#ወልቃይት ጠገዴ #ታምራት ላይኔና #ያሬድ ጥበቡ Vs #አዲሱ ለገሰ እና #አለምነው መኮነን ……..#ኢህዴን #ብአዴን…
((ክፍል አምስት))
ከክፍል 1 – ክፍል 4 ያለውን ከዚህ ላይ ያንብቡ
በቅርብ አመታት የወልቃይት ውዝግብ በህዝቡ ዘንድ መስረፁን ተከትሎ ብዙ ጉዳዮች መሰማት ጀምረዋል፡፡ በ2008 ዓ.ም የወልቃይት እንቅስቃሴ መነሳቱን ተከትሎ የቀድሞው የኢህዴን/ብአዴን ሊቀመንበር የነበረው አቶ ታምራት ላይኔ ወልቃይትን በተመለከተ የግላቸውን ምስክርነት በኢሳት ቀርበው በ2008 መስጠት ችለዋል፡፡ የኢህዲን ታጋይ የነበሩት አቶ ያሬድ ጥበቡም ወልቃይትን በተመለከተ ማብራሪያ መጠታቸው የሚታወስ ነው። አቶ ታምራትም እንዳሉት የወልቃይት ጠገዴ እንዲሁም የራያና አላማጣ አካባቢዎች ጉዳይ #በትጥቅ ትግሉ ወቅትም ይነሳ እንደነበርና ጉዳዩ ግን ከድል በኃላ በህዝበ ውሳኔ ይፈታል የሚል ስምምነት ተደርሶ እንደነበር አብራርተዋል፡፡ እንደ አቶ ታምራት አባበል ህወሀት በመጀመሪያዎቹ ወቅቶች #በግልጽ በኃላ ደግሞ #በድብቅ እነዚህን አካባቢዎች የትግራይ መሬቶች መሆናቸውን ይናገር ነበር፡፡ ቆይቶ ደግሞ በካርታ መልኩ አዘጋጅቶ ለህዝቡና ታጋዩ አስተምሮበታል፡፡ የትግራይ ህዝብም ካርታውን በየግድግዳው ሁሉ ይለጥፈው እንደነበር አቶ ታምራት ካዩት ተነስተው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡ አቶ ታምራት ራሳቸውም ጭምር በአማራ ህዝብ ላይ የፈፀሙት በደል ቢሆንም ይህን ምስክርነት የሚሰጡት ቢያንስ ሀይማኖተኛ ከሆኑ በኃላ በመሆኑ ምስክርነታቸውን ማመኑ የተሻለ ነው፡፡ ደግሞም ፖለቲካዊ ትግል ሆደሰፊነት ነው።
አቶ ታምራት ይቀጥላሉ፤ የወልቃይት ጠገዴና ሌሎቹ የወሎ መሬቶች ወደ ትግራይ የተከለሉበት አግባብ በትግሉ ወቅት ተደርሶበት በነበረው ስምምነት ሳይሆን በአብዛኛው ሕውሀት ቀድሞ ባስቀመጠው እቅድ መሰረት ነው ይላሉ፡፡ ይህ ድርጊት እንዴት እንደተፈጸመም በወቅቱ ስለነበረው ሁኔታ ከሚያስተውሰው ተነስቶ ተገቢ መረጃ ሰጥቶናል፡፡
