
ኤርትራ ከኢትዮጵያ በመገንጠል ራሷን የቻለች ሃገር ከሆነች እነሆ 25 ዓመት ሆነ። ይሄ ታሪካዊ ሕዝበ-ውሳኔ ተካሂዶ የነበረው በዚህ ሳምንት ነበር።
ሕዝበ-ውሳኔው የአካባቢውን መልክአ ምድራዊ ገፅታ ከመቀየር ባሻገር ለተለያዩ በርካታ ክስተቶች በር ከፍቷል። ሕዝበ-ውሳኔውን ተከትሎም በነበሩት ዓመታት ጉዳዩ ከውይይት ጠረጴዛ ሳይነሳ ሲያነጋግር አሁን ድረስ ዘልቋል።
በተለይ ሁለቱ ሃገራት ለዓመታት የዘለቁበት ደም አፋሳሽ ጦርነት ሲቀሰቀስ ሕዝበ-ውሳኔው የኤርትራን ይፋዊ ነፃነት ከማስገኘት ባሻገር ፍቺው በተገቢው ሁኔታ ያለመፈፀሙ ውጤት ነው የሚሉ አሉ።
ሕዝበ-ውሳኔው ከተካሄደ ከ25 ዓመታት በኋላ ዛሬ ኤርትራ ከኢትዮጵያ የተለየችበት መንገድን በሚመለከት አሁንም በሁለቱ ሃገራት ዜጎች የተለያየ አስተያየቶች ይንፀባርቃሉ።
ኤርትራ ከኢትዮጵያ በይፋ የተለየችበት ሕዝበ-ውሳኔ እስካሁን ድረስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ መነጋገሪያ እንደሆነ ነው።
በሕዝበ-ውሳኔው ተሳትፈው የነበሩ ኤርትራዊያንም ነፃ ሃገር መመስረታቸውን ቢያምኑም በሃገሪቱ ውስጥ ያለው ሁኔታ ለሕዝቡ ሙሉ ነፃነትን በማጎናፀፉ ላይ ጥያቄ አላቸው።
ሕዝበ-ውሳኔውን ደግፈው ከተሳተፉት ኤርትራዊያን መካከል እጋእት ሃዲሽ አንዷ ነች። እርሷም ከነመላው ቤተሰቧ ሕዝበ-ውሳኔውን የደገፈችው በሙሉ ልቧ እንደነበር ትናገራለች።
በዚያ ወቅት የ17 ዓመት ታዳጊ እንደነበረች የምታስታውሰው እጋእት ድምጿን ለመስጠት ስትል በእድሜዋ ላይ አንድ አመት ጨምራ በሕዝበ-ውሳኔው ለመሳተፍ ትላለች።
“ሕዝበ-ውሳኔው በተካሄደበት ጊዜ ከቤተሰቦቼ ጋር ሱዳን ውስጥ ነበትርኩ። ከልጅነቴ ጀምሮ ያሳለፍኩት መከራ ከባድ ስለነበር ነፃነት ለእኔ ትልቅ ቦታ አለው። ሕዝበ-ውሳኔው ከጨለማ ወደ ብርሃን የመውጣት ያህል ስለነበር ደግፈነዋል” ስትል ወቅቱን ታስታውሳለች።
ለኤርትራ ነፃነት ድምፅ መስጠታቸው እንዳማይቆጫቸው የሚናገሩት ሌላው በሕዝበ-ውሳኔው የተሳተፉ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ ግለሰብ አሁን በሃገሪቱ ባለው ሁኔታ ደስተኛ እንዳልሆኑ ግን ይናገራሉ።

“በዚያ ጊዜ ብዙዎቻችን ነፃነትን ለማግኘት የነበረን ጉጉት ከፍተኛ ስለነበር ደስታችን ወደር አልነበረውም። ነገር ግን ከነፃነት በኋላ ሰላሟና ኢኮኖሚዋ የጠነከረ ኤርትራን ለመገንባት ሙከራ የተደረገ ቢሆንም፤ ቀስ በቀስ ግን ነገሮች እየተወሳሰቡ መጥተው ነፃነት ትረጉሙን አጥቷል። ለዚህ ነው በርካቶች ነፃነትን መምረጣችን ያስገኘልን ነገር ምንድን ነው? በማለት እየጠየቁ ያሉት” በማለት ከነፃነት በኋላ ያለው ሁኔታ ጥያቄ ውስጥ መውደቁን ያመለክታሉ።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካል ሳይንስ መምህር የሆኑት ዶክተር ያዕቆብ አርሳኖ ደግሞ ሕዝበ-ውሳኔው ሕዝብን ያላካተተ የሁለት ኃያላን ውሳኔና ስምምነት ነው በማለት ይናገራሉ።
