April 3, 2018
ጠገናው ጎሹ
የሃሳቤንና የአስተያየቴን አላማ ግልፅ ላድርግ ። አላማዬ የአርበኝነትን የንድፈ ሃሳብ (theory) ትርክት ለመተረክ አይደለም ። እሱ ለታሪክና ሥነልቦና ተመራማሪዎች የሚተው ነው ። የእኔ አላማ አርበኝነት (patriotism) በተወሰነ ዘመን እና ሁኔታ ከሚፈፀም ታሪካዊ ጀግንነት (heroism) ጋር ብቻ የሚያያዝ ሳይሆን መቸምና የትም ለማህበረሰባዊ (ህዝባዊ) ሁለንተናዊ ደህንነት ፣ መብት ፣ ክብር ፣ ሰላም ፥ ፍቅርና ብልፅግና የሚለግሱት የተጋድሎ ማንነት መሆኑን ከምር ልብ እያልን እንራመድ ለማለት ነው ። “አዬ! አርበኝነት ምን ማለት እንደሆነ መች አጣሁት” የሚሉ ወገኖቼ እንደሚኖሩ አውቃለሁ ። የምንረዳበት ስፋትና ጥልቀት ልዩነት መኖሩ እንዳለ ሆኖ የአርበኝነት ታሪክ ባለቤት ለሆነው የአገሬ ሰው የአርበኝነትን ምንነት ያጠዋል የሚል የግብዝነት አመለካከት የለኝም ።
እኔ እያልኩ ያለሁት ግን የአርበኝነት ባህሪና የተግባር ውሎ የውጭን ጠላት ለመመከት ብቻ ሳይሆን አገር በቀል የውርደትና የመከራ አገዛዞችን ድል ነስቶ እንደሰውና እንደዜጋ ተከብሮ፣ ተከባብሮና ከፈጣሪው የተለገሰውን የአገሩን ሃብት በሚዛናዊነትና በመተሳሰብ ጥቅም ላይ ለማዋል የሚያስችል የሰብእና አቋም ነውና ከምር ልብ እንበለው ነው ። ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ እየተነሳን ግን ተመልሰን አይወድቁ አወዳደቅ እየወደቅን የባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ሰለባ ሆነን የዘለቅነው ሁሉም ከቁጥጥራችን (ከአቅማችን) በላይ ሆኖብን አይደለም ። ከሰው ፍጥረት የተለየን የምድር ሃጢአተኞች በመሆናችን ፈጣሪያችን ሊቀጣን ፈልጎም በፍፁም አይደለም ። እንዲህ አይነት ጨካኝ አምላክም የለምና።
አዎ! እንደማነኛውም ሰብአዊ ፍጡር ሃጢአትነትን ከሚያስከትሉ ባህሪያትና ተግባራት ነፃ ልንሆን ከቶ አንችልም ። ልክ ለሌለው ሰብአዊ ጉስቁልናችን እና ብሄራዊ (አገራዊ) ውርደታችን ግን ከእኛ አልፎ ፈጣሪም ሆነ ሌላ ውጫዊ አካል በዋናነት ተጠያቂ የሚሆኑበት ምንም አይነት አሳማኝ ምክንያት የለም። አይኖርምም። ቅጥ ላጣው ውድቀታችን ሃላፊዎችም ፣ ተጠያቂዎችም ፣ ትክክለኛውን የእርምት እርምጃ ወሳጆችም እኛው እኛው ብቻ ነን ። ምክንያቱም መሆን ያለብንን ሆነን እንድንገኝ እና ማድረግ ያለብንን አድርገን እንድንገኝ የሚያስችለን እርምት ለማድረግና እርምጃ ለመውሰድ ያለመቻላችን አባዜ ነው የመከራና የውርደት ዘመናት እያስቆጠረን ያለው ። በእውነት እንነጋገር ካልን በዚህ ረገድ ሳይሳካልን አያሌ ዓመታትን ያስቆጠርንበት ሌላው አይነተኛ ምክንያት የቅድመ አያትና የአያት የአርበኝነት ተጋድሎን ታሪክ እየተረክን የራሳችን ዘመን አርበኞች ሆነን አለመገኘታችን ነው ።
ይህ ትውልድ ከጨካኝ አምባገነን ገዥዎች መዳፍ ነፃነቱንና መብቱን ፈልቅቆ ለማውጣት የሚያደርገው ተጋድሎ እስከአሁን ከመጣንበት የውድቀት መንገድ በእጅጉ በተሻለ ሁኔታ እየታገለ መሆኑ የሚበረታታ ቢሆንም አሁንም በእኛነት የአርበኝነት ስሜትና አቋም ላይ ለመቆም ያለበት ፈተና ከቶ ችላ የሚባል አይደለም። አሁንም በግልፅ መነጋገር ካለብን ለሩብ ምዕተ ዓመት የመጣንበት ተሞክሯችን የሚነግረን በሚያጓጓ አኳኋን የደመርንውንና ያባዛነውን የፖለቲካና ማህበራዊ ካፒታላችን ( political and social capital) መልስን በዜሮ የማባዛት አዙሪት ሰለባ እንደነበርን ነው ። ይህ ሃቅ እጅግ መሪር እንደሆነ እገነዘባለሁ። ደፍረን ለመቀበልና የሚበጀውን የማድረግ ፍላጎቱና ድፍረቱ እርቆ እየታየን እንደ በረሃ ሰጎን አንገታችን ደፍቀን ለማለፍ ( ማለፍ ከቻልን) ካልከጀልን በስተቀር ሃቁን ከቶውንም አናመልጠውም ።
የአሁኑ ወጣት ትውልድ ካለፉት ሁለትና ሶስት ዓመታት ጀምሮ እያደረገ ያለው በጣም የሚያጓጓ የዴሞክራሲዊንና የሰብአዊ መብትን የማስከበር ትግሉ ተመሳሳይ የውድቀት (የክሽፈት) እጣ ፈንታ እንዲገጥመው ጨርሶ መፍቀድ አይኖርበትም ። አዎ! ይህ ትውልድ በራሱ የአርበኝነት ውሎ የራሱን የነፃነት ፣የፍትህ ፣ የሰብአዊና የዜግነት መብት ፣ የእኩልነት ፣ የአብሮነት ፣ የሰላምና የብልፅግና ሥርዓት ምሥረታ ታሪካዊ ምዕራፍን አጠናቆ ማለፍ አለበት ። ከዚህ ያነሰ ተልእኮና ሚና መጠበቅ እራስን የባርነት ተገዥ ከማድረግ አልፎ ለትውልደ ትውልድም ይህኑ ከሰው በታች የሚያውል ማንነትን ማውረስ ነው የሚሆነው ። ከዚህ በላይ ደግሞ በቁም መላልሶ መሞት የለም ። አይኖርምም ።
እጅግ በጦዘ ሁኔታ የሰሞኑ የህዝብ መነጋገሪያ እና ከአገር ውስጥ እስከ ዲያስፖራ ኢትዮጵያና ዓለም አቀፍ ማህበራዊና ነባር ( social and tradtional) የመገናኛ አውታሮች ዜና እና የዜና ትንታኔ ትኩረትን የሳበውንና ህወሃት/ኢህአዴግ በፖለቲካ ሴራው ለውሶ ለታዳሚው የኢትዮጵያ ህዝብ ያቀረበውን የተሃድሶ ተውኔት ተከታትየዋለሁ። ገና በድርጊት ያልተፈተነውን የዶክተር አቢይ አህመድን ወደ ከፍተኛው የሥልጣን ርከን የመምጣት ጉዳይ የማየው ከዚሁ የዚህ ትውልድ የወቅቱ ፈተና እና ፈተናውን ለመወጣት ከሚያደርገው ጥረት አንፃር ነው ።
ይህን እጅግ ታሪካዊና ወሳኝ የፖለቲካ ማርሽ እና አቅጣጫ መቀየሪያ ጊዜና ሁኔታ ቅጥና ልክ በሌለው የስሜት ግልቢያ ለማስተናገድ መሞከር ወይ የፖለቲካ ነፈዝነት (naivity )ነው ፣ወይም ከመርህ ሳይሆን ከአጉል ጭንቀት የሚመጣ ነው ፣ ወይም ደግሞ “ብልጥ ልጅ እየበላ ያለቅሳል” በማለት የዕለት ጉርሱን ከጌታው እጅ እየጠበቀ አይኑን እንደሚያቅበዘብዘው እንስሳ እራስን ዝቅ ማድረግ ነው ። ይህ አገላለፄ ለአንዳድ ወገኖቼ ከረርና ያለ እንደሆነና ወደ ውስጠ አእምሮ ለማስገባትና ለመረዳት እንደሚያስቸግር እረዳለሁ ። በእኔ ግንዛቤና አረዳድ ግን እውነቱ እሱ ነውና ዳር ዳሩን ከመዞር ደፍሮ በመጋፈጥ የሚበጀውን ማድረግ የግድ ነው ባይ ነኝ ።
