180 አባላት ያለው የኢህ አዴግ ምክር ቤት በአብላጫ ድምጽ ዶ/ር አብይ አህመድ የድርጅቱ ሊቀመንበር እንዲሆኑ መረጠ:: በዚህም መሰረት ዶ/ር አብይ የሃገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስተር ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል::

ዶ/ር አብይ የኦህዴዶችን እና የብአዴኖችን ድምጽ ማግኘቱ የተገለጸ ሲሆን በአጠቃላይ 108 ድምጽ ማግኘቱ ተገልጿል:: ዶ/ር አብይ አህመድ ቦታውን እንዳይዝ ሕወሃቶች ከፍተኛ ትግል ሲያደርጉ መቆየታቸው አይዘነጋም:: የህወሓቶች ምርጫ ደመቀ መኮንን እንደነበር ሲገለጽ የቆየ ሲሆን የብ አዴን አባላት ሳይቀሩ ድምጻቸውን ለዶ/ር አብይ መስጠታቸውን ለዘ-ሐበሻ የደረሰው መረጃ አመልክቷል::

 

_____
ዶክተር አብይ አህመድ ማን ናቸው? (ኢህአዴግ ከበተነው መረጃ የተገኘ)
የትውልድ ስፍራ፦ ጅማ ዞን
 
የትምህርት ዝግጅት፦ የመጀመሪያ ዲግሪ በኮምፒውተር ኢንጂነሪንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪ በትራንፎርሜሽናል ሊደርሺፕ እና ቼንጅ፣ ማስተርስ ኢን ቢዝነስ አድሚኒስትሬሽን እና በክሪፕቶ ግራፊ እንዲሁም የዶክትሬት ትምህርታቸውን በ“ፒስ ኤንድ ሴክዩሪቲ” አግኝተዋል።
 
የስራ ልምድ፦ በመከላከያ ሚኒስቴር ውስጥ እስከ ሌፍተናንት ኮሎኔል ድረስ በተለያዩ ስፍራዎች ሲያገለግሉ ቆይተዋል፣ የፌደራል ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ የልህቀት ማእከል ዋና ዳይሬክተር በመሆን አገልግለዋል፣ በኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ ውስጥም በምክትል ዳይሬክተርነት አገልግለዋል። በተጨማሪም የኢፌዴሪ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመሆኑ አገልግለዋል።
 
የኦሮሚያ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ካቢኔም በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የከተማ ልማት እና ቤቶች ቢሮ ሃላፊ በመሆን ሰርተዋል።
 
ዶክተር አብይ አህመድ የኢህአዴግ አባል ድርጅት የሆነው ኦህዴድ ሊቀመንበር ናቸው።