ከደረጀ ደስታ

ቆዩ ተብለን የለ! እርሟን ብታፈላ…በምንለው ሰበር ዜናቸው እስኪሰብሩን ይህን የትዝብት ሙዚቃ እየሰማን እንቆይ።

የአቶ መለስ የመቃብር ሥፍራ በሁለት የፌደራል ፖሊሶች 24 ሰዓት እየተጠበቀ መሆኑን ሄዶ የተመለከተ ሰው ሲነግረኝ ችላ ብዬ ትቼው ነበር። እነ እስክንድር ነጋን ወደ እስር ቤት የነዱ ፖሊሶችን ስመለከት ትዝ አለኝ። መልሰው ያሰሯቸው ስለ ትዕቢትና ጥላቻቸው ወይስ መጠን ስላጣው ፍርሃታቸው እሚለው ጥያቄ ሳይሆን አይቀርም ወደዚያ የወሰደኝ። ሞተውም ይፈራሉ እንዴ እያልኩ፣ ሀሳብን ሀሳብ አንስቶት ፣ የእስረኞች ቤተሰቦች ዘንድ ወሰደኝ። ደግሞ እንደፈረደባት ከ6 ዓመታት በኋላ ለልጇ ስንቅ ቋጥራ እምትሄድ ያንዳቸው እናት፣ ሚስት፣ ወይም እህት የሆነች ሴት ታየችኝ። ወንዶች እንኳ ያው ሁሌ ስንገድልም ሆነ አሟሙቀን ስናስገድልም ጭካኔ ሰለማያጣን የሴቶች እንባ አይታየንም። ቢጨንቀኝ ከገዳይ ከአሳሪዎቹ ወገን የሆኑት ሴቶች፣ በተለይ እንደ ቀዳማይ እመቤት ያሉት ግን ስለ እነኚህ እናቶች እንባ ሲያስቡ ምን ያስቡ ይሆን ብዬ ወደዚያም አሰብኩ። በተለይ ባለቤታቸው እስር ቤቶችን ሙዚየም እናደርጋለን ያሉት የአቶ ኃይለማርያም ሚስት ምን ይሉ ይሆን?

አይ እሳቸውማ ብዬ ተውኩት። የራሳቸው ጉዳይ ይዟቸው ሰሞኑን ብርቱ ድካም ላይ መሆናቸውን የሰማሁ መሰለኝ። ባለሥልጣናት ከሥልጣን ሲወርዱ ወደፊት መጦሪያ እሚሆን ቤት እየተሰራላቸው መሆኑን ሰምተናል። የቤቶቹ ፕሮጀከት ለጥበቃም ሆነ ለድርጅታዊ ህይወት ቀጣይነት እንዲመች የጋራ መኖሪያ እንዲሆን ታስቦ የተሰራ ነው። ሰፈሩ ገበያው መዝናኛው መዋኛው የጋራ እንዲሆን ሆኖ ተሰርቷል። ከጠቅላይ ሚኒስትርነት እየተነሱ ያሉት ኃይለ ማርያም ደሳለኝ ይህ ይጠብቃቸዋል። ቤቶቹ ጥቃቅን ነገሮች ቢቀሯቸውም አልቀዋል ማለት ይቻላል። ቢሆንም ለጠቅላይ ምኒስትሮች ብቻ ሳይሆን ለሌሎችም ከፍተኛ ባለሥልጣኖች ስለሆነ የተሠራው የአቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ባለቤት አላስደሰተም። ቀዳማይ እመቤቲቱ ቤቱን እየተመላለሱ መከታተሉ አድክሟቸዋል። ከሁሉ ከሁሉ ያበሳጫቸው የመዋኛው ገንዳ የጋራ ሆኖ ተሰርቷል መባሉ ነው። ሴትዮዋ ተሟገተው ለጠቅላይ ሚኒስትሩ ቤት ብቻ እሚሆን የመዋኛ ገንዳ እያሰሩ ነው መባሉ ግን ትንሽ ልብወለድ መሰለ!

እንግዲህ ሰሞኑን ለታሰሩት ጋዜጠኞች ስንቅ ለማቀበል እምትሄድ እናትና የወደፊት መኖሪያ ቤቷን ሥራ ግንባታን ለመከታተል በምትሄድ ሴት መካከል ያለውን ልዩነት ማሰብ ነው። ይህ እናቱ የሞተችበትና ገበያ የሄደችበት እኩል ያለቅሳል- ብለው አቅልለው እሚገላገሉት ተረት አልመሰለኝም። ይህን የተገነዘበ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታና ሰዎቹ ምን እያሰቡ እንደሆነ መረዳት ይችላል። ምንም እንኳ ዋነኞቹ ባለሥልጣኖች እንደዚህ የውሸት ባለሥልጣናት ከሆኑ ሰዎች ጋር መኖሪያ ተጋርተው ይኖራሉ ተብሎ ባይጠበቅም፣ የአብዛኞቹ ቤት አሜሪካና በሌላው አገር እሚሰራ የዶላር ቤት መሆኑን መገመት አያዳግትም። አገርም ሆነ ውጭ አገር ቢሆንም ግን ሌላ ነገር መግለጹ አይቀርም። እነዚህ ሰዎች ገና ገዝተው ገዝተው ሲደክማቸው መጦሪያቸውን ሁሉ ሳይቀር በረጅሙ ለማድረግ ያቀዱ ተስፈኞች ናቸው። ወይ አልገባቸውም ወይ አልገቡንም!