የህዝብ ጥያቄ መሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ለውጥ ማለትም ሥር ነቀል ወይም የህወሃት/ኢህአዴግን የመከራና የውርደት ሥርአት ከሥሩ ነቅሎ በእውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርአት መተካት መሆኑ እየታወቀ ምናልባት በዚህኛው የገዥው ቡድን የተሃደሶ ዘመቻ ጠቅላይ ሚኒስትር የሚሆነው ፖለቲከኛ ሰው ከመቸውም የተሻለ የተሃድሶ ሲሳይ (በረከት) ሊያመጣ ይችላል የሚባል ከሆነም አልሸሹም ዘወር አሉ ብቻ ሳይሆን የባሰ እራስን ወደ ፍርፋሪ ተመፅዋችነት አውርዶ መጣል ነው ። ከዚህ የከፋ በቁሙ የሞተ የፖለቲካ ሰብእና ደግሞ የለም።
የአሁኑ ወቅት የህዝብ ጥያቄ በአይነቱም በስፋቱም ገዥው ቡድን በለመደው የማታለያ (ማዘናጊያ) ሴራውና የግድያ ሃይሉ ተጠቅሞ ለመቀልበስ ከሚያደርገው በላይ ርቆ የሄደ መሆኑ የሚያጠያይቅ አይደለም ።ጥያቄው ለአመታት በንፁሃን ላይ የአካልና የሥነ ልቦና ሰቆቃ እየፈፀመ ፣ የአያሌዎቹን ህይወት እየቀጠፈ ፣ ወሬ ነጋሪ የሌላቸውን በርካታ ንፁሃን ዜጎችን ድራሻቸውን እያጠፋ ፣ የንፁሃን ኢትዮጵያውያንን ቤተሰብ ብትንትኑን አውጥቶ ለመከራ ህይወት እየዳረገ እና ቤተዘመድንና ወዳጅን ለማይሽር ብርቱ ሃዘን እየዳረገ ሶስት አስርተ አመታት ሊያስቆጥር ሶስት ዓመት ብቻ የቀረው የህወሃት/ኢህአዴግ የፖለቲካ ሥርአት ይወገድና አዲስና ዴሞክራሲያዊ ሥርአት ምሥርታና ግንባታ ላይ እንረባረብ ነው ። በሌላ አገላለፅ ከዚህ በኋላ የኢትዩጵያ ህዝብ በስመ ተሃድሶ ጊዜ እየገዛና አዳዲስ ሴራ እየሸረበ ተመልሶ የመከራና የሞት በትሩን የሚያስርፍበትን አገዛዝ የሚሸከምበት ትክሻና የሚታገስበት ምክንያት ጨርሶ አክትሟልና ይልቁንስ ለሁሉም ወደ እሚበጀው የብሄራዊ እርቅና የዴሞክራሲያዊ ሥርአት ሽግግር ዛሬውኑ እንግባ ነው ። አራት ነጥብ!
አዎ! አያቶቻችንንና ቅድመ አያቶቻችንን እግዚአብሔር ከፊት የመራቸውና ከኋላም ተከትሎ የረዳቸው ሆ!ብለው በአብሮነት ፣ በፍቅር ፣ ለትውልደ ትውልድ አርቆ በማሰብ ፣ እና የአርበኝነታቸውም የረጅም ጊዜ ራእይቸው የጋራ ነፃነት ፣ፍትህ፣ ሰላም፣ ሰብአዊ ክብር ፣ እድገትና ብልፅግና ስለመሆኑ አምነውና ተማምነው መስዋትነት በመክፈላቸው ነው ።
እንደቅድመ አያቶቻችን ፈጣሪን የነፃነትና የፍትህ አርበኝነታችን ባርክልን ብለን መሬት ላይ የወረደ ቁም ነገር ከመፈየድ ይልቅ በየቤተ እምነቱና በየሰበካ አደባባዩ በራስ ስንፍና እና ስግብግብነት ምክንያት እያደር እየከፋ የሄደውን መከራና ውርደት በፈጣሪ እያመካኘን እግዚኦ!የማለታችንና ህዝብ በተአምር ነፃ እወጣለሁ የሚል ሥነ ልቦና ተጠቂ ሲሆን እንደ ድነት መቁጠራችን በእጅጉ ግራ እሚያጋባ ነው ። ለምን? ቢባል ፈጣሪ ሰው አርጎ የፈጠረን ከእርሱ እገዛ ጋር ጥረንና ግረን የሚበጀንን ሁሉ እውን እንድናደርግ እንጅ በተአምር ሰርቶ የሚያኖረንና ከባርነትና ከውርደት ነፃ የሚያወጣን አውርድልን እያልን ሌት ተቀን እግዚኦ ! እንድንል በፍፁም አይደለም ። ይህ የስንፍና እና የተሸናፊነት እንጅ የአርበኝነት ሰብአና ከቶ ሊሆን አይችልም ።
እናም በዚህ ረገድ ያለው የአርበኝነት ጎደሏችን በቅንነትና በመንፈሰ ጠንካራነት ይሟላ ዘንድ ብርቱ የአርበኝነት ታጋድሎ ግድ ይለናል ። ትውልዱ እጅግ ከታመመበት ሥርአተ ማህበረሰብ ተፈውሶ በአዲስና ሁለንተናዊ ጤንነትና ደህንነት መኖር ካለበት ከዚህ የተሻለ ምርጫ የለውም ::
በርግጥ የእኛ የአርበኝነት ፈተና ከቅድመ አያቶቻችንና አያቶቻችን የአርበኝነት ተጋድሎ የሚለየው የውስጥ (የእርስ በርስ) የመሆኑ ጉዳይ በአንፃራዊ መልኩ የባእድ (የውጭ) ወራሪን ለመመከት የምንተባበረውን ያህል ቀላል ሊሆን አይችልም። በእውነት ስለእውነት ከተነጋገርን ግን ይህ መከራከሪያችን ምክንያት ፍለጋ ካልሆነ በስተቀር ብዙም የሚያስኬደን አይደለም ። ምክንያቱም ጥያቄው ከሩብ ምእተ አመት በላይ የገጠመን የመከራና የውርደት አገዛዝን በሚመጥን የአርበኝነት ስሜትና ተጋድሎ ሃላፊነታችንና ተልኳችን ተወጥተናል ወይስ አልተወጣንም የሚል እንጅ የፈተና ቅለትና ክብደት የለውም የሚል አይደለም ።
መላልሰን የመውደቃችን አዙሪት ወይም አባዜ የሚሽከረከረው እውነተኛ አርበኝነት (real sense of patriotism) በሚጎለውና አቅጣጫውንና መድረሻውን እየሳተ ባስቸገረን የራሳችን ምህዋር (የለውጥ ፈላጊነት መንገድ) ዙሪያ ነው ። ምን ጎደለ? ብለን ከምርና ከቅንነት መጠየቅ የችግሩን አፈታት መንገድ የምናይበት ሀሁ ነውና አዋቂነት ነው ። የጎደለው አያቶችና ቅድመ አያቶች ነፃና ሉአላዊ አገር ለማቆየት ደምና አጥንት በተከፈለበት የአርበኝነት የወርቅ መዝገብ ላይ ጽፈው ያቆዩልንን የመጀመሪያውን የነፃነት ተጋድሎ ታሪክ ምዕራፍ ወደ ሁለተኛው ማለትም የውስጣዊ ነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የሰብአዊ ክብር ፣ የዜግነት መብት ፣ የእኩልነት ፣ የህግ የበላይነት ፣ የሰላምና ብልፅግና እና በአጠቃላይ የህዝብ ሉአላዊነት ምእራፍ የማሸጋርገር አርበኝነት ጉዳይ ነው ። አሁን ያለንበትን ሁኔታ ከዚህ መሪር እውነታ ጋር አያይዘን ካላየነውና ካላስኬድነው ወደ ኋላ ተንሸራተን የባለጌና ጨካኝ ገዥዎቻችን የጉልቻ ለውጥና የተሃድሷቸው ፍርፋሪ ተመፅዋቾች ሆነን ነው የምንቀጥለው ።