላትነት የፈረጁትን “አላዋቂ ሳሚ አማራ ነን ባዮች” እየደገፍኩ እንዳልሆነ ለማስረዳት እወዳለሁ።
