April 11, 2018 – Konjit Sitotaw

የዶ/ር አብይ አህመድ ምርጫ
እና
ሁለቱ ፖለቲካዊ አንደምታዎች
***
ብሩህ ዓለምነህ
(በመቀሌ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህርና ‹የኢትዮጵያ ፍልስፍና› መጽሐፍ ደራሲ)

***
በዚህ ጽሑፍ የኦሮሞ ወጣቶች (ቄሮ) አብዮትና የዶ/ር አብይ አህመድ ምርጫ በኦሮሞ ብሔርተኝነት ውስጥ ያመጣውን ሥር-ነቀል ለውጥና አጠቃላይ የአገሪቱ የፖለቲካ ምኅዳር ላይ ያለውን አንድምታ እንመለከታለን።
መጋቢት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ዶ/ር ደብረፅዮን ወ/ሚካኤል እና አቶ ሽፈራው ሽጉጤ በተወዳዳሪነት በተሳተፉበት በኢሕአዴግ ም/ቤት በተደረገው ሚስጥራዊ ምርጫ ላይ ከኦሕዴድ የተወከሉት ዶ/ር አብይ አህመድ በከፍተኛ የድምፅ ልዩነት የድርጅቱ ሊቀመንበር ሆነው ተመርጠዋል፡፡ “የኢሕአዴግ ሊቀመንበር የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ይሆናል” በሚለው የሕገ መንግሥቱ አንቀፅ መሠረትም የተወካዮች ም/ቤት የዶ/ር አብይን ሹመት መጋቢት 24፣ 2010 ዓ.ም አፅድቆታል፡፡
ይኽ ምርጫ የተካሄደው በፖለቲካ ምኅዳሩ ላይ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በዛሉበት፣ የግል ሚዲያው በኮሰመነበት፣ ሕዝቡ አማራጭ አጥቶ ተስፋ በቆረጠበትና በኦሕዴድ በኩል የታየውን የለውጥ ፍላጎት ተስፋ ያደረገበት ወቅት ላይ ስለነበረ፣ ምርጫው በሁሉም ኢትዮጵያውያን ዘንድ በጣም በጉጉት ሲጠበቅ ነበር፡፡ ኢሕአዴግ በ27 ዓመታት የሥልጣን ዘመኑ ውስጥ ባደረጋቸው ድርጅታዊ ግምገማዎች ሁሉ፣ “ነቅዣለሁ”፣ “የሥልጣን አተያይ ላይ ተንሸዋርሬያለሁ”፣ “በጥልቀት በስብሼ በጥልቀት ታድሻለሁ” ወዘተ. እያለ እዚህ ደርሷል፡፡
ዶ/ር አብይ ወደ አመራሩ የመጡትም ሕዝቡ ኢህአዴግ ላይ ተስፋ በቆረጠበት በዚህ ወቅት ነው፡፡ በመሆኑም ዶ/ር አብይ ለኢሕአዴግ የመጨረሻ ዕድሉ ናቸው፡፡ ዶ/ር አብይም ቢሆኑ በበዓለ ሲመታቸው ቀን የተናገሩት ይኽንኑ ነው፤ “ከዚህ በፊት ብዙ ዕድሎችን አግኝተን ሳንጠቀምባቸው አባክነናቸዋል፤ ይኼም ዕድል እንዳይባክንብን በጥንቃቄ ልንጠቀምበት ይገባል” ነበር ያሉት፡፡
ኢሕአዴግ ለ27 ዓመታት በኢትዮጵያውያን መካከል አገራዊ መግባባት ለማምጣት ሞክሮ ያልተሳካለትን ዕድል በስተመጨረሻ በኦህዴድና በዶ/ር አብይ አማካኝነት ለማሳካት ከጫፍ የደረሰ ይመስላል፡፡ ለዚህም ነው ኢሕአዴግ በዶ/ር አብይ በኩል የመጣውን ዕድል እንዳያባክነው መጠንቀቅ ያለበት፡፡