ይህ ምልከታየና ግንዛቤዪ የተሳሳተ ቢሆንና ነገሮች ሁሉ ያለፈውን መከራና ውርደት ወደ ታሪክነት በሚቀይር ሁኔታ ተለውጠው ብናያቸው በሃሴት ከሚፈነድቁት ወገኖቸ አንዱ ብሆን እንዴት ደስ ባለኝ ። በገዥዎቻችን እየሆነ ያለው ግን ጉልቻ በመለዋወጥና በአዲሱ ጉልቻ በኩል “በሚለገሱ” የፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተሃድሶ ሽርፍራፊና ፍርፋሪ ምፅዋዕቶች ደልሎ ሥልጣነ መንበርን የማስቀጠል እና መጨረሻው ግን በእጅጉ አስከፊ (tragic) የሚሆን የፖለቲካ ተውኔት ነው ። ሩብ ምዕተ አመት ሙሉ ስለፈሰሰው የንፁሃን ደምና በየማጎሪያና ማሰቃያ ማእከሉ በዚህ ምድር ያለው ሰቆቃ ሁሉ ስለተሞከረባቸው ንፁሃን ዜጎች ቢያንስ ይቅርታ የመጠየቅ የሞራልና የሰብአዊነት ስሜት የሌለው የፖለቲካ ጨዋታ የማያሳስበን ከሆነ የራሳችን የበሽታ ምንጭ አላወቅነውም ወይም ተለማምደነው ህመሙን ችለን እንቀጥላለን ከማለት የተሻለ ትርጉም ፍለጋ መድከም ያለብን አይመስለኝም ።
ይህ ያለንበት ፈታኝ ወቅትና ሁኔታ በስሜትና ስሜት በሚፈጥረው ቅጥ ያጣ ጉጉት ሳይሆን በተረጋጋ ፣ በአየር ላይ በምናውላቸው የተስፋ ቃላት ብቻ ሳይሆን ከመሬት ላይ በወረደ ምክንያታዊነት ፣ የመሰለንን ሁሉ እንደመጣልን በመዘርገፍ ሳይሆን በኀላፊነት ስሜት ፣ በተቀነጫጨበ ሳይሆን መሠረት ባለውና በተቀናጀ ምልከታ ፣ወዘተ የመመልከት ትእግስትንና ብቃትን ይጠይቀናል ።
ገዥዎቻችን ሰሞኑን መንበረ ሥልጣናቸውን ለማስቀጠል በር ዘግተው ተጨቃጨቁ ፣ ተካረሩ ፣ ቡጢ ቢጤ ቃጣቸው ፣ በተለይ ኦህዴዶች እና የቅሚቲን ያህል ደግሞ ብአዴኖችም ህወሃትን አጣቢቂኝ ውስጥ አስገብተው አሹት ፣ በርእዮተ ዓለም ትልቅ ስንጥቅ ተፈጠረ ፣ ወዘተ የሚለው ወሬ (መረጃ) በሙሉ ወይም በከፊል እውነት ቢሆን እንኳ ህወሃቶች ሌሎችን የግንባሩ አባላት ስሜትና አካሄድ እያዳመጡና እየለኩ አሁን ያጋጠማቸውን የፖለቲካ አጣብቂኝ ማለፍ የማይችሉ ቂል ፖለቲከኞች አድርጎ የማየቱ ነገር በራሱ ከእውነትነት ይልቅ ስሜታዊነት የተጫነው ነው ።
በሌላ በኩል ደግሞ ህወሃት ለረጅም አመታት በፖለቲካው ተውኔት በታማኝ ረዳትነት ወይም ዋና ረዳትነት ያገለገሉት የግንባሩ አባላት ፈጣሪያቸውና አሳዳጊያቸው በሁኔታው ተገዶ በአንፃራዊ መልኩ የነፃነት ስሜት እንዲሰማቸው ማድረጉን እንደ ትልቅ ለጋስነት ቆጥረው የህዝቡን ጥያቄ ከመሠረታዊ ለውጥ በመለስ ያሉ ማሻሻያዎችን በማድረግ የእነሱን ሥርአት ለማስቀጠል አይስማሙም ብሎ ማሰብ ወይ ደካማነት ነው ፣ ወይ ደግሞ አስጠቂ የዋህነት ነው ። የሚያዥጎደጉዱትን እርባና ቢስ መግለጫ እያነበብን የምንደርስበት መደምደሚያ ልፍስፍስ ነው ። አንዳንዴም በእውን የተጋጩ የሚያስመስሉ ዲስኩሮቻቸውን እያዳመጥንና ከምር መሆኑን በድርጊት ማለትም በቃላት ክርክር ወይም ንትርክ ደረጃ ሳይሆን በፖሊሲ ንድፈ ሃሳብ ፣ ቀረፃና አፈፃፀም ክርክር (debate) ባላረጋገጥንበት የምንሰጠው ትንታኔና የምንደርስበት ድምዳሜ መልሶ የሚያሳስተን እራሳችን ነው ።
ሰሞኑን እንደምንታዘበው የህዝባዊው መሠረታዊ ለውጥ ትግል እንዴት? ፣ በየት በኩል? ወደየት አቅጣጫ? ወዘተ ብለን መነጋገሩን የአቆምን እስኪመስል ድረስ ስለ ጠቅላይ ሚኒስትር ምደባና ያመጣልናል ብለን ስለምንመኘው ሁሉ በመዘክዘክ ላይ እንገኛል ። የዘከዘክነው የማይጨበጥ ተስፋ ሁሉ እንደተዘከዘከ ውሃ ሲቸለስበት ግራ ወደ መጋባቱና ወደ ቁዘማው ፖለቲካ እንዳንመለስ ልብ ማለት አለብን ።
አርበኝነት የእርቅ ፣ የመቻቻል እና ተስፋን የመሰነቅ ሰብእና ጭምር ቢሆንም አሁን እንደምንታዘበው የሚጨበጥ ነገር በሌለበት (ባልታየበት) ቅጥ ባጣ የተስፈኝነት ፈረስ መጋለብ ግን በጭራሽ ስህተት ነው ። የዚህ ውጤት የከፋ የሚሆነው ደግሞ በማቴሪያልም ሆነ በሞራል ተመልሶ ለማንሰራራት በእጅጉ አስቸጋሪ የመሆኑ ጉዳይ ነው ። ይህን ደግሞ እኩይና ሴረኛ ገዥዎቻችን አሳምረው ያውቁታል ።ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ ተክነውበታልና ። እድሜ ለአገልጋይነት ፈጥረውና ኮትኩተው ላሳደጓቸው የሴራው አመንጭና አዘጋጅ ግንባር (ኢህአዴግ) ታዳሚዎች ማለትም ለብአዴኖች ፣ ለኦህዴዶች ፣እና ለደህዴኖች ህወሃት ከነሱ ጋር ያለውን ጨዋታ ለምን ፣ እንዴትና መቼ መጫወት እንዳለበት አሳምሮ ያውቀዋል ።
በአመት ውስጥ ሁለት ጊዜ በህግ ማስከበር ስም የማሸበሪያ አዋጅ እያወጁ በማይታክት የሴራ ጉንጎና እና ሥልጣን ማሰንበቻ ስብሰባ የመጠመዳቸው ጉዳይም ምንም ሌላ ሚስጥር የለውም ። የተሃድሷቸውን የምፅዋት ፍርፋሪ በማቅረብ (“በመለገስ”) የህዝብን የሥርዓት ለውጥ ጥያቄ ነበልባል ጨርሶ ዉሃ ሊቸልሱበት ባይችሉም አያረግቡትም ብሎ ማሰብ ግን የለየለት ቂልነት ነው ።
በራሳቸው ተነሳሽነትና አነሳሽነት ሳይሆን ለበርካታ አመታት በውስጡ የቆዩበት ሥርአት በህዝብ እምቢተኝነት እየራደ መሆኑን ተረድተው ራሳቸውን ወቅቱ ከሚጠይቀው ሁኔታ ጋር ለማስማማት በአንፃራዊ እይታ ጠንከር ያለ ዝንባሌ ያሳዩና ዝንባሌያቸውንም ቢያንስ በንግግር ደረጃ ያመላከቱ የግንባሩ ፖለቲከኞች በተለይም በኦህዴድ ውስጥ መገኘታቸው እሰየው የሚያሰኝ ነው ።