ታምራት እንደገለጸው ደርግ እንደተደመሰሰ የተቋቋመው የሽግግር መንግስት ክልላዊ ምርጫዎችን ለማድረግ ክልሎች ስለሚካለሉበት ሁኔታ ጥናት እንዲደረግ ወሰኖ ነበር፡፡ ለዚህ ጥናት መነሻም ሁኖ ያገለግል ዘንድ ደግሞ ደርግ አቋቁሞት ከነበረው የብሄረሰቦች ጥናት ኢንስቲትዩት የሚገኙ ግብአቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ ተደረገ፡፡ በወቅቱ የኢህዴን ማእከላዊ ኮሚቴ አባልና ኢህዴንን ወክሎ የሽግግር መንግስቱ ም/ቤት አባል የነበረው አቶ ዳዊት ዮሀንስ በጥናቱ ተሳታፊ እንደነበር ከታምራት ንግግር መገንዘብ ተችሏል፡፡ ከዚህ ላይ መገንዘብ የሚቻለው በሽግግር መንግስቱ ጸድቆ ተግባር ላይ የዋለው #የአማራን ህዝብ ጥቅም በእጅጉ የነካ ካርታ የተዘጋጀውና የጸደቀው #በኢህዴን ሙሉ #ፈቃደኝነት መሆኑ ነው፡፡ የወልቃይት-ጠገዴ፤ የራያና አላማጣ አካባቢ የአማራ ህዝቦችና መሬታቸው ወደ ትግራይ ሲካለሉ ኢህዴን አብሮ ወስኗል፡፡ ይህ ፀረ- አማራ የሆነ ካርታ የጸደቀው ህገ መንግስቱ ከመጽደቁ በፊት በሽግግሩ ዘመን ቻርተር አቶ መለስ ዜናዊ በመራው የምክር ቤት ስብሰባ እነደነበር ታምራት ግልጽ አድርጎታል፡፡
ይህም ማለት አማራ ባልተሳተፈበት መንግስት በጸደቀ ካርታ አማራ መሬቱን እንዲያጣ ተደረገ ማለት ነው፤ እዚህ ላይ አቶ ያሬድ ጥበቡ በ2016 የፃፈውን ጥሩ አገላለፅ ልጨምርበት።
”በእኔ እምነት መፈቀድ የሌለበት፣ ተከዜን አይነት የተፈጥሮ ወሰን ተሻግሮ በሌላ ማህበረሰብ እቅፍ ውስጥ ተጠግቶ የኖረ የወሰን ተጎራባች ህዝብ፣ ካስጠጋው ህዝብ መሬት ላይ ቆርሶ በመውሰድም ሆነ፣ ቁጥሩ ከአስጠጊው መብለጡን እርግጠኛ ሲሆን፣ በህዝበ ውሳኔ
(ሪፍረንደም) ሽፋን ያስጠጊውን ህዝብ መሬትና አስተዳደር መንጠቅ ሊፈቀድለት አይገባም” ይላል
አቶ ያሬድ እንግዲህ በወቅቱ ከነበሩ ቁንጮ የኢህዴን ሰዎች አንዱ ነበርና ለምስክርነት መጥራቱ እዚህ ጋርም አስገዳጅ ይሆናል። ከትልግ ጉዞ ትዝብቱ አንዱን ዓርፍተነገር እናምጣው እና የታጋዮችን ምስክርነት እንጨምርበት።
ሁለቱን ቁንጮ የኢህዴን ሰዎች ስለወልቃይት ጠገዴ የሰጡትን ምስክርነት መልሸ ወደዚህ ማምጣቴ ያለ ምክንያት አይደለም። ይልቁንም ይህ ጉዳይ ወደድንም ጠላንም ከኢህዴንና ከአሁኑ ብአዴን ጋርም ስለሚገናኝ በአንድ በኩል የአሁኑ ብአዴን አመራሮች ስለ ወልቃይት ጉዳይ በድፍረት ቢያነሱ ስህተት አለመሆኑን ማረጋገጫ ለመስጠት በሌላ በኩልም እነዚህን የህዝብ ጥያቄ የሚያነሱ አመራሮች አንገት ለማስደፋት የሚጥሩ ነባር የኢህዲን አመራሮችና ከብአዴንም እጅግ አደገኛ የሚባሉ ግን ወሳኝ ቦታ ላይ ያሉ ሰዎች ችግራቸው መለስ ብለው ይመለከቱ ዘንድ በማሰብ ነው።