ዶክተር አቢይ ዛሬ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ ከመመረጡ እጅግ ቀደም ብሎ እጅግ ብዙ ህዝብና የፖለቲካ ድርጅቶች ያልተለመደ አይነት ድጋፍ ሰጥተውታል። ሰወችም ድርጅቶችም በሀሀገራችን ውስጥ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል፤ ከፋፋዩን ስርአት እንዲያከትም ያደርጋል፣ የኢትዮጵያንም ታላቅነት እንደገና ከፍ ያደርጋል በማለት ብዙ ተስፋ እንዳደረጉበት በተለያየ መልክ ተገልጧል።
ያም ሆኖ ግን በእርግጠኛነት መናገር ያልተቻለው በ ኢህአዴግ ውስጥ የሚኖረው ድጋፍ ምን ያክል እንደሆነ ማወቅ ነበር።አ ሁን ግን ሁኔታው ቁልጭ ብሎ ታይቷል።
ዶክተር አብይ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ሆኖ መመረጡ ያውም በ109 ድምጽ በህወሀት መራሹ መንግስት ውስጥ ስላለው ሁኔታ ያመላከተው እጅግ ከፍተኛ ነገሮችን ነው።
በመጀመሪያ ኢህአዴግ እንደ ኢህአዴግ አንድነት የሌለው ብቻ ሳይሆን ከፍተኛ መሰነጣጠቅ የደረሰበት ድርጅት መሆኑን እና ስንጥቁም በቀላሉ የማያገግም እጅግ ጥልቅና ሰፊ መሆኑን ነው።
ሁለተኛ የህወሀቱ የዶክተር ደብረጽዮን ያገኘው አጠቃላይ ድምጽ እንደ እናት ጡት ሁለት ብቻ መሆኑ ራሱ ህወሀት ውስጡ ያልተረጋጋና እጅግ ከፍተኛ መከፋፈል ያለበት መሆኑን ያሳያል።ለነገሩ አባይ ወልዱን ከስልጣን ካባረሩበት ጉባኤ ጀምሮ ይህ መከፋፈል እጅግ ጥልቅ እንደነበር ሲነገር የቆየ ነው። ያም ሆኖ ግን ህወሀቶች ደብረጽዮንን አለመፈለጋቸው ሳይሆን የነርሱ ተወካይ እንደማያፈንፍ ሲያውቁ ድምጻቸውን እስትራተጂክ በሆነ ሁኔታ ለሌላ ተወካይ ሰጥተዋል ማለት ነው።
ሌላው ተወዳዳሪ ሽፈራው ሽጉጤ ደግሞ ባፍቃሪ ህወሀትነቱ በሰፊው የሚታወቅ ግለሰብ ነው። ህወሀት ከነበረው 45 ወንበር ውስጥ ለደብረጽዮን ድምጽ ከሰጡት ከሁለቱ በስተቀር ሌሎቹ በሙሉ ለሽፈራው ሽጉጤ ድምጽ ሰጥተዋል ብለን ብንገምት ፤ ህወሀትም ሆነ የርሱ ድጋፍ የነበረው ሽፈራው ሽጉጤ ከራሱ ከደቡብም ይሁን ከሌሎቹ ያገኘው 16 ድምጽ ብቻ ነው ማለት ነው (43 ዌያኔወች+ 16 ደቡብ እና ሌሎች)። ይህም ማለት ህወሀትና አጋሮቹ ባሁኑ ሰአት በኢህአዴግ ውስጥ ያላቸው ድጋፍ እጅግ ደካማ ነው ማለት ነው።
ይህ ሁኔታ ዶክተር አብይና ለደጋፊወቹ አሁን በእጃቸው የገባውን ስልጣን እጅግ ጥልቅ የሆነ እርምጃን ለመውሰድ የሚያስችል ማንዴት ይሰጣቸዋል። ከመጀመሪያውም ዶክተር አብይ በኦሮሚያም ሆነ በሌላው የ ኢትዮጵያ ህዝብ የአይዞህ ባይነትን ድጋፍ ያገኙት ሕወሀት ሲያቀነቅነው ከነበረው አጀንዳ በተለየ መልኩ የለውጥ አጅንዳ ይዘው ስለተንሳቀሱ ስለነበር ነው። አሁን ደግሞ ከህዝብ ብቻ ሳይሆን በራሱ በኢህአዴግም ውስጥ ጭምር የለውጥ አጅንዳ በሰፊው ለማስተግበር የሚያሰችላቸው ከፍተኛ የሞራልም የፖለቲካ ድጋፍም አላቸው ማለት ነው። ይህ ነው ሰፊ የፖለቲካ ካፒታል ማለት።
ስለዚህም ዶክተር አብይና ደጋፊወቻቸው ያለምንም ማመንታት መሰረታዊ ለውጥን እውን የሚያደርግ እርምጃወችን ለመውሰድ የሚያሰትላቸው ሰፊ እድል አላቸው። በዚህም መሰረት ይህን ሰፊ የፖለቲካ ካፒታል ከንግንርና ከተስፋ ባለፈ ተጨባጭ እርመጃወችን በመውሰድ ሊጠቀሙበት ይገባል። ይህ ማለትም
-
የህዝባችንን የዴሞክራሲያዊና ፖቲካዊ መብት ማክበር
-
የብሄራዊ እርቅና መግባባትን ፣ ሁሉን አሳታፊ የሆነ የፖለቲካ ስርአት መፍጠርን፡ ይህን ለማድረግ ከሁሉም ባለድርሻወች ጋር ይፋ ውይይት መጀመርን
-
የፖለቲካ እስረኞች (ከትላንት ወዲያ በድጋሜ የታሰሩትን እነ እስክንድርን መፈታትን ጨምሮ)
-
አፋኙን ያስቸኳይ ጊዜ አዋጅና፤ በየቦታው የሚታየውን ጭፍጨፋ ህዝብን ማስሸበር ወዘተ ባስቸኳይ እንዲቆም ማድረግ
-
አፋኝ የሆኑትን የሚዲያ፣ የሲቪክ ማህበራት አዋጅ ወዘተ መሰረዝ ወዘተ ይጠይቃል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስቴር ህዝብ ወደሚፈልገው የለውጥ አቅጣጫ የሚያመራ መሆን አለመሆኑንም ገና ከመጀመሪያው ለህዝብ ከሚያደርገው ንግግር ጀምሮ ማየት ይቻላል።

