March 23, 2018

ጠዋት ስነሳ፣ መብራት ጠፍቷል። ውሃም የለም። ኢንተርኔት ከተዘጋ ወራት አልፈውታል። በሆቴሎች ብቻ የተወሰነውና “መጣ! ጠፋ” የሚባለው ዋይፋይም መብራት ከሌለ አይኖርም። እኩለ ቀን ላይ ዋይ ፋይ አለው ወደተባለ ቦታ ስሄድ መብራት “ተመልሶ ሄዷል”።

ሆቴሉ በር ላይ 800 ብር የወጣበትን ውሃ የተሸከመ ቦቲ ቆሟል። ጀኔሬተር እንዲነሳ አዝዞ የተመለሰው ማኔጀር ኮሪደር ላይ ቆሞ ቦቲውን እያየ ይተክዛል። ለጀኔሬተር ነዳጅ፣ ለውሃ የሚያወጡት ገንዘብ እንዳለ ሆኖ ደንበኞች መብራት ሲጠፋ ጥለው ይወጣሉ። ሆቴሎች ባዶ ናቸው። ይህ ጎንደር ላይ ነው፣ ባህርዳር ላይ፣ ደሴ ላይ ላይ፣ አማራ ክልል ተመሳሳይ ነው!

መብራት ኃይል እንዲህ ሲያበራ ሲያጠፋ ከርሞ የወሩ መጨረሻ ላይ ያላሰቡትን ክፍያ ይቆልልባቸዋል።

የአንድ ድርጅት የሕዝብ ግንኙነት ” ባለፉት ሶስት ወራት መብራት አልነበረም። የወሩ መጨረሻ ሲመጣ ግን 36 ሺህ ብር ክፈሉ ተባልን። መብራት በነበረበት ጊዜ በዛ ቢባል ከ14 ሺህ ብር በላይ ክፈሉ ተብለን አናውቅም። መብራት በሌለበት ወቅት እንዴት ይህን ያህል ገንዘብ እንከፍላለን ብለን ስንጠይቅ የሚቀጥለው ይሻሻላል ተብለን ነበር። በቀጣዩ ግን 30 ሺህ ብር ነው ክፈሉ የተባልነው” ሲል አዝኖ ነግሮኛል።

አማራ ክልል በመሰረተ ልማት የደቀቀው ቀዳሚ ክልል ነው። ይህም ሲሆን የበጀት እጥረት አይደለም። ሆን ተብሎ “አደህይቶ የመግዛት” ስልት እንጅ! ሕዝብ ያለ አቅሙ ግብር እየከፈለ አገልግሎቱን ግን አያገኝም። የመብራት፣ የውሃ፣ የመንገድ አገልግሎቶች በማጣቱ ኪሳራው የአገልግሎት ብቻ አይደለም። ከፍተኛ ወጭም አለበት። አንድ ሆቴል ውሃ ገዝቶ፣ ለጀኔሬተር ነዳጅ ገዝቶ፣…… ያም ሆኖ ደንበኞቹንም አጥቶ ነው። ገቢ አጥቶ፣ ከስሮ ነው!

አብዛኛዎቹ አማራ ክልል ውስጥ የሚደረጉ ኢንቨስትመንቶች ሌላ ቦታ እንዲደረጉ ውትወታ እንደሚደርስባቸው ይነገራል። “አይሆንም” ሲሉ መልሱ በቀል ነው። ካለ አቅማቸው ግብር ይቆለልባቸዋል፣ ውሃና ነዳጅ ገዝተውም፣ መብራት ጠፍቶ ከርሞም ያልበራላቸውን መብራት ዋጋ ይከፍላሉ።

እኔ እንዳየሁት የአማራው የሌለው ግብር የከፈለበት አገልግሎት ነው። እነዚህ አገልግሎቶች የሌሉባቸው ሌሎች ክልሎችም ይኖራሉ። ሆኖም አገልግሎቶች እንጅ እነሱ የሉም አይባሉም። በሳምንትና ሁለት ሳምንት መታዘብ እንደቻልኩት መሃል ሀገር የሚገኝ ሰው እንኳ አማራው “ልማት” በሚባል ነገር ራቁቱን መቅረቱን ካላየው በስተቀር አይረዳውም።

አማራ አለ? የለም?

