ከሰለሞን ስዩም

ከዚህ ቀደም፣ መኩሪያ ቡልቻ (ፕ/ር) ያስቀመጠውን የትውልዶች እድሜ የጠየቀው የኦሮሞ ንቅናቄ ያለፈባቸው ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እርከኖች መሠረት አድርጌ ሰፋ ያለ አስተያየት በፌስ ቡክ አስነብቤ ነበር፡፡ በወቅቱ የሌላኛውን የኦሮሞ ጉዳዮች ተመራማሪ መሀመድ ሀሰን (ፕ/ር) ምደባ መነሻ በማድረግ አስተያየት እንደምሰነዝርም ቃል ሰጥቼ ነበር፡፡ ነገር ግን፣ በቃሌ መሠረት መሄድ የተለያዩ ምሁራን የሚጋሯቸውን ተለዋዋጮች/አንጓዎች መደጋገም እንደሚያስከትል ተረዳሁ፡፡ በመሆኑም፣ መሀመድን እንደአንድ የመረጃ ምንጭ ብጠቅስም መኩሪያን መነሻ ባደረኩበት አስተያየት ውስጥ ያልተካተቱትን አጠቃላይ ሀሳቦች፣ “ከብርቱ ጥቂቶች ጀምሬ፣ ከሜጫ ቱላማ እስከ ቄሮ ( #MechaTulama_Qeerroo_Qeerretti ) በወፍ በረር አያለሁ፡፡ አምስት በስሱ የተቃኙ እርከኖች ይወጠዋል፡፡ ስድስተኛ እርከን በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ ስለሚሆኑንን ጉዳዮች የመጡልኝን ሀሳቦች የሰጠሁበት ነው፡፡ 


ይህ ክፍል ትረካ ብቻ ነው፡፡ ትችት በክፍል ሁለት እናያለን፡፡ አስተያየታችሁ ለሁለቱም ወሳኝ ነው፡፡

ማሳሰቢያ፡-
በሳባ ፊደል የፃፍኳቸውን አፋን ኦሮሞ ቃላት ግዕዝ ፊደል—የመጀመሪያ የአማርኛ ፊደላት- ሀ፣ ለ፣ ሐ፣ መ፣ ሰ … አልተጠቃምኩም፡፡ ራብዕ እንጂ፡፡ ትርጉም አልባ ነውና፤ ለምሳሌ “ገዳ” ሳይሆን “ጋዳ”፣ “ቱለማ” ሳይሆን “ቱላማ” እላለሁ፡፡ አማርኛ የማይጠራውን “Dha” ሌሎች እንደሚያደርጉት በ “ደ”/”ዳ” አልተካሁም፤ “ዴራ” ሳይሆን Dheeራ የምለው ለዚህ ነው፡፡ 

ደረጃ አንድ
ደመቅሳ/ዎች

ኦሮሞ፣ በሁለንተናው የሁለተኛ ደረጃ ዋጋ የተሰጠው የባህል ቡድን ነበር፡፡ ይኸንን ምደባ እምቢ ማለት የጀመረ የትኛውም ንቅናቄ የመጀመሪያው እና ወርቃማው እርከን ነው፡፡ የተማሩ፣ አዕምሯቸው በህዝባቸው ባህል መዋረድ የተብሰከሰከ ግለሰቦች፣ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ ፀሐፊዎች … ትኩረታቸውን ወደ ህብረተሰባቸው ቋንቋ፣ ታሪክ፣ ባህል፣ ማንነት… ሲመልሱ የተገኘ እርከን ነው፡፡ ሆኖም በዚህ እርከን፣ ሰፊው ሕብረተሰብ፣ የሚደርሱበትን ብሔራዊ ጉዳቶች አስተውሎ የላቀ አግራሞት ውስጥ አይገባም፡፡

የዚህን እርከን አብነቶች ላቅርብ፡፡ በግለሰብ ደረጃ ለኦሮሞ ብቻ ሳይሆን ለግዛተ-አፄዋም ቢሆን ፈር ቀዳጅ ከሚባሉ ምሁራን አንዱ የሆነው ኦኔስሞስ ነሲብ (አባ ገመቺስ) ነው—ጵንጤ ክርስቲያኑ፡፡ ባህሩ ዘውዴ (ፕ/ር) “Pioneers of Change …” በተባለ ድርሳኑ ሰፊ ምስክርነት ሰጥቷል፡፡ አባ ገመቺስ አበርክቶቱ እንደጀማሪ ሳይሆን የላቀ ነበር፡፡ እርሱ የወቅቱን አይበገሬ የማንነት ክህደት ግንብ እንደሚናድ ማሳየት ነበር የተያያዘው፡፡ ስነ-ፅሁፍ ለአንድ ህብረተሰብ በደግም ሆነ በክፉ ዘመናት፣ ወሳኝ የስልጣኔ እና የመነቃቂያ መሳሪያ ነው፡፡ ኦኔስሞስም፣ ከዘመኑ ገዥ ሀሳብ በተቃራኒ፣ አፋን ኦሮሞ የስነ-ፅሁፍ ቋንቋ መሆን መቻሉን በተግባር ያረጋገጠ የመጀመሪያው ሰው ነው፡፡ (የአጋሩ አስቴር ገኖ ድርሻ እንዳይረሳ፡፡)
እንደ መኩሪያ ቡልቻ ምስክርነት ደግሞ፣ ስነ-ፅሁፍን በአፋን ኦሮሞ ከማስተዋወቁ ባላነሰ፣ በምዕራብ ኦሮሚያ አካባቢዎች ትምህርትንም “ሀ” ብሎ ያስተዋወቀ ሰው ነው፡፡ በተጨማሪም፣ በአካባቢው ትምህርት ተወዳጅ እንዲሆን ብዙ የለፋ የሀገር ባለውለታ ነው፡፡ ባህሩ ዘውዴም ከላይ በተመለከተው ድርሳኑ አረጋግጧል፡፡

ሌላኛው የዚህ እርከን አብነት፣ ሼክ በክሪ ሳጰሎ ነው፡፡ ታላቁ ባለቅኔ፣ በኦሮሞ ታሪክ እና ባህል ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ስምንት (8) ስራዎችን ያበረከተ ከመሆኑም በላይ፣ እ.ኤ.አ በ1956 ዓ.ል የአፋን ኦሮሞ መፃፊያ ፊደል ለመቅረፅ ችሏል፡፡ በክሪ፣ በዚሁ አዲስ የአፋን ኦሮሞ ፊደላት በተፃፉ ግጥሞቹ (ቅኔያቱ)፣ የኦሮሞን የታሪክ ጉዞ ተንትኗል፤ ቀጣይ እርምጃዎችን ጠቁሟል፡፡

መሀመድ ሀሰን በበኩሉ፣ የሼክ በክሪን ቅኔያት፣ ማጠንጠኛ ጭብጦች ዘርዝሮ አቅርቦልናል፡፡ እንደ መሀመድ ትንተና፣ ጊጤዎቹ (foci) በዓለማዊና መንፈሳዊ ርዕሰ-ጉዳዮች የሚከፈሉ ሲሆን፣ ከዓለማዊ ግጥሞቹ የመጀመሪያው ዘውግ የኦሮሞን (መልክዐ)ምድር፣ ህዝብ፣ ወንዞች፣ ሐይቆች፣ ሸለቆዎች ሜዳና ሸንተረሮች እንዲሁም እንስሳት የሚያወድስ ነው፤ ሁለተኛው ዘውግ እንዲሁ የኦሮሞ ሕዝብ ‹በአማራ› “ቅኝ-አገዛዝ” ስር ነበር ባላቸው ዘመናት፣ ያያቸውን ዘግናኝ ፍዳዎች የሚመሰክር ነው፡፡

ከሁለተኛው ዘውግ ውስጥ፣ አንዱ ግጥሙ የሸዋ አማሮችን “ቅኝ-አገዛዝ” ከጣሊያን ቅኝ አገዛዝ ጋር በማወዳደር፣ የጣሊያኖቹ ከሞላ ጎደል የተሻለው መጥፎ እንደነበር የሚደመድም ነው፡፡ በርግጥ የሼኩ ዘመነኛ የምትሆን አንዲት አደሬ፣ ጣሊያንና የሀገር ውስጥ ወራሪዎቹን አወዳድራ የፊተኞቹ የተሻሉ እንደነበሩ መመስከሯን ተስፋዬ ገብረአብ በ “የደራሲው ማስታወሻ” ድርሳኑ አካቷል፤ ቢያወዛግብም ቅሉ፡፡ ሼክ በክሪ ከፃፋቸው ደብዳቤዎች በአንደኛው፣ የአማራ አስተዳደርን ሁኔታ በዝርዝር ከማተቱም በላይ፣ የኦሮሞ ሕዝብ ንቅናቄ ቀስ እያለ ለአብዮት ደርሶ በአሸናፊነት እንደሚወጣም ተንብዮ ነበር፡፡

በክሪ በዚህ ትግሉ ከፍተኛ መነቃቃት ከመፍጠሩ በተጨማሪ፣ የሕዝቡን ፍቅርና አክብሮትም ለመጎናፀፍ ችሏል፡፡ ዛሬ ላይ፣ የቀረፀው ፊደል እና ቁመናውን የወከለ ሀውልት የትውልድ መንደሩ ጨለንቆ ቆሞለታል፡፡
ከላይ ባየናቸው ሁለቱ ወሳኝ ግለሰባዊ አብነቶች እና ሌሎች ብዙ እዚህ ያልተጠቀሱ ተጋድሎዎች መረዳት የምንችለው መሰረተ-ነገር ቢኖር፣ የተማሩ—(የነቁ) ኦሮሞዎች፣ ክርስትያንም ሆኑ ሙስሊም፣ ስለትምህርት አስፈላጊነት እና በራሳቸው ቋንቋ ስለሚፃፉ የስነ-ፅሁፍ ውጤቶች የሚጨነቁ መሆናቸውን ነው፡፡ በተጨማሪም ሁለቱ ሰዎች— ጴንጤው ኦኔስሞስ እና ሙስሊሙ በክሪ፣ ንቁ ኦሮሞ ሀይማኖት ዘለል ብሔራዊ ንቃት እንደነበረው ህያው አብነቶችም ጭምር ናቸው፡፡ በሌላ በኩል፣ የህይወት ታሪካቸው ሲታይ (እስር እና ስደት)፣ የኢትዮጵያ አገዛዞች፣ አፋን ኦሮሞ እና የኦሮሞ ባህላዊ ማንነት ላይ ፍላጎት ባሳደሩ ሰዎች ላይ ለሚያደርሱት ከፍተኛ ጭካኔም ምስክር ናቸው፡፡

ደረጃ ሁለት

ሁለተኛው እርከን Peter Alter እ.ኤ.አ በ1989 “Nationalism” ሲል በሰራው ጥናት ውስጥ ባካተታት አንዲት አንቀፅ የምንወክለው ይመስላል፡፡ እንዲህ ትነበባለች፡-

In political mobilization, comes when the learned interest of the minority spreads to the other sectors of the population, when it’s transformed in to channeled political agitation by a minority that thinks interms of the nation.

(Alter 1989: 79)

እዚህም በሁለት የታሪክ ሁነት አብነቶች ወክለን የምናይ ሲሆን፣ ንቅናቄዎቹ፣ በተለይ ቡድናዊ ቅርፅ በያዙባቸው ሂደቶች ላይ እናተኩራለን፡፡

 የሜጫና ቱላማ ውልደት ሂደት
(መኩሪያ ቡልቻ ሜጫና ቱላማን ደረጃ ሶስት ላይ ያስቀምጣል፡፡)
ከኦሮሞ ብሔር ትግል አንፃር ሲታይ፣ እርከን ሁለት መሰረቱን ያደረገው በ1955 ዓ.ል (እ.ኤ.አ 1963) ለመቋቋም የበቃው የሜጫና ቱላማ መረዳጃ ማህበር ባለፈባቸው ቅድመ እና ድህረ ጊዜያት ናቸው፡፡ የነቃው ትውልድ የሚመራው ሁለተኛው ንቅናቄም ነበር፡፡

በዚህ ማህበር ታሪክ ውስጥ ከነቤተሰቡ ኩሩ ታሪክ ከማኖሩም በላይ ከማንም በላይ የተቋሙን ታሪክ የሰነደልን ኦላና ዞጋ እንዳስቀመጠው፣ ትምህርታቸውን አምቦ ከተማ የተከታተሉ የቀድሞ ተማሪዎች “ሀገረ ህይወት መረዳጃ ማህበር” በሚል ስያሜ (የወቅቱ የአምቦ ስም ነው) ህብረ ብሄራዊ ድርጅት መሰረቱ፡፡ ኦላና ባይነግረንም፣ በህብረ ብሄራዊነት የተደራጁት፣ የወቅቱ አስተዳደር ስለሚያስገድድ እንጂ ዋነኛ ትኩረታቸው ይኸው ማንነቱ የተካደው የኦሮሞ ህዝብ እንደሆነ ኋላ ላይ ካከናወኗቸው ተግባራት መረዳት ይቻላል፡፡ በመሆኑም፣ ከጎሳ፣ ከፖለቲካ፣ እና ከኃይማኖታዊ ጉዳዮች ፍፁም የተራራቀ እንደሆነ ማሳየት ነበረባቸው፡፡ በመጨረሻ የምናገኘው ውጤት ግን አንዱ የተደራጁለት ዓላማ ይኸንኑ ክልከላ መደምሰስ ሆኖ እናገኛለን፡፡