የዶክተር አቢይ አህመደን የግንባሩ ሊቀ መንበርና የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆኖ የመመረጥ ጉዳይም መታየት ያለበት ከዚህ ያለተቻኮለና ያለተጋነነ ምልከታ ጋር በሚመጣጠን ሁኔታ መሆን ይገበዋል የሚል እምነት አለኝ ። ነፃነትና ዴሞክራሲ አፍቃሪዎችን ጨምሮ በርካታ የአገሬ ሰዎች በስሚታዊነትም ሆነ ለውጥን በመናፈቅ የሚያጋንኑትን ያህል መሆን ያለበት ግን አይመስለኝም ። እንዲያውም የህወሃትና እሱን የሙጥኝ የሚሉ የግንባሩ አባላት የሴራ ፖለቲካ ሰለባ መሆን ነው ። ይህን ሴራ አክሽፎ እንዴት በድል አድራጊነት መውጣት ይቻላል የሚለውን ግዙፍ ጉዳይ ትቶ “የግልገሉ ቆለጥ ወርዶ ዱብ ይይልኛል ብላ … “ እንደተባለቸው እንስሳ ምናልባት በኢህአዴግ የሚሾም ወይም የተሾመ ጠቅላይ ሚኒስትር የድርጅቱን እምነት ፣መርህ ፣ ፖሊሲ ፣ መመሪያ ሰነድ መደርደሪያው ላይ ወርውሮ የራሱ ሥልጣን እንዳለው ባለሥልጣን የህዝቡን የለውጥ ጥያቄ እውን በማድረግ ታሪክ ይሠራል ማለት እርሱም ያለበትን አጣብቂኝ ያለመረዳት ሌላ ድንቁርና ነው ።
ከዶክተር አቢይም ሆነ በአመለካከት ከሚቀባርቸው ጓዶቹ አጠቃላይ የሆነ ግን የህዝብን ቀልብ የሚስብ ንግግር (rehtric of populism) ከመስማት የዘለለ ከህወሃትና ከግንባሩ ጋር የሚያጋጭ ተጨባጭ የመርህ ፣ የፖሊሲ፣ የፖለቲካውን ምህዳር የተሻለ የማድረግ ፣ የተለየ የረጅም ጊዜ ራእይን ይፋ የማድረግ እና ሌሎችንም አሳሳቢ ጉዳዮችን በተመለከተ የሰማነውም ሆነ ያየነው ተግባራዊ እርምጃ የለም ።
ብዙውን ጊዜ ተደጋግመው የሚጠቀሱት በኦህዴድ መግለጫ ተጠቀሱ የሚባሉት የመደብ እንጅ የብሄረሰብ ጭቆና የለም እና ከተቃዋሚዎች ጋር ለመነጋገር ፈቃደኛ ነን አሉ የሚባለው ነው ። እነዚህ አባባሎች የፈላጭ ቆራጭ ሥልጣኑን በህዝብ ሊነጠቅ እንደሚችል በከፍተኛ ስጋትና በሴራ ሽረባ ላይ የተጠመደውን ህወሃት ከነአቶ ለማ መገርሳ ጋር ለምን ይህን ትናገራላችሁ ከሚል አተካራ ውስጥ ያስገበዋል ብሎ መደምደም የወቅቱን የገዥዎች የፖለቲካ ጨዋታ የሚመጥን አይመስለኝም ።
ሌላው የዶክተር አቢይን ወደ ከፍተኛው የሥልጣን እርከን መውጣት ለውጡን ወደ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ይወስዳል ለሚለው በማሳመኛነት ተደጋግሞ የሚሰማው በትምህርት ደረጃና በሥራ ልምድ ረገድ ብቃት አላቸው የሚለው ነው ። እንደእኔ ግንዛቤ በትምህርትና በሥራ ልምድ ያገኘውን ተሞክሮ በብቃትና በተሟላ ግልፅነት ( with ability and articulation) የመጠቀም ችሎታውን ወይም እንደግለሰብ ያለውን ልምድና ችሎታ በተመለከተ ጥያቄ የሚያስነሳ እንዳልሆነ መረዳት የሚቻል ይመስለኛል ። ይህ ማለት ግን የተበላሸ የፖለቲካ ሥርአትን አወላልቆ በተሻለ (በአዲስ) መገጣጠም (ማዋቀር )እና እንዲሠራ ማድረግ ያስችላል ማለት አይደለም ። አይሆንምም። እንደኛ አገር ባለው የፖለቲካ ሥርአት ውስጥ እንደግለሰብ የሚኖረን የተሞክሮና የእውቀት ብቃት ሚዛን ቢደፋማ ምንኛ በታደልን ነበር ። እውነቱ ግን እሱ እዳልሆነ ለመረዳት ፊደል ቆጥሮ መገኝትም አያስፈልግም ።
የዶክተር አቢይን ጉዳይ በእጅጉ ፈታኝ የሚያደርገው ለ27 አመት በአባልነትና በልዩ ልዩ ኀላፊነት ላይ የቆየበትን ብቻ ሳይሆን መርጦና መርቆ በሾመው የገዥው ግንባር የፖለቲካ ቅርጫት ውስጥ ሆኖ እኛ የምንመኘውን አይነት የመሠረታዊ ዴሞክራሲያዊ ሽግግር ማመቻቸት አለበት የሚለው የገንዛ አገራችን የፖለቲካ እውነታ (political reality) እጅግ አቅልሎ ማየት ነው ወይም በስሜት የመነዳት ችግር ነው ። ለምን አያደርገውም? ብሎ የሚጠይቀኝ መኖሩ ተገቢ ነው ። መልሴ በፍፁም የሚል አይሆንም ። መልሴ የሚሆነው አዎ! ሊሞክረው ይችላል ። ይህን ለማድረግ የሚችለው ግን ሀ) እጅግ የላቀ (extraordinary) አርበኝነትን ይጠይቃልና ለሱ ዝግጁ ከሆነ ለ) የሚመጣውን ሁሉ (all the consequences) ከህዝቤ ጋር ሆኜ እስከ መስዋእትነት ለመቀበል አይገደኝም ካለ ሐ) ለረጅም አመታት የቆየሁበት ሴረኛና እኩይ የፖለቲካ ክለብ ከረፋኝ ካለ ብቻ ነው ። ከዚህ መለስ የሚኖረው አማራጭ የተሃድሶ የፍርፋሪ ወይም የምፅዕዋት እርምጃዎችን እየወሰደና እያስወሰደ ህዝቡ ለተጨማሪ ፍርፋሪ ወይም ምፅዋዕት በትግሥት እንዲጠብቅ ፕሮፓጋንዳውን አጠናክሮ መቀጠል ነው ። የሚሆነው እስከሚሆን ድረስ ። ለማነኛውም የርዕሰ መስተዳተዳድሩን (head of government ) በቃለ መሃላ ሲረከብ በሚያደርገው ዲስኩር ቢያንስ አዝማሚያውን ለመገንዘብ እንችላለን። ግን ቸር ያሰማን ማለቱ አይከፋም።
እስኪ እራሳችን እንዲህ እንጠይቅ ፥ አርበኝነት (patriotism) ለዚህ ትውልድ ያለው ትርጉም ምንድነው? የዚህን ትውልድ የነፃነትና የፍትህ ትግልን እንዴት ነው የምንረዳው? እንዴትስ ነው በቅጡ መሬት አስይዘን (በተግባር) የምንለካው ? የመከራና የውርደት ቀንበር ያሸከሙንን ደንቆሮና ጨካኝ ገዥዎች ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ አስወግደን በምትኩ የሚበጀንን ሥርዓተ ማህበረሰብ እውን የምናደረገውስ እንዴት ነው ? የጎደለንን ዘርፈ ብዙ ጎደሎስ በምንና እንዴትስ ነው የምናሟለው ? የጋራ የነፃነትና የፍትህ አርበኝነትን ብሶትና ስሜታዊነት ከተጫነው አልገዛም ባይነት ጋር እየዘበራረቅን ሩብ መዕተ ዓመት የዘለቅንበትን አባዜ ሰብሮ መውጣት የሚያስችል አርበኝነት ለምን ጎደለን ? በየክልላችን ፣ በየቋንቋችንና በየቡድኖቻችን ስም ተለያይተን አደባባይ እየወጣን እና በተናጠል እየተደብድበንና እየተገደልን ለመቀጠላችን ከዋነኛ ምክንያቶች አንዱ የመደማመጥ ፣ የመቻቻል ፣ የመተባበርና የጋራ እጣ ፈንታን በአብሮነት የመወሰን አርበኝነት ስለጎደለን አይደለም እንዴ ? ህዝባዊ እንቅስቃሴዎችን በየክልላችንና በየብሄርሰባችን ስም የእኔ/የእኛ ይበልጣል ወይስ የእነዚያ የሚል መልክት እስኪሰጥ ድረስ በስሜት ከምንጋልብበት ፖለቲካዊና ሥነ ልቦናዊ አዙሪት የሚያወጣን አርበኝነት አያስፈልገንም እንዴ?