ጀኔሬተሩ ተነስቶ ዋይ ፋይ ተጠብቃ ስትከሰት አንዳንድ የፌስቡክ ወዳጆቼ ፕሮፌሰር መስፍን ባነሱት አጀንዳ ላይ ለምን አስተያየት አትሰጥም የሚል መልዕክት አስቀምጠውልኝ አገኘሁ።

በዚህ ወቅት፣ “አማራ የለም” የሚለው አጀንዳ ለምን እና ለማን እንደሚጠቅም ግራ ይገባኛል። ፕሮፌሰር መስፍን በብዙ ሀሳቦች ላይ በተመስጦ የሚነበቡ ቁምነገሮችን እያቀረቡ በአማራ ጉዳይ ለምን አሁንም ድረስ ችክ እንዳሉ ሌላ እንቆቅልሽ ነው።

ትዝብቱን የበረታ የሚያደርገው ፕሮፌሰር መስፍን የመብት ተሟጋች መሆናቸው ነው። የሰመጉ መስራች እንደሆኑ ይነገራል። ለአንድ ሰብአዊ መብት ተሟጋች ቀዳሚው የግለሰብና የህዝብ ምርጫ ነው። አንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋች “እኔ አማራ ነኝ” ያለ ሲመጣ ከመቀበል ውጭ ሊከራከረው አይገባም። “በአማራነቴ ተጠቃሁ” ካለ “አይ አማራ የለምና በአማራነትህ አልተጠቃህም” ሊሉት አይገባም። እንኳን እሳቸው ሀገር ውስጥ ያሉት የውጭ ሀገር ተቋማትም በማንነቱ ተጠቃሁ ካለ ማንነቱን አክብረው የሚያተኩሩት ጥቃቱ ላይ ነው። ምክንያቱም አማራ ሆኖ የተጠቃ፣ አማራ ተብሎ የተጠቃ እንጅ ማንነቱን የሚያውቀው ፕሮፌሰር መስፍን አይደሉም። አሊያም የሰብአዊ መብት ተሟጋች አይደሉም ማለት ነው!

ፕሮፌሰር በፃፉት ፅሁፍ አማራ የለም ለማለት ዘመን ያሳለፉ መዝገበ ቃላትን እንደ ዋቢነት ተጠቅመዋል። ፕሮፌሰር ዛሬ አማራ የለም ብለው ለመከራከር ትናንት አማራ ተብሎ በተለያየ መንገድ የተቀመጠውም ትርጉም ለራሳቸው መከራከሪያ ጠምዝዘዋል። እነዚህ መዝገበ ቃላት የተፃፉበት ወቅት፣ አውድና የማህበራዊ ሳይንስ እውቀት ደረጃ አከራካሪ ሆኖ እነዚህ መዝገበ ቃላት “አማራ መጥፋት አለበት” ብሎ ከተነሳ ገዥ፣ እና “በአማራነቴ ተጠቅቻለሁ” ብሎ አደባባይ ከወጣ የተጠቃ ሕዝብ በላይ ፕሮፌሰርን ያሳምናሉ ብሎ መገመት አይቻልም። ጉንጭ አልባ ክርክር ካልሆነ በስተቀር!

የትህነግ/ሕወሓት ማንፌስቶ ማጠንጠኛ የአማራ ሕዝብ ነው። በወቅቱም ተቃዋሚ የነበሩት ፕሮፌሰር “አማራ የሚባል ሕዝብ የለም” ብለው አልሞገቱም። “አማራን አጠፋለሁ፣ አማራን አከርካሪውን ሰበርኩት” የሚለውን ዝም ብለው “በአማራነቴ ተጠቃሁ” ለሚለው “የለህም” ማለታቸው ለበዳዮቹ ሽፋን ከመስጠት ያለፈ ሰብአዊ ርህራሄም ሆነ ምክንያት አይታይበትም።

ፕሮፌሰር ጎሰኝነትን እፀየፋለሁ ይላሉ። አማራ የሚባል “ጎሳ” የለም ይላሉ። አማራ ነን ያሉትን ደግሞ ጎሰኞች ይሏቸዋል። አማራ የለም ካሉ፣ አማራ ነን የሚሉት ጎሳ የላቸውም ማለት ነው። ጎሰኝነት የለም ማለት ነው። ፕሮፌሰር ግን አማራ የሚባል ጎሳ የለም እያሉ፣ አማራ ነን የሚሉትን “ጎሰኞች” ይሏቸዋል። ይህ ሌላ ግራ መጋባት ነው!