ወደ አመሰራረቱ ሂደቱ እንመለስ፡፡ ምናልባትም በ1953 ዓ.ል መጨረሻ፣ ሻምበል አየለ ወልደስላሴ የተባሉ የመብት አቀንቃኝ፣ “ሀገረ ህይወት መረዳጃ ማህበር”ን ከመስራቾቹ ተቀብሎ መምራት ጀመረ፡፡ በሌላ በኩል ይህንኑ አከባቢ መሠረት ያደረገ ሌላ ማህበር በሻለቃ ስዩም ለማ አመራርነት ይንቀሳቀስ ነበር፡፡ አሁን አንድ ማርሽ ቀያሪ አጋጣሚ ተፈጠረ፡፡ ኮሎኔል አለሙ ቂጤሳ በሁለቱም ወገን ለአባልነት ይጠየቃል፡፡ ኮሎኔሉ የተሻለውን በመምረጥ የአንደኛው ቡድን አባል ከመሆን ይልቅ ጥቂት አይበገሬዎች ብቻ የሚያደርጉትን ከወነ—የሁለቱንም ማህበራት አመራሮች በማወያየት እና በማሳመን መዋሃድ የተሸለ እንደሆነ አሳመነ፡፡ (ኦላና 1985)

በ1954 ዓ.ል አጋማሽ ላይ “የጅባትና ሜጫ መረዳጃ ማህበር” በሚል ስም አንድ ሆነው መጡ፡፡ ኮሎኔል አለሙ ቂጤሳም ሊቀ-መንበር ሆኖ ተመረጠ፡፡ በሌላ ወገን፣ በተመሳሳይ ወቅት፣ አቶ ኃይለማርያም ጋመዳ የሚመራው “የሸዋ ቱላማ መረዳጃ ማህበር” በሚል የሚንቀሳቀስ ድርጅት ነበር፡፡ ስለ ሌላኛው ድርጅት የሰማው አቶ ኃይለማርያም ጋመዳ በበኩሉ፣ ሁለቱ ማህበራት መዋሃድ እንዳለባቸው አሳመነ፡፡ ጥር 16 ቀን 1955 ዓ. ም፣ ጉለሌ ላይ በተደረገው ጉባኤ በይፋ ተዋህደው፣ አቶ ኃይለማርያም ጋመዳ የአዲሱ ማህበር ሊቀ-መንበር በመሆን ተመረጠ፡፡ (ኦላና 1985)

ማህበሩ፣ አስራ ሶስት (13) ሰዎች ያሉበት ፖሊሲ አውጪ ቦርድ ነበረው፤ ከነዚህ አራቱ ወታደራዊ መኮንኖች፣ ሁለቱ የሕግ ባለሙያዎች፣ ቀሪዎቹ የመንግሥት ቢሮ ኃላፊዎችና እና የንግድ ሰዎች ነበሩ፡፡
ለመሆኑ ማህበሩን ከአስር አመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ፣ በመጀመሪያ፣ ከአንድ ትምህርት ቤት “የቀድሞ ተማሪዎች ስብስብ” ወደ ሸዋ ጠቅላይ ግዛትን የሚሸፍን “የራስ አገዝ እድርነት” ከዚያም ወደ የመላ አሮሞ ህዝባዊ ንቅናቄ እንዲሁም አብዛኛውን ደቡብ እና ጥቂት የሰሜን አከባቢዎች የሚሸፍን ብርቱ ተቋምነት ያስመነደገው የመጨረሻው መንስኤስ ምንድነው?

ስለዚህ ድርጅት በዚህ መጠን እንድናውቅ ከፍተኛ ውለታ የዋለልን ኦላና ዞጋ እንደሚለን፣ 1958 ዓ.ል የሜጫ ቱላማ መረዳጃ ማኀበር በተጠናከረ መንገድ እንቅስቃሴ ያደረገበት ዓመት ነበር፡፡ ኮሎኔል ሳህሌ ብሪ (ከ1948-1988ዓ.ል. ገንዘብ ያዥ) መጋቢት 26 ቀን 2010 ዓ.ል በ OBS ቴሌቭዥን ላይ ቀርበው እንደመሰከሩት፣ በ1958 ዓ.ል የቀለበት ስነ-ሥርዓት ነበራቸው፡፡ በእለቱ አቶ ኃይለማርያም ጋመዳ ጄኔራል ታደሰ ብሩን አግባብቶ አባል ማድረግ ችሎ ነበር፡፡ የታደሰ መምጣት የማህበሩ ማርሽ ቀያሪ ሁነት ሆነ፡፡ እንቅስቃሴው በእጅጉ እየሰፋና እየተጠናከረ ሄደ፤ ወደ ማህበሩ የሚጎርፈው ሰው መቆሚያ እስከማጣት ደረሰ፡፡ በዚያ ላይ ከላኛው ማህበራዊ መደብ የሚጎርፈው አባል ተፅዕኖው ቀላል አልነበረው፡፡ ጄኔራሉ የትምህርት፣ የድርጅት ማስፋፊያ እና የአማካሪ ቦርድ ኮሚቴዎችን በተመሳሳይ ጊዜ መምራት ጀመረ፡፡ ለውጡ አስገራሚ ሆነ፡፡

ታደሰ ብሩ፤ ፀጋም እርግማንም

በሀገሪቷ ከሜጫና ቱላማ በጊዜ የቀደሙ ብዙ ማህበራት ነበሩ፤ ለአብነትም የትግሬ ልማት ድርጅት መረዳጃ ማኀበር— ዶክተር መንገሻ ገብረሕይወት በዋና ፀሐፊነት የመሩት፣ የዓለም ገና [ወላይታ] የመንገድ ሥራ ማኀበር— ብርጋዲዬር ጄኔራል ይልማ ሺበሺ በፕሬዝዳንትነት የመሩት፣ የመንዝና ይፋት የመረዳጃ ማኀበር—አቶ አዲስ ወልደየሱስ ዋና ፀሐፊነት የመሩት፣ የወሎ መረዳጃ ማህበር—አቶ (ኋላ ፊት አውራሪ) አመዴ ለማ በፕሬዚደንትነት የመሩት … ወዘተርፈ ፡፡ ሆኖም ለጋው ሜጫና ቱላማ ላይ የአገዛዙ ትኩረት በዛ፡፡ “ለምን?” ያልን እንደሆነ አሁንም መልሱ ጄኔራሉ ይሆናል፡፡

በተለይ የትምህርት ቋሚ ኮሚቴ መምራቱ፣ በፊደል ሰራዊት ዘመቻ መሪነቱ ጥንካሬውን ለሚያውቀው የዘውድ መንግሥት እንቅልፍ የሚነሳ ነበር፡፡ ኮሎኔል ሳህሌ በ OBS ቴሌቭዥን ወጋቸው እንደነገሩን የዘውዱ መንግሥት ኦሮሞን እንኳን ተምሮ ሳይማርም ያለልክ ይፈራ ነበር፡፡ ታደሰ ከዚህ በተጨማሪ የድርጅት ማስፋፊያ እና የአማካሪ ቦርድ ኮሚቴዎችን በተመሳሳይ ጊዜ መምራቱ መንግሥትን ያለልክ አቃዠው፡፡
John Markakis ወቅቱን በጥልቀት ባየበት “ETHIOPIA: Anatomy of A Traditional Polity” ዘመን ተሸጋሪ መፅሀፉ፣ የአፄው መንግሥት በፍትሀ-ብሔሩ፣ በሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስቴር፣ የህዝብ ደህንንት ክፍል እና ኋላ ላይ ደግሞ በ “Special Branch” ከፍተኛ ክትትል እና ጫና ያደርግ እንደነበር ይነግረናል፡፡ምክንያቱንም ዘርዝሯል፤ ማህበሩ ወጣቶች እና የተማሩ ኦሮሞ የአዲስ አበባ ነዋሪዎችን ከማንጋጋቱ በተጨማሪ፣ ታደሰን ጨምሮ የጄኔራል ዳዊት አብዲ የስራ አስፈፃሚ አባል መሆን፣ የጄኔራል ጃጋማ ኬሎ አባልነት እና የመቶ አለቃ ማሞ መዘምር አመራር ያስገኙለት የሰው ኃይል፣ የገንዘብ አቅም (ከኦሮሞ ህዝብ በተሰበሰበ ገንዘብ፣ ወለጋ ውስጥ የኦሮሞ ዩኒቨርሲቲ ለማቋቋም እስከማቀድ ሄዷል፤)፣ ዝና፣ እና ህዝባዊ ተቀባይነት፣ ቆቁ አገዛዝ በቁጥር አንድ ስጋትነት እንዲይዘው አድርጓል፡፡

(አይደክሜውን ማሞ መዘምር በተመለከተ፣ መተኪያ የለሽ ትግሉ እና አንገቱን ለገመድ የሰጠበት ፍፃሜው—“ማሞ መዘምር— የነፃነት ነብይ” በሚል ርዕስ በፌስ ቡክ ገፄ ተርኬዋለሁ::)
Markakis በገፅ 179 ላይ የስርዓቱን ስጋት እንደደመደመው፡-

The [Oromo] composition of its membership, and the wide focus of its efforts encompassing southern provinces with vast [Oromo] populations, raised fears of unified [Oromo] activity that could easly turn political. The prominence of the [Oromo] military men […] reinforced these fears. The behavior of some of these leaders, particularly General Tadesse Biru, was considered inflammatory.

ታደሰ ብሩ በየደረሰበት ሁሉ ለኦሮሞ የድህነቱ፣ የጭሰኝነቱ እና የባሪያነቱ ዋነኛ መንስዜ ምኒልክ ያካሄደባቸው መሬት የመንጠቅ ወረራ መሆኑን እንዲረዱ ይሰብክ ነበር፤ በወቅቱ ይኽን ሀሳብ ማንሳት ስ

ርዓቱን ከማፍረስ አይተናነስም፤ ከታደሰ ከፍተኛ ማእረግ አንፃር ሲመዘን ደግሞ ስድብ ጭምር ነው፤ እሱ ግን የምኒልክ ወራሽ በሆነው የወቅቱ አገዛዝ ላይም እንዲነሳሱ፣ መሬታቸውን እንዳይለቁ፣ መሬታቸው ላይ እንዲሞቱ ይመክር ነበር፡፡
ሆኖም የታደሰ ዝና፣ የማህበሩን ታላቅ ባለውለታ፣ የአቶ ኃይለማርያም ጋመዳን ዋርካነት ማሳነስ አይችልም፤ የማህበሩ የመጨረሻ ፕሬዚዴንት የነበረው ድርቢ ደምሴ ቦኩ በግል እንዳጫወተኝ የማህበሩ መሃንዲስ፣ ወሳኝ ሀሳቦች አመንጪ እና ስንት የተባለለትን ታደሰ ብሩ በአባልነት የመለመለው ራሱ ኃይለማርያም ጋመዳ ነው፡፡ ሌላው፣ በ90ዎቹ ውስጥ፣ ማህበሩ እስኪዘጋ ሰራተኛ የነበረ አባተ አሸና የተባለ ወዳጅ እንዳጫወተኝ፣ ፕሬዚዴንት ኮሎኔል አለሙ ቅጤሳ ንግግር ባደረጉ መጠን፣ ኃይለማርያም ጋመዳን እያነሱ ማንባታቸው የተለመደ ሲሆን ውለታው ፍፁም እንዳይዘነጋ ይወተውቱ እንደነበር አጫውቶኛል፡፡

ከአንድ ከተማ የጀመረው ማህበር፣ መላ ኦሮሚያን አዳረሰ፡፡ ነገር ግን ከዚህም አልፎ ታሪካዊ የኢኮኖሚ እና የማንነት ጭቆና የሚጋሩትን ውስን የሰሜን እና ሰፋ ያለ የደቡብ አካባቢዎች ላይም አሻራውን አኑሯል፡፡ በፈር ቀዳጅ ውሱን ንቁ ኦሮሞዎች የተለኮሰውን የትግል ችቦም፣ ህዝባዊ መሠረት እንዲኖረው አስችሏል፡፡

 የDheeራ “አብዮት”
ኦላና ለግንቦት 1958 ዓ.ል (Markakis፣ November 1966 ይላል) በአርሲ Dheeራ አንድ ህዝባዊ ስብሰባ ተጠርቶ ነበር ይላል፡፡ ነገር ግን ከጠቅላይ ግዛቱ በደረሰው መረጃ መሠረት የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ስብሰባው እንዳይደረግ አገደ፡፡ ኮሎኔል ሳህሌ ብሪ እንዳሉት፣ የደህንነት ክፍሉ ክልከላውን የለጠፈው በማህበሩ ቢሮ ነበር፡፡ ለአርሲ ጠቅላይ ግዛት ፖሊሲ ዋና አዛዥና ለፖሊስ ሠራዊት ጠቅላይ ጽሕፈት ቤትም፣ ስብሰባው እንዳይደረግ በኃይል ጭምር እንዲያስፈፅሙ ትዕዛዝ ሰጠ፡፡ (ኦላና 1985)

የክፍለ ሀገሩ እንደራሴ ደጃዝማች ሣህሉ ድፋዬም ለአዘጋጅ የአገር ሽማግሌዎች ዛቻ አዘል ጥብቅ ማስጠንቀቂያ ሰጠ፡፡ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ፣ ቁጥር 541 ላይ “የሜጫ ቱላማ መረዳጃ ማኀበር ኢተያ ላይ ቅርንጫፍ እናቋቁማለን ብለው ነበር ፡፡ ዓላማቸውን ብንጠይቅ ሕዝቡን መሰብሰብ ነው ስላሉን አልተቀበልናቸውም፡፡” በማለት ይፋ አደረገ፡፡ (ኦላና 1985)