ለነዚህና ተያያዥ ጥያቄዎች የሚኖረን መልስ አወንታዊ ነው ካልን እንዴትነቱን ማስረገጥ መቻል አለብን ። እንደ እኔ ግንዛቤና አረዳድ “ምንም እንኳ ለሩብ ምዕተ ዓመት የመጣንበት መንገድ በአብዛኛው የስኬት ሳይሆን የውድቀት መሆኑ እውነት ቢሆንም አርበኝነት ከመሪሩ የውድቀት ተሞክሮ በመማር የነፃነት ፣ የፍትህ ፣ የሰብአዊና ዴሞክራሲያ መብት ፣ የእኩልነት ፣ የሰላምና የጋራ ብልፅግና ሥርዓትን እውን የማድረግ ተጋድሎ ነውና አሁን ያለንበት እውነታም ይህኑ እውን የማድረግ ትግል ነው” የሚለው በሚገባ የሚያስማማን ይመስለኛል ። እንተና ወርዶ እንቶኔ ተሾመ እያሉ በበሰበሰና ህዝብ በቃህ ካለው ረጅም ጊዜ በሆነው ሥርዓት ውስጥ በሚቀያይሯቸው ጉልቻዎች ለዚህ ግልፅና ግልፅ ለሆነ የህዝብ ጥያቄ መልስ ለመስጠት የቻላቸዋል ብሎ ማሰብ ፖለቲካ ቂልነት ነው።
አርበኝነት (patriotism) እያንዳንዱ ትውልድ በሚኖርበት ዘመን ሊያጋጥመው እንደሚችል የፈተና ክብደት (challenge) እና እንደሚፈጠርለት መልካም አጋጣሚ (opportunity) የየራሱን ታሪካዊ ተልኮ ለመወጣት የሚያደርገው የጀግንነት ተጋድሎ ነው ። ለዚህ ነው ይህ ትውልድ በዚህ በ21ኛው ክፍለ ዘመን ከሩብ ምእተ አመት በላይ ተሸክሞት የኖረውን የመከራና የውርደት ቀንበር መስበር ካለበት ይህን ለማድረግ የሚያስችለው የአርበኝነት ተጋድሎ ግድ የሚለው ። ፈተናውም የሚጀምረው እዚሁነው።
ለመሆኑ አርበኝነት (patriotism) ምን ማለት ነው?
አርበኝነት መገለጫዎቹ ሰፊና ጥልቅ በመሆናቸው በዚች አስተየታዊ ጽሁፍ መግለፅ ባይቻልም ለግንዛቤና ለምሳሌ ያህል መጠቃቀሱ ግን መልካም ነውና እንደሚከተለው ልቀጥል።
አብዛኛው የአገራችን ታሪክ የአገርን ነፃነት ከውጭ ወራሪና ተስፋፊ ሃይሎች ለመከላከልና መክቶ ለመመለስ የተደረጉ የጦርነት ውሎዎች ታሪክ በመሆኑ የአርበኝነትን ምንነት ብዙውን ጊዜ የምናያይዘው ከዚሁ የታሪካችን ኩነት ጋር መሆኑ እውነት ነው ። ትክክል እንጅ ስህተትም አይደለም ። አገርንና ወገንን ማፍቀርና አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜም ተመን የማይወጣለትን የህይወት መስዋእትነት እስከ መክፈል ዝግጁ ሆኖ መገኘት የአርበኝነት መሠረታዊ ባህሪና ተልእኮ ነውና ። የቅደመ ወላጆቻችንና የወላጆቻችን የአገር ነፃነትና ሉአላዊነት ( political independence and soverngnity) የአርበኝነት ተገድሎና ድል የሚነግረንና የሚያረጋግጥልንም ይህንኑ ግዙፍና ጥልቅ እውነታ ነው ።
የአገራችን የፖለቲካ ታሪክ የውስጥ ወይም የዜግነት ነፃነትን ፣ ፍትህን ፣ መብትን ፣ በህግ የበላይነት የመተዳደርን ፣ ወዘተ ሥርዓት ለመፍጠር የሚደረጉ ታጋድሎዎችን እንደ አርበኝነት እውቅና ለመስጠት የሚያስችል ሆኖ ስለማያውቅ እንጅ የአርበኝነት ባህሪና ተልእኮ የውጭ ወራሪ ጠላትን ድል በማድረግ ብቻ የሚወሰን ወይም የሚለካ አልነበረም። አይደለምም ።
ቅድመ አየቶቻችንና አያቶቻችን በአርበኝነት ተጋድሏቸው የውጭ ወራሪና ተስፋፊ ሃይሎችን መክተው ነፃነቷና ሉአላዊነቷ የተከበረ አገር ሲያስረክቡን በተሠራው ታሪክ እየተኩራራን እንድንኖር ሳይሆን እንደሰውና እንደዜጋ ተከብረንና ተከባብረን የምኖርባት ምድር ትሆን ዘንድ (ኢትዮጵያ) ቀጣይ የአርበኘነት ሥራ እንደሚጠብቀን ከቶ አላጡትም። ከተሞክሯቸው በሚቀዳ ፣ በተመጠነና እጅግ ጥልቅ በሆነ መልክት በአገኙት አጋጣሚ ሁሉ አስገንዘበውናል ። ቸግሩ መልክቱን እየሰማን ወይም እያነበብንና የቁጭት ከንፈር እየመጠጥን ዘመን ከማስቆጠራችን አባዜ ላይ ነው ። ከዚህ አዙሪት ሰብሮ ለመውጣት የነፃነት ተግሉን ይበልጥ በተጠና ፣በታቀደ፣በተቀነባበረ/በተቀናጀ እና በአጠቃላይ መሄጃውንና መዳረሻውን ያለምንም ብዥታ ጠንቅቆ በሚያውቅና እና ሊኖሩ የሚችሉ ፈታኝ (ሥጋት ፈጣሪ) ሁኔታችን እያስወገደ የመከራና የውርደት ዘመን አብቅቶ የጋራ ብልፅግና ፣ የክብርና የመከባበር ዘመንን እውን ለማድረግ የሚያስችል የአርበኝነት አመራርና ተሳትፎ የግድ ይላል። ለዚህ ነው ከነፃነት ( political independence) ተጋድሎና ድል በኋላ ያ ትውልድ ተስፋ ያደረገው የውስጥ የፖለቲካ ሥርዓት ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ ሰብአዊ መብት ፣ እኩል የዜግነት ተጥቃሚነትና የጋራ ብልፅግና የሚያረጋግጥበት መሆኑ ቀርቶ ወስላቶችና የድል አጥቢያ አርበኞች የተሰገሰጉበት የመሆኑን እውነታ ለተተኪው ትውልድ እንዲህ ሲል ስንኝ ቋጥሮ መልክቱን ያስተላለፈው ።
ኢትዮጵያ አገሬ ሞኝ ነሽ ተላላ ፣
የሞተልሽ ቀርቶ የገደለሽ በላ።
ታዲያ የዚህ ትውልድ ፈተና የሚጀምረው ይህን የቀደምት ወላጆች መሪር ሃቅ በእውን ተረድቶ አገርን የገደሉና ያስገደሉ ወይም አሁንም እየገደሉና እያስገደሉ ያሉ ግለሰቦችና ቡድኖች የተሰገሰጉበትን ወንጀለኛ የፖለቲካ ሥርዓት በአርበኝነት ተጋድሎ አስወግዶ የራሱን የድል አድራጊነት ስንኝ መቋጠር ሲገባው ያንኑ የሰቆቃ ስንኝ መፅናኛ ይመስል የንግግሩ ማሟያ ከማደረጉ አዙሪት ነው ።
የወቅቱ (የአሁኑ) የእምቢ ለነፃነቴ የአርበኝነት ንቅናቄና መስዋዕትነት ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ከዚህ ክፉ አዙሪት የምንወጣበትን መሠረታዊ መፍትሄ በሚያስገኝ አኳኋን የማስኬዱና ለፍፃሜ የማብቃቱ ጉዳይ ማነኛውንም ቅንና ነፃነት ናፋቂ ኢትዮጵያዊ ሊያሳስበውና አስፈላጊውን ሁሉ እንዲያደርግ ግድ ሊለው ይገባል የሚለውን ደጋግሞ ማስገንዘብ ተገቢ የሚሆነውም ለዚህ ነው ።