በሌላ በኩል ደግሞ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ በየትኛውም መመዘኛ ስህተት እንዳልሆነና ይህ ጉዳይ በአስቸኳይ እልባት ካልተሰጠው ኪሳራው ያልተገመተ እንደሚሆን ለመጠቆም ነው።በተለይም አዲሱ ጠ/ሚ/ር ይህንን ጉዳይ ሳይውል ሳያድር ተመልክቶ እነ ወልቃይትና ራያን ወደ ቤታቸው እንዲመለሱ ልዩ ኮሚቴ አዋቅሮ ካልሰራ በስተቀር ለራሱም ዘመን ሌላ ዋጋ እንደሚያስከለው መግለፅ ትክክል ነው ብየ አምናለው።ህወሃት ባለፈው ሳምንትም የወልቃይትና ራያ አማራዎችን ማሰር መጀመሩን እየሰማን ነው።ይህ ነገር ጥያቄውን ለማዳፈን የሚያደርገው የቅድመ አፈና ምልክት ቢሆንም እነዚህን የአማራ ግዛቶች ግን አፍንጫውን ተይዞ ይመልሳል።ነገር ግን አስከፊ የሚሆነው ጥያቄእ በአጭር ጊዜ ውስጥ ስርዓቱ ካልመለሰው ስርዓቱን ብቻ ሳይሆን ንፁሃን ዜጎችንም ሊጎዳ እንደሚችል ሊገነዘቡት ይገባል ባይ ነኝ።በዚህ መነፀር ካየነው 27 ዓመት ሲገደልና ሲፈናቀል ከኖረው የአማራ ህዝብ በላይ በየትኛውም ቦታ የሚኖሩ ትግሬዎች ያለበደላቸው ሁሉ በህወሃት ስም ዋጋ ሊከፍሉ ይችላሉ።የህዝብ ጥያቄ አፋጣኝ እና ተገቢ ምላሽ ካልተሰጠው ሰላማዊ መንገድን መከተል ሊያቆም ይችላል።
እንዴው ነገር እንዳላበዛና የኢህዲንን ጉዳይ አሁንም ትንሽ ልበልበት።
የኢህዴን/ብአዴንና የወልቃይት ጉዳይ
ከላይ ከተገለጸው የአቶ ታምራት ላይኔ ንግግርም ይሁን የአቶ ያሬድ ጥበቡ ፅሁፍ ላይ መገንዘብ እንደሚቻለው፣ በትግሉ ወቅት ጭምር የወልቃይትና የወሎ መሬቶችን ጉዳዩ ይነሳና ይወድቅ የነበረ ጉዳይ መሆኑን ነው፡፡ ኢህዴን ህብረ ብሄር ድርጅት ስለነበር በወቅተ ለጉዳዩ ብዙም ትኩረት እንዳልሰጠው፤ ሁኖም ግን ጉዳዩ ከድል በኃላ በህዝበ ውሳኔ ይፈታል የሚለው የጋራ አቋም ነበር፡፡ ጉዳዩ በጠቅላለው የአገሪቱ ጉዳይ በሚፈታበት አግባብ ይፈታል ተብሎ ታስቦ እንደነበር መገንዘብ ይቻላል፡፡ ታምራት እንደሚለው የወልቃይትና የወሎ መሬቶች ጉዳዩ አንዴ ተወስኖ አድሯል ከሚል መነሻ ከሽግገር መንግስቱ ምስረታ በኃላ ቸላ የተባለ ጉዳይ ሆነ፡፡ ጉዳዩን አንስቶ ከሕውሀት ጋር ለመወያት በሌላ ጉዳዮች ላይ የነበሩ ጫናዎች የነበሩ ቢሆንም ከወልቃይት ጠገዴ አንጻር ግን ከህውሀት በኩል ብዙ ጫና እንዳልነበር ታምራት ይገልጻል፡፡ ስለሆነም ኢህዲን በኋላም ብአዴን ችላ ብሎታል ማለት ነው። ታምራት እንዳለው የወልቃይት ጉዳይ በአንድ ወቅት ኢህዴን ወደ ብአዴን ከተቀየረም በኃላ፤ በብአዴን ጉባኤ ላይም ተነስቶ እንደነበር ፤በዚህ ወቅትም ጉዳዩም ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ስምምነት ተይዞ የነበረ ቢሆንም ጉዳዩን ብአዴን እንደ ድርጅት ጠንከር ብሎ አላየውም፡፡ አንዱ ችግርና ስህተት እዚህ ላይ ነበር፤ይለናል ታምራት፡፡እርግጥ ነው ብአዴን ላይ በርካታ ጉዳዮች የመደረክ ማሞቂያ ሆነው ቀርተዋል።
አቶ ታምራት አማራን ህዝብ ለጥቃት በማጋለጥ በኩል ቀዳሚው ተወቃሽና ተጠያቂ ነው፡፡ ሁኖም ቢያንስ አሁን የሚያውቀውን ነገር መናገሩ ጥሩ ነው፤ ገና ሌላም እንጠብቃለን፡፡
አሳዛኙ ነገር ግን የአቶ ታምራት ምክትል የነበሩት አቶ አዲሱ ለገሰ በ2008 ዓ.ም በክልሉ ም/ቤት ታላቁ አዳራሽ ውስጥ በተካሄደ ብአዴን ኮንፈረንስ ላይ ወልቃይትን በተመለከተ ሰጡት የተባለው ምላሽ ብዙውን ሰው ያሳዘነ እንደነበር ከመድረኩ ተሳታፊዎች ያገኘነው መረጃ ያስረዳል።
የአቶ ታምራት ምክትል አቶ #አዲሱ ለገሰ <<በትግሉ ወቅትም ይሁን ከዚያ ወዲህ ስለ ወልቃይት ጉዳይ አንድም ቀን ሲነሳ ሰምቸ አላውቅም>> ብለው በህዝብ ፊት መናገራቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡ እንዲህ ነው የአማራ ነገር፡፡ አሁን ባለው ሁኔታ የኢህአዴግ ም/ቤት ባስቀመጠው አቅጣጫ የወልቃይት ችግር ይፈታል ብሎ እንደማያምን ታምራት ተነግሯል፡፡ የብዙው ሰው እምነነትም ይህ ሁኗል፡፡ እኔ የህወሃትን ታሪክ የማላውቀው የዚህ ዘመን ወጣት እንኳን ኢህአዴግ የሚባለው ኩባንያ (ከፖለቲካ ያቅ Plc ነቱ ያደላብኛል) ይህንን የረጅም ጊዜ ችግር እፈታለው ቢል ሊያታልልና ጊዜ ሊገዛ እንጅ ከልቡ እንዳልሆነ ልብ ልንል ይገባል። ከብአዴን አንጻርም ምንም ተስፋ የለም፡፡ ይህንን የምለው የድርጅቱ ቁንጮዎች አዲሱ ለገሰም ይሁን በአለምነው መኮንን የወልቃይት ጥያቄ እንዳይነሳ አስፈላጊው የማፈን ስራ እንደሚሰሩ ከንግግራቸው ስለተረዳው ነው። ወይን መፅሄት ላይ አቶ አለምነው የሰጠው ቃል ለዚህ ከበቂ በላይ ነው፡፡ ምናልባት አሁን አቋሙን ቀይሮ ወደ አማራ ህዝብ ገብቶ ለሆነ አላውቅም። የወልቃይት ጥያቄ ታፍኖ ለመቅረቱ በብአዴን ውስጥ የአለምነው መኮንን ያክል ተጠያቂ አይኖርም፡፡ በሰሜን ጎንደር የሚመደቡ አመራሮች ብቻ ሳይሆኑ ክልል ላይ ያሉም አንዳንድ አመራሮች የወልቃይት ጉዳይ እንዲፈታ ጥረት አድርገዋል። የእነዚህ ጉዳይ ግን ያከተመው ብአዴን 2008 ዓ.ም ላይ በሰጠው መግለጫ ነው። ከዚያ ወዲህ የሚኖራቸው እይታ ድርጅታዊ ሳይሆን ግልሰባዊ ነው ማለት ነው።ነገር ግን አለምነው ራሱንም ድርጅቱንም ከህዝብ አራራቀው እንጅ የወልቃይትን ጥያቄ ከአማራ ህዝብም ከደጋፊ አመራሮችም ማራቅ አልቻለም።
