በኢትዮጵያ ለተፈጠረው ፖለቲካዊ ቀውስ ኃላፊነቱን እንደሚወስድ የኢህአዴግ ምክር ቤት አስታወቀ፡፡ የፓርቲው ምክር ቤት ከባለፈው ማክሰኞ መጋቢት 11 እስከ ማክሰኞ መጋቢት 18 ቀን 2010 ጀምሮ የተካሄደውን ዝግ ስብሰባ አስመልክቶ ዛሬ ባወጣው የአቋም መግለጫ፣ በሀገሪቱ ለተፈጠረው አለመረጋጋት እና ግጭት እንዲሁም የፖለቲካ ቀውስ ምክንያቱ የአመራሩ ድክመት መሆኑን የገለጸ ሲሆን፤ ለእነዚህ ችግሮችም የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ‹‹ኃላፊነት ይወስዳል›› ሲል ገልጽዋል፡፡ ፓርቲው በሀገሪቱ ለተፈጠሩት ችግሮች ‹‹ኃላፊነቱን እወስዳለሁ›› ብሎ ሲናገር ይህ የመጀመሪያው እንዳልሆነ ይታወቃል፡፡
ታህሳስ ወር ላይ ለ17 ቀናት የተካሄደውን የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ፡- ‹‹ለሰው ህይወት መጥፋት እና ለደም መፍሰስ ምክንያት የሆኑ ችግሮች የተከሰቱት በስራ አስፈጻሚ ኮሚቴው ድክመት ነው፡፡›› ሲል ገልጾ የነበረው ፓርቲው፤ በዚሁ መግለጫው ላይም ‹‹ለተፈጠሩት ችግሮች ህዝብን ይቅርታ እንጠይቃለን›› ማለቱ ይታወሳል፡፡ የታህሳሱ መግለጫ በወጣ በጥቂት ጊዜ ውስጥ በወልድያ፣ በጨለንቆ እና በሌሎች የሀገሪቱ ክፍሎች በተወሰደ የኃይል እርምጃ፤ ንጹኃን ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ሌሎች ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ዜጎችም ቆስለው እንደነበር አይዘነጋም፡፡

በባለፈው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ስብሰባ ‹‹ተጸጽቻለሁ›› ሲል እንደ መሳለቅ አድርጎት የነበረው ኢህአዴግ አሁንም በድጋሚ ሌላ ‹‹የተጸጽቻለሁ›› መንፈስ ያለው መግለጫ ይዞ ብቅ ማለቱ ተስተውሏል፡፡ ከዚህ በኋላ ደም አፋሳሽ የሆኑ ችግሮች እንዳይፈጠሩ እና የፖለቲካ ቀውሱም እንደሚፈታ ሲዝት የከረመው ገዥው ፓርቲ፤ ከታህሳስ እስከ መጋቢት ባሉት አራት ወራት ብቻ በርካቶችን ገድሎ ብዙዎችን ማቁሰሉ ይታወቃል፡፡ በሀገሪቱ ውስጥ የሚፈጸም ግድያ እና እስራት በቀጠለበት በዚህ ሰዓት፤ ፓርቲው አሁንም ‹‹የተጸጸተ›› አስመስሎ፤ ከዚህ በኋላ ተመሳሳይ ድርጊት እንዳይከሰት ምሎ መገዘቱን ዛሬ ካወጣው መግለጫ ለመረዳት ተችሏል፡፡

መግለጫውን የታዘቡ አስተያየት ሰጪዎች፣ ‹‹ኢህአዴግ የሚባል ፓርቲ አንድ አይደለም መቶ ዕድል ቢሰጠው እንኳ የማይለወጥ እና ባለበት የሚረግጥ አምባገነን ቡድን ነው!›› ሲሉ ተናግረዋል፡፡ አክለውም ‹‹ህዝብ ከፓርቲው የሚጠብቀው መለወጥን ሳይሆን ስልጣን መልቀቅን ብቻ ነው›› ሲሉም ፓርቲው በህዝብ ዘንድ ምንም ዓይነት ስፍራ እንደሌለው አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል፡፡ ታህሳስ ላይ በተካሄደው የ17 ቀናት ስብሰባ፣ በሀገሪቱ ለተከሰቱት ችግሮች ዋነኛ ተጠያቂው የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ነው በማለት በወቅቱ የገለጸው ገዥው ፓርቲ ለእነዚህ ችግሮችም አመራሩ ኃላፊነት ይወስዳል ማለቱ አይዘነጋም፡፡ ለተፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነት መውሰድ የህግ ተጠያቂነትን እንደሚያስከትል የገለጹ ታዛቢዎች በበኩላቸው፤ በሀገሪቱ ደም አፋሳሽ ሁኔታ እንዲፈጠር ያደረጉ የፓርቲው አመራሮች እስካሁን ተጠያቂ አለመሆናቸውንም ይገልጻሉ፡፡ አንድም አመራር ተጠያቂ ባልሆነበት ሁኔታ፣ ‹‹ለተፈጠሩ ችግሮች ኃላፊነቱን እንወስዳለን›› ብሎ በድጋሚ መግለጫ ማውጣት ሹፈት ነው ሲሉም ታዛቢዎቹ አክለዋል፡፡

BBN Daily Ethiopian News March 30, 2018