የጥቂት ገዥዎችና የግብረ በላዎቻቸው ኢ-ዴሞክራሲያዊና ሙሰኛ ሥርዓት አስከፊ ውጤትን ለማሳየት ከእኛ ከራሳችን አልፈን ማስረጃ ፍለጋ የምንሄድበትና ምሳሌ ድርደራ የምንደክምበት ምክንያት ጨርሶ የለም ። እራሳችን እናታለው ካላልን በስተቀር ። ያ አገር የማስከበር የአርበኝነት ተጋድሎ ትውልድ ከድል ማግስት የገጠመው ፈተና ይኸው የውስጥ ነፃነት እጦት ሰለባ የመሆኑ ጉዳይ ነበር ። አዎ! ለነፃነት ከተጋደሉት ይልቅ ወስላቶችና የድል ማግሰት አድር ባዮች የተሰየሙበት ሥርዓተ ፖለቲካ ሰለባ መሆን በእጅጉ ልብ ይሰብራል ። ያ ሁሉ ለማመን የሚያቅት የደምና አጥንት ዋጋ የተከፈለባት አገር የጥቂት ገዥዎችና የድል አጥቢያ እበላ ባዮች (ተባዮች) ገደብ የሌለው ሥልጣን ተሸካሚና መፈንጫ ስትሆን እንዴት ህመም አይሆን ? እንዴት ልብ አያደማ? እንዴትስ አይከፋና አይከረፋ ? ንፁሃንና አገር ወዳድ ዜጎች በአስተዳደራዊ በደል ምክንያት በተወለዱበትና ባደጉበት ቀየ ወይም አካባቢ በነፃነትና በባለመብትነት ሰርተው ለመኖር ባለመቻላቸው ዘመድና ወገን ሳይሰናበቱ ርቆ የመሄድን አስከፊነት እንዲህ በማለት ነው በወርቅና ሰም ስንኝ ቋጠሮ የገለፁት ፥
እኔው እዘገዋለሁ ደጄን እንዳመሉ ፣
የት ሄደ ቢሏችሁ ከፍቶት ሄደ በሉ ።
ልብ እንበል! ያ ትውልድ በወቅቱ በነበረው ነባራዊና ንቃተ ህሊናዊ ሁኔታ ምክንያት ውስጣዊ ነፃነቱን፣እኩልነቱንና መብቱን የማስከበር አርበኝነትን ውጤታማ ለማድረግ ባለመቻሉ ሲከፋው ቀየውን ትቶ ህልውናውን ለማቆየት ያስችለኛል ወደ እሚለው የአገሩ ክፍል (አፈር) ነው የተጓዘው ። በመስዋትነት ባስከበራት አገር ባይትዋር ያደረገው ሥርዓተ ፖለቲካ በሄደበት ሁሉ ተዘርግቶ የሚጠብቀው ክፉ መረብ መሆኑም ሳይዘነጋ ።
በዚህ ረገድ የዚህ ትውልድ ተግዳሮት የከፋና የቆየውን የአገርና የወገን ፍቅር አርበኝነት በእጅጉ የሚፈታተን ነው ። አዎ! በዚያ ትውልድ የአርበኝነት ተጋድሎ ከነፃነቷ ጋር የተረከባትን አገር የሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ማለትም የውስጥ ዴሞክራሲያዊ ነፃነትን ፣ፍትህን፣ መብትን ፣ እኩልነትን ፣ ሰላምና ብልፅግናን በማጠናቀቅ ተከብሮና ተከባብሮ ከመኖር ይልቅ የእንስሳ አይነት አሟሟትን ሳይቀር ተቀብሎ በገፍ መሰደድን እንደአማራጭ የመውሰዱን አዝማሚያ (trend) ልብ ብሎ ለሚያስተውል በእጅጉ ያሸማቅቃል ።
እንደገና ልድገመውና አንዱ የዚህ ትውልድ አባል የሁለተኛውን የአርበኝነት ምዕራፍ ለማጠናቀቅ ሲጋደል ሌላው ከጎኑ ያለው ስደትንና ከስደት መሳካት በኋላ የሚኖረውን “ዘመናይ ህይወት” እያለመ የሚካሄድ የፖለቲካዊ ሥራ ትግሉን ጨርሶ ይገተዋል ባይባልም መከራውንና መስዋትነቱን ግን ያራዝመዋል ። ያከፈዋልም ።
ለዚህም ነው የአርበኝነት (patriotism) ምንነት ፣ ለምንነትና እንዴትነት ከስሜታዊነት ያለፈ ጥልቅና ሰፊ የአገርና የወገን ፍቅር ሰብዕና እንደሆነና ለሱም መስዋትነት ለመክፈል ዝግጁ የመሆን ቁርጠኝነት ነው የምንለው። ።
እናም ፥
- አርበኝነት የሃገርንና ወገንን ደህንነትና ክብር በተመለከተ ከቶ የማይደራደሩበት የዕውነተኛ ህዝባዊ ፍቅር (integrity) ሰብእና ነው ።
- አርበኝነት በክፉ አትምጡብን እኛም ክፏችሁን ከቶ አንወድም ባይነት ነው።
- አርበኝነት የጌታና የባሪያ (ሎሌ) ግንኙነትን መፀየፍ ብቻ ሳይሆን ምንጊዜምና የትም የመዋጋት ጀግንነት ነው።
- አርበኝነት በእኩልነት ፣ በመደማመጥ ፣በመከባበር ፣ በመቻቻል ፣ እና በወዳጅነት ላይ የተመሠረተ የውስጥም ሆነ የውጭ ግኑኝነት የመፍጠርና ተለያይቶ ከመውደቅ ይልቅ ተደጋግፎ የመነሳት ማንነትን የማጎልበት እንጅ ጭፍን ወይም ስሜት ወለድ ወይም ከእኔ/ከእኛ ወዲያ ላሳር ባይነት የተጠናወተው ብሔረተኝነት (nationalism) አይደለም ።
- አርበኝነት ከራስ ወገን (ዜጋ) አልፎ ለሰብአዊ ፍጡር ሁሉ ሰብአዊ መብትና ክብር የመቆርቆርና የሚቻለውን ሁሉ የማድረግ እጅግ ሰፊና ጥልቅ ሰብአዊ እሴት (value) ነው።
- አርበኝነት ከራስ እጣ ፈንታ (destiny and fate) አልፎ ለትውልደ ትውልድ የተሟላ ህልውና ፣ ደህንነት ፣ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ አብሮነት ፣ ሰላም ፣ ፍቅርና ብልፅግና ብሩህ ራዕይንና የህይወት ተሞክሮን በሃላፊነት ስሜት የማስተላለፍ ዝግጁነትና ፈቃደኝነት ነው ።
- አርበኝነት የአንድ አገር ህዝቦችን ለፖለቲካ ሥልጣን መወጣጫና ማራዘሚያ ሲባል በብሄር/ብሄረሰብ/ነገድ/ጎሳ እና ቋንቋ ለያይቶ የመግደልና ማጋደል ብርቱ ወንጀል እንዲቆም ብቻ ሳይሆን ጨርሶ እንዳይደግም ለማድረግ የሚያስቸል የሞራልና የተግባር ልዕልና ያለው ሰብእና ነው።
- አርበኝነት በታሪክ ሂደት የተሠሩ ስህተቶችን በተመለከተ የሚነሱ ሂሳዊ ምልከታዎችንና አረዳዶችን በምክንያታዊነትና በትምህርታዊነት አስተናግዶ በዛሬና በነገ ሥራዎች ላይ የመረባረብ ማንነት እንጅ የታሪክ ስህተት ሂሳብ አወራርዳለሁ ከሚል የእብደት ስሌት ጋር ጨርሶ ግንኙነት የለውም ።
- አርበኝነት መብቴንና ክብሬን አላስደፍም ባይነት እንጅ ያለመቻቻልና ይቅር ያለመባባል ማንነት በፍፁም አይደለም ።