ኦላና፣ ለመግለጫውም ሆነ ለፀጥታው መሥሪያ ቤት ክልከላ መንስኤው፣ እንደሰደድ እሳት በኦሮሞ አካባቢዎች የተቀጣጠለው እንቅስቃሴ ነው ይላል፡፡
አብዮቱ አሁን ግድ አለ

የማህበሩ አመራር ክልከላውን ሲመለከት ለውይይት ቁጭ አለ፡፡ ብርቱ ውሳኔ፣ ወይ መገዛት ወይ እምቢኝ ማለት፤ ሌላ ምርጫ፣ ሌላ ማለዘቢያ የለም፡፡ ወሰነ፡፡ ከዚህ ጥሪ ፈርቶ መቅረት (1) ለሌላ የተፈቀደ፣ ለኦሮሞ ሲሆን የተከለከለ ህገወጥነትን መደገፍ ነው፤ (2) መተሳሰር ከጀመረው ኦሮሞ ጋር መቆራረጥ ነው የሚሉ ውሳኔዎችን፡፡

በመሆኑም፣ ጥቅምት 5 ቀን 1959 ዓ.ል ብ/ጄኔራል ታደሰ ብሩ፣ ብ/ጄኔራል ዳዊት አብዲ፣ ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽ፣ ዶ/ር ሞጋ ፍሪሳ፣ አቶ በቀለ መኰንን፣ አቶ ተስፋዬ ደጋጋ፣ አቶ ገ/ስላሴ ወልዲያ፣ መ/አለቃ ማሞ መዘምር፣ አቶ ደጀኔ ቦጂኣ፣ አቶ ኤጄታ ፈይሳ፣ ወታደር ጨመዳ፣ ወታደር ኃይለማሪያም ዲማና ሌሎችም ከአዲስ አበባ በአቶ ዳዲ ፈይሳ የሚመራውም የአዳማ ቅርንጫፍ አንድ ላይ በመሆን ዴራ ከተማ ገቡ፡፡ (ኦላና 1985)

ህዝቡም በበኩሉ፣ ቀደም ሲል ለሁለቱም ወገን ያልተቋረጠ ማስጠንቀቂያ ሲሰጥ የነበረውን ክፍል ከምንም አልቆጠረም፡፡ ለፍልሚያ ጭምር ተዘጋጅቶ ነበር፡፡ ለምሳሌ የአርሲ ቅርንጫፍ መስራች ሀጂ ሮበሌ ቱሬ

“… መብቱና ነፃነቱን ለማስከበር ልቡ ለተነሳሳ ሕዝብ ይቅርና፣ ለወዳጇ ልቧ የተነሳሳ አንዲት ሴት እንኳ፣ ወደ ኋላ አትመለስም” በማለት መቀስቀሱ ተመዝግቧል፡፡ እውነትም በለቱ ለአዲስ አበባው ቡድን በብዙ ሺህ ወጥቶ ነው ደማቅ አቀባበል ያደረገላቸው፡፡ (ኦላና 1985)

ጥንቃቄ ግን የሁለቱም ወገን ገንዘብ ነበረች፤ ከአዲስ አበባ የሄዱት ጄኔራል ታደሰ ብሩንና ደጃዝማች ከበደ ብዙነሽን ብቻ በስብሰባው ላይ እንዲቆዩ በማድረግ ሌላው አካባቢውን እንዲቃኝ በጥበቃነት መደቡ፡፡ ከህዝቡ በኩልም፣ መሣሪያ ይዘው የመጡት በአቶ ዳዲ ፋይሳ መሪነት የጥበቃ ግዳጅ ተሰጥቷቸው ስብሰባው ማካሄድ ጀመረ፡፡
በመሃል በጭላሎ አውራጃ ገዥ በደጃዝማች አስፋው ሺአምጥና በአውራጃው ፖሊስ ዋና አዛዥ በኰ/ል ልብሰቃል የተመራ የክልሉ አስተዳደር ተወካዮች ቡድን በስፍራው ደርሶ “ስብሰባው ሕገወጥ ነውና በትኑ!” የሚል ትእዛዝ ሰጠ፡፡ ተሰብሰቢው በበኩሉ እግዱ አገዛዙ በብሔር ማንነታቸው የተነሳ የሚያደርግባቸው አድልኦ እንጂ ረኃብ፣ በሽታና ድንቁርና የመዋጋት ዓላማ ይዞ የሚንቀሳቀስ ስብስብ ሕገ ወጥ ሊሆን እንደማይችል ባንድነት አሳወቁ፡፡ ይልቅስ በስብሰባው ላይ ሳይጋበዙ በመገኘታቸው ባስቸኳይ አከባቢውን እንዲለቁ አስገደዷቸው፡፡

ክርስቲያን፣ ሙስሊም፣ ወቄፈታ ሳይል በአስር ሺዎች የታደመ ኦሮሞ፣ በውይይቱ የደረሰባቸውን ኢኮኖሚያዊ ብዝበዛ እና ፖለቲካዊ ጭቆና ግልፅ አደረገ፡፡ የተቀናጀ እና አንድነት ያለው የመጀመሪያው የኦሮሞ ስብሰባ በመሆኑ የአንድነት ጥቅም በእጅጉ አስተዋለበት፡፡ ኦሮሞ ዳግመኛ ላለመለያየት ተማማለ፡፡ ሀጂ ስምቢሮ የተባለ ተሰብሳቢ፣ የኦሮሞ ሕዝብ አንድነት መቼም አስፈላጊ መሆኑን ሲያብራራ፣ “ትንንሽ ምንጮች ሲቀላቀሉ ወንዝ ይፈጥራሉ፤ አያሌ ወንዞችም ተደባልቀው ትልቅ ባህር ይሆናሉ፤ የኦሮሞ ህዝብም ብሄርና ሀገር የሚኖረው ሲሰባሰብ ነው” አለ፡፡

ሙስሊሞች፣ በክርስትያኖች የታረደ ዕርድ እንዲሁም ክርስቲያኖች በሙስሊሞች የታረደ ዕርድ ተመገቡ፡፡ ይህ እስከ ዛሬ ያልተሰማ ታሪክ በመሆኑ፣ ገዢ ልሂቁን የሚያስቆጣ ተጨማሪ መንስኤ ሆነ፤ ከሁሉ በላይ ደግሞ ማርካኪስ፣ “National and class conflict in the Horn of Africa” በተባለ ድርሳኑ ገፅ 260 ላይ እንደገለፀው ስብሰባው የተካሄደው በኢትዮጵያ እንዳይነገር በአዋጅ በታገደው አፋን ኦሮሞ መሆኑ፡፡
በቀጣይ የተካሄዱ ስብሰባዎችም በሙሉ፣ በአፋን ኦሮሞ ነበሩ፤ በዚያ መቆሚያ አልባ ጉልበቱ፣ ባለተሰጥኦው ወጣት መኮንን ማሞ መዘምር (መቶ አለቃ) የፃፋቸው ድራማዎች በስብሰባው ቀረቡ፡፡
በዚያ ታላቅ ህዝባዊ ስብሰባ፣ አንደበተ-ርቱዕ ተናጋሪዎች በአፋን ኦሮሞ ንግግር አደረጉ፣ ድራማዎች፣ ግጥሞች እና የፀሎት ስነ-ሥርዓት ቀርበው፣ ተሰብሳቢውን በቁጭት እንባ አራጩ፤ በአገዛዙ ላይ እንዲነሳሱም ገፋፏቸው፡፡ የተደረገባቸውን ክልከላ እና እንደ ሁለተኛ ዜጋ መታየት፣ በግልፅ የተረዱበት እለት ነበር፡፡ ነፃ መሆን እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ህዝቦች እኩል የመታየት መብታቸውን ለማስከበር ቁርጠኝነታቸውን የገለጡበትም ነበር፡፡ አገዛዙ እንደፈለገው ሲበጫጭቃቸው እንዳልነበር፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ ኦሮሞን በቀላሉ እርስ በርሱ የማጣላት እና የመከፋፈል አቅሙ ክፉኛ ተዳከመ፡፡

በመሆኑም፣ ገዢ ልሂቁ፣ ውሎ ሳያድር፤ ማህበሩን ማፍረስ፣ ለአማራጭ የማያቀርበው ሌላ መግፊኤ ሆኖ አገኘው፡፡

የማህበሩ ተቋማዊ እድገት ውጤቶች

ማህበሩ፣ ሦስት የፖለቲካ ተቋማዊ የእድገት ሽግግሮችን አልፏል፡፡

የመጀመሪያው በውድቀት የተጠናቀቀ ነበር፡፡ የተላንቀጡ (assimilated) ክርስቲያን ኦሮሞዎችን ወደ የኦሮሞ ፖለቲካ ንቃት መቀላቀል ያለመቻል ውድቀት፤
ሁለተኛው፣ ከከፍተኛ ጥረት በኋላ የተመዘገበ የስኬት ምዕራፍ ነበር፡፡ ማህበሩ፣ እስከዚያ ጊዜ ድረስ ብዙም ትኩረት ባይሰጠውም ከባባድ አሉታዊ የስርዓቱ ፖለቲካዊ መለያዎችን ገልጧል፡፡ በተለይ በአማራ ልሂቃን አካባቢ የነበረውን ከባድ ኦሮሞ-ጠልነት እና የኦሮሞ ጥላቻ፡፡ በ1930ዎቹ እና 40ዎቹ የተማሩ ኦሮሞዎች ለቁጥር አይገቡም ነበር፡፡

ዳዊት ወልደ ጊዮርጊስ“Red tears: war, famine and revolution in Ethiopia” በተባለ መፅሐፉ “እነዚያ ጥቂት ‘ዕድለኛ’ ኦሮሞዎች ወደ ኢትዮጵያ ሥርዓት ልብ እና መንፈስ የሚቀላቅላቸውን መስፈርት ይዘዋል” ይላል፡፡ አብዛኛዎቹ ክርስቲያኖች ነበሩ፤ በባህል አማራ ከመሆናቸውም በላይ የሚያወሩትም አማርኛ ነበር፡፡ ቀንደኛ የኢትዮጵያዊ (ጠቅላይ) ብሔርተኝነት አቀንቃኞች ነበሩ፤ ለንጉስም ታማኝ ነበሩ፡፡ ነገር ግን ይህ ሁሉ ሆኖም፣ በአማራ ልሂቃን ዘንድ በእኩልነት አይታዩም ነበር፡፡

ሙኩሪያ ቡልቻ በበኩሉ “Survival and Reconstruction of Oromo National Identity” በሚለው ጥናቱ ስለነዚህ ተለንቃጮች (አስሚላንዶ) ኦሮሞዎች የሚከተለውን ይላል፡-

The life of assimilated Oromos was often peripheral. In spite of their total submission to “pressure for their cultural suicide and to the dominance of the Amhara over non-Amhara peoples in all aspects of life”, they were seldom treated as equales by Amhara. The Amharazation of the Oromo and other groups was attemted “with out integrating them as equales or allowing them to share poser in any meaningful way” As the “Amhara mask” they wore was often too transparent, assimilated Oromos rarely reached decision-making positions within the Ethiopian bureaucracy.

እንግዲህ ይህንን ሁሉ የማንነት መስዋዕትነት ከፍለውም እንኳ ውሳኔ ሰጪነታቸው ይህ ነው ተብሎ የሚጠቀስ ያለመሆኑን መኩሪያ አብራርቷል፡፡

እነዚህ የተላንቀጡ ክርስቲያን ኦሮሞዎች፣ ምንም እንኳ ማንነትን ያክል ነገር ለጠቅላዩ ባህል ገብረው፣ ያልሆኑትን ቢመስሉም፣ በአማራው (ጠቅላዮቹ) ልሂቃን መገለልና መድልኦ እየተደረገባቸው እንደሆነ ወይ አይረዱም አልያም ተቀብለውት ነበር፡፡ ሆኖም በስተመጨረሻ እነዚህ ወገኖች ይኸንን ሁኔታ ተረድተው ለንቅናቄ እንዲሰለፉ ማድረግ ተቻለ፡፡

ሶስተኛው በንጉሱ ፍቃድ ቢነጠቅም፣ የ1966ቱን ታሪካዊ ሁነት ተከትሎ፣ ወዲያው አካሄዱን ፖለቲካዊ ማድረግ መቻሉ ነው፡፡ በዚህ ሽግግር የመጣው አዲሱ ፖለቲካዊ አተያይ በብዙ የተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ኦሮሞዎችን ስምና ስሜት በመጠቀም የማነቃነቂያ መሳሪያ እንዲሆን አስችሎታል፡፡

በተመለከተው ከፍተኛ ጫና ስር ሆኖም፣ የኦሮሞን ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ እና ባህላዊ አያያዝ ማሻሻያዎችን፣ እንዲሁም የትምህርት እና የጤና ተቋማት ተደራሽነት ጠይቋል፡፡ በአቅሙም ተግብሯል፡፡ ለኦሮሞ የጋራ ፍላጎት እና ህብረት እንዲሁም ሰዋዊ ክብር እንደ ትዕምርት (symbol) ሆኖ አገልግሏል፡፡ ከ1960ዎቹ ጀምሮ ላቆጠቆጠው የኦሮሞ ብሔርተኝነት አዲስ የፖለቲካ ልምምድ ምዕራፍ ከፍቷል፡፡ የምዕራፉ ልምምድ፣ የኦሮሞ ልሂቃን የህዝባቸውን ሀብት በማደራጀት እና ተግባራቸውን በማዋደድ፣ ጨቋኙን የኢትዮጵያ ሥርዓት መገርሰስ እንጂ ጭቆና ላይ ከተመሰረተ የፖለቲካ ሥርዓትና የህብረተሰብ መስተጋብር ለመውጣት የገዢው በጎ ፈቃድ መቼም እንደማይገኝ አስተምሯቸዋል፡፡ ወደ ኋላ ላይ ደግሞ የብሄሩ የመብት ጥያቄ የአጠቃላዩ የኢትዮጵያ ህዝብ የዴሞክራሲ ጥያቄ አካል ተደርጎ እንዲቃርብ አስችሏል፡፡