ሆኖም ግን የዶ/ር አብይ በዓለ ሲመት ከተከናወነ በኋላ አንድ ሳምንት እንኳን ሳይሞላው በኢሕአዴግ የፌስቡክ ገጽ ላይ የተለቀቀው መልዕክት በዶ/ር አብይ ምርጫ ያልተደሰቱ ከፍተኛ አመራሮች መኖራቸውን የሚያመላክት ነው፡፡ መልዕክቱ እንዲህ የሚል ነው፣ “ኢሕአዴግ የተግባር ድርጅት ነው ሲባል ሕዝብን በማማለል የማይሆነውንና የማይተገበረውን ሁሉ ቃል በመግባት የሚነጉድ ድርጅት ሳይሆን፤ ሠርቶ በሚያስመዘግባቸው ውጤቶች ማሳየት በመቻሉ እንጂ!!” ይኼ እንግዲህ ዶ/ር አብይ በፓርላማው ንግግራቸው ላይ ለሕዝቡ የሰጡትን የለውጥ ተስፋ ለማጣጣል የተጻፈ መልዕክት መሆኑ ነው፡፡ ዶ/ር አብይን ከምርጫውም በፊት “በተራ ሕዝበኝነት የተጠለፈ” የምትል ክስ ከፍተኛ አመራሩ አካባቢ ሲሰነዘርበት ነበር፡፡
“ማማለል” ወንጀል እንኳ ቢሆን በማይፈፀሙ ዕቅዶች ሕዝብን በማማለል ኢሕአዴግን የሚያክል የለም፡፡ ኢሕአዴግ ላለፉት 27 ዓመታት አቅዶ ያልፈፀማቸው ዕቅዶቹ በጣም ብዙ ናቸው – የኮንዶሚኒየም ግንባታ፣ “የተለጠጠው” የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ፣ በየአካባቢው የመሠረት ድንጋይ ተቀምጦላቸው የተረሱ ፕሮጀክቶች በጣም ብዙ ናቸው፡፡ ኢሕአዴግ ይኼንን ሁሉ ጉድ ይዞ “በማይተገበር ዕቅድ ሕዝብን ማማለል” የሚለው ክስ ነገር ፍለጋ ካልሆነ በስተቀር ተዓማኒነት የለውም፡፡ ለማንኛውም ይህቺ ክስ በከፍተኛ አመራሩ ውስጥ ለውጥን የሚፈልግና የማይፈልግ ሁለት ቡድን እየተፈጠረ እንደሆነ ጥሩ ምልክት ነች፡፡
የመልዕክቷ ነገር ገርማኝ ነው እንጂ አነሳሴ እንኳ የዶ/ር አብይ ምርጫ በሁለቱ ብሔርተኝነቶች (በዘውግና በኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት) ላይ ያመጣውን ፖለቲካዊ አንደምታዎች ለመዳሰስ ነበር፡፡ እስቲ በየተራ እንያቸው፡፡
ጠላት ቅየራ
***
ብሔርተኝነት ሁለት ባሕሪዎች አሉት፤ የመጀመሪያው ያለ ጠላት መኖር የማይችል መሆኑ ነው፡፡ በጠላትነት የሚፈርጀውም ፖለቲካዊ ሥርዓትን አሊያም ሕዝብን በጅምላ ሊሆን ይችላል፡፡ በመሆኑም የጠላቱ ዓይነት የብሔርተኝነቱን ዓይነት ይወስነዋል፡፡ ብሔርተኝነቱ እንዲቀየር ከተፈለገ የጠላቱን ዓይነት መቀየር ነው፡፡ ልክ ጠላት ሲጠፋ ብሔርተኝነቱም አብሮ ይጠፋል፡፡
ለምሳሌ፣ በ1950ዎቹና 60ዎቹ በአገራችን የነበረው የብሔርተኝነት ዓይነት ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ሲሆን ጠላቱም ዘውዳዊው አገዛዝና የባላባቱ ሥርዓት ነበር፡፡ ልክ የ66ቱ አብዮት ዘውዳዊውንና የባላባቱ ሥርዓት ሲያጠፋ ብሔርተኞቹ አንድም መጥፋት ነበረባቸው ወይም ደግሞ ሌላ ጠላት መፈለግ ነበረባቸው፡፡ በዚህ ወቅት ነበር ኢሕአፓ ደርግን፣ የዘውግ ብሔርተኞች ደግሞ አማራን ያገኙት፡፡