- አርበኝነት ከስህተት የማይማሩ የውስጥም ሆነ የውጭ የአገርና የህዝብ ጠላቶችን ክፉ ባህሪ ፣ እምነት ፣ ፖሊሲና ተግባር አሸንፎ በምትኩ ለሁሉም የሚበጅ ሥርዓተ ማህበረሰብ የመፍጠር እንጅ የቂምና የበቀል ማንነት ፈፅሞ አይደለም ።
- አርበኝነት ደምና አጥንት የተከፈለበት አገር እና አገርን አገር ከሚያደርጉት ምሰሶዎች ዋነኛ የሆነው ሰው(ህዝብ) በአገር በቀል ገዥዎች የሚደርስባቸውን መከራና ውርደት ከማንምና ከምንም ቀድሞ የሚታደግ ሰብአዊ ልዕልና ነው ።
- አርበኝነት ቃልና ተግባርን አገናኝቶ ከትናንት ለዛሬ ፣ከዛሬም ለነገ የላቀ ውጤትን የማስመስዝገብ ብቃት ያለው ልዕለ ሰብእና ነው ።
- አርበኝነት የወቅቱ ከፋፋይ ፣ዘረኛ ፣ ዘራፊ ፣ ጨካኝና አፍራሽ ገዥ ቡድኖች ሥልጣነ መንበራቸው በተናጋ ቁጥር “እኛ ከሌለን ኢትዮጵያ የምትባል አገር ጨርሶ አትኖርም” የሚል የእብደት ፕሮፓጋንዳ ሲረጩ “አገር አፍራሾች እና ህዝብ አዋራጆች እናንተ ትፈርሳላችሁ እንጅ አገር በፍፁም አይፈርስም ፥ እኛም እንደ ነፍስ ወከፍ ዜጋና እንደ ህዝብ ይህ እንዲሆን ፈፅሞ አንፈቅድላችሁም“ የሚል የዜግነትና የህዝባዊነት ልዕልና ነው ።
- አርበኝነት እንደ አሁኑ የመገናኛና የመረጃ ሳይንስና ቴክኖሎጅ ባልዘመነበትና ከሰው መልክተኛ ፧ ከነጋሪትና ከቀንደ መለከት (ጡሩምባ/እምቢልታ) በስተቀር ሌላ የመገናኛ ዘዴ በሌለበት ዘመንም ህዝብ ከያለበት ክተት ብሎና በአንድ ጊዜ ለአንድ እጅግ ታሪካዊ ተልኮ የተመመበትና ድል በዓለም ወርቃማ መዝገብ የተመዘገበት የአገሬ ህዝብ የማንነት መገለጫ ነው ። የአድዋውን ድል ልብ ይሏል። በመሆኑም የአሁኑ ትውልድ እራሱን ከጨካኝ አምባገኖች ነፃ አውጥቶ በመረጠውና በሚበጀው ሥርዓት እንደ ዜጋና እንደሰው ተከብሮና ተከባብሮ መኖር ካለበት የእናቴ ቀሚስ አደናቀፈኝ ሰበቡን ትቶ ባገኘው ዘዴ ወይም መንገድ ሁሉ በመጠቀም የመከራውና የውርደቱ እድሜ እንዲያጥር ማድረግ አለበት ። የነፃነት አርበኝነት የተመቻቸ ሁኔታን እየጠበቁና እየመረጡ የሚፈፅሙት ጀግንነት አይደለም ።
- አርበኘነት ቅድመ ወላጆቻችንና ወላጆቻችን በደምና አጥንት መስዋዕትነት አስከብረው ያስረከቡንን አገርና ማንነት ከባለጌና ጨካኝ ገዥዎች ነፃ አውጥተን በነፃነት ከመኖር ይልቅ በተገኘው አጋጣሚና በየትኛውም አቅጣጫ በገፍ ስንሰደድ ትናንት ነፃ እንዲወጡ በረዳናቸው አገሮች የወታደርና የፖሊስ ሃይሎች ሳይቀር የሚደርስብን ከእንስሳትም ዝቅ የሚደርግ ስቃይና ወርደት እንዲያከትም በማድረግ ነፃ በወጣች አገር በነፃነትና በኩራት ለመኖር መቻል ነው ።
- አርበኝነት ሃይማኖታዊ ሰብእናን እና ተልኮን አገረ እግዚአብሔር ለምንላት ምድር ደህንነትና እረኛው ነን ለምንለው ህዝብ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ ሰብአዊ ክብር ፣ ሰላም ፣ፍቅርና ብልፅግና እንዲውል አድርጎ የመገኘት የዜግነት ግዴታና የመንፈሳዊነት ሰብእና ሚዛን ነው ። “እንኳን ህዝቤ (ሰው) የቅድስት አገሬ ምድርም ከቶ እንዳይገዙልህ ገዝቻለሁ” በማለታቸው በእጃቸው የነበረው የክርስቶስ መስቀል የጦር መሣሪያ መስሎ የታያቸው አገር ወራሪ ፋሽስቶች በመትረየስ የረሸኗቸውን አቡነ ጴጥሮሰን እንኳን በዚያ ዘመን ለነበረ ይቅርና ታሪኩን አንብቦ ወይም ሰምቶ በአይነ ህሊናው ወደ ኋላ ሂዶ የሆነውን ለማየት ለሚሞክር ለዚህ ትውልድ አባል አርበኝነት ምን ያህል ጥልቅና ሃያል ሰብዕና እንደሆነ ብዙ ከማንበብ በላይ አእምሮውን ዘልቆት ይገባል ።
- ሃይማኖታዊ አርበኝነት የታላቁ መጽሐፍ እውቀትን ፣ ቅዳሴን አሃዱ አብ ብሎ ጀምሮ አባታችን ሆይ ብሎ መጨረስን ፣ በሰላ አንደበት ወንጌል መስበክን ፣ የምስጋና ዝማሬ ማበርከትን ፣ የዘወትር ፀሎት ማድረስን ፣ ፆምን አክብሮ መፆምን ፣ ተማፅኖ (ምህላ) ማቅረብን ፣ መበአ ማቅረብን ፣ ወዘተ ከአገር ደህንነትና ከህዝብ ነፃነት ፣ፍትህ ፣ ሰብአዊ መብትና ክብር ጋር በማያያዝ ትርጉም ያለው (በተግባር የሚገለፅ) ተልእኮ የመወጣት እምነታዊና ሞራላዊ ልዕልና ነው ። በሌላ አገላለፅ ሃይማኖታዊ አርበኘነት አስፈላጊ ሆኖ ከተገኘ አቡነ ጴጥሮስን ሆኖ እስከመገኘት ድረስ የሚሄድ እንጅ ከቤተ እምነት አውድና ከአደባባይ ወይም ከመድረክ ስብከት ብቻ የሚገኝ ሰብአዊም ሆነ መንፈሳዊ ልዕልና አይደለም ። የአሁን አሁን ነገረ ሥራችንን ልብ ለሚል ቅንና እውነተኛ ወገን በዚህ ረገድ እየገጠመን ያለውን ድክመት ከፖለቲካው ድክመት የተሻለ አይደለም ።
- ትክክለኛው ሃይማኖታዊ አርበኝነት በፈጣሪ ሳይሆን በእኛው በራሳችን ልክ የሌለው ስንፍና እና ውድቀት ምክንያት ከዓመት ዓመት መከራና ወርደታችን ይበልጥ እየከፋ መሄዱን ልባችን /ህሊናችን እያወቀው በተለምዶ ” እንኳን በሰላምና በደስታ አደረሰን ! “ እየተባባልን ራሳችንን የመሸንግል ማንነት አይደለም ። በራሳችን ስንፍና እና ውድቀት ምክንያት የገባንበትን የመከራና የውርደት አዙሪት ” እርሱ (ፈጣሪ) ባይለው ነው “ እያልንና በፈጣሪ ለማመካኘት ይረዳን ዘንድ ታላቁን መጽሐፍ ሳይቀር በሚያመቸን አተረጓጎም እየተረጎምን “የወንጌል አርበኞች ነን” እያለን የምንመፃደቅበት እኛነታችን በፍፁም ሰብአዊም ሆን መንፈሳዊ ልዕልና የለውም። እናም የዚህ ትውልድ የአርበኝነት ተጋድሎውና ፈተናው ዘርፈ ብዙ ነውና ለዚህ በሚመጥን አኳኋን እራሱን ማዘጋጀት ግድ ይለዋል ።