ፍሬ ነገር፡-
ለዚህ ነው፣ ኮሎኔል ሳህሌ ብሪ፣ “አንድ በማህበሩ ስብሰባ ላይ ተጋብዞ ለመጀመሪያ ጊዜ የተገኘ ሰው፣ የሚርመሰመሰውን ሰው ተመልክቶ፣ ‘እናንተ ሰዎች! ህንፃ ድልድይ እንገነባለን የምትሉት ነገር መሬት ላይ በአካል የለም፤ በሰው አእምሮ ላይ ከሆነ ግን በሚገባ ገንብታችኋል’ አለኝ” ያለው፡፡

“Define and Destroy”
1958 ዓ.ል በቀዳማዊ ኃይለሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ልዩ ልዩ የመረዳጃ ማኀበራት የሚሳተፉበት ውይይት ተዘጋጀ፡፡

የመንዝና ይፋት እና የትግሬ መረዳጃ ማኀበራት፣ በየማኀበሮች እጅ የሚገኝ ሀብት ይከፋፈልልን ሲሉ አሳሰቡ፡፡ ቀስቱ ወደ እሱ መወርፈሩን የተረዳው የሜጫ ቱላማ የመረዳጃ ማኀበር ተቃወመ፡፡
ቀጥሎ በአክሊሉ ሀብተወልድ የሚመራው የሚኒስትሮች ምክር ቤት ማክሰኞ ነሐሴ 10 ቀን 1958 ዓ.ል ባደረገው ስብሰባው ማህበራቱን የተመለከተ ሕግ አወጣ፤ በ1959 ዓ.ል “የማኀበሮች ምዝገባ ደንብ” ሆኖ ወጣ፡፡ የፈለገውን ማህበር ማፍረስ፣ መቀላቀል፣ “18 ልዩ ሁኔታ” በሚል ድንጋጌ ደግሞ ልዩ ጥበቃ የሚደረግላቸው እንዳሉ ዘረዘረ፡፡ ይኸም ትኩረቱ ሜጫ ቱላማ እንደነበር አያጠያይቅም፡፡

ኦላና እንደዘገበው፣ ጥቅምት 18 ቀን 1959 ዓ.ል በወጣችው አዲስ ዘመን ጋዜጣ ቁጥር 556 “በጐሣ ላይ የተመሠረተ የልማት ማኀበሮች መቋቋም ይጠቅማል? ወይስ አይጠቅምም?” በሚል ርእስ ቅዳሜ ጥቅምት 19 ቀን በወ.ወ.ክ.ማ. አዳራሽ ውይይት እንደሚደረግ ማስታወቂያ ተነገረ፡፡ ተካሄደ፡፡

እንዲህ አይነቱ መንገድ ዛሬም ያለ ነው፤ ኢህአዴግ አንድ የሚፈራውን ድርጅት ለማፍረስ፣ ግለሰብ ለማሰር፣ እንዲሁም በአሸባሪነት ለመፈረጅ ሲፈልግ ቀደም ብሎ በETV/EBC ይዘምትበታል፡፡ “አንዳንድ” የአዲስ አበባ ነዋሪዎች እንዲያወግዙት ያደርጋል፡፡ ወንድሞች ፈረንጆች “define and destroy” ይሉታል ይኸን መንገድ፡፡

በመጨረሻም ድርጅቱ ታገደ፡፡ ታደሰ ብሩ የሚገኝበት ቡድን ንጉሱ ድረስ ፍትህ ፈልጎ ቢቀርብም አላሰፈነላቸውም፡፡ በዚህ እለት የኦሮሞ ንቅናቄ ወደ ቀጣዩ እርከን አማተረ፡፡

ደረጃ ሦስት

ሦስተኛ ደረጃ የሚባለው፣ ህዝቡ በተገቢው ሁኔታ ተነቃቅቶ የብሔራዊ ንቅናቄው መግፍኤ የሰፊው የህብረተሰቡ ክፍል የወል ግንዛቤነት ደረጃ ሲያገኝ ነው፡፡ ከኦሮሞ አንፃር በተለይ ከ1983 ዓ.ል በኋላ ያለውን ጊዜ መውሰድ ይቻላል፡፡ በርግጥ ከ1984 ዓ.ል ወዲህ በራሱ፣ የኦነግን ከሽግግር መንግስቱ መገፋት ተከትሎ፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ንቃት አዲስ አቅጣጫ ደረጃ አራት ስር ለብቻው እናያለን፡፡ ኦነግ፣ የሜጫና ቱላማ አባላት የነበሩ ልሂቃን እንደመሰረቱት ይታወቃል፡፡ የኦሮሞን የማይገሰሱ መብቶች ለማስመለስ እና ለማስከበር ታግሏል፤ በኦሮሞ ሕዝብ ልብ ውስጥም ሰርፆ ለመግባት አልከበደውም ነበር፤ ለኦነግ የርዕዮተ ዓለም ነዳጅ ሆኖ ያገለገለው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነበር፡፡ የኦነግ መመስረት ምን አስገኘ ለሚለው መልሱ እነሆ፡-

“… የብሔራዊ ንቅናቄ መፈጠር ህዝቡ አሊያም አንድ ማህበረሰባዊ ቡድን ወደ ‹ብሄርነት› (Nationhood) የሚያደርሰው ሀዲድ ላይ መውጣቱን ማሳያ ነው፡፡ ወደ ፖለቲካዊ ድርጊት መሸጋገሪያ ነው፤ ራሳቸውን እንደ ብሔር የሚያዩ የብሔር አሊያም የሕዝብ አካላት የራሳቸውን መንግሥት የመመሠረት ሙከራ፡፡” ነው፡፡
(Alter 1989 22-23)

ቀደም ሲል፣ የኦነግ የፖለቲካ ፕሮግራም፣ የኦሮሞ ብሔራዊ ትግል፣ ዴሞክራሲያዊ የኦሮሚያ ሪፐብሊክ መመስረት መሆኑን በግልፅ አስቀምጧል፡፡ በተጨማሪ፣ በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኢትዮጵያና የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት አንድነትን ይሰብካል፡፡ በተጨማሪም የሌንጮ ላታን “Horn of Africa as A Common Home Land” መውሰድ ይቻላል፡፡ ኦነግ፣ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ንቅናቄ ከማህበራዊ ወደ ፖለቲካዊ ይዘት ለመሸጋገሩ ማሳያ ነው፡፡ የኦሮሞ ብሄርተኝነት ብስለት ማሳያ ነው የሚሉም ወገኖች አሉ፡፡

ከ1966 እስከ 1983 ዓ.ል ድረስ ወታደራዊው መንግሥት፣ የኦሮሞ ነጻ አውጪ ግንባርን፣ ከህዝቡ አርቆ በሀረርጌ፣ ባሌ እና ወለጋ ጥቂት ቦታዎች ነጥሎ ነበር፡፡ የዘርፉ ተንታኞች የወታደራዊው መንግሥት፣ የሰፈራና መንደር ምስረታ ፕሮግራም አንዱ አላማ፣ ኦነግን ከህዝቡ በመነጠል የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ግለት ጋብ ማድረግ እንደነበር ይፅፋሉ፡፡ የሆነው ሆኖ፣ በተራው ወታደራዊው መንግሥት እንዲወድቅ የኦነግ አስተዋፅኦ ቀላል አልነበረም፡፡ ለዚሁ አስተዋፅኦውም በግንቦት ወር 1983 ዓ.ል ለንደን ላይ፣ በዚያው ዓመት ሐምሌ ወር ደግሞ በአዲስ አበባው ጉባኤ ተሳታፊ ለመሆን ችሏል፤ ህወሓት ጋባዥ እኔ ነኝ ብትልም ቅሉ፡፡

መረራ ጉዲና፣ የኦነግን በጉባኤው መሳተፍ ከላይ ከገለጽነው ምክንያት ጋር አያያይዘውም፤ በመረራ ትንተና መሠረት የኦነግ ተሳታፊነት የመነጨው፡ “የኦሮሞ ህዝብ ቁጥር ከፍ ማለት ለፖለቲካ ሚዛኑ ያለው አስተዋፅኦ፣ ኦነግ የአንድነት ኃይሎች ላይ የያዘው አሉታዊ አቋም፣ ኦነግ እንዲካተት ሕግዴፍ በሕወሓት ላይ ያሳረፈው ጫና እንዲሁም የኦነግ መካተት አዲስ ለሚመሰረተው መንግሥት ከዓለም ማህበረሰብ ዘንድ በሚያሰጠው ሞገስ” ላይ ተንተርሶ እንደሆነ ይገልፃል፡፡
ኦነግ፣ እስከ ሰኔ 1984 ዓ.ል ድረስ፣ የኢትዮጵያ ሽግግር መንግሥት አካል ነበር፡፡ በዚች አጭር ጊዜ ታዲያ የኦነግ ካድሬና ወታደር ያልረገጠው የኦሮሚያ ክፍል አልነበረም፡፡ የኦሮሞን ብሔራዊ ንቅናቄ ከተወሰኑ ቡድኖች ወደ ብዙኃኑ ያጋባው (ከሜጫና ቱላማ ቀጥሎ) ይህ እንቅስቃሴ ሳይሆን እንደማይቀር፣ ከግምት ባለፈ ማመን ይቻላል፡፡ ስለኦነግ ተጨማሪ “ኦነግና የሽግግሩ መንግስት” በሚል ርዕስ “የኦሮሞ ጉዳይ …” መፅሓፌ ላይ ተካቷል፡፡

1983 ዓ.ልን ተከትሎ ለኦሮሞ ብሔርተኝነት መፍጠን፣ ሦስት መሰረታዊ ምክንያቶች ነበሩ፤ ቀለል ያሉት ሁለቱ ተፃራሮዎቹ ያልተማከለ አስተዳደር ድንጋጌ እና የሕወሓት የኦሮሚያ ቁጥጥር ሲሆኑ ዋነኛው ግን የኦሮሞ (ውክልና የያዙ) ድርጅቶች፣ ፣ ተቋማት እና ግለሰቦች (ልሂቃን፣ ምሁራን፣ ፖለቲከኞች) ተግባራት እንዲሁም ሞጋቹ ቁቤ ትውልድ ነው፡፡

የኦሮሞ የተለየ የራስ ማንነት አረዳድ የተመለሰው ከ1983 ዓ.ል በኋላ ነበር፡፡ በአፋን ኦሮሞ የተጻፉ ህትመቶች ተበራክተው ነበር፡፡ ኦነግ፣ ከ1968 ዓ.ል ጀምሮ ሲጠቀምበት የነበረው የላቲን ፊደል- “ቁቤ አፋን ኦሮሞ”-“Qubee Afaan Oromo” ተብሎ ስራ ላይ ውሏል፡፡ (በነገራችን ላይ፣ ጥላሁን ጋምታ፣ በ1985 ዓ.ል በሰራው፡- “reasons for choosing the Latin Script for developing Afaan Oromo Alphabet” የተባለ ጥናቱ፣ የቁቤ ተወዳጅነት፤ “በጣም የለማ፣ ከየትኛውም ፊደል በላይ ለፅሁፍ አመቺ የሆነና ከየትኛውም ቋንቋ ጋር ለመጓዝ እራሱን ያዘጋጀ” ሲል አብራርቶታል (ጥላሁን ጋምታ፣ 1993፡ 37)፡፡

በርግጥ ከዚህ ፊደል በላይ የዘመኑን ስልጣኔ የተዋወቀ የለም፡፡ በ1968 ዓ.ል መጀመሪያ አካባቢ፣ በአፋን ኦሮሞ መጽሐፍም ሆነ የአየር ሰዓት መሸፈን አይቻልም ነበር፡፡ በርግጥ ዛሬ የኦሮሚያን ዕጣ-ፈንታ ለመወሰን የሚደረገው የርዕዮተ- ዓለም ትግል፣ የህትመትም ሆነ የአየር ሰዓት አፋን ኦሮሞን በመጠቀም የሚካሄድ ነው፡፡ በ1966 ዓ.ል አንድም የህትመትም ሆነ የአየር ሰዓት ስርጭት እንዳለመኖሩ፣ 20 ዓመት ብቻ (በ1986) በአፋን ኦሮሞ የሚቀርቡ የሚዲያ ውጤቶችን በሙሉ ለመከታተል ከባድ መሆኑን ማን ይገምት?