የባህልና የማንነት መብትን ለማስከበር ተብሎ በጥቂቶች የሚጀመረው የዘውግ ብሔርተኝነት ግን ሥልጣንን በአቋራጭ ለማግኘት ጥሩ ዘዴ መሆኑን ሲገነዘቡ ብሔርተኝነቱ ሁለተኛውን ባሕሪ መላበስ ይጀምራል – ተረክ (Narrative) መፍጠር፡፡ ይኼም ተረክ የሚፈጠረው “ለእውነት ግድ በማጣትና ታሪክን እየቀሸቡ ቂም መቋጠሪያ በማድረግ›› ነው፡፡ ብሔርተኞች የጠላት መኖርን አጥብቀው የሚፈልጉት “ታሪክን እየቀሸቡ ቂም ማስቋጠር” በሚለው መርህ በመሄድ “እንወክለዋለን” የሚሉት ሕዝብ ላይ “የመከበብና የመጠቃት” ሥነ-ልቦናን ለመፍጠር ነው። በአሁኑ ወቅት በኢሕአዴግ ውስጥ ያሉት የዘውግ ብሔርተኝነቶች እነዚህን ሁለት ባሕሪዎች በመላበስ ለሥልጣን የበቁ ናቸው፡፡ ከእነዚህ የዘውግ ብሔርተኝነቶች ውስጥ አንደኛው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ነው፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት በተለያዩ ደረጃዎች አልፎ በአሁኑ ወቅት የአገሪቱን ፖለቲካ እየቀየረበት ያለው መንገድ በጣም አስገራሚ ነው፡፡
ፕ/ር መኩሪያ ቡልቻ Survival and Reconstruction of Oromo National Identity በሚለው ሥራቸው ውስጥ ከጥቂቶች ተነስቶ ሕዝባዊ ንቅናቄ ለመሆን የበቃውን፣ ከባህል ጥያቄ ተነስቶ ወደ ፖለቲካዊ ጥያቄነት ያደገውን፣ ከራስ ገዝ አስተዳደር ተነስቶ ነፃ የኦሮሚያ መንግሥትን እስከመናፈቅ የሄደውን የኦሮሞ ብሔርተኝነትን በ4 ደረጃዎች ይከፍሉታል፡፡ የቀድሞው አንድነት ፓርቲ አመራር አባል የነበረው ሰሎሞን ስዩም ደግሞ በ2008 ላይ የአዲስ አበባ ማስተር ፕላንን በመቃወም በመላው ኦሮሚያ የተቀሰቀሰውን ሕዝባዊ አመጽ በ5ኛ ደረጃነት ይጨምረዋል፡፡ “ከጠላት ቅየራ” አንፃር ካየነው ግን የኦሮሞ ብሔርተኝነት ያለፈባቸውን ደረጃዎች በሁለት ነው የምንከፍለው – ከ2008ቱ የማስተር ፕላኑ ተቃውሞ በፊትና በኋላ፡፡
የ2008ቱን የማስተር ፕላኑን ተቃውሞ እንደሌሎች ተቃውሞዎች ተራና የተለመደ የፖለቲካ ክስተት አድርጋችሁ እንዳትቆጥሩት፡፡ ክስተቱ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ጠላት የቀየረበት ነው፡፡ በዘውግ ብሔርተኝነት ውስጥ ደግሞ ጠላት መቀየር ብሔርተኝነቱን ሥር ነቀል በሆነ መንገድ ይቀይረዋል፡፡ ኢሕአዴግ የወደቀው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ጠላቱን ከአማራ ወደ ራሱ ወደ ኢህአዴግ የቀየረ ዕለት ነው – በ2008 ዓ.ም፡፡
የቄሮ ውለታ