እንግዲህ እውነታው ይህ ከሆነ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት ጥያቄው መቋጫው ምን ይሆን? ብለን እስኪ እንጠይቅ።
የወልቃይት ጉዳይ መፍትሄው ቀላል ነው? ብለን ካነሳን መልሱ አይደለም ነው፡፡ አይደፈሬ የአማራነትን ስሜት የተላበሰ ቆራጥ አመራር ይጠይቃል። የህወሃትን የበላይነት የሚዋጋ የፌደራል አመራራም ይጠይቃል። በአሁኑ ወቅት ይህንን ስንገመግመው በስርዓቱ ውስጥ ሁለቱንም ማግኘት አይቻልም።ስለዚህ የወልቃይት ጉዳይ መፍትሄ የሚያገኘው በሁለት መንገድ ይሆናል ማለት ነው።በአንድ በኩል የአማራን ጥቅም ሊያስከብር የሚችል ሀይል ከአማራው ህዝብ ሲፈጠር ሲሆን (አሁን ይህ ጉዳይ ጥሩ ይመስለኛል) በሌላ በኩል ወጥ የሆነ ብሄራዊ ጥቅም የሚያስተሳስረው ኢትዮጵያ የተባለ አገር ሲፈጠር ነው፡፡ ይህ ሁለተኛው ጉዳይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ ለዓመታት የተሰራን የብሄር ፖለቲካና ክልላዊ አደረጃከት መናድ ከባድ ይመስላል። አሁን አንድ አገር ብሄራዊ ጥቅም የሚባል ነገር የለም፡፡ ይህንን ጉዳይ ( ምስጋናው 2010 በመፅሀፉ ገጽ 271 ላይ በዚህ መልኩ በዝርዝር አስቀምጦታል። ይህንን ጉዳይ እንዳለ ማንበቡም ጠቀሜታ አለው።
እውነት ነው፤ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ እንዲህ በቀላሉ ሊፈታ የሚችል አይደለም፤ ጉዳዩ ከብዙ ነገሮች ጋር ተወሳስቧል፡፡ የወልቃይት ጠገዴ ጥያቄ ለትግራይና ለአማራ በየራሳቸው ትልቅ ትርጉም አለው፡፡ ወልቃይት-ጠገዴ ለትግራይ የአለም አቀፍ በር ናት፣ ማለትም ወልቃይት ለትግራይ ሱዳንን በመጠቀም ከውጩ አለም ጋር መገናኛ ድልድይ ነው፤ ወልቃይት ለትግራይ የሀብት ምንጭ ነው፡፡ ይህም ማለት ደግሞ ወልቃይት ለትግራይ የህይዎት ጥያቄናት ማለት ነው፡፡ ወልቃይት ለትግራይ አማራን ለመቆጣጠር ወሳኝ ስትራቴጅክ አካባቢ ናት፤ ወልቃይትን መቆጣጠር ህውሀት ወደ ሌሎቹ የጎንደር ለም ከባቢዎች(ጠገዴ- ማርዘነብ፣ አብደራፊ- አርማጭሆ፣ መተማ፣ ቋራ፤ ወዘተ) ለሚያደረግው ዝግመታዊ ተስፋፊነት ቁልፍ ቦታ ነው፡፡ ወልቃይት ጠገዴ ለአማራ ደግሞ ከትግራይም የባሰ ነው፡፡ ከላይ እንዳነሳሁት #ወልቃይት ጠገዴ ለአማራ ህዝብ ሁሉም ነገር ነው፡፡ ወልቃይት ለአማራ የማንነት ጉዳይ ናት፤ ወልቃይት ለአማራ የታሪክ ጥያቄ ናት፤ ወልቃይት ለአማራ የመሬት( ርስት) ጥያቄ ናት፤ ወልቃይት ለአማራ የክብር ጉዳይ ናት፤ ወዘተ…፡፡
እንግዲህ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ ለሁለቱ ህዝቦች እንዲህ ወሳኝ ጥያቄ ነው፤ በአሁኑ ወቅት የወልቃይት ጉዳይ በጣም የተወሳሰበ አስቸጋሪ ነጥብ ሁናለች፡፡ ምን አልባትም በሁለቱ ህዝቦች መካከል አላስፈላጊ ጣጣ ውስጥ ልንገባ ይችል ይሆናል፡፡ ምክንያቱም ትግሬና አማራ ወልቃይትን የህልውናና የማንነትና የክብር ጉዳይ አድርገው በመውሰዳቸው ነገሩ እጅግ ተወሳስቧል፡፡ የጠገዴ ወልቃይትን የማንነት ጥያቄ ለመመለስ ጉዳዩ እነዲህ የተወሳሰበና ፈታኝ ቢሆንም፣ ከመቸውም ጊዜ የተሸሉ እድሎችም እንዳሉ ማየት ግን ይቻላል፡፡ ለምሳሌ በየኣካባቢው ማለትም በአገር ውስጥም ሆነ በውጭ ሀገር በህውሀት ላይ ግፊቱ ጨምሯል፡፡ የጠገዴና ወልቃይት ህዝቦች የማንነት ጥያቄ አሁን አዳማጩ በዝቷል፤ በአገር ውስጥም በውጭም ደጋፊ ማሰባሰብ ተችሏል፡፡
አሁን የጠገዴ ወልቃይት ጉዳይ የኢትዮጽያ ህዝብ በተለይም የአማራ ህዝብ ጥያቄ ሁኗል ፡፡ ዛሬ መድረክ በተፈጠረ ቁጥር የወልቃይት ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳ ሁኗል፡፡ ለዚህ ማሳያ ይሆን ዘንድ በየ2008 ዓ.ም ባ/ዳር ላይ በተካሄደ አመታዊ የዲያስፖራ መድረክ የወልቃይት ጠገዴ ጉዳይ አነጋጋሪ ሁኖ መነሳቱ ይታወሳል፡፡ በዚህ መድረክ ተሳታፊ ከነበሩት አንዳንድ የዲያስፖራ አባለት የተነገሩት አባበሎች የጉዳዩን አሳሳቢነት ያሳያሉ፡፡ አንድ ተናጋሪ እንዲህ አለ ፡- እኛን/ ጎንደሬዎችን ማለቱ ነው / ብትፈልጉ ወደ ኦረሞ ፤ ብትፈልጉ ወደትግራይ ፤ ብትፈልጉ ወደ ሱዳን ፤ ብትፈልጉ ወደሌላው የኢትዮጽያ ክልል ክፍል እንድንከለል አድርጉን ፤ ብቻ ግን ከወልቃይት አትለዩን ብሎ ተናገረ፡፡
