March 29, 2018
መጋቢት 20, 2010
አማራው የመሪ ድሃ አይደለም!!! ድምፅ የሚሆኑት ድርጅቶችንም ፈጥሯል!!!
የአማራ ሕዝብ ባለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት፤ ለቁጥር የሚያስቸግር ሰዎች አልቀውበታል። ከግምት በላይ የሆነ ንብረት ወድሞበታል። በመላ ኢትዮጵያ ከቀየው ተፈናቅሏል፣ ተባሯል። በሚዘገንን ሁኔታ ታስሯል። ኢ-ሰብዓዊ በሆነ መንገድ ተገድሏል። በኢትዮጵያ ውስጥ በአማራዎች ላይ የደረሰውና በመድረስ ላይ ያለው አረመኔያዊ ግፍና በደል፤ ከሌሎች ዘግናኝ ድርጊቶች በተጨማሪ፤ እኛን ልጆቻቸውን በዓለም ዙሪያ እንድንበተን ማድረጉ ነው። እኛ የአማራ ልጆች፤ በየተበታትንበት ቦታ ሁሉ፤ ከወገናችን የሚደርሰን ዜናና በዜና ማሰራጫዎች የምንመለከተው በወገናችን ላይ የሚደረገው የዘር ማጽዳት ዘመቻ፤ እንቅልፍ ይነሳል። በምንችለው መንገድ ሁሉ ከዘመዶቻችን ጋር ሆነን፤ ይሄን ግፍ መቋቋም የተፈጥሮ ግዴታችን ነው።
በርግጥ ለረጅም ጊዜ የአማራው ማህበረሰብ ከቅድመ አያቶቹ የተረከበውን የኢትዮጵያን አንድነት የመጠበቅ አደራ በማሰብ በዘር መደራጀቱን አልተቀበልነውም ነበር። ነገር ግን ላለፉት ሀያ ሰባት አመታት በአማራው ላይ ያነጣጠረ የዘር ማጽዳት ዘመቻ የአማራውን ሕልውና አደጋ ላይ በመጣሉ በዘራቸው ተደራጅተው ዘሩን ሊያጠፉት የመጡትን ጠላቶቹን ለመመከት የሚችለው እና ከመጥፋት የሚድነው ብቸኛ አማራጭ አማራው በአማራነቱ በያለበት ተደራጅቶ እራሱን ከተጋረጠበት የመጥፋት አደጋ መጠበቅ መሆኑን አምኖ፤ በሀገር ቤት ገበሬው ወገናችን በያለበት በጎበዝ አለቃ ተደራጅቶ ነፍጥ አንስቶ እየታገለ ይገኛል። እኛም በውጭ ሀገራት በስደት የምንገኝ ልጆቹ በያለንበት ቦታ፤ በተለያየ አደርጃጀት በመደራጀት ትግሉን አቅማችን በፈቀደው መጠን ለመደገፍ በቆራጥነት ተነስተናል። እኛ በየቦታው የተደራጀነው አማራዎች፤ መሠረታዊ ጉዳያችን የአማራው ወገናችን ሕልውና በመሆኑ፤ በአማራ የፖለቲካ ድርጅቶቻችን፣ በተለያዩ ከተማዎች ባቋቋምናቸው የአማራ ኅብረተሰብ ማህበራት፤ የአማራ ሙያ ማህበራትን እና የዜና ማስራጫ ተቋማቶቻችን፤ በአንድነት በትግሉ ለመተባበር ተፈቃቅደን፤ አንድ የአማራ የመሪዎች ማዕከል አቋቁመናል።
ይህ ማዕከል የአማራ የፖለቲካ ድርጅቶችና ማኅበራት ስብስብ (አድማስ) ይባላል። ይህም ስብስብ መላ የአማራ ታጋይ ድርጅቶችን በአንድ በማምጣት፤ በሀገር ቤት የሚካሄደው የወገናችን ትግል ከግቡ እንዲደርስ ከፍተኛ ጥረት ያደርጋል። እዚህ ለመድረስ ያካሄድነው ጉዞ ቀላልና ለስላሳ አልነበረም። አማራው ራሱን ችሎ እንዳይደራጅና፤ በወገኑ እየደረሰ ላለው የዘር ማጽዳት ዘመቻ ከታጋይ ወገኑ ጋር አብሮ እንዳይቆም፤ ፖሊሲ ቀርጾ አማራውን ለማጥፋት እየታገለ ካለው የትግሬዎቹ ቡድን በተጨማሪ፤ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ መንገድ ከዚህ የጥፋት ጎን አብረው የተሰለፉ አካላት አሉ። እነዚህ አካላት፤ በተደጋጋሚ በአንድ በኩል፤ የአማራ ታጋይ ድርጅቶች የሉም፣ ቢኖሩም ብቁ አይደሉም፣ የሚል ዘመቻ አድርገዋል። በሌላ በኩል የአማራው ተወላጆች ወደ ተደራጁት ድርጅቶች እንዳይቀላቀሉ ከፍተኛ የማጥላላት ዘመቻ ከማድረግ ባሻገር የአማራ ድርጅቶችን ለማጣጣል ከፍተኛ ጥረት አድረገዋል።