ደረጃ አራት
“በመሆን መብት” መገደብ

(በመኩሪያ ቡልቻ አተናተን፣ አራተኛው ደረጃ፣ የተለያዩ ዘውገ ብሄረተኛ ነፍጥ አንጋቾች በብዛት ወደ ትግሉ ተቀላቅለው የደርግ መንግሥት ከወደቀ በኋላ የኦሮሞ ትግል የሰፊው ሕዝብ ትግል መሆኑ ነው::)
የድህረ 1983 ዓ.ል መገለጫዎች

1. የንቅናቄው ህዝባዊ መሆን፣
2. የፌዴራሉ አወቃቀርና በውስጡ ያካተታቸው ተቃርኖዎች ናቸው፡፡

በኔ እይታ፣ ይህ ወቅት የትግራይ ገዥ ልሂቃን ኦሮሞ የመሆን መብቶች—ነፃነቶች(+ve Rights) ብቻ ተከብሮ፣ ከማድረግ መብቶች—ነፃነቶች (-ve Rights) በዘዴ ታቅቦ የቆየበት ነው፡፡ በሰር አይዛያ በርሊን ትንታኔ መሠረት የመሆን መብቶች—ነፃነቶች (positive rights) ኦሮሞ የመሆን፣ “ኦሮሞ ነኝ” ብሎ ራስን መግለፅ ልንል እንችላለን፡፡ የችግሩ ቁልፍ፣ የመሆን መብቶች፣ ያለተከታያቸው፣ ብቻቸውን የማይቆሙ የመሆናቸውን ያህል፣ ኢህአዴግ በበኩሉ ከዚህ በላይ እንዲሄዱ የሚፈቅድ ገት ያልነበረው መሆኑ ነው፡፡ በበርሊን ትንታኔ የማድረግ መብቶች—ነፃነቶች (Negative Rights) ማለት “ከሆነ አካል እና ከሆነ ጉዳይ ነፃ መሆን ወይም መጠበቅ” ማለት ነው፡፡
የክልሉን ውክልና የያዘው ኦህዴድም የትግራይ ገዥ ልሂቃን እጅ ከመሆን አላለፈም ነበር፡፡
የመሆን መብቶች ትሩፋቶች

አንዱ በራስ ቋንቋ መማር ሲሆን በውጤቱም ስነፅሁፋዊ እድገት ይመጣል፡፡ ከ1872 እስከ 1984 ዓ.ል (ለመቶ አስራ ሁለት አመታት) ድረስ ከታተሙ ህትመቶች ይልቅ፣ ከ1985 እስከ 1986 ዓ.ል ባለው ጊዜ ውስጥ (በአንድ ዓመት ብቻ) የታተሙ የአፋን ኦሮሞ ስነ-ፅሁፎች በቁጥር እንደሚልቁ ማን ይገምት! ከ1985 እስከ 1986 ዓ.ል ብቻ ስምንት ሚሊዮን ቅጂ የነበራቸው 58 የመማሪያ መጻህፍት በአፋን ኦሮሞ ታትመዋል፡፡ ያን ተከትሎ የኦሮሞ ተወላጅ ህፃናት (ይህ ፀሀፊው በዚህ ሂደት ያለፈ ነው)፣ በአፋን ኦሮሞ መማር ችለዋል፤ ምሁራኑም ጥናትና ሙግቶቻቸውን በዚያው ቋንቋ በማድረጋቸው የእውቀት ሥርዓት ፈጥረዋል፡፡ የቀደመውን የአማርኛ የእውቀት መንገድ ብቸኝነት የተገዳደሩበት ፍጥነትም እጅግ አስገራሚ ነበር፡፡ የኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንም ለቋንቋው ፅዩፍ እንዳልነበረች፣ መዝሙሮችን፣ እንዲሁም ስብከቶችን በአፋን ኦሮሞ አዘጋጀች፡፡ (ሲጀምር “የሰይጣን ቋንቋ” እስከማለት የሄዱ ቀሳውስት ነበሩ፡፡ በርግጥ አፋን ኦሮሞ ብቻ አልነበረም የተጠላው፤ አፈወርቅ ገብረ ኢየሱስ ትግሬ መስደቢያ ቃላት ሲያጥሩት “ጉሮሮ በሚፍቅ ቋንቋቸው” ይላል በአጤ ምንሊክ እና ኢትዮጵያ መፅሀፉ፡፡) ቤተ ክርስቲያኗን በማለዘብ ረገድ ብዙ የኦሮሞ ምሁራንን የሰበሰበው “ማህበረ ቅዱሳን” ከፍ ያለ ድርሻ አለው፡፡ በለውጡ ሰሞን፣ ኦሮሞ ያልሆኑ ሰዎች ጭምር፣ አፋን ኦሮሞ የሚሰጥባቸውን የማታ ክፍለ ጊዜያት ማጨናነቅ ያዙ፡፡

ከቀድሞ ባልደረባዬ ኦቦ ኩምሳ ቃበታ ጋመቹ (አአዩ) ባገኘሁት መረጃ መሠረት የቁቤ ትምህርት ቤት በመክፈት ለመጀመሪያ ጊዜ ትምህርት የሰጡ ሰዎች ራሱ ኩምሳ ቃበታ ጋመቹ፣ አለማየሁ ቁቤ ጭራት እና አለማሁ ነዳ (Nadhaa) ነበሩ፡፡ በመቀጠል ጥላሁን ጋምታ (ዶ.ር)፣ ተሰማ ታዓ (ፐ/ር) እና ዘላለም ባንቲ የመሳሰሉ ሰዎች ተቀላቅሏቸዋል፡፡

ይህ የመሻሻል ሂደት ተስፋ የሰጠው ካለ ተሳስቷል፤ ምክንያቱም ዘላቂ አልነበረም፤ በ2003 ዓ.ል (ከ24 ዓመታት በኋላ) በአፋን ኦሮሞ የሚወጡ የስነ-ፅሁፍ ውጤቶች፣ ከሁለት ዲጂት አይበልጡም፤ የእጅ-አዙር “ቀኝ ገዢዎቹ” ህወሓቶች፣ በአፋን ኦሮሞ መናገር ከቻሉ በኋላ፣ ቋንቋውን ሌላው እንዲያውቅባቸው የፈለጉ አይመስልም፡፡ በርግጥ ዛሬ በአፋን ኦሮሞ መናገር አያሸማቅቅም፤ “ጋላ” የሚለው “አዋራጅ” ቃልም እየቀረ ነው፤ (ይህ ድምዳሜዬ የጌታቸው ኃይሌን ቀጣይ ተጠቃሚነት አይመለከትም፤ “አንድ አፍታ ላውጋችሁ” እና “አባ ባህሬይ ድርሰቶችና ሌሎች ኦሮሞን የተመለከቱ” መፃህፍቱን ተመልከት፡፡) አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲም አፋን ኦሮሞን እስከ ሁለተኛ ዲግሪ ይሰጣል፡፡ ሥነ-ፅሁፍ ግን የለም፡፡ “አዲስ አበባ (ፊኒፊኔ) ዋና ከተማችሁ ናት” ሲላቸው የነበረው ሕወሓት ኦህዴዶቹ በአፋን ኦሮሞ የሚያስተምር አንድ መደበኛ ትምህርት ቤት እንዲከፍቱ እስከ 2009 ዓ.ል አልፈቀደም፡፡ “በሕግ ይወሰናል” የተባለው የፊንፊኔና የኦሮሚያ ግንኙነት መስመርም ቢሆን ቄሮ እስኪያናውጣቸው ክርችም ካዝና ውስጥ ነበር፡፡ አሁንም እንደተንጠለጠለ ነው፤ ቢያንስ ቤተ-መንግስቱ ያለበት Dhaካ-አራራ (Dhakaa araaraa-የእርቅ አምባ) የአንድ ክቡር የኦሮሞ ቤተሰብ ንብረት መሆኑን የሚያስታውስ እንኳ የለም፡፡

የስነፅሁፍ ዋጋው የሚመዘን አይደለም፤ ሁለንተናዊ ነው፡፡ በአፋን ኦሮሞ የተፃፈ አንድ ሰነድ፣ የኦሮሞ መስተሃልይ፣ የኦሮሞ ነፍስ፣ የኦሮሞ መንፈስ፣ የኦሮሞ የፅርአርያም አተያይ፣ እና በፅርአርያም ውስጥ ያላቸውን ቦታ አመልካች ነው፡፡ ቋንቋ የአስተሳሰብ ነፃብራቅ ነው፡፡ በርግጥ ቅድመ 1968 ዓ.ል አፋን ኦሮሞ እና የኦሮሞ ባህል የመይምነት እና የኋላ ቀርነት መገለጫ በመሆኑ የውርደት ምንጭ ነበር (መኩሪያ ቡልቻ 1984፡ 103)፡፡ እነዚያ ቀናት ለዘለዓለሙ ያለፉ የመሰላቸው ብዙዎች ነበሩ፡፡ እውነቱ ያ አይደለም፤ በተለይ ቅድመ 2007 ዓ.ል ከተመለከትን መሀመድ ሀሰን፣ ብዙ ለውጦች ቢኖሩም ነገሮች ገና ናቸው ማለቱ ተገቢ ድምዳሜ ነው፤ “Oromo nationalism has not yet achieved its ultimately goal of creating self-governing Oromoia, but it has fundamentally altered the Oromo perception of themselves and how they are perceived by others”

ቢያንስ ከ25 ዓመታት በፊት መሀመድ ሀሰን፣ ከአንዱ የሕወሓት ባለሥልጣን ጋር ባደረገው አምስት ሰዓታት የፈጀ ውይይት፣ የኦሮሞ ብሔርተኝነት የማይመለስበት ደረጃ ላይ ለመድረስ፣ የተወሰኑ ጊዜያት እንደሚጠብቅ እንዳብራራለት መግለፁን አስታውሳለሁ፡፡ እንግዲህ፣ ከቁጥጥራቸው ከመውጣቱ በፊት ንቅናቄውን በመከፋፈሉ እና በማምከኑ ተግባር ላይ ቅንጣት ያክል የማይቦዝኑት ለዚህ ነበር፤ ነው፡፡ ጊዜአቸውን ለዘረፋ ለማዋል፡፡ ይህ ደግሞ የኦነግን ወታደራዊ ክንፍ ለማምከን የተሄደበትን የክህደት መንገድ ያካተተ ጭምር ነው፡፡ ዛሬ እንዴት ያምኑ ይሆን?

የኢሕአዴግ አመራሮች (የውሸት መሆን አለበት)፣ የሥልጣን ጠቅላይነቱ (monopoly) ከአማራ ልሂቃን እጅ በመውጣቱ ብሔራዊ ጭቆና አብቅቷል ብለው “ያምናሉ”፡፡ እውነቱ ግን ኦሮሚያ እስከ ቄሮ መምጣት ድረስ የተሸነፈች ግዛት ነበረች፡፡ ሆኖም ዛሬም ሙሉ እኔነት አላረጋገጠችም፡፡ ኦሮሞቹ፣ የዲሞክራሲ ማዕከል የሆነው በነጻነት የመደራጀት መብት አልነበራቸውም፡፡ እስከ ቄሮ መምጣት ድረስማ በኦሮሚያ ከሕወሓት ትዕዛዝ የማይቀበል ድርጅት መደገፍ፣ እስከ ሕይወት መስዋዕትነት ድረስ ዋጋ ወጥቶለታል፡፡ (ዝርዝሩን “ኦሮሞ ስለሆንኩ እና ዋጀብሎ” በሚል ርዕስ ማስነበቤን አስታውሳለሁ)፡፡

ነገር ግን የትግራይ ገዥ ልሂቅ ቀይዶ የያዘው የኦሮሞ የማድረግ መብቶች—ነፃነቶች (-ve Rights) ያለመረጋገጥ በስተመጨረሻ የሚታለፍ አልሆነም፡፡ የክልሉን ውክልና የያዘው ኦህዴድም የትግራይ ገዥ ልሂቅ እጅ ከመሆን ያለማለፉ ህዝቡ የመናቅ ስሜቱን እስከ መጨረሻው እንዲሸከም አላስቻለም፡፡

ደረጃ አምስት
የህወሓት ፌዴራል መንግሥት አይጠግቤነት እና የሰላ ጫፍ የደረሰው ቄሮ

ሚያዝያ 2006 ዓ.ል መጨረሻ አካባቢ፣ የማስተር ፕላኑ ጉዳይ፣ ለመረጃ ቅርብ የሆኑ ሰዎች ዘንድ ደርሶ ነበር፤ እስከዚህ ጊዜ ድረስ የኦሮሞ ህዝብ መብቶች በተለመደው የመሆን መብቶች—ነፃነቶች (positive rights) ላይ የተገደበ ነበር፡፡
በተቃራኒው፣ ኦሮሞ መሆን (“ነኝ” ማለት—በኢሬቻ አይነቱ የሚገለፅ) ብቻውን ውጤት እንደማያስገኝ ቄሮ/ቄሬቲ ተደርቶ ኖሮ፣ በኦሮሞነቱ ለ‹ማድረግ› የተጎናፀፈውን መብቶች ሁሉ ከመተግበር የሚያግደው ምድራዊ ኃይል መኖር እንደሌለበት ተገነዘበ፡፡ ከላይእንዳየነው የማድረግ መብቶች—ነፃነቶች (Negative Rights) ማለት “ከሆነ አካል እና ከሆነ ጉዳይ ነፃ መሆን ወይም መጠበቅ” ማለት ነው፡፡
***
ተወዳጁ አስተማሪዬ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) በበኩሉ ስለ የማድረግ ነፃነቶች ሲዘረዝር፣ “… በነፃነት የመንቀሳቀስ፣ የመሰብሰብና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቶች ተጠቃሽ ናቸው፡፡” ይላል፡፡ ዳኜ ነፃነቶቹ እና የኢህአዴግ መንግሥት ያላቸውን የግንኙነት ሚዛን በተመለከተ፣ ከሪፖርተር ጋዜጣ ጋር (31 December 2017) ባደረገው ቃለ-መጠይቅ “… እነዚህ መብቶች በሰፊው የተገደቡ ናቸው፡፡ ዜጎች እንዲህ ዓይነት ነፃነትና መብቶች እንዲተገብሩ መንግሥት ጣልቃ ያለመግባትና መታቀብ ያለበት ሲሆን፣ እየሆነ ያለው ግን በተቃራኒው ነው፡፡ እናገራለሁ ስትል ስለማንና ስለምንድን ነው የምትናገረው? ትባላለህ፡፡” በማለት የፓርቲውን ቀሊልነት አሳይቷል፡፡
አሁንም ከዳኛቸው ጋር የሚያገናኘኝን አንድ የግል ትዝታዬን አጋርቼ ልለፍ፡፡