***
የቄሮ አብዮት አጠቃላይ የአገሪቱን ወቅታዊ የፖለቲካ ምኅዳርን የቀየረ ሲሆን፣ ያስመዘገባቸውንም ስኬቶችም በ4 ነጥቦች ከፋፍለን ማየት እንችላለን፤ 1) የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ጠላት በማስቀየር፤ 2) አገራዊ መግባባትን በማምጣት፤ 3) በሕዝቦች መካከል የወንድማማችነት እሴትን በመጠገንና በማምጣት (የአገሪቱን አንድነት በመመለስ) እና እንዲሁም 4) በሕዝብ ስም መነገድን በማስቀረት። በዚህም እስከ 2008 ዓ.ም. ደረስ በኦነግና በቀድሞው ኦሕዴድ ሲመራ የነበረው የድሮው የኦሮሞ ብሔርተኝነት ላለፉት 50 ዓመታት ያላገኘውን ድል፣ የቄሮ አብዮት በሁለት ዓመታት ውስጥ ማሳካት ችሏል፡፡ ኢትዮጵያም ከመበታተን ስጋት ወጥታ እንደ አገር የመቆየት ተስፋዋ የለመለመው የቄሮ አብዮት ባመጣቸው በእነዚህ አራት ስኬቶች የተነሳ ነው። እስቲ በየተራ እንመልከታቸው።
ብሔርተኝነት በዋነኛነት የልሂቃኑ እንቅስቃሴ ነው፡፡ እነዚህ ልሂቃኖች ግን እንቅስቃሴያቸውን ወደ ሕዝቡ ለማውረድና ብዙ ደጋፊዎች ለማግኘት ተረክ ይፈጥራሉ፡፡ ሕዝብን የሚያንቀሳቅሱበት ብቸኛው መንገድ እንደዚህ ዓይነት ተረኮችን በህዝቡ ውስጥ ማሰራጨት ነው፡፡ የተረኮቹም ዋነኛ መፈብረኪያ መርህ “ታሪክን እየቀሸቡ ቂም መቋጠሪያ ማድረግ” የሚለው ነው፡፡ ይኽ ተግባር በዘውግ ብሔርተኝነት ውስጥ የልሂቅነት ዋነኛ መለኪያ ነው፡፡
የኦሮሞ ብሔርተኝነት በእንደዚህ ዓይነት የቆዩ ተረኮች ላይና “አማራ እንዲህ አድርጎሃል” በሚለው የታሪክ ቁዘማ/ተብሰልሳይነት ላይ በተቸከለበት ወቅት ላይ፣ የኦሮሞ ወጣት (ቄሮ) ግን አሁን ካለው ሥርዓት ጋር ግብግብ ላይ ነበር፡፡ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከዚህ የታሪክ ተብሰልሳይነት የባነነውና ቄሮ አሁን ካለው ሥርዓት ጋር ግብግብ መግጠሙን የተረዳው በማስተር ፕላኑ ተቃውሞ ወቅት ነበር፡፡ ቄሮን ተከትሎም የኦሮሞ ብሔርተኝነት በ50 ዓመታት ታሪኩ ውስጥ ጠላት የቀየረው በዚህ ወቅት ነበር፡፡
አዲሱ የኦሮሞ ብሔርተኝነት ከፍታም አቶ ለማንና ካቢኔያቸውን ወደ አመራርነት አመጣ፡፡ የአቶ ለማ ካቢኔም በየጎራው ሲሻኮቱ የነበሩ አመለካከቶችን ወደ አንድ በማምጣት አገራዊ መግባባትን ለመጀመሪያ ጊዜ ማምጣት ችሏል። በኦሕዴድ ድርጅታዊ መግለጫ ላይም ሆነ በዶ/ር አብይ “የአብረን እንሥራ” ጥሪ ላይ በውጭና በአገር ውስጥ ያለው ተቃዋሚ ሁሉ አዎንታዊ መልስ መስጠቱ ቄሮ በአዲሱ ኦሕዴድ በኩልእያመጣ ያለውን አገራዊ መግባባት የሚያሳይ ነው።