የእነዚህ ክፍሎች የመጀመሪያ ጥረት አማራ እንዳይደራጅ ማድረግና ጠንካራ የአማራ ድርጅት እንዳይኖር ነበር። የአማራው መደራጀት አይቀሬ ሲሆን ደግሞ እነሱ በሚፈልጉት ለነሱ ግብዓት እንዲሆን ፈለጉ:: በዚህ አማራው እንዳይደራጅ እና እንዳይተበበር እንቅፋት ለመሆን ከዛም አልፎ የተደራጁትን ድርጅቶች ለመበታተን የሚደረገውን የጥፋት ዘመቻ በግምባር ቀደምትነት መምራት ላይ የሚገኙት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊወርጊስና ፕሮፌሰር ጌታቸው በጋሻው ናቸው። ለረጅም ጊዜ በዚህ ጉዳይ ላይ ተሰማርተው፤ ከፍተኛ የማፍረስ ተልኳቸውን ለመተግበር ሲሯሯጡ ቆይተዋል። እነዚህ አማራ ነን ለማለት እንኳን የማይደፍሩ ግለሰቦች፤ የአማራ ድርጅቶችን እና ማህበራትን ወደ አንድ እናመጣለን የሚል ማባበያ በመያዝ በተለያየ ቦታ የተደራጁትን የአማራ ድርጅቶች ለማሰባሰብ እና እነሱ ለሚፈልጉት አላማ ለመውሰድ ያደርጉት ጥረት አደገኛነት የአማራ ድርጅቶችን ግንዛቤ እንዲኖራቸው ያደረገ ነበር። የአማራ ድርጅቶችም የሰጧቸው ምላሽ “የአማራ ድርጅቶችን ለማስተባበር እና ወደ አንድ ለማምጣት የናንተ ጣልቃ ገብነት አያስፈልገንም በራሳችን ለራሳችን እንሰራዋልን እየሰራንበትም ነው:” የሚል ነበር። (ግለሰቦቹ ድርጅቶችን ለማሰባሰብ ብለው ሲያደርጉ የነበረውን የአንቅስቃሴ ሂደት የሚያሳይ ሙሉ መረጃ እጃችን ስላለ አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ ለህዝብ ይፋ እንዲሆን ይደረጋል)።
የአማራ ድርጅቶች የመሰባሰብ እና የመተባበር ጉዳይ በሌላ የሶስተኛ ወገን አነሳሽነት የሚሆን ጉዳይ ሳይሆን ከሕዝባችን በተደጋጋሚ የሚነሳ ጥያቄ በመሆኑ እና በተለያየ መልኩ የተደራጀን የአማራ ድርጅቶችም በጽኑ የምናምንበት በመሆኑ ከየካቲት ሰላሳ እስከ መጋቢት ሁለት በዋሽንግተን ዲሲ ባካሄድነው ዝግ የመሪዎች ስብሰባ የአማራ ድርጅቶች በተለይም በዚህ በሰሜን አሜሪካ የምንቀሳቀስ ድርጅቶች በየግላችን ከምናደርገው የትግል አበርክቶት እልፍ ያለ አዲስ የትብብር ምዕራፍ ጀምረናል። በዚህም ህዝባችን ደስታውን በተለያየ መንገድ በመግለጽ ላይ ይገኛል። ይህንን ተከትሎ አማራው የተለያዩ የፖለቲካ እና የስቪክ ድርጅቶች እንዲሁም ማህበራት እና የመገናኛ ብዙሃን በመተባበራቸው ደስ ብሎት፤ የትግሉ አካል በመሆን፤ ወገኑ በሚያደርገው የሕልውና ትግል አስተዋፆውን ለማድረግ በሚሯሯጥበት በዚህ ሰዓት፤ ሌላ የአማራውን ትግል