ባሳለፍነው ወርሃ የካቲት የአገር ነፃነትንና ሉአላዊነትን ለማስከበር ከተደረጉ ታሪካዊ ተጋድሎዎቻችን አንዱንና ዋነኛውን ለአንድ መቶ ሃያ ሁለተኛ ጊዜ ዘክረናል (አክብረናል)። አዎ! ከእኛ አልፎ በመላው ዓለምና በተለይም በአህጉረ አፍሪካ በባዕዳን ወራሪና ቅኝ ገዥ ሃይሎች አገዛዝ ሥር ይማቅቁ ለነበሩ ህዝቦች ሁሉ አገራዊ ነፃነትና ክብር ተወዳዳሪ የሌለው የደምና የአጥንት ዋጋን የሚጠይቅ የአርበኘነት ተጋድሎ እንደሆነ በአርያነት ያስመዘገንበት ወርቃማ የእኛነታችን መገለጫ ነው ። የአድዋው የነፃነት ተጋድሎ ታሪካችን።
ያ ትውልድ ዘርና ሃይማኖት ፣ ቋንቋና ባህል ፣ እነሱና እኛነት ፣ ደሃና ሃብታም ፣ አስገባሪና ገባሪ ፣ ሴትና ወንድ፣ ወጣትና አዛውንት ፣ ቀዳሽና አስቀዳሽ ፣ አሰጋጅና ሰጋጅ ፧ ወዘተ ሳይባባል ተደባልቆ በፈሰሰ ደም እና ተነባብሮ ወድቆ በተከሰከሰ አጥንት ነፃነቷና ሉአላዊነቷ የተከበረች ኢትዮጵያን ለተተኪው ትውልድ አስተላልፏል ።
ከዛሬ መቶ ሃያ ሁለት ዓመት በፊት መሆኑን ልብ እንበል! ይህን የምለው ያለ ምክንያት አይደለም ። ያ ትውልድ የደምና የአጥንት ዋጋ ከፍሎ ነፃነቷና ሉአላዊነቷ የተከበረ አገርን ለተተኪ ትውልዶች ሁሉ ሲያስተላልፍ ከዘመን ጋር አብሮ ከሚዘምን የብሩህ ተስፋ ራዕይ ጋር እንጅ ዛሬ በሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን በሁሉም የህይወት ሂደታችን የዓለም ጭራነት ምሳሌዎችና ምፅዋት ተመፅዋቾች እንድንሆን ከቶ አልነበረም ። በሌላ አገላለፅ ያ ትውልድ ከቶውንም ተመን በማይወጣለት መስዋዕትነት የውጭ ወራሪ ሃይሎችን ድባቅ መትቶ ለትውልድ ያቆያትና ያስረከባት አገር በአገር በቀል ገዥዎች የባርነት ፣ የመከራና የውርደት ምድር እንድትሆን እንዳልነበር የማይገነዘብ የአገሬ ሰው የሚኖር አይመስለኝም ። እየገደሉ እየፈወስን ነው ፣ እያዋረዱ እያከበርን ነው ፣ እያስራቡ እያጠገብን ነው ፣ እያፈረሱ እየገነባን ነው ፣ ወዘተ ከሚሉን ደንቆሮና ጨካኝ ገዥ ቡድኖችና የጥቅም ተጋሪዎቻቸው በስተቀር ።
አዎ!ያ አባታዊና እማዊ ራዕይ ትውልዶች ሁሉ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ ሰብአዊ መብት ፣ የዜግነት ክብር ፣ ዘላቂ ሰላም ፣አብሮነት ፣ ፍቅርና ብልፅግና በሰፈነባት አገር ይኖሩ ዘንድ በንፁህ አእምሮና ልቦና የታለመ ራዕይ ነው ። ያ ትውልድ የራሱን ወርቃማ የአገር ነፃነትና ሉአላዊነት ምዕራፍ አስመዝግቦ ማለፉ በተተኪ(ተረካቢ) ትውልዶች ለሚከናወኑ ቀጣይ የውስጣዊ ነፃነነት ተጋድሎ ምዕራፎች ጥልቅና ግዙፍ አርአያ ሊሆን እንጅ ስለሱ (ስለዚያ ትውልድ) ገድል እየተረኩና እና በሱም እየተኩራሩ ለመኖር አልነበረም ።አይደለምም ።
ያ የአድዋው ትውልድ የኖረበት እና የአሁኑ ትውልድ እየኖረ ያለበት የዘመን ፣የነባራዊና ህሊናዊ ሁኔታ ልዩነት እንደተጠበቀ ሆኖ ሁለቱም የሚጋሯቸው መሠረተዊ የአርበኝነት መርሆዎችና የተጋድሎ ውሎዎች መነሻቸውና መዳረሻቸው ግን አንድ ነው ። መነሻቸው አገራዊና ወገናዊ ባርነትን ፣ መከራና ውርደትን እምቢ ማለት ሲሆን መዳረሻቸው ደግሞ ነፃነት ፣ ፍትህ ፣ እኩልነት፣ ክብር ፣ ፍቅር ፣ ሰላም ፣የጋራ ብልፅግና እና ደስታ የሰፈነባት አገር የማየት የጋራ ራዕይ (vision) ነው ።
በየጊዜው የተፈራረቁ ኢ-ዴሞክራሲያዊና አምባገነናዊ የፖለቲካ ሥርዓቶች በህዝብ ሁለንተናዊ ህይወት ላይ ባስከተሉት ውድቀትና መከራ ላይ ያለን እይታና አረዳድ አንድ አይነት ባለመሆኑ (ሊሆንም ስለማይችል) በዚሁ ዙሪያ የምናደርገው የሃሳብ ልውውጥ አስተዋይነትን ፣ የሃላፊነት ስሜትንና ፖለቲካዊ ጥበብን ይጠይቃል ። እንኳን በአሁኑ የፖለቲካ ትኩሳት ወቅት ወደፊት ልንመሠርተው በምንፈልገው ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትም ጨርሶ ልናስወግደው የምንችለው ጉዳይ አይደለም ።ማድረግም የለብንም ። ማድረግ የምንችለው በታሪክ ሂደትም ሆነ በሌሎች ማህበራዊ መስተጋብሮቻችን ዙሪያ ሊኖሩ የሚችሉ (የሚኖሩ) የአስተሳሰብና የአመለካከት ልዩነቶችን የአገርንና ህዝብን መሠረታዊ ፍላጎትና ደህንነት አደጋ ላይ እስከአልጣሉ ድረስ በነፃነትና አግባብነት ባለው አሠራር ማስተናገድ ነው ። የዕውነተኛ ዴሞክራሲ ባህሪና ተግባርም ይኸው ነው ።የዕውነተኛ አርበኝነት ሰብዕናም ይኸው ነው ። ይህን ማስተናገድ የሚችል ሥርዓተ ማህበረሰብ ባለቤቶች አለመሆናችን ነው ዛሬ የምናየውንና የምንሰማውን ህዝባዊ አልገዛም ባይነት የፈጠረው ።
ባለጌና ጨካኝ ገዥ ቡድኖች ከሩብ ምዕተ ዓመት በላይ የተጠቀሙበትን የመከራና የውርደት አገዛዝ ለማስቀጠል አሁንም ማሳደድን ፣ ማሰቃየትን ፣ ማሰርንና መግደልን በአዋጅ በሽብር አዋጅ አስደግፈው ቀጥለውበታል ። በሌላ በኩል የእኩይ ፖለቲካቸው ማስፈፀሚያ አይነተኛ መሣሪያ የሆነው የጥላቻና የመለያየት ሴራ “ደምህ/ሽ ደሜ ነው!” በሚል የወገን ጥልቅ የአብሮነት ስሜት እየከሸፈ መሆኑ በእጅጉ ሚያበረታታ ነው ። ይህ እጅግ ግዙፍና ጥልቅ የአብሮነት ሃይለ ቃል በሚገባ ወደ መሬት ወርዶ የዚህን ትውልድ የነፃነት አርበኝነት ተጋድሎ የሚያስተሳስር ሃይል መሆን አለበት ። የዚህ ትውልድ የነፃነት አርበኝነት ውሎ ስኬታማነት ወይም ውድቀት የሚለካውና የሚወሰነው የጀመረውን የእኩይ ገዥዎችን እኩይ የፖለቲካ ሴራ ጨርሶ በማስወገድ በምትኩ ዕውነተኛ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓተ ማህበረሰብን መመሥረት በመቻል ወይም ባለመቻል ነው ።
በጎውን ሁሉ ተመኘሁ !!!
