April 9, 2018

አብዛኛው ካልሆነም ደግሞ መላው የኢትዮጵያ ህዝብ ለማለት በሚያስችል ሁኔታ  ከራሱና ክልጆቹ በላይ አገሩን ይወዳል በሚል ቢቀመጥ ማጋነን የሚሆን አይመስልም። የዚህ ህዝብ መከበሪያዉም፣ መኩሪያውም፣ አለኝታውም  ኢትዮጵያዊነቱ  እንደሆነ  ሲናገር ዉሎ ሲናገር ቢያድር የሚሰለች አይደለም። አለመሰልቸት  ብቻ ሳይሆን ውድ ህይወቱንም አሳልፎ ይሰጣል።  ለዚህም ነው የውጭ ሃይሎች ሊወሩን  በሞከሩባቸው ጊዚያት ሁሉ  እያንበረከከ ወደመጡበት እንዲመለሱ ሲያደርጋቸው የነበረው። ይህን ጉዳይ አይደለም ተንበርክከው የተመለሱት እንደ ሻዕብያ፣ ጣሊያን እና ድርቡስሽ የመሳሰሉት ይቅርና  ሌላውም የአለም ክፍል ሳያቅማማ የሚመሰክረው ሃቅ ነው። በዚህ ረገድ ሮም ላይ ኢትዮጵያን የሚያኮራ ገድል የሰራውን ጀግና -አብዲሳጋን ይስታውሷል።

ይሁንና የናት ሆድ ዥንጉርጉር እንደሚባለው የአባቶቻችን ብሂል ሁሉ እነአቶ መለስ ዜናዊ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እንዲደፈቁ የፈፀሙት በደል ቀላል አልነበረም።  እነ አቶ መለስ ኢትዮጵያን እንደ እስር ቤት እንጂ እንደ የማንነት መገለጫቸው አድርገው ይመለከቷት ስላልነበረ  አይደለም ኢትዮጵያዊነትን  ሊያጎለብቱ የሚችሉ ስራዎች  መስራት  የኢትዮጵያችን ስም እንኳን “ያች/ይህች አገር” ከሚል በዘለለ በወጉ ለመጥራት እንኳን ሲተናነቃቸው ማየት የተለምደ ሂደት ነበር። እንዲያዉም ባንድ ወቅት አቶ መለስ በግልፅ የነገሩን ከሁሉም በላይ የሚያስደስታቸው ነገር ወርቅ  ከሆነው ከክልላቸው ህዝብ መፈጠራቸው እንጂ ኢትዮጵያዊ መሆናቸው አልነበረም። አቶ መለስ ሲያስፈልጋቸው ደግሞ ኢትዮጵያዊነት ሰው ሲፈልገው የሚያጠልቀው እንጂ ተገዶ የሚጎናፀፈው ካባ ሊሆን አይገባም ይሉን ነበር። በርግጥ ይሄ አባባል በግርድፉ ሲያዩት ትክክል ሊሆን ይችላል። ይሁን እንጂ እርሳቸው እንዲህ አይነት ንግግር በሚያደርጉበት ጊዜ ኢትዮጵያዊነትን ምን ያህል ንቀውና  አቃለው እየተመለከቱት እንደሆነ መገንዘብ ይሳናቸዋል ብሎ ለማሰብ ይከብዳል። አቶ መለስ እንደ ሃገር መሪ ለኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ክብደት ሰጥተዋቸው ቢሆን ኖሮ  የዚህ አይነት ግዴለሽ ንግግር አያደርጉም ነበር። የብሄር ብሀረሰቦችና ህዝቦች መብት  መከበር ያለበት መሆኑን አፀዕኖት ለመስጠት ፈልገው ከነበረም ከአንድ የሃገር መሪ የማይጠበቅ የዚህ አይነት ሓላፊነት የጎደለውና ግዴለሽ የሆነ ንግግር ከሚያደርጉ ቁምነገሩን በሌላ ሓላፊነት የተሞላበት መንገድ ሊያስረዱን በተገባ ነበር።