የሚያዳክሙበትን መንገድ ቀይሰው “አንድ አማራ” የሚል ድርጅት ፈጥረናል ብለው፤ በአደባባይ ወጥተዋል። ስለሆነም ምንም እንኳ ከላይ የተጠቀሱት ግለሰቦች የፈጠሩት አዲስ ድርጅትን አስመልክቶ ምንም ለማለት ፍላጎቱ ባይኖረንም የድርጅቱን ምስረታ ይፋ መሆን ተከትሎ ከመስራቾቹ ሁለት ግለሰቦች እንዲሁም በድርጅቱ መሪነት የተውከሉት ግለሰቦች በዚህ በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የተለያዪ የአማራ ድርጅቶችን መደራጀት አስመልክቶ ከተነገሩ ብዙ ጉዳዯች ውስጥ በተለይም፤
1ኛ. የአማራ ድርጅት የለም፣
2ኛ. ቢኖሩም ድርጅቶቹ የድርጅት ቁመና የላቸውም:: መሪዎቻቸውም የአማራ ስነ ልቦና የላቸውም፤
የሚሉት ሁለት ጉዳዯች አማራው በሚችለው እና በሚመቸው አደረጃጀት ተደራጅቶ ለአለም አቀፉ የአማራ ህዝባዊ ንቅናቄ የድርሻውን እየተወጣ ባለበት ሰዓት ሁሉንም በዜሮ አባዝቶ እኛ ብቸኛው ተወካይ መጣንልህ አይነት በእብሪት እና በቅጥፈት የተሞላበት አካሄድ ምላሽ ስለሚያስፈልገው እና ስለ ድርጅቶች የተቀሰሩት እጣቶች ወደ እኛ ስለሚያመለክቱ ይህንን መግለጫ ልናወጣ ተገደናል:: ከላይ እንደተገለጸው ጠንካራ የአማራ ድርጅቶች መኖር ብቻ ሳይሆን የተበታተነው እንቅስቃሴያችንን ተፈጥሯዊ ሂደቱን ተከትሎ መስመር እንዲይዝ በአንድ ጥላ ስር ተሰባስበናል። ለዚህም የትግል ሽግግር ከህብረተሰቡ የመጣው ምላሽ በተናጠል እንቅስቃሴ ሲያደርጉ የነበሩ ድርጅቶች መሬት ላይ ህዝባቸውን ለማንቃት እና ለማደራጀት ያደረጉትን ጥረት ያሳያል። አሁንም ህዝባችን ከዚህም ከዛም በሚመጡ የህልውና አደረጃጀታችንን ለማወናበድ በሚሞክሩ ሃይሎች ሳይበገር መደራጀቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥራያችንን እናቀርባለን::
አድማስ- የአማራ ድርጅቶች እና ማኅበራት ስብስብ የአንድም አማራ ሃሳብ መቅረት የለበትም በሚል ፅኑ መርህ ላይ ተመስርቶ የተፈጠረ የድርጅቶች የትብብር ስብስብ እንደመሆኑ ምንም እንኳ ከላይ የተጠቀሰውን ድርጅት ፈጣሪዎቹ ለሚፈልጉት አላማ ያመቻቹት እና ያሰባሰቧቸውንም ወጣቶች ለዚሁ አላማቸው የሚጠቀሙባቸው ቢሆንም በዚህ ሂደት ውስጥ ተሳትፎ እያደረጉ ያሉ የህዝባቸው በደል አንገብግቧቸው የሚችሉትን አስተዋጽኦ ለማድረግ በቅንነት ተሳትፎ የሚያደርጉ አማራዎች እንዳሉ ስለምናስብ እነዚህ ወጣቶች በሚፈልጉት አደረጃጀት የሚፈልጉትን የአድማስ አካል የሆነ ድርጅት ተቀላቅለው ለአማራው ህዝባዊ ትግል ይጠቅማል የሚሉትን ሃሳብ ከወንድም እህቶቻቸው ጋር እንዲያዋጡ ለትግሉም የሚችሉትን አስተዋፆ እንዲያደርጉ ጥሪያችንን እናቀርባለን:: አማራው እስከ አሁን የመጣበት መንገድ ማንነቱን አሳጥቶታል፥፥ ለተከታዮ ትውልድ ግን ይህን ውርደት ማስተላለፍ አይገባንም። ስለዚህም ለቆምንለት አንድ አላማ ህብረታችንን እናጠናክር። ህብረታችንን በንቃት እንጠብቅ!!!
