March 27, 2018
በ 14/07/2010 ዓ.ም. ሰሜን ጎንደር በወገራ ወረዳ እንቃሽ ቀበሌ ቀንባዳ ልዩ ቦታው አርብ ገብያ ተብሎ በሚጠራው ቦታ ላይ ለወያኔ ጠቁመው እየመሩ የህዝብ ልጆችን የሚያስመቱ ላይ እርምጃ ተወሰደባቸው። ከአሁን በፊት ሁለቱን ወጣቶች አደራጀው ጋሻውንና መልካሙ ጋሻውን እርሻ ላይ እያሉ የወያኔን ሰራዊት በመምራት አምጥተው ለሞት የዳረጓቸው የወያኔ ተላላኪ ወንድማማቾች ካሳው ታየና ደሴ ታየ በተለመደው ስራቸው ሌሎችን ለማጥመድ ወደ ቦታው ያመሩ ሲሆን ይህን የሠሙት የጎበዝ አለቆች ፈጥነው ተወርውረው በመድረስ በከፈቱት ተኩስ ዋና ጠቋሚ የሆነውን ካሳው ታየን በመግደል ከሌሎች ጋርም ለሠዓታት የወሠደ ውጊያ ካደረጉ በኋላ ተጨማሪ ኃይል ስለመጣባቸው ምንም ጉዳት ሳይደርስባቸው በድል ወደ ቦታቸው ተመልሠዋል፡፡
የጎበዝ አለቆቹ የወያኔ ተላላኪዎች ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በተደጋጋሚ የተሰጣቸውን ማስጠንቀቂያ አሻፈረኝ ስላሉ እራሳችንን ለመከላከል ተገደናል ይህንንም አጠናክረን እንደምንቀጥል እንዲታወቅ ብለዋል።
ሌላው በሳምንቱ ማብቂያ ወያኔ የአማራ ወጣቶችን የሚያጠምድበት የተለመደውን የከተሞች መድረክ ፕሮግራም በዳባት ከተማ አዘጋጅቶ ነበር፡፡ በፕሮግራም አብዛኛው የከተማው ወጣቶች ያልተገኙ ሲሆን የተወሰኑ ደግሞ ምን እንደሚካሄድ ለማረጋገጥ ተገኝተው ነበር፡፡ በተዘጋጀው መድረክ ወያኔ ራሱ ያዘጋጃቸው ባንዳዎች ለ27 አመታት ምንም አይነት ልማት በማይታይባት በዳባት ከተማ ላይ እየተሰራ ያለው ስራ መልካም ነው በማለት ንግግር ማድረግ ሲጀምሩ የሃሰት ወሬ መስማት የሰለቸው ነዋሪም የምትሉት ነገር ሃሰት ብቻ ሳይሆን ቁጣችንን አባብሶታል በማለት ተጋፍጧቸዋል።
ወጣቱ ከሃገር ተሰዶ፣ ከአስራ ሁለት ሰዓት በኋላ መንቀሳቀስ በማይችልበት፣ ለአብዛኛው ወጣት የስራ እድል ባልተፈጠረበት ሁኔታ ያልታየ ልማት አለ የሚል ሪፖርት መስማት አንፈልግም በማለት ስብሰባውን አቋርጠው ሲወጡ ኗሪውም ተከትሏቸው ወጥቷል። የተካሄደው የመድረክ ስብሰባም በጭራሽ የዳባትን ህዝብ የማይወክል ነበር፡፡ ህዝቡ ዳባት የፋብሪካ ሳይሆን የኩበት ጭስ ያፈናት ከተማ እንድትሆን ያደረጋት ወያኔ ነው። ዳባት በስሯ የነበሩት ወልቃይት ጠገዴ መመለስ አለባቸው ብለው አስረግጠው ነግረዋቸዋል።
