March 28, 2018

ዶ/ር አብይ አህመድ የኢህአዲግ ሊቀመንበር ምናልባትም የኢትዮጵያ ቀጣዩ መሪ ሆነዉ በኢህአዲግ በመመረጣቸዉ ብዙ አስተያየት እየተሰጠ ነው።  ካሉት የኢህአዲግ ሰወች ዶ/ር አብይ መመረጣቸዉ በዚህ ወቅት በራሱ ግብ ተደርጎ ባይታይም ጊዚያዊ ጥቅም አለዉ።  በወያኔ ሚስጥራዊ አሰራርና ያለፈዉ የተንኮል ታሪክ  የተነሳ፣ ዶ/ር አብይ ወደስልጣን እንዲውጡ የተመረጡበት ግብ  በግልጽ አይታወቅም።  ሆኖም ግን በዚህ ፖለቲካ ቀዉስና የህዝብ አመጽ ዉስጥም ቢሆን የዶ/ር አብይ አህመድ መመረጥብዙ ዜጎች ተስፋ እንዲኖራቸው አድርጓል።

በአገሪቱ አንድነት ላይ አንዣቦ የነበርዉ አደጋ ጊዚያዊ መፍትሄ ያገኘ ይመስላል።  ኢትዮጵያ መፍረስ አለባት፣ ኢትዮጵያዊነት የሚባል ነገር ፈጽሞ የለም፣ በቅኝ ግዛት ተይዘናልና የመሳሰሉትን የአገር አንዲነት የሚያፈርሱ አስተዛዛቢ መልዕክቶችን ሲያስተላልፉ የነበሩት ጠባብ የጎሳ ፖለቲከኞችን አፋቸዉን እንዲዘጉ ያደጋል።  በመጠኑም ቢሆን የወያኔወችን ከፋፍይ ስልት ሊገዳደሩ ይችል ይሆናል ተብሎም ተስፋ ይደረጋል።  የዶ/ር አብይ የአመራር ችሎታ የሚመዘነው ከእንግዲህ በኋላ በሚሰሩት ስራ ብቻ ነው።

በእዉነት የህዝቡን ብሶት የሚያዳምጡ  ከሆነ፣ ዶ/ር አብይ ብዙ ፈተናወችን ሊጋፈጡ ነዉ። እንደዚሁም ብዙ ዕድል ከፊታቸዉ አለ።  ችግሩን በስልትና በጀግንነት ተጋፍጠው፣ ይህን ያገኙትን ዕድል ተጠቅመዉ፣ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን መጥቀም የሚችሉት አገሪቱን ወደዚህ ችግር ያደረሳትን የችግሩን ምንጭ በመለየት ችግሩን በትክክልና በፍጥነት መፍታት የሚያስችል ስልት በመንደፍ በተግባር ላይ ካዋሉ ብቻ ነው።

አገራችንን ለዚህ አሁን ለገባችበት ችግር ያበቃት ወያኔ በስልት የገነባዉ ዘረኛ፣ ከፋፍይ፣ ዘራፊ፣ አፋኝ፣መሰሪ፣ ጨካኝና፣አምባገነን ስርዓት ነው። የችግሩ ምንጭ ስርዓታዊ (systemic) ነዉ።  ችግሩ ከግለሰብና ከአንድ ዘውግ በለይ ነው።  ስለዚህ የግለሰብ መቀያየር ወይንም የአንድ ጎሳ መሪ ሂዶ የሌላ ጎሳ መሪ መምጣት ችግሩን አይፈታዉም።  ከአሁን በፊት “ትግላችን የችግሩ ስር የሆነዉን ስርዓቱን ማስወገድ ላይ ያትኩር” በሚል ርዕስ አገራችን ለገባችበት ፖለቲካዊ ቀዉስ ዋናው መንስኤ ወያኔ የገነባዉ ስርዓት መሆኑን በዝርዝር ለማሳየት ሞክሪያለሁ።  ዶ/ር አብይም ሆነ ሌላ ቀጣይ የአገሪቱ መሪ የኢትዮጵያን ችግር የሚፈቱቱ መጀመሪያ ይህን  አገር-አጥፊ ስርዓት የሚወገድበትን መንገድ ሲፈጥሩና የህግ የበላይነትና የዜጎች ዕኩልነት የሰፈነበት ስርዓት እንዲመሰረት በቅንነት ጥረት ሲያደርጉ ነው።

እዚህ ላይ የሚነሳው ጥይቄ፣ በዚህ ወያኔወች በመሰረቱት ስርዓትና የስለላ ድርጂት ዉስጥ ያደገና አሁንም ስርዓቱ ዉስጥ ያለ፣ በወያኔ ጦር ቁጥጥር ስር የሚኖር ዶ/ር አብይ በምን መንገድ ነው ስርዓቱን ሊያፈርሱ የሚችሉትና የተፈለገዉን ለዉጥ የሚያመጡት?  ለዚህ ዋናዉ መልስ ህዝብን ማዳመጥ፣ ቀናነትና ከህዝብ ጋር በመቆም ነው።  የኢትዮጵያ መሪ ከሆኑ ተጠሪነታቸው መሆን ያለበት በፓርቲ ፖለቲካ፣ በጎሳ፣ ቋንቋ፣ ወይንም ሃይማኖት ሳይለያዩ ለኢትዮጵያ ህዝብ ነው።  መመኪያቸውም መሆን ያለበት ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ እንጂ ኢህአዲግና እግር-ብረት የሆነው ዲሞክራሲያዊ ማዕከላዊነት መሆን የለበትም።  ይህንም ለማድረግ አቶ ሃይለመሪያም ያጡትን ወኔ ዶ/ር አብይ ሊኖራቸው ይገባል።