የቄሮ ውለታ የኦሮሞ ብሔርተኝነትን ጠላት በማስቀየርና አገራዊ መግባባትን በማምጣት ብቻ የሚወሰን አይደለም፡፡ ውለታው የኦሮሞ ብሔርተኝነት በሌሎች ሕዝቦች ዘንድ በጥርጣሬ ከመታየት እንዲወጣና ጭራሽ ድጋፍ አግኝቶ (ወንድማማችን ፈጥሮ) የጠቅላይ ሚኒስትርነት ደረጃ ላይ እስከማድረስ የደረሰ ነው እንጂ፡፡ “በኦሮሚያ የሚፈሰው ደም የኔም ደም ነው” የሚል መፈክር የተስተጋባበት የሐምሌ 2008ቱ የጎንደር ሰልፍም ሆነ፣ በጥቅምት ወር 2010 ዓ.ም. የተከናወኑት “የጣና ኬኛ” እና የአቶ ለማ መገርሳ የባሕር ዳር ጉዞ መታየት ያለበት የመንግሥት ሚዲያ “እሳትና ጭድ” በሚላቸው በሀገሪቱ ሁለት ታላላቅ ብሔሮች መካከል እንዲላላ የተደረገውን የወንድማማችነት ስሜት ለመጠገን ካለው ፋይዳ አንፃር ነው። የዶ/ር አብይ ምርጫ ም የዚህ በአማራና በኦሮሞ መካከል የወንድማማችነት ስሜትን ለመጠገን እየተደረገ ያለው ጥረት ፍሬ ማፍራቱን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡
የቄሮ አብዮት ፖለቲካዊ አንድምታ በኦሮሞና በአማራ ሕዝቦች መካከል የወንድማማችነት እሴትን በመፍጠር ብቻ አይወሰንም፤ ይልቅስ ፖለቲካዊ አንድምታው ከወደ ትግራይም ሳይቀር ትኩረትን እየሳበ ነው፡፡
የብሔር ፓርቲዎች ራሳቸውን የብሔራቸው ብቸኛ ተወካይ አድርገው ስለሚያቀርቡ ፓርቲዎቹ ላይ በሚነሳ ሕዝባዊ አመፆች ወቅት የዚያ ብሔር ተወላጆች የጥቃት ዒላማ ይደረጋሉ። በኦሮሚያና በአማራ ክልሎች ላይ በተቀሰቀሰው ሕዝባዊ አመጽ ወቅትም ትግራዋዮች የጥቃት ኢላማ የተደረጉት በዚህ ስሌት ነበር። “ቄሮ ያመጣው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ግን…” ይላሉ የወቅቱ የአረናው ሊቀ መንበር አቶ አብረሃ ደስታ ሰሞኑን በፃፉት በፌስቡክ ገፃቸው ላይ “ቄሮ ያመጣው የኦሮሚያ የኢኮኖሚ አብዮት ግን ሕወሓትን ከኦሮሚያ በማባረር የትግራይ ተወላጆች ተለይተው የጥቃት ዒላማ የሚሆኑበትን ምክንያት አስቀርቷል። በዚህም ቄሮ የትግራይ ሕዝብ ባለውለታ ነው።” አቶ አስራት አብርሃም ደግሞ “ቄሮ በመራው አብዮት የተነሳ በትግራይ ሕዝብ ስም የሚነገድበት ዘመን አብቅቷል›› ብሏል፡፡ በተቃራኒው፣ ፌዴራል ፖሊስ ባለፈው ታኅሣሥ ወር 2010 ዓ.ም. “ቄሮ ላይ ምርመራ አደርጋለሁ” ማለቱ ይታወሳል፡፡ ድምፀ ወያነ በቅርቡ በፌስቡክ ገፁ ላይ ባሰባሰበው አስተያየት ደግሞ 65% የሚሆኑት ትግራዋዮች በዶ/ር አብይ ምርጫ ደስተኞች መሆናቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነትና የቅይጥ ማንነቴዎች ማንሰራራት