በዚህ ንግግር አንዳንድ ተሰብሳቢዎች በትከዛ እንደተዋጡ ይነገራ፡፡ አንዳንዶቹ ደግሞ ይህ አነጋገር እኮ ወልቃይትና ጎንደር ምን ያህል የጠበቀ ቁርኝት እንዳላቸው የሚያስገነዝብ ነው ብለው መናገራቸው ተሰምቷል፡፡ እውነት ነው ጎንደርና ወልቃይት ትስስራቸው እንዲሁ በቃላት የሚገለጽ አይደለም፡፡ አብዛኛው አማራ ህዝብ በተለይም የጎንደር በጌ ምድር ህዝብ የወልቃይት ከጎንደር መለየት ምቾት አልሰጠውም፤ እንዳውም ቡዙዎቹ የወልቃይትን ከጎንደር መነጠል ሲያስቡ አንድ እጃችን እንዳጣን ይሰማናል ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
ለዚህ መሰለኝ አርቲስት ሻንበል በላይ እንዲህ ሲል የዘፈነው፦
ወልቃይት ጠገዴ ድፍን አርማጭሆ ዳንሻና ሁመራ፣
ሰው ጎንደሬ ነው መሬቱም የአማራ፡፡
(መሬቱ የጎንደር ነዋሪው አማራ ቢለው የተሻለ ይሆን ነበር)
በታሪክ ደምቃ ያየናት፣
የአማራ አገር ናት ወልቃይት፡፡
ቁሜ እናገራለሁ እኔ አልጠየቅም ፣
ወልቃይት ጎንደር እንጅ ትግራይ ሁኖ አያውቅም፡፡
ፊዳ ተሸክመን የመከራ ጭነት፣
ወልቃይት ከሌለ የለም ጎንደሬነት፡፡
ታሪክ አዋቂዎች እስኪ ተናገሩ፣
ተከዜ አይደለም ወይ የጎንደር ደንበሩ፡፡
ተውኝ ልኑርበት አትለዩኝ ከዘሬ፣
እኔ ወልቃይቴው ጎንደር ነው አገሬ፡፡
አገር እየመሩ ማዳላት ለምን ነው ፣
ኧረ በህግ አምላክ ወልቃይት ጎነደር ነው፡፡
ይሁን እንጅ የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት የማስከበር የትግል ፈተናዎች እጅግ መክበዳቸው አይቀርም፡፡ እነዚህን ፈተናዎች በነዚህ ጥሩ አጋጣሚዎች ሸፍኖ ለድል የመብቃቱ ጉይ የተቋቋሙት ኮሚቴዎች በሂደቱ ላይ የአላማ ጽና ፤ የርእዮት ጥራት፤የመስዋትነት ዝግጁነትን ይጠይቃል። ከምንም በላይ ግን ጥያቄው የመላው አማራ ህዝብ በመሆኑ ህዝቡን የማንቃትና የማደራጀት በመረጃ የመመገብ ስራ አሁንም በተከታታይ መሰራት አለበት። የሚመኩባቸው ኃይሎች መንሸራተት ሲጀምሩ መፍረክረክ ሊመጣና ጥያቄው እንደገና የመዳከም እድል ሊገጥመው ይችላል፡፡ ስለሆነም የተጀመረው ትግል ለድል ይበቃ ዘንድ ትልቅ ዋጋ የሚጠይቅ መሆኑ አይቀርምና ለዚህ መዘጋጀትና አስፈላጊውን ዋጋ እየከፈሉ በሰላማዊና ህጋዊ መንገድ ጥያቄውን ጫፍ ማድረስ የትውልዱ ቤት ስራ መሆን ይገባዋል፡፡ ያለ በለዝያ አማራ በታሪኩ ብቻ እየተኮፈሰ ወደ መኖር ይወርዳል፤ ይህ ማለት ደግሞ አማራ ትውልዱን ማስቀጠል አልቻለም ማለት ነው፡፡
….. በቀጣዩ ክፍል 6 ደግሞ ወየልቃይት ጠገዴን ጥያቄ ለመፍታት አይቀሬ ፈተናዎች ምን ሊሆኑ ይችላሉ? በሚል እቀጥላለው።