አንድ ሰው እኔ አማራ ነኝ ካለ ሊከበርለት የግድ ነው። በተለይ አማራ ነህ ተብሎ እየተጠቃ ባለበት ሁኔታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉትን የሌሎች ማንነቶች እያከበሩ “አይደለህም” ማለት ድርቅና ብቻ ተብሎ የሚታለፍ አይመስለኝም።

ፕሮፌሰር ሶስት መንግስታትን አሳልፈዋል። በዚህም ታሪክን፣ ፖለቲካን በደንብ አድርገው የሚያውቁ ሰው ናቸው። በማንነት ጉዳይ እኛ የዚህ ዘመን ልጆችም ልንከራከራቸው እንችላለን። ለምሳሌ እኔ በዚች የቅርብ ቀን የፍርድ ቤት ትዝብቴ ብልታቸው ላይ ውሃ የሚንጠለጠልባቸው አብዛኛዎቹ የአማራ ልጆች መሆናቸውን ታዝቤያለሁ። ይህም ትህነግ “አማራን አጠፋለሁ” ብሎ የጀመረውን ፖሊሲ እያስፈፀመ ስለመሆኑ ግልፅ ነው! ዝርዝር ማቅረብ እችላለሁ። ሲመረመሩ “አማራን እናጠፋዋለን” እየተባሉ ነው። እነ አበበ ካሴ፣ እነ አስቻለው ደሴ፣ እመ ዮናስ፣………በተመሳሳይ መንገድ ስቃይ አይተዋል። እነሱም አማራ በመሆናቸው እንደተጠቁ ያምናሉ። አቁሳዮቹ ፈርጀው ሲበድሉ፣ የቆሰሉት በማንነታቸው መጠቃታቸው በአንደበታቸው ሲናገሩ ፕሮፌሰር ምን ቤት ነኝ ማለታቸው ይሆን?

ጎንደር ካገኘኋቸው ወጣቶች መካከል አብዛኛዎቹ ፕሮፌሰር መስፍንን ይጠሏቸዋል። በእርግጠኝነት መናገር የምችለው ፕሮፌሰር ጎንደር ፒያሳ ላይ በእግራቸው ቢንቀሳቀሱ የሚወቅሳቸው ሰው ብዙ ነው። ከዛ ያለፈ የሚያስብም ይኖራል። ይህ የሚያሳየው ማንነቱን ብቻ ሳይሆን፣ በማንነቱ የሚያጠቃውን ብቻ ሳይሆን “የለህም” የሚለውን አንድ ግለሰብም ያውቃል ማለት ነው!

በሌላ በኩል ግን ፕሮፌሰር “አማራ የለም” በማለታቸው የሚሳደብ ይኖራል። ስድብ በምንም መመዘኛ የሚደገፍ አይደለም። አማራ ነህ ተብሎ እየቆሰለ ለሚገኝ አካል “የለህም” የሚል አጀንዳ ቁስል ላይ በርበሬ እንደመጨመር ነው! ፕሮፌሰር እየተከራከሩ ያሉት ከብሔርተኛ ጋር መሆኑም መታወቅ አለበት!

ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን ይህን የቆሰለ ሕዝብ ማንነት ፕሮፌሰር ላይ ስድብ ባወረዱባቸው ፌስቡከኞች ማጣጣልና ማጥላላት ተገቢ አይደለም። ስድብ አግባብ አይደለም ሌላ ክርክር ነው። በምንም ሁኔታ ፕሮፌሰርን መሰደባቸው ግን ክር ትክክል ሊያደርጋቸው አይችልም! ከምንም በላይ ግን ሌላው ማንነቱን ጠቅሶ ተጠቃሁ ሲል እውነት የሆነው “አማራ በመሆኔ ተጠቃሁ” ሲል “የለሁም” ማለት እየተፈፀመ ያለውን በደል ወደጎን ብሎ ማለፍ ብቻ አይደለም!

እኔ አይደለሁም፣ ነኝም የማለት መብት እንዳለኝ ሁሉ “እኔ አማራ ነኝ” የሚለው መብቱ ነው! የራሱን ማንነት የሚያውቀው እሱ ነውና መቀበል ግዴታዬ ነው! በተለይ አማራ ነህ ተብሎ እየተጠቃ፣ አማራ በመሆኔ ተጠቃሁ እያለ “የለህም” ማለት የለየለት የአስተሳሰብ አምባገነንነት ነው! የመብት ተሟጋች ነኝ የሚል አካል ደግሞ አንድ አካል ማንነት መቀበል ግዴታ አለበት! ለቁስሉ መጠብቀቅ አለበት። ማንነቱ ሳያከብር፣ ለቁስሉ ሳይንጠነቀቅ “ቆሰለ” ብሎ መጮህ አይቻለውምና!