***
የዶ/ር አብይ ምርጫ ሁለተኛው ፖለቲካዊ አንድምታ ከራሳቸው ቤተሰባዊ ሁኔታ ይነሳል፡፡ ዶ/ር አብይ ከኦሮሞና ከአማራ ወላጆች የተወለዱ፣ በእስልምና ሃይማኖት አድገው በኋላ ላይ ወደ ክርስትና የገቡ፣ በኦሮሞ ባህል አድገው አማራ ሚስት ያገቡ፣ ኢትዮጵያዊ ዝንጉርጉርነት የሚታይባቸው ሰው ናቸው፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ከዚህ የባህል፣ የሃይማኖትና የብሔር ዝንጉርጉርነት ውጭ የሚገልፀው ነገር የለም፡፡ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም “ኢትዮጵያ ከየት ወዴት?” በተባለው መፅሐፋቸው ውስጥ ኢትዮጵያዊነትን እንዲህ በማለት ይገልፁታል፤ “ኢትዮጵያዊነት ብዙና የተለያዩ ኅብረተሰቦች የተዋኻዱበት አካል ክፍል መሆን ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ከጎሰኝነት በላይና ውጭ የሆነ አጠቃላይ ማንነት ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት የዜጎች ውጥንቅጥ መሬት ባለቤትነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት የደጋው ብርድና የቆላው ሙቀት የሚገናኙበት ኃይል ነው፡፡ ኢትዮጵያዊነት ለሙሴ፣ ለክርስቶስና ለመሐመድ የሚጨሰው ዕጣን በእርገት መጥቆ የሚደባለቅበት እምነት ነው፡፡” (1985፡ 31)
ዶ/ር አብይ የእንደዚህ ዓይነት ኢትዮጵያዊ ዝጉርጉርነት ጥሩ መገለጫ ናቸው፡፡ ቅይጥ ማንነቴዎች ከተለያዩ ባህሎችና ማንነቶች የሚጋሩት ሥነ ልቦና ስላላቸው ልክ እንደ ዘውግ ብሔርተኞች ወደ ውስጥ የታመቀ ማንነት ሳይሆን ወደ ውጭ የተበተነ ማንነት ነው ያላቸው። ይኼም የተበተነ ማንነት መጠጊያውና መጠለያው ይኼኛው ወይም ያኛው ብሄር ሳይሆን ኢትዮጵያዊነት ነው። የኢሕአዴግ የብሔር ፖለቲካ ግንላለፉት 27 ዓመታት ለዚህ ቅይጥ ሕዝብ ዕውቅናና ፖለቲካዊ ውክልና በመንፈጉ የተነሳ በአገሩ ላይ መጠጊያና መጠለያ አሳጣው።
ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት የሚመነጨውም ከዚህ ብትን ማንነትና ዝጉርጉርነት ነው፡፡ ይህ ቅይጥነት ደግሞ ለ100 እና ለ200 ዓመት የቆየ ሳይሆን ሺሕ ዓመታትን የተሻገረ ሐቅ ነው፡፡ ለዚህ ነው ዶ/ር አብይም ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን በሚያወድሰው በፓርላማው ንግግራቸው ላይ “ማንነታችን እንዳይለያይ ሆኖ የተሰናሰለ፣ እንዳይነጣጠል ሆኖ የተገመደ፣ የተዋደደና የተዋኻደ ነው፤” ያሉት፡፡ ላለፉት 27 የኢሕአዴግ ዘመናት ውስጥ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት በዚህ ፓርላማ ላይ በዚህ ከፍታ ነግሶ አያውቅም። በዚህ የዶ/ር አብይ ንግግራቸው የተነሳም ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነት ዳግም የማንሰራራት ምልክቶች አሳይቷል፡፡