የማድረግ መብቶች ያላቸው የተግባራዊነት ዕድል በዘርፉም ይለያያል፤ በ2005 ዓ.ል ሁለተኛ አጋማሽ ላይ፣ ከአስተማሪዬ ዳኛቸው አሰፋ (ዶ/ር) ጋር በዋናው በር ወደ ስድስት ኪሎ ዩኒቨርሲቲ እየገባን ነበር፤ ዩኒቨርሲቲው በር ፊት ለፊት በሚገኘው “ድባብ” የሚባል መናፈሻ ፊት ለፊት አንዱ ባህታዊ ይሰብካል፡፡ ዕለቱ 27 ነበር፤ ኦርቶዶክሶች መድኃንአለምን የሚያስታውሱበት፡፡ የያዘው ድምፅ ማጉያ ሀገሩን ሁሉ የሚያናጋ ድምፅ ይተፋል፤ በዚያ ላይ መልዕክቱ ወዮታ ይበዛበታል፡፡ “የፖለቲካ ፍልስፍና” ኮርስ የሚሰጠን ዳኜ፣ Liberty ላይ ደርሶ ነበር፤ ወደ ክፍል እንደገባን “በዚህ ሀገር የመናገር ነፃነት ተፈቅዷል፤ አሁን ዩኒቨርሲቲው ፊት ለፊት አደባባይ ላይ ቆሞ የሚሰብክ ባህታዊ አልፈን ነው የመጣነው፤ የመናገር ነፃነት ተፈቅዷል፤ ቁምነገሩ ግን መናገር የተፈቀደው ምንድነው? የሚለው ነው፡፡ እዚህ ክፍል ውስጥ ሰብስቤ የማስተምራችሁን ከዩኒቨርሲቲ ቅጥር ወጥቼ፣ እንኳን በማይክራፎን መስበክ ይቅርና ቢንሾካሾክ ከየት መጣ የማልለው ፖሊስ አንጠልጥሎኝ ሲሄድ ታያላችሁ” ሲል አስደመመን፡፡

ቀደም ሲል በኦሮሞ ውክልና በሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ ከፊል ኦሮሞ ልሂቃን፣ ምሁራን እና ንቁ ዜጎች ዘንድ ሲቀነቀን የከረመው ከ“ባህል ብሔርተኝነት” (ውጤቱ ከሁለቱም ከሚያጣቅሰው ዋቄፈና በቀር በብዛት ወደ የመሆን መብቶች ያመዝናል) ወደ የ“ፖለቲካ ብሔርተኝነት” የመሸጋገር ጉዳይ ሰፊ መሠረት ወደ መያዝ ገባ፡፡ ይኸውም እውነተኛ የፌዴራል አተገባበር፣ የተገባውን (what deserves) ድርሻ የመፈለግ—በፌዴራል መንግሥት ደረጃ ባሉ ውሳኔ የመስጠት እና የማስፈፀም ስልጣን ተገቢውን ሚና መያዝ፣ ከፈተና ያልተላቀቀውን ሀገራዊ ህልውና እና የብሔር ግንባታ ሂደት ማገዝ፣ በአጠቃላይ እውነተኛ ነፃነት፣ የሕግ የበላይነት እና የስፋኔ ፍትህ ጥማት ሁሉን አቀፍ የትግል ሽግግር እንዲያደርግ አስገደዱ፡፡
እነዚህ መሻቶች ጎምርተው ሳለ፣ ሳይደግስ አይጣላም እንዲል ያገር ሰው፣ 2007 ዓ.ል ሲባት፣ ቤንዚን አቀባይ ተገኘ፡፡ በህዝቦች ስም፣ ያለምንም ህዝባዊ ተሳትፎ እና ያለበቂ ጥናት “Master Plan” የተባለ ስመ ጥፉ ፕሮጀክት ተዋወቀ፡፡ አሁን ላይ፣ ለለውጥ ያገነገነው ቄሮ/ቄሬቲ ወግድ ከዚህ ለማለት አይኑን አላሸም፡፡

ከአመሰራረቷ ገበሬውን በማፈናቀል አሀዱ ያለችው አዲስ አበባ፣ በ33 ዓመታት ብቻ ቆዳዋን በ 143% (አንድ መቶ አርባ ሶስት በመቶ) ጨመረች፡፡ በ1953 ዓ.ል በተደረገ ልኬት አዲስ አበባ 21,800 ሔክታር የቆዳ ስፋት ነበራት፡፡ ከ33 ዓመታት በኋላ፣ በ1986 ወደ 53,014 ሔክታር ተለጠጠች፤ በ1996 ዓ.ል በወጣው የከተማዋ መሪ ዕቅድ ደግሞ የ54,000 ሔክታር ስፋት እንዳላት ተደነገገ፡፡

በህወሓት/ኢህአዴግ ዘመን ደግሞ ባሰባት፡፡ እንደሰደድ ከመስፋፋቷም በላይ፣ ያለምንም እና ያለበቂ ካሳ የሚፈናቀሉ ገበሬዎች በዚሁ ምጣኔ ሲሰፉ፣ ቀውሱ ሀገራዊ መልክ ወደ መያዝ ገባ፡፡ እስከዚህ ጊዜ ድረስ ከህወሓት የተቸራቸውን መሬት የመዝረፍ መብት (privilege) ‹ሲያጣጥሙ› የከረሙት የኦህዴድ ካድሬዎችም ህዝባዊ ነበልባሉ እየገረፋቸው መጣ፡፡ ውስጥ ውስጡን ተቃውሞ የሚያደርጉ እና ተቃዋሚውን ቄሮ/ቄሬቲ የሚያበረታቱ ካድሬዎች ብቅ ብቅ አሉ፡፡
ማስተር ፕላን ፕሮጀክቱ እኤአ ሲተዋወቅ የጅማና የሀሮማያ ዩኒቨርሲቲ ተቃወሙ፡፡

የኦህዴድ አመራሮችን ለማወያየት አዳማ ላይ በተደረገ ‹ውይይት›ም መረር ያሉ ተቃውሞዎች ተሰሙ፤ ጎላ ብለው ከወጡት ውስጥ የአሁኑ #Team_Lemma አካል የሆነው የታከለ ኡማ በንቲ ንግግር ዋናው ነው፡፡
እብሪት የህዝቡን የተቀውሞ ግለት እንዲለካ ያልፈቀደለት ህወሓት ቤንዚን የማርከፍከፍ ሚና ተወጣ፡፡ ቄሮ እየተብሰከሰከ እያለ፣ ግንጪ ከተማ አጠገብ የሚገኘው የጭሊሞ ደን በከፊል ለ‹ባለሀብት› ተሰጥቷል ተብሎ ጉዳት ማስተናገድ ጀመረ፡፡ መላ ኦሮሚያን እንደ ሰደድ የሸፈነውን ሁለተኛ ዙር ተቃውሞ የመለኮሱ የታሪክ ድርሻም የግንጪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪዎች እጅ ገባ፡፡ እኤአ ህዳር 12 ቀን 2015፡፡

ህወሓት፣ ሀዋሳ ላይ ከተደረገ ስብሰባ የተገኘ የአባይ ፀሀዬ ድምፅ ነው በተባለ ንግግር ይህንን ፕሮጀክት የሚቃወሙትን ሁሉ “ልክ እናስገባቸዋለን” ስትል እየተቀጣጠለ የመጣውን ተቃውሞ የመቆስቆስ ድርሻ ተወጣች፡፡ ቀድሞም ሲነገር የሰነበተው የእኛ እና የእነሱ ጉዳይ የማያሻማ ሆነ— በፈለኩት መንገድ አስፈፅማለሁ ባዩዋ ህወሓት፣ ልክ የሚገባው ደግሞ ኦህዴድ እና ቆሮ/ቄሬቲ ሆነው ተለዩ፡፡
***
አሁን ውጥረቱ አይሏል፤ የክልሉ መንግሥትም ሲጨንቀው፣ ህዝብ እንዲያወያዩ እና እንዲያረጋጉ አንድ ሰው ወደ ቡራዩ ላከ፡፡ ቀድሞም ከወሳኝ ኃላፊነቶች የሚገፋው ‹ለህዝብ በመወገኑ› ነው ተብሎ ውስጥ ውስጡን የሚወራለት ይህ ሰው፣ የህዝቡን ተቃውሞ ሙቀት ለመለካት ጊዜ አልወሰደበትም፡፡ “እናንተ ካልፈለጋችሁ ማን [አባቱ] ይጭንባችኋል! ካልፈለጋችሁ ይቀራል” ሲል የከተማዋን ነዋሪ ባንዴ ማረከ፡፡ ይህ እለትም፣ በከተማዋ ሳይወሰን፣ የኦሮሚያን ጉዳይ በሚከታተሉ ሰዎች ሁሉ ዘንድ #ለማ_መገርሳየተባለን ተራማጅ ኦህዴድ ወለደ፤ በኦህዴድ የተላላኪነት ታሪክ የታሰሩ ‹ተቃዋሚዎች› ሳይቀሩ፣ ቢያንስ “እስኪ እንየው!” ለሚል ጥርጣሬ ተዳረጉ፤ የሙክታር ከድር መንግሥትም፣ ይኸኑ ተራማጅነቱን በማየት ስራ አስፈፃሚ እንኳ ሳያደርግ መዶሻ አቀብሎ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባኤ እንዳደረገው የሚሰማው ሹክሹክታም ጮክ ተብሎ የሚነገር ‹እውነት› ሆነ፡፡

ሰደዱን የማያንቀላፋ በማድረፍ ቴክኖሎጂ-ማህበራዊ ሚዲያ፣ የሳተላይ ቴሌቪዥን-ኢሳት፣ ኦ.ኤም ኤን፣ የተለያዩ ተሟጋች ግለሰቦች፣ ጀዋር መሀመድ … የነበራቸውን ሚናም በየቦታቸው እናነሳለን፡፡

ከሁለት አመታት ወዲያ፣ ኦህዴድ “ነፃ ድርጅት ነኝ” ስትል ትከራከር ነበር፡፡ አሁን የአደባባይ እውቀት ሆኖ ማንም አልፎ ሂያጅ ምስክርነት የሚወጣው፣ ኦህዴድም የማትክደው ቢሆንም፣ ማስመሰሉን፣ ስርዓቱም የአንዳንድ ኦሮሞ ሰዎችን የፊት ጭምብል ተውሶ በማጥለቅ አግዟቸው ነበር፡፡ በውጤቱም ጥቂት የማይባሉ ልሂቃን፣ ምሁራን፣ ተሟጋቾች ግለሰቦች እና ድርጅቶች፣ ተመራማሪዎች፣ አበዳሪ ሀገራት … ማታለል ችሎ ነበር፡፡ እውነቱ ግን ኦህዴድ የተተወላት ነገር ቢኖር የውሳኔ ስልጣን ሳይሆን ዘረፋ ነበር፡፡ ተደማሪ ውጤቱ የሙክታር ካድርን ኦህዴድ አላላውስ ይላል፤ ይሄኔ ስራ አስፈፃሚው-ጫፌ ኦሮሚያ ለማ መገርሳ እጅ ላይ ጣላት፡፡

ለማ ጊዜ ሳያባክን በሙክታር ዘመን ቆሞ ቀርነት ላይ ሲያጉረመርሙ የነበሩ ወጣት እና ተራማጅ ሰዎችን ያቀፈ ከቢኔ አዋቀረ፤ በተለያዩ ኃላፊነቶች ላይ ቆይተው በተለመደው የኦህዴድ ባህሪ፣ የለውጥ ሂደቱን ማደናቀፍ የቀጠሉትን እንደ በከር ሻሌ አይነቱን በትምህርት እና በሌሎች ምክንያት ከቦታውም ከአከባቢውም አራቀ፡፡ “ጌታችን ህዝባችን” ነው ሲል የቅቡልነት ዕጦት ነቀርሳ የሆነባቸውን ጉዳይ መድፈር ጀመረ፡፡ በመቀጠል “የኢኮኖሚ አብዮት” የሚል እንቅስቃሴ በማድረግ፣ ቀደም ሲል ከፍተኛ ተቃውሞ በሚያቀርቡ አከባቢዎች የፋብሪካ ግንባታ ፕሮጀክት ማስተዋወቅ እና የመሠረት ድንጋይ መጣል ጀመረ፤ በሰው አእምሮ የነበረው የህወሓቱን ኢፌርት መገዳደር በመሆኑ ተደነቀለት፡፡

