March 24, 2018
የፕሮፌሰር መስፍን ነገር!
ፕሮፌሰር መስፍን በአማራ ጉዳይ በጻፉት ነገር ወቀሳ ሲመጣ መለስ ለመስጠት ሞክረዋል፡፡ መልሳቸው በጠቅላላው በስድብ የተሞላና ምንም ቁምነገር የሌለው ነው ማለት ይቻላል፤ ከዚህ በፊት ደጋግመው የተናገሩትን የራሳቸውን ሐሳብ ራሱ የሚቃረንም ነው፡፡ ፕሮፌሰሩ ለአንዳንዶች ጣዖት ለሌሎች ደግሞ የሰይጣን ቁራጭ ተደርገው ይሳላሉ፡፡ እሳቸውም ይህን ያውቃሉ፤ እንዲህ እንደፈለጉ ለምንም ለማንም የማይጠቅመውን እንቶ ፈንቶ የሚናገሩት ግን ምናልባትም እንደጣዖት የሚመለከቷቸው ሰዎች ጋሻ እንደሚሆኗቸው በማሰብ ሳይሆን አይቀርም፡፡
በስድብ ከተሞላው መልሳቸው ዛሬ የተሻለ የተናገሩት ‹‹አማራ የሚባል ሕዝብ የለም›› አላልኩም ማለታቸው ብቻ ነው፡፡ ምንም እንኳን ከዚህ በፊት ካሉት ከራሳቸው ሐሳብ ጋር የሚጋጭ ቢሆንም ይህን ማመናቸውም መልካም ነገር ነው፡፡ የአማራን መኖር ለማረጋገጥ ይህን ያክል ክፉና ደግ እስኪባሉ ድረስ መቆየት አልነበረባቸውም፡፡ በሽግግሩ ወቅት አማራ የሚባል ሕዝብ ሳይኖር ሊወከል አይችልም ብለው እኩል ከሕወሓት ጋር የተስማሙበት ድምጽና ምስል ከታች ማዳመጥና ማየት ይቻላል፡፡ ሕወሓት በጊዜው ያለው አማራ አለ ግን ባይወከልም እኛ እንወክለዋለን ሲሆን ፕሮፌሰር መስፍን ግን አማራ የለም፤ የሌለ ሕዝብ ደግሞ ሊወከል አይችልም የሚል ሐሳብ ነው ያንጸባረቁት፡፡ ሁለቱም ክሕደት ሆኖ ሕዝባችን ሀይ ባይ በሌለበት ተጨፍጭፏል፡፡
እንደዕውነታው ከሆነ ፕሮፌሰር መስፍን ለእኔ የዕውቀትም የሞራልም መመህር ናቸው ብዬ አላስብም፤ እሳቸው ራሳቸውን የሁሉም ነገር መለኪያ አድርገው እንደሚያስቡ ሁሉም ሰው እንደዚያ ያስባቸዋል የሚል እምነትም የለኝም፡፡ ይህ ነገር እሳቸውን እንደጣዖት የሚያመልኳቸውን ሰዎች ሊያስከፋ እንደሚችልም አውቃለሁ፡፡ እርግጥ ነው አምልኮ ምክንያታዊነትን አይቀበልም፤ ስለሆነም ማንም ሰው የሚያመልከውን ሲተቹበት አይወድም ይህን ስለምረዳ ያለአመክንዮ የሚያስተጋቡ ሰዎች ቢኖሩ ብዙም አይገርመኝም፡፡
አሁን ለምን የሞራልና የዕውቀት ማጣቀሻ መሆን እንደማይችሉ ላስረዳ፡፡ አንድ ሰው እስከሠራ ድረስ ይተቻል፤ እንኳንስ እሳቸው ፈጣሪም ይወቀሳል፡፡ እሳቸውም ‹‹ጃንሆይን›› ሌባ ሌባ እያለ አንቆ የገደለን ሥርዓት፤ ለአገር ቅን አሳቢ ምጡቅ ምሁራን በአንድ ጀምበር ለቀበረ የመርማሪ ኮሚሽን ሆነው ሠርተዋል፡፡ የእሳቸው ሚና ምንም ይሁን ምን በዚያ መሳተፍ በራሱ ትርጉም አለው፡፡ ስለሆነም እሳቸውን መተቸት ተገቢም ብቻ ሳይሆን የግድም ነው፡፡