የኢሕአዴግ ፖለቲካ ግን ይኼንን ሐቅ በመካድ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ኢሕአዴግ አገሪቷን በብሔር ሸንሽኖ በሐሳብ ሳይሆን በብሔር ለተደራጁ ኃይሎች ያከፋፈለበት ምክንያት “በከተሜነት፣ በባህል፣ በሃይማኖትና በብሔር መቀላቀል የተነሳ ቅይጥ ማንነት ያላቸው ዜጎች ቁጥር በጣም አነስተኛ ነው” በሚል የአስተሳሰብ መነሻ ነው፡፡ እንደዚህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚመጣው ደግሞ ከመሃሉ (ከከተሞች መስተጋብር) በተነጠሉና ጠርዝ ላይ ከሚገኙ ገጠሮች ነው፡፡ ምንም እንኳ አርሶ አደሩ ብሔርተኛ ባይሆንም ከእንደዚህ ዓይነት ከተነጠሉ አካባቢዎች የሚወጣው ልሂቅ ግን የአገሪቱን ሕዝቦች የሚመለከተው ልክ እንደራሱ አድርጎ ነው፡፡
ኢሕአዴግ ከተቃዋሚ ፓርቲዎች ጋር የተካረረ ውዝግብ በገባበት የ1997ቱ ምርጫ ወቅት አቶ መለስ ዜናዊ ተቃዋሚዎችን ያስጠነቀቁበት መንገድ ለዚህ አባባላችን ጥሩ ማሳያ ነው፡፡ አቶ መለስ እንዲህ ነበር ያሉት፣ “እኛ የአርሶ አደር ልጆች ነን፤ በመሆኑም የምናራምደው ፖለቲካ የባላገር ፖለቲካ ነው። ስለዚህ እንደ አመላችን ያዙን።” ይኽ የአቶ መለስ ንግግር የአገራችን ፖለቲካ በገጠርና በከተማ ሰዎች፣ ባልተቀየጡ ማንነቶችና በቅይጥ ሰዎች መካከል የሚደረግ (Center – Periphery) የፖለቲካ ሽኩቻ እንደሆነ ግልፅ ያደረገ ንግግር ነው።
አቶ አንዳርጋቸው ጽጌም የኢሕአዴግ አባል በነበሩበት ወቅት በ1985 ዓ.ም. ባሳተሙት “የአማራ ሕዝብ ከየት ወዴት?” በሚለው መጽሐፋቸው ላይ ቅይጥ ማንነት ያላቸውን ሰዎች “የማንነት ቀውስ ያለባቸው፣ በብሔር ድርጅቶች ውስጥ አስጠቂዎች፣ ለዘብተኞች፣ ግራ የተጋቡና ከብሔር ማንነት ይልቅ ኢትዮጵያዊነትን የሚመርጡ ናቸው” በማለት ይኮንኗቸዋል። በሌላ አነጋገር ኢትዮጵያዊ ማንነት በትክክል የሚኖር ማንነት ሳይሆን ግራ የተጋቡ ቅይጥ ማንነቶች የፈጠሩት ምናባዊ ማንነት ነው እንደማለት ነው። አቶ አንዳርጋቸው በኢትዮጵያ ውስጥ ቅይጥ ማንነት እንዳለ ቢያምኑም ቁጥሩ ግን አጅግ አነስተኛ በመሆኑ ራሱን የቻለ የፖለቲካ ኃይል ሆኖ ሊወጣ አይችልም የሚል እምነት ነበራቸው።
በዚህ ኢሕአዴጋዊ ድምዳሜ ከሄድን ትክክለኛውና በኢትዮጵያ ሊኖር የሚገባው ፖለቲካ ባልተቀየጡ ማንነቶች የሚመራው የብሔር ፖለቲካ ነው ማለት ነው። አቶ አንዳርጋቸው በወቅቱ እንደዛ ያሉት የኢትዮጵያን ሕዝብ በኢሕአዴግ መነፅር ስላዩት ነው። ከኢሕአዴግ ከወጡ በኋላና የኢሕአዴግን መነፅር አውልቀው “ነፃነትን የማያውቅ ነፃ አውጭ” የሚለውን መጽሐፍ በ1997 ሲጽፉ ግን አቋማቸው ትክክል እንዳልነበረ አምነዋል። ራሳቸውንም የዚህ ቅይጥ ማንነት ተጋሪ መሆናቸውን ተናግረዋል።