ኢትዮጵያ ግን ማህፀኗ  የተባረከ ነውና አሁን ደግሞ ለሃያ ሰባት አመታት ስንናፍቃቸው የነበሩትን  ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚዘምሩ ልጆቿ ብቅ ብቅ እያሉ ያሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከነዚህ የኢትዮጵያ ልጆች አንዱ የሆኑት ደግሞ ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር አብይ አህመድ ናቸው። እኝህ ሰው የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊነትን ክብር አስፈላጊነት መግለፅ የጀመሩት ገና ወደ ጠቅላይሚንስትርነት ቦታቸው ከመምጣታቸው በፊት ነበር። በዚህ ረገድ ባንድ ወቅት “We do not inherit the earth from our ancestors; we borrow it from our children “የሚለውን የአሜሪካኖች አባባል ተውሰው (ምንም እንኳን እርሳቸው እንደተዋሱት ባይነግሩንም) ኢትዮጵያችን “ከአባቶቻችን የወረስናት ሃገር ሳትሆን ከልጆቻችን የተዋስናት ሃገር ነች፡ ስለዚህ ተንከባክበን፣ በደንብ ጠብቀንና አስውበን ለልጆቻችን መመለስ ይኖርብናል” ብለው  ነበር።

ዶ/ር አብይ ጠቅላይ ሚንስትር ከሆኑ በኋላ ደግሞ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያዊነት ካፋቸው የሚጠፉ ቃላት አልሆኑም። ሁሉም እንደሰማው እኝህ ሰው የበዓለ-ሲመታቸውን ንግግር ሲያደርጉ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን  ከሃያ  በላይ ጊዜ ጠርተዋል። በኋላ ላይ ባደረጉት  የኢትዮጵያ ሶማሊ ብሄራዊ ክልላዊ መንግስት ጉብኝታቸው ወቅትም ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት የሚሉት የተከበሩ ቃላቶች ካፋቸው አልተለዩም ነበር። ዶ/ር አብይ ብቻ ሳይሆኑ በዙሪያቸው ያሉ ጓዶቻቸውም ጭምር ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነትን እንደዜማ ሲያቀነቅኑት እየሰማን ያለንበት ወቅት ላይ ደርሰናል። ሁኔታው  ይበልጥ የሚያስደስተው ደግሞ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እየተቀነቀኑ ያሉት “ሲፋቁ ኦነግ” ናቸው  እየተባሉ ስላቅ ሲነገርባቸው ከነበሩት የኦህዴድ (OPDO) አባላት ዉስጥ  በወጡ መሪዎች መሆኑ ነው።  በዚህ ረገድ ሩቅ መንገድ መጓዝ ሳያስፈልገን አቶ ለማ መገርሳ የተናገሩትን ማስታወስ ብቻ በቂ ነው። እንደ አቶ ለማ አባባል ኢትዮጵያዊነት “ሱስ” ወይም “ሓሽሽ” ነው። አቶ ለማ ቀጥለውም ሲናገሩ ኢትዮጵያን ማንም ተነስቶ ሊበትናት፤ ማንም ተነስቶ ሊሰበስባት የምትችል ሃገር አይደለችም። አቶ ለማ  አክለውም  ኢትዮጵያዊነት በደምና በታሪክ የተሳሰረ በቀላሉ ሊፈርስ የማይችል ልዩ መለያ እንድሆነ አስረዱን።

እንዚህንና መሰል ሁኔታወችን በማየት ነው እንግዲህ እውነት እነ አቶ መለስ የደፈቋቸውን ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት እነ ዶ/ር አብይ እንዲያንሰራሩ ያደርጓቸው ይሆን የሚል አወንታዊ (positive) እና የደስታ ስሜት የሚጭር ጥያቄ ለማንሳት አስገዳጅ ሁኔታ የተፈጠረው። በርግጥ ከልብ መሆንና አለመሆኑን ደግሞ በቀጣይ ተግባሮቻቸው ልናይ እንችላለን ብለን ተስፋ እናደርጋለን።