Team_Lemma ወርቅነህ ገበየውን (ዶ/ር) በማለሳለስ፣ አባ ዱላ የሚያሳድደውን የምርኮ ታሪኩን እንዲዋጋ እና መለስ ዜናዊ የሸረበበትን ከኦሮሚያም ከፌዴራል መንግስቱም ነቅሎ የማንሳፈፍ ሴራ እንዲበቀል ዕድል በማመቻቸት፣ በተራው የተለመደውን የማረጋጋት እና የማሸማገል ኃላፊነት ተወጥቶ እውቅና እንዲያተርፍላቸው ከፍ ከፍ አደረጉት፡፡ ከፌዴራል መንግሥት ኃላፊነቱ እንደሚለቅ እስከመናገር ደፈረ፡፡
ሌሎች ህዝባዊ ድጋፍ ያስገኙላቸውን ሁነቶች አለፍ አለፍ ብለን እንጥቀስ፡-

ኦሮሚያ ቴሌቭዥን በስም ወደ ኦ.ቢ.ኤን (OBN) ከመቀየሩም በላይ አብዮቱን በሚያራግበው ኦ.ኤም ኤን (OMN) ፎርማት ተቀረፀ፤ የክልሉ የመንግሥት ቃል አቀባይ Adisu Arega Kitesa አዲሱ አረጋ፣ በማህበራዊ መገናኛ በኩል ያደረገው ወደ ህዝብ የመቅረብ፣ ደፋር የድርጅቱና የግሉ ውሳኔዎች እና አተያየቶች የማድረስ ተግባራት፣ “ኦህዴድ ህወሓትን አሻፈረኝ እያለ ይመስላል” የሚለው ሀሳብ እንዲንሸራሸር አገዘ፡፡ የፓርቲ ዲሲፕሊን አዲሱን ሲሸብብ Dereje Gerefa Tulu ያፍረጠርጠዋል፡፡

ኢምቦጭ ለማረም ወጣቶችን ወደ ባህርዳር በመላክ ያደረጉት ተምሳሌታዊ ተግባር እና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ለመፍጠር ነው ተብሎ ወደ አማራ ክልል የተደረገው ጉዞ እና የለማ ንግግር በአማካይ እና በቀኝ ክንፍ አሳቢዎች ዘንድ ተቀባይነት አስገኘለት፡፡ አስገኘላቸው፡፡

ህወሓት በኦነግነት ፈርጃ ስታሰቃያቸው ከነበሩት እንደ Taye Dende’a አይነቱን ሾመ፤ 17 ቀናት የፈጃው የኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ ስብሰባ ተከትሎ፣ የግንባሩ ድርጅቶች አራቱ ሊቃነመናብርት በጋራ የሰጡትን መግለጫ ተከትሎ ለማ መገርሳ ተቀባይነቱ እጅግ ከፍ አለ፡፡ በዚህ ተግባራቱ የህወሓት ደጋፊዎች- Daniel Birhane ኦህዴድን ማውገዝ መያያዛቸው ለውጡ እውነተኛ ነው ለሚለው ተጨማሪ አስረጂ ሆነ፡፡ በሶማሌ ክልል እና አዋሳኝ አከባቢዎች ይኖሩ የነበሩ ኦሮሞዎች ላይ የደረሰው የአካል ጉዳት፣ ሞት እና በመቶ ሺዎች መፈናቀል የህወሓት የእጃዙር ጦርነት ተደርጎ መታመኑ በኦህዴድም ሆነ በኦሮሞ ዘንድ አንድነትን አጠናከረ፤ የተፈናቃዮቹ በአዲስ አበባ ዙሪያ መስፈር እና የህወሓትን የህዝብ ስብጥር የመለወጥ ፕሮጀክት ማክሸፍ ሌላ ድል አስገኘላቸው፡፡

በኦሮሚያ ልዩ ዞን ከተሞች በብዛት የተሾሙት ሴት ከንቲባዎች ያሳዩት ቁርጠኝነት፣ ህወሓትን እና ወታደራዊ ኃላፊነታቸውን ተገን አድርገው ሀገሪቷን በህገ ወጥ ንግድ የሚያምሱ ተጋሩ ፊት ለፊት መረር ብሎ መቆም፣ የኦሮሚያ ፖሊስ ህዝባዊ ወገንተኝነት፣ የኦህዴድ ከኢሬቻ እጁን መሰብሰብ፣ የህ/ተ/ም ቤት በጠራው ህዝባዊ ውይይት ላይ #Team_lemma ያሳየው ቁርጠኛ አቋም እና ስብሰባውን መበተን (Shimelis Abdisa እና አዲሱ አረጋ በአብነት) እና ህወሓት አደጋ ላይ የወደቀ ህገ ወጥ ጥቅሟን ለማስጠበቅ በወጠነችው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በምክር ቤት ከክልሉ የተወከሉ አባላት ያሳዩትን ተቃውሞ መጠቃቀስ ይቻላል፡፡

ከገደብ ያለፈው የቀኙ ኃይል ውግዘት እና ውጤቱ
ጀዋር ሲራጅ መሀመድ

Jawar ሲራጅ መሀመድ ቀደም ብሎ ተወልዶ ነበር፤ ዋነኛ ትኩረቱን የኦሮሞ ጉዳይ አድርጎ በኢትዮጵያ እና በአፍሪካ ቀንድ ላይ በሚሰጣቸው አስደማሚ አስተያየቶቹ ይታወቃል፡፡ ስለወቅታዊ ጉዳዮች ፖለቲካዊ ትንታኔዎችን እንደዋዛ ያሚያዥጎደጉድ አፍላ ወጣት ነበር፤ ቀስ በቀስ በኦነግ የቆዩ አመራሮች የተያዘውን የዲያስፖራ አየር መሰንጠቅ ገባ፤ በሀገር ውስጥም እየታወቀ መጣ፤ እኔም አንድነት ፓርቲ በየሳምንቱ እሁድ በሚያዘጋጀው ትምህርታዊ ውይይት ላይ ስለሰላማዊ ትግል በስካይ ፒ ትንታኔ እንደሚሰጥ ከጋዜጣ አንብቤ ለመጀመሪያ ጊዜ ሰማሁት፡፡ የቀጭን ድምፁን አይመቼነት በአፍዛዥ መልዕክቱ ሻረው፤ የለቱ ማስታወሻ ዛሬ ድረስ በእጄ አለ፡፡
ጀዋር ድንግዝግዙን የኦሮሞ ጉዳይ ብርሃን እየረጨ ለመውጣት ያለፈባቸውን አንዳንድ አብነቶችን አለፍ አለፍ እያልኩ በጥቂቱ ላንሳ፤

እንደአብዛኛው ኦሮሞ ጀዋር በቀደሞው የኦሮሞ ትግል ላይ ተስፋ ማድረግም፣ ተስፋ ማጣትም ነበረው፤ እሱ በሚኖርበት፣ ዲያስፖራው ዘንድ ቦታ የነበረው ኦነግ ነበር፤ ጀዋርም በድርጅቱ ላይ ተስፋ ከማድረግ ወደ ማጣት ሲደርስ ዝም አላለም፤ እኤአ በ2009 “FAILURE TO DELIVER: THE JOURNEY OF THE OROMO LIBERATION FRONT IN THE LAST TWO DECADES” በሚለው ትንታኔያዊ ትችቱ መነጋገሪያ ሆነ፤ ጭብጡን መጭመቅ ከተቻለኝ ልሞክር፡፡ እኤአ በ2001 ላይ ኦነግ “Transitional Authority” እና “Shanee Gumii” በሚባሉ እርስ በርስ የሚወነጃጀሉ አንጃዎች ተከፈለ፤ የለውጥ ኃይል ነኝ ብሎ የወጣው አካል በበኩሉ እኤአ በ2008 እንዲሁ ለሌላ መሰንጠቅ መንስኤ ሆነ፤ በየጊዜው በሚያጋጥሙ መሰነጣጠቆች የርዕዮተ አለም ልዩነቶች እና አከባቢያዊ መቧደን ዋነኞቹ መንስኤዎች ተደርገው ቢነገሩም፣ ጀዋር የቀውሱ ሁሉ ምንጭ “ውጤት አልባነት” ነው ሲል ደመደመ፡፡ በከፍፍሉ የተነሳ በአንድ ቤተሰብ አባላት መካከል እንኳ የጎራ ልዩነት እየተፈጠረ፣ በምንም የማይለያይ ቤተሰብ፣ በዚህ ፋይዳ ቢስ ድርጅት መለያየት እንደሌለበት አሳሰበ፡፡

(በርግጥ መሳይ ከበደ (ፕ/ር) “The OLF: Ideological or Leadership Buncraptcy?” ሲል Sep. 2009 ላይ በጀዋር ትንታኔ ላይ ትችት አቅርቧል፤ መሳይ “Jawar criticizes everything except the most important issue, namely, ideological guidance of the OLF” ይላል፤ የምጋራቸው ሀሳቦች አሉት፡፡

ሊጠገን ከሚችለው በላይ ሄዷልና ተስፋችሁን ሙሉ በሙሉ ከዚህ ብላሽ ስብስብ አንሱ ብሎ ወደ ሌላ የትግል ስልት እንዲያማትሩ ቀሰቀሰ፤ ላካ አንድነት ፓርቲ ያቀረባቸው የትግል ስልቶችን አማራጭ አድርጎ ወደ ስራ ለመግባት እየተንደረደረባቸው ኖረዋል፡፡

በቀጣዮቹ ጊዜያት የተለያዩ ብርቱ ስራዎችን ሲያከናውን በመቆየቱ ከኦነግ ውጪ ሌላኛው ተዋስኦ በጀዋር መወከል ጀመረ፡፡ June 2013 አልጀዚራ ቴሌቭዥን ላይ የሚቀርበው AJStream ስለኦሮሞ እንዲናገር ጋበዘው፤ አዘጋጇ በመሀል“Are you Oromo first or Ethiopia first” ስትል ጥያቄ አቀረበችለት፤ ጀዋር ሳያቅማማ “I’m Oromo first” ሲል መለሰ፡፡ ይህ መልስ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ተከታታዮች መካከል ግዙፍ ስምጥ ፈጠረ፤ ጀዋር በሚናገርላቸው ዘንድ አብሪ ኮበብ ሆኖ ወጣ፤ በተቃራኒ ያሉት ሰይጣን አድርገው መተረክ ተያያዙ፡፡ በአጠቃላይ የጀዋር ‹አወዛጋቢነት› ከፍ አለ፡፡

ምናልባት የአፍ ወለምታ እንዳይሆን በሚል ይመስላል የተለያዩ ቲዩቦች፣ (ለምሳሌ EthioTube) ይህንኑ ጥያቄ አቀረቡለት፤ ረገጥ አድርጎ አረጋገጠ፡፡ ይሄኔ በአንድ ወገን ሰውን ከኦነግ ተስፈኝነት አውጥቶ ሌላ ተስፋ የሰጠ መሲህ ሆኖ ሲወሰድ በሌላ ወገን የኢትዮጵያ አንድነት አደጋ ተደርጎ ተሳለ፡፡

በሌላ ጊዜ ባደረገው ንግግር በትውልድ አከባቢው ያሉ ክርስቲያኖች እንኳን ሊጨቁኗቸው ቀርቶ ቀና ብለው ቢሄዱ በሜንጫ እንደሚሏቸው ተናገረ ተብሎ የቀኙ ኃይል ውርጅብኝ ወረደበት፤ ከልክ እስኪያልፍ፡፡ በውግዘቱ የቀኝ እሳቤ የሚያመዝንባቸው እንደ ኢሳት ዓይነቶቹ ሚዲያዎች በነበራቸው ከፍ ያለ ተሳትፎ የኦሮሞን በደል፣ መሻት እና ርዕይ የሚያሳይ አማራጭ ሚዲያ እንደሚያስፈልግ አመነ፡፡ በዚሁ መጠን፣ በሌላ ወገን ያለው ደግሞ፣ ጀዋርን በመከላከል ሂደት ተሰልፎ ሙሉ በሙሉ አገዘፈው፡፡

እንዳለውም፣ እኤአ March 3 ቀን 2014 OMN ኦሮሚያ ሚዲያ ኔተዎረክ የተባለ አማራጭ ሚዲያ ተመሰረተ፡፡ በምስረታው ሂደት የአንበሳ ድርሻ የነበረው ጀዋር ሲራጅ መሀመድ ዳይሬክተር ሆኖ ተመረጠ፡፡ አንደበተርቱዕ እና ፈጣኑ ጀዋር አሁን ሀሳቡን ያለገደብ የሚያደርስበት መንገድ አገኘ፤ የማትጋፋው የኦሮሞ ጉዳይ ተንታኝ፣ የመብት ጠበቃ እና የተቃውሞ ስትራቴጂስት ሆነ፡፡

በዚሁ ዓመት ኢህአዴግ ከፍተኛ ስህተት ሰራ፤ በህገ መንግስቱ አንቀፅ 49 ላይ ቢደነገግም፣ ኦሮሚያ ክልል ከአዲስ አበባ ላይ ያለው ልዩ ተጠቃሚነት ለ20 ዓመታት ዝርዝር ወጥቶለት ያለመተግበሩ ከፍ ያለ የተቃውሞ ምንጭ መሆኑ ቢታወቅም፣ እብሪተኛው ህወሓት፣ እኤአ በ2014 ሌላ የ‹አዲስ አበባ›ን አይጠቅቤነት የሚያሳይ አጀንዳ ይዞ ከተፍ አለ፤ ማስተር ፕላን፡፡