የሰብአዊ መብት ተቆርቋሪ ድርጅት በማቆም የሰብአዊ መብት ተሟጋች ነኝ የሚሉት ፕሮፌሰር መስፍን የሰው ልጆችን መብት መርገጥ ለሌላው ቡድን እንጅ እሳቸውን እንደሚመለከት ብዙም ግንዛቤ ያላቸው አይመስልም፡፡ ፕሮፌሰር መስፍን ምንም ዓይነት ሐሳብ ይዘው ይምጡ ያን ሐሳብ የሚተች ሁሉ የግለሰቦችን ማንነትና ክብር እየነኩ ይተቻሉ፡፡ በዚህም በዙሪያቸው የሚያጨበጭቡላቸው፣ በየልደት በዓላቸው እንደነ ሚጡና ቤቢ ኬክ የሚቆርሱላቸው፣ ወዘተ ወዘተ ሰዎች ብቻ ናቸው የሚቀርቧቸው፡፡ ስለዚህ በሳቸው ዘንድ የሐሳብ የበላይነት የሚባል ነገር የለም፡፡ ከዚህ በፊት በነዳንኤል ክብረት፣ በነፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ ላይ የሰጡትን ውርጅብኝ ማየት ይቻላል፡፡
አሁን ደግሞ አማራ የለም ማለታቸውን ተከትሎ የተሰነዘረባቸውን ትችት የመለሱበት መንገድ በእጅጉ ያሳዝናል፤ ሀበሻ ሲተርት ‹‹ካረጁ አይበጁ›› የሚለው አባባል እንደሚሰራ የሚያሳይ ይመስላል፡፡ ከዚህ ላይ ለመግለጽ የሚያሳፍር ስድብ ደርድረው ደርድረው ‹‹አማራ አለ›› የሚል ድምዳሜ ላይ ደረሱ፡፡ አማራ አለ ያሉትም ምናልባት በdementia ከዚህ በፊት ያሉትን ረስተው ሳይሆን አይቀርም፡፡
ትውልድን በጅምላ፣ አማራን በጅምላ እየተሳደቡ እሳቸውን የሚሰድባቸው ሰው ቢኖር ለምን ይገርማል? አንድ ሰው ወደታች ሲወርድ የሚሆነው ይኼው መሆኑን መረዳት ብዙም ከባድ አልነበረም፡፡ የሞራል መምህር ለመሆን በሕይወት የተገለጠ ሥራ ያስፈልጋል፡፡ በዚህ ሥራቸው የሚናደድ ሰው ከዚያስ ያለፈ ቢያደርግ ምን ይደንቃል! ጋዜጠኛ ጌታቸው ሺፈራው በጎንደር የታዘበው ይኼኑ ነው፡፡
አዋቂ ሰው ለዕውቀት ክርክር ቦታ ይሰጣል፤ የሚተችን ሁሉ ስድብ በማከናነብ አሳዳጊ የበደለህ እያሉ እንዲፈሩ ማድረግ እኔ አዋቂነትም ሞራላዊም ነው ብዬ ማሰብ ይከብደኛል፡፡ ትውልድን ሁሉ አሳዳጊ የበደለህ ከማለትም የእሳቸው አባትና እናት እንዴት አድርጎ እንዳሳደጋቸው ታሪካቸውን ቢነግሩን በሕይታቸው ምናልባትም ትምህርት ልንቀስም እንችል ይሆናል!!