ከሁሉም መጀመሪያ በኢህአዲግ እግር-ብረት መታሰር ተላቀዉ ከሰፊዉ ኢትዮጵያዊያን ጎን የቆሙ መሆኑን፣ የህዝቡን ጥያቄ ለመመለስ መዘጋጀታቸዉን መቁረጣቸዉን ሳይዉል ሳያድሩ ለህዝብ በይፋ ማሳውቅ አለባቸዉ።  በዚህም ከኢትዮጵያዊያን ዘንድ ተዓማኝነትን ድጋፍንና ጠለላን ማግኘት ይጀምራሉ።  ህዝቡን ከያዙ የወያኔ ሃይል ላያስፈርቸው ይችላል። በአገሪቱ ባለደርሻወች፣ ዜጎች፣ ወይንም አጠቃላይ ህዝቡ ጋር በመሆን ሃይላቸዉን በማዳበር በአዲስ ዓይን አገሪቱ አሁን የገባችበትን ችግር መንስኤና ስርዓቱን በአዲስ መንፈስ መፈተሽና ለዉጥ ማማጣት ይጀምራሉ። ለዚህም ሁሉንም የፖለቲካ እስረኞችን መፍታትና ከተቃዋሚወችና ባለድርሻወች ጋር በግልጽ መወያየት የመጀመሪያዉ ተዓማኝነት የመገንቢያው እርምጃ ነው።  በዜጎች ላይ የሚፈጸም ሰቆቃና ግድያ መቆም አለበት።  የመብት መንፈጊያ ህጎች መሰረዝ አለባቸዉ።

አሁን አገራችን ካለችበት ሁኔታ ልናያት ወደምንፈልገው የህግና የፍትህ በላይነት የሰፈነባት ኢትዮጵያ ለመድረስ የሁሉም ኢትዮያዊ ተሳትፎና አስተዋፅዖ ያስፈልጋል። እንዴትና በምን ስልት መቼ እዚያ እንድረስ የሚለው በህዝብ ዉይይትና ምርጫ የሚወሰን በመሆኑ፣ አንድ የአገር መሪ ብቻዉን ሁሉን አውቅልሃለሁ ብሎ መቅረብ የለበትም።  ህዝብ፡በአገሩ፡ጉዳይ፡ወሳኝ መሆን አለበት። የመሪዉ ተቀዳሚ ተግባር ዜጎች በአገራቸዉ ጉዳይ ላይ በነጻነትና ዕኩልነት የሚሳተፉበትና በፍላጎታቸው ለአገራቸው አስተዋፅኦ የሚያደርጉበትን ስርዓት እንዲፈጠር ማመቻቸት ነው።

ህዝብን የናቀ መሪና “ስልጣን ያመጣዉ ዕውቀት” አገርን ወደ ጥፋት ይመራል።  ህዝብን ማዳመጥ ይገባቸዋል። እዉነትን በማይናገሩ ደካሞች ተከቦ፣ አገርን በትክክል መመራት አይቻልም።  የተለየ ሃሳብን ማራመድ ወይም ሃሳብን መቃወም ጠላትነት አይደለም።  እንዲያዉም የአንድ አገር የጥንካሬ ምንጭ ሆኖ መታየት አለበት።  ይህን የህዝብ አመፅ ማዕበል ማቆም አይቻልም። ነገር ግን ማዕበሉን ወደ በጎ ሃይል መቀየርና በጥቅም ላይ ማዋል ብልህነት ነው።  የዶ/ር አብይ እጣ ፋንታ የሚወሰነው አገራችንን ለዚህ አሁን ለገባችበት ችግር ያበቃትን ወያኔ በስልት የገነባዉን ዘረኛ፣ ከፋፍይ፣ ዘራፊ፣ አፋኝ ጨካኝና፣አምባገነን ስርዓት ለመቀየር በሚያደርጉት በተግባር የሚገለጽ አስተዋጽዖ ነው።  ከዛ ዉጭ የሚድረግ ጊዜ የመግዣ ወይንም ከላይ ከላይ የሆነ፣ የችግሩ ምልክት ላይ ያተኮረ የጥገና ለዉጥ፣ አገሪቱን ወደከፋ አደጋ ይወስዳታል።  ህዝብን ሰምቶ ህዝብን ይዞ ለህዝብ የሚበጅ ለዉጥ ማምጣት ይቻላል።  ዶ/ር አብይ ይህን ማድረግ ይችላሉን?  ይህ ጊዜ የሚያሳየን ነው።

ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር፤