ወዲያው ነበር ተቃውሞ የቀረበበት፤ ጀዋርም በዚሁ አመት “Fight or perish” ባለው ሀሳቡ “The only asset the Oromo people used to have was land. Now that is being taken away at lightening speed. Therefore the Oromo got NOTHING left to loose.” ሲል አሳሰበ፡፡ ክፍል ሁለት ላይ ስለታደሰ ብሩ ስናነሳ “እርሱ ግን የምኒልክ ወራሽ በሆነው የወቅቱ አገዛዝ ላይም እንዲነሳሱ፣ መሬታቸውን እንዳይለቁ፣ መሬታቸው ላይ እንዲሞቱ ይመክር ነበር” ካልነው መሳ ለመሳ መጣ፡፡ ቄሮ በበኩሉ “lafaaf lafee” ሲል በአባቶቹ ብሂል አሳጠረው፡፡ “የለመሬት እና ያለአጥንት አይቆምም” የሚል የቃል በቃል ትርጉም አለው፡፡

OMN ኢትዮጵያ ውስጥ አየር ላይ በቆየባቸው ጊዜያት፣ የቄሮን መረዳት በማቀራረብ፣ ባንዱ የክልሉ ጫፍ የሆነው ሁሉ ወዲያው ወደ ሌላኛው ጫፍ በማድረስ፣ ኦሮሞነትን እና እሴቶቹን በማስታወስ ልዩ ድርሻ ነበረው፡፡

ጀዋር መሃመድ፣ ለሚዲያ ተቋሙ ገንዘብ ለማሰባሰብ በሚጓዝባቸው ቦታዎች ሁሉ ኮርኳሪ ንግግሮችን በማድረግ፣ ምልምል ተቃዋሚዎችን ከመማረኩም በላይ፣ ቋሚ ኮሚቴዎችን በማደራጀት፣ ባልተለመደ ሁኔታ ምሁራንን፣ ልሂቃንን፣ ቴክኖክራቶችን፣ አቀንቃኞችን በዚህ አላማ ዙሪያ ለመሰብሰብ ችሏል፡፡

አሁንም ሌላ ስህተት ከህወሓት፡፡ ማስተር ፕላኑን ተከትሎ በመጣው ከፍተኛ ያለመረጋጋት፣ ኦሮሚያ አካባቢ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች በብዛት ተቋርጠው ነበር፤ ሆኖም፣ የሀገሪቷ የትምህርት ሚኒስቴር የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና በተለመደው ጊዜ እንደሚደረግ አሳወቀ፤ ቄሮ/ቄሬቲ፣ OMN እና በጀዋር የሚመራው የአቀንቃኞች ቡድን ጊዜው እንዲራዘም ወተወቱ፤ በተቃራኒው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቃሉ ፀና፡፡ ቀናት ሲቀሩት ማስጠንቀቂያ ከጀዋር በኩል ደረሰው፤ መስሪያ ቤቱ እስከፈተናው ቀን ድረስ ተረጋጉ በሚለው መልእክቱ ፀና—“… ፓንትሽን አውልቂ አለኝ፣ ምንም አልተረጠርኩም …” እንዳለችው ልጅ፡፡ ጀዋር ቀደም ሲል በእጁ ያስገባውን ፈተና “ኦሮሞ ተለይቶ መጠቀምም ሆነ መገለል የለበትም” በሚል መርህ በኢንተርኔት አሰራጨ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱም አሻፈረኝ ያለውን ጊዜ እንዲያራዝም አስገደደው፡፡ አሁን ጀዋር እንደኦሮሞ መብት አቀንቃኝ ያማያወላዳ ቅድምና አለው፡፡
2017 ሙሉ በሙሉ ጊዜውን በኢንተርኔት ላይ አደረገ፡፡ በኦሮሚያ ከጫፍ እስከ ጫፍ በየአከባቢው የተደራጀው Qeerroo_Qarree መረጃ ወደ ጀዋር ቋት፣ እሱ በበኩሉ ለመላው ማህበረሰብ ማድረስ ተያያዙ፤ ቄሮ/ቄሬቲ የስርዓቱን ሽርፍራፊ ገመናዎች ሳይቀር በአፈ ቀላጤው በኩል አደባባይ ላይ አሰጣ፡፡ ከየአቅጣጫው የተቃውሞ ስትራቴጂ አማራጮችን ወደ ቋቱ የሚልከው ቄሮ/ቄሬቲ፣ ጀዋር አለስልሶ ያቀብለው ቀጠለ፡፡ መንገዶችን በመዝጋት፣ ከንግድ በመታቀብ፣ እቤት ውስጥ በመዋል፣ ነዳጅ ከውጪ እንዳይገባና ሀገር ውስጥ እንዳይንቀሳቀስ በማድረግ የተካሄዱትን ስኬታማ ተቃውሞዎች ያለእረፍት እንደመረጃ ቋት በማገልገል ከፍተኛ ኃላፊነት ተወጣ፡፡ የጫናው ብዛት እስረኞችን ከማስፈታት ጀምሮ ጠ/ሚኒስትሩን እስከማስለቀቅ ደረሰ፡፡

በዚህ ወቅት ጀዋር ክፉኛ የሚተችበትን አንድ ነገር ቀየረ፤ የክልሉ እንቅስቃሴ ብቻ ከማገዝ ቀጥቶ፣ በሌሎች ብሔር ብሔረሰብ አካባቢ ላሉ የለውጥ አንቅስቃሴ ትኩረት ሰጠ፤ እንዲታገዝም ሀገራዊ ጥሪ ማቅረብ ጀመረ፤ Nov. 17, 2017 ደግሞ “The Oromo Alternative፡ Freedom, Equality, Justice and Dignity in a Participatory Democracy” በሚል ርዕስ ከኢዝቂኤል ገብሳ (ፕ/ር) ጋር በፃፉት ትንታኔ እንዳኖሩት፣ ኦሮሞ ለኢትዮጵያ የሚያቀርበው አማራጭ፣ ተሳትፎን ካረጋገጠ ዴሞክራሲ የሚመነጭ ነፃነት፣ እኩልነት እና ፍትህ መሆኑን አፀኑ፡፡

(ጀዋር March 20, 2018 በ4ኛ አመቱ AJStream ላይ ተጋብዞ ሲቀርብ ግን ተቺዎቹ ተጋሩ ብቻ ይመስሉ ነበሩ፡፡)

የካቲት 23 ቀን 2010 ዓ.ል የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አላማ እና የድምፅ ቆጠራ ሂደቱ የፈጠረው ክፍተት ሌላ ዙር ከባድ ተቃውሞ ሲቀሰቅስ Jawar Mahamod Siraj “ካህንዬ የነፍሴ አገልጋይ፣ እንቅልፍ አትተኛም ወይ” የሚለውን አዘመረ፡፡

በአጠቃላይ ጀዋር 
1. 1.3 ሚሊየን የፌስ ቡክ ተከታይ ያለው፣
2. ሁነቶችን መጠቀም የሚችል፣
3. ለማቀንቀንም ሆነ ለጥልቅ ትንታኔ የሰላ አዕምሮ ያለው፣
4. ብዙ ኃይል በዙሪያው እና በኦሮሞ አማራጭ ላይ የሰበሰበ፣
5. የማያንቀላፋ/አይደክሜ ብርቱ ታጋይ ነው፡፡

ውለታው ከባድ ነው፡፡ ከነጓዶቹ፡፡
ታዲያ እንዳትስቱ፤ ጀዋር ጥንካሬው ብቻውን ኢምንት ነው፤ የሚነድ ሳይኖር እሳት ቆስቋሽ ብቻውን አይፈይድም፤ የጀዋር ስም፣ የጀዋር ዝና፣ የጀዋር ጉልበት፣ የጀዋር ታታሪነት ከቄሮ ሞት አይፈሬነት ጋር ተዳምሮ ፍሬ የሚሰጥ ነው፣ የጀዋር ሁለንተና  ቄሮ ቄሬቲ ነው፡፡

ታዲያ እንዳትስቱ፤ ጀዋር መልአክ አይደለም፤ ስህተቶች/ድክመቶች ነበሩበት፤ ስለእነዚህ ጉዳዮች ትግሉ ከቅልበሳ ድንበር ሲወጣ እንነጋገራለን፡፡ ራሱም ይተርክልናል፡፡
ከዚህ እጅግ አድካሚ፣ አሳማሚ እና አሰልቺ ስራ ጡረታ የሚወጣበት ጊዜ ቅርብ እንዲሆን እመኛለሁ፤ ወደ ምሁራዊ ትንታኔው፣ ወደ አካዳሚክ ትምህርቱ ይመለስ ዘንድ፡፡
ወደ ሀገሩ ኢትዮጵያ በቅርቡ ይመጣ ዘንድ፡፡
አሜን! ጀዋር መሀመድ ሆይ ወደ ኢትዮጵያ ቶሎ ና!
***
እንዲሁ፣ እንዳትስቱ፤ የኦህዴድ ወደ ኦሮሞ ማዘመም የዚህ ሁሉ ምራቂ ናት!! ምራቂ iii—!!!!
የጀዋር ስኬት፣ የአብይ አህመድ (ዶ/ር) ምርጫ እና ሹመት ጨምሮ ባለፉት ሶስት አመታት የሆነው ሁሉ፣ በዋናነት የቀሮ/ቄሬቲ ውጤት ነው፡፡
ምክንያቱም፣ ይህ ይመጣ ዘንድ፡-
በተቃውሞው፣
1. በሰልፍ፣ በድንበር አካባቢ ችግር እና በእስር ቤት ከ5000 ያላነሱ ታጋዮች ወድቀዋል፡፡
2. ከ20000 የማያንሱ ታጋዮች ቆስለዋል፡፡
3. 150000 በላይ የሚሆኑት የእስር ቤት ደጃፍ ረግጠዋል፤ የወጡና እዚያ የተቆለፈባቸውን ጨምሮ፡፡
4. ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ከቤት ንብረት፣ ከቀዬ እና ትዝታቸው ተነቅለዋል፡፡

እኔም የኦሮሞን ትግል “ከማሻሻያ፣ አመፃ እስከ አብዮት” የተጓዘ ነው የምለው በነዚህ ምክንያቶች ነው፡፡

ደረጃ ስድስት
እጃችን ከምን?

1. የዚህቺን ሀገር እምብርት ማስታወስ ተምሳሌታዊ ነው፤ የሆራ አርሳዲ እንደተጠበቀ ሆኖ ሆራ ፊንፊኔ ላይ ኢሬፋና ማድረግ አስፈላጊ ነው፡፡ በቀጣዩ መጀመር፡፡
2. በዘመናዊ የኦሮሞ ታሪክ ውስጥ ሜጫና ቱላማን የሚፎካከር ተቋም የለም፡፡ የተዘጋውም በስርዓቱ ህገወጥነት ነው፡፡ አሁን መከፈት አለበት፤ ካሁኑ እንቅስቃሴ፡፡

ለማህበሩ መመስረት፣ ማደግ እና አስተዋፅኦ ማበርከት የየአገዛዙን ገፈት የቀመሱ ኑሯቸውን እና ህይወታቸውን የሰው ተለይተው መታሰቢያ ሊቆምላቸው ይገባል፡፡ የግድ ሀውልት አይደለም፡፡

 ታደሰ ብሩ በንጉሱ መንግስት ስር የፊደል ሰራዊት ዘመቻን መርቷል፡፡ በማህበሩም የትምህርት ኮሚቴን መርቶ ስኬታማ ሆኗል፡፡ አሁን ታዲያ የእውቀት ማዕከል እና የልሂቃን ማፍሪያ (ኦህዴድ በፊንፊኔ ከጀመረችው በላቀ) በስሙ አያስፈልግም?
 አቶ ኃይለማርያም ጋማዳ በሙያው ጠበቃ ነበር፤ ለማህበሩ መጎልበትም፣ ለዜጎች ፍትህም ጥብቅና ቆሟል፤ አሁን በተራችን በስሙ የህግ ጉዳዮችን የሚያሰለጥን እንዲሁም ለፍትህ መረጋገጥ ነፃ የጥብቅና አገልግሎት የሚሰጥ ተቋም አያስፈልግም?
 በኮሎኔል አለሙ ቂጤሳ ስም የአመራር ማሰልጠኛ፣

 በኦሮሞ ትውፊት ክምችቱ ድርቢ ደምሴ ስም የጋዳ ስርዓት እና የኦሮሞ ትውፊት የሚያጠና ተቋም አስፈላጊ ነው፡፡

3. ዋቄፈታ የእምነት ነፃነቱ ሊታወቅ እና የቀብር ስፍራ ሊሰጠው ያስፈልጋል፡፡
4. የጋዳ ስርዓት ማዕከላት ማንሰራራት አለባቸው፡፡ ኦዳ ናቤ (ከ1115 ጀምሮ)፣ ኦዳ ሮባ (ከ1315 ጀምሮ)፣ ኦዳ ቡልቱም ወዘተርፈ፡፡
5. ባለፉት ሶስት ዓመታት ውስጥ በየአካባቢው (በሀገር ውጪ ጨምሮ) ተምሳሌታዊ ሚና የነበራቸውን ቄሮ-ቃሬ መዘከር፡፡
6. ተቃውሞውን በማፈንዳት የአብሪነት ሚና የነበራቸውን (2014 ሀሮማያና ጂማ ዩኒቨርሲቲዎች፣ 2015 ግንጪ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት፣ አምቦ) ማስታወስ፤ ጉብኚት መዳረሻ ማድረግ፡፡
7. “የሆነ ቦታ ያለ ኢፍትሃዊነት፣ የትም ያለ ኢፍትሃዊነት ነው” እንዲሉ ቄሮ-ቃሬ በማንም ግለሰብ/ህዝብ ላይ የተቃጠን አደጋ ያለልዩነት ያወግዛል፣ ይዋጋል::