March 23, 2018
አፄ ሚኒሊክ የባርያ ፈንጋይ ነበሩ ሲሉን ይደንቀኝ ነበር። በእርሣቸው ዘመን ዓለም በባሪያ ጉልበት የሚዘወር የኢንደስትሪ ዐቢዬት ላይ ነበረች። በዘመኑ ነፃ የነበሩ ሠዎች ሣይፈቅዱ በባርነት ቀንበር ስርም ነበሩ። እኔን የበለጠ የሚደንቀኝ ያልነበርኩበት ዘመን የባርነት ስርዐትም አይደለም። እኔን የሚገርመኝ ባለሁበት ይህ የህወሃት የስልጣን ዘመን በፈቃዳቸው በባርነት የሚያገለግሉ ፓለቲካዊ ባሪያዎች ጉዳይ ነው።
ህወሃት የሚሾምልንም በፈቃደኝነት ህሊናቸውንና ህዝባቸውን ለንዋይ እየሸጡ ለሆዳቸው ያደሩና ሆዳቸውን በህወሃት ትርፍራፊ የሚሞሉ የኛዎቹን ባሪያዎችና ታማኝ አገልጋዩን ነው። የህወሃትን አፓርታይዳዊ ስርዐት የቆመው በነዚሁ ፈቃደኛ ባሪያዎች ተባባሪነት ነው። ጣሊያንም ሃገራችንን በወረረበት ወቅት ዱር ገደሉን፣ ሜዳ ሸንተረሩን ሠንጥቆ ወደ መሃል ሃገር የገባው በመለመላቸውና ለጥቅም ወገናቸውን በሸጡ መንገድ መሪ ባንዳዎች አማካይነት እንደነበር ትውስ ይለናል። ህወሃት እነዚህን ባሪያዎች የሚሾምልን እነርሱን በማየት የባርነት ስርዐት የለም ብለን እንድንቀበልና ዓለምም እንዲያምን ነው።
የስርዐቱ ጋሻ ጃግሬ ግለሰቦችን በመሾም የገለማና ያበቃ ስርዐትን ማደስ አይቻልም። ስርዕቱን የገለማ ያደረጉት እነዚሁ ለሆዳቸው ያደሩና የገለሙ ግለሰቦችም ናቸው።
የሃገሬ ኢትዮጵያ ህዝብ የሚፈልገው የስርዐት ለውጥ እንጂ የባሪያ ፈንጋዮችን በፈረቃ መቀያየር አይደለም። ነፃነትና ዲሞክራሲ የምንጎናፀፈው የህወሃትን ባርያ ሎሌዎች በመለዋወጥ ሣይሆን መሠረታዊ የስርዐት ለውጥ ማምጣት ስንችል ብቻ ነው።
‘ተነሱና ለፀሃይ ሰላምታ ስጡ’ በሚለው የሱዛን ቃሲም መፅሃፍ ውስጥ ይህን እናገኛለን::
“በዚህ ዓለም ውስጥ እጅግ አደገኛ የሆኑና እኩይ ተግባራትን የሚቆሠቁሱ ህዳጣን አናሣዎች ሣይሆኑ የነርሱን እኩይ ተግባር የሚይራምዱና በነርሱ ስም የሚተገብሩ ናቸው:: ለአብነት ያህል እንግሊዞች ህንድን በወረሩበት ወቅት የእንግሊዞቹን እኩይ ተግባር ተቀብለው ወረራውን ለመመከት የሚፋለሙትን ህንዳውያን ይገሉ የነበሩት እራሣቸው ህንዳውያን ነበሩ:: በሌላ አነጋገር ጥቂት ህንዳውያን ከእንግሊዛውያኑ ለሚሠጣቸው ሽርፍራፊ ክፍያ ሲሉ እንግሊዞቹን ተክተው ህንዳውያንን ሲገድሉና ሲያስገድሉም ነበር:: ዛሬም በተለይ በአፍሪካና መካከለኛው ምስራቅ ከምዕራባውያን ነብሰ ገዳዮች ጎን ተሠልፈውና ወግነው ለሚከፈላቸው ንዋይ ሲሉ ወገኖቻቸውንና የሌሎች ጎሣ ተውላጆችን ያለ ርህራሄ የሚገድሉ መሆኑ ነው:: እነዚህ ለሽርፍራፊ ጊዜያዊ ክፍያና ጥቅም አድረው ና ህሊናቸውን ሸጠው በዚህ ተግባር ባይሰማሩ ኖሮ እኩይ ሃይሎች እኩይ ተግባር ለመፈፀምም ባልቻሉ ነበር:: ያው ገንዘብ የተራቡትን ፣ ተስፋ የቆረጡትን ፣ ተስፋቸው የተሠበረውን ፣ ገብጋቦችንና ችግርተኞችን እስካማለለ ድረስ በወንድማማቾች መካከል የሚደረገው ጦርነት ማብቂያ የለውም::”
(“Rise Up and Salute the Sun”)
Suzy Kassem
# ምርጫችን ዲሞክራሲያዊ መንግስት እንጂ የክሌፕቶክራት መቀያየር አይደለም
# ህወሃት ይሞታል