ምንም እንኳ ኢሕአዴግ ለቅይጥ ማንነቴዎች ትኩረት ባይሰጥም፣ ይኽ ሕዝብ ያለው ቁጥር ግን በጣም ብዙና አብዛኛውን የአገሪቱን የተማረ ኃይል ያካተተ ነው፡፡ እናም ኢሕአዴግ ለዚህ ሰፊ ሕዝብ ዕውቅና ሲነፍግ በተዘዋዋሪ የአገሪቱ ዋነኛ የሰለጠነ ኃይል ላይ ነበር የፈረደው፡፡
ይኼንን ደግሞ በኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት ማግስት አቶ መለስ ዜናዊ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህራንን በሰበሰቡበት ወቅት አቶ ሙልጌታ ጉልማ ከተባሉ መምህር ተነግሯቸው ነበር፣ እንዲህ በማለት፣ “የብሔርን ነገር እንደ ማታገያ አድርጋችሁ ከሚገባው በላይ ስላጋነናችሁት ሰፊ ቁጥር ያለውን ቅይጥ ሕዝብ እንዳታዩ አድርጓችኋል፡፡ ሆኖም ግን ቴክኖክራቱና ቢሮክራቱ ያለው እዚህ ውስጥ ነው፡፡ የብሔር ፖለቲካው እንዳለ ሆኖ ይኼንን ቅይጥ ሕዝብ የምታስተናግዱበት ሥርዓት ጎን ለጎን ካልዘረጋችሁና የአገር ግንባታችሁ ላይ የማታሳትፉት ከሆነ አንድም ይሰደድባችኋል አሊያም በዝምታው ያምፅባችኋል፡፡” ነበር ያሉት፡፡
ሆኖም ግን ኢሕአዴግ ይኼንን የምሁራኑን ምክረ ሐሳብ ከመስማት ይልቅ ቅይጥ ማንነቴዎች የፖለቲካ ውክልና ለማግኘት የሚያደርጉትን ጥረት ሲያደናቅፍ ነው የኖረው፡፡ ኢሕአዴግ ቅይጥ ማንነት የፖለቲካ ኃይል ሆኖ እንዳይወጣ ላለፉት 27 ዓመታት ሦስት የማሸማቀቂያ ሥልቶችን ተጠቅሟል፤
አንደኛ፡- ከተሞችን የብሔርና የነፍጠኛ ከተሞች በማለትና ለሁለት በመክፈል፣ የቅይጥ ማንነት መፈጠሪያና ማናኸሪያ የሆኑ አካባቢዎችን “የነፍጠኛ ከተሞች” በማለት ማሸማቀቅ፣
ሁለተኛ፡- ይኽ ሕዝብ የፖለቲካ ውክልና ለማግኘት የሚያደርገውን ጥረት “በአንድነት ስም የተሸፈነ ስውር የአማራ አጀንዳ” በማለት ማሸማቀቅ፣
ሦስተኛ፡- ቅይጥ ማንነቴዎች በቀበሌ መታወቂያቸው ላይ ሳይቀር አንዱን ብሔር እንዲመርጡ ማስገደድ።
በእነዚህ ማሸማቀቂያ ስልቶች የተነሳ ላለፉት 27 ዓመታት ይኼ ቅይጥነትና ዝንጉርጉርነት እውቅና ተነፍጎት አንገቱን ደፍቶ የኖረ ቢሆንም፣ የዶ/ር አብይ መመረጥን ተከትሎ ግን ቀና ቀና ማለት ጀምሯል፡፡ ይኽ ሕዝብ በአብዛኛው ከተሞች አካባቢ የሚገኝ ሲሆን፣ እንደነዚህ ዓይነት ሰዎች በብሔርና አገራዊ ጥያቄዎች ላይ ማመቻመች (Compromise ማድረግ) የሚችሉ ናቸው። አሁን ኦሕዴድ ውስጥ ወደ አመራር የመጣው እንደዚህ ዓይነት ኃይል ነው። ዶ/ር አብይ ላይም የዘውግና ኢትዮጵያዊ ብሔርተኝነቶች ተስማምተውና ተዋሕደው እያየን ነው፡፡