የኤርትራ ሕዝበ-ውሳኔ ሲካሄድ ለዚህ የሚሆን የአደባባይ ውይይትም ሆነ ለዚህ የሚያግዝ ዝግጅት እንዳልነበረ የሚናገሩት ዶክተር ያዕቆብ ሂደቱ “ሕዝብን ያላሳተፈና ሁለቱ ሃገሮች በአንድ ላይ ሊተዳደሩበት የሚችሉበት አማራጭ ሥርዓት ምን መሆን እንዳለበት ምንም አይነት መክክር ያልተደረገበት የአሸናፊዎች ውሳኔ ነው የሚመስለው” ይላሉ።
በኢትዮጵያ የሚኖሩትና በሁለቱ ሃገራት መካከል ሰላም ለመፍጠር ጥረት እያደረገ ያለው ኮሚቴ ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ይስሃቅ ዮሴፍ ሕዝበ-ውሳኔው የኤርትራን ሕዝብ ፍላጎት ያማከለ ነበር ይላሉ።
ለሕዝበ-ውሳኔው እንኳን በቂ ዝግጅት እንዳልተደረገ የሚያምኑት አቶ ይስሃቅ “ሕዝቡ ከከፈለው መስዋዕትናት አንፃር በዚያ ወቅት የነበረው ስሜት ሲታይ ሂደቱን ወደኋላ መመለስ የሚቻል ነገር አልነበረም።”
ሕዝበ-ውሳኔው በተካሄደበት ሁኔታ እንዲፈፀም ሙሉ ፈቃደኝነትና ድጋፍ ያደረገው የኢትዮጵያ መንግሥት የሃገሩን ብሔራዊ ጥቅም የሚያስጠብቁ ጉዳዮችን በወቅቱ ባለማንሳቱ በበርካቶች ዘንድ ወቀሳ ይሰነዘርበታል።
በወቅቱ የገዢው ፓርቲ ዋነኛ አባል የሆነው የህዝባዊ ወያኔ ሃርነት ትግራይ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል የነበሩት ወይዘሮ አረጋሽ አዳነ፤ ሕዝበ-ውሳኔው የሁለቱን ሃገራት ሕዝቦች ቀጣይ ጥቅም ከግምት ውስጥ ያስገባ እንዳልነበር ያምናሉ።
ሕዝበ-ውሳኔው ከመካሄዱ በፊት ሁለቱ ሃገራት የተለያዩበት መንገድ በአግባቡ የተካሄደ እንዳልነበረ የሚያምኑት ወይዘሮ አረጋሽ “ሕዝበ-ውሳኔው ከኢትዮጵያ በኩል ያለውን አስተያየትና የሕዝቡን ሙሉ ፍላጎት መሰረት አድርጎ የተካሄደ አልነበረም” ይላሉ።
ኤርትራዊያን የዛሬ 25 ዓመት ለአስርታት ከተደረገ ጦርነት በኋላ በተደረገው አነጋጋሪ ሕዝበ-ውሳኔ ነፃነትን መርጠው የራሳቸውን ሃገር ሲመሰርቱ በአካባቢው የነበረው የእርስ-በርስ ጦርነት መቋጫ እንደሚያገኝ በበርካቶች ዘንድ ታምኖ ነበር።
ነገር ግን ከሕዝበ-ውሳኔው አምስት ዓመታት በኋላ አሁን ድረስ መቋጫ ወዳላገኘው ወደ ሌላ ደም አፋሳሽ ጦርነት ሁለቱ ሃገራት ሲገቡ ነገሩ የበለጠ እንቆቅልሽ ሆኖ ነበር።
ሦስት አስርታት ለሚጠጋ ጊዜ ስልጣን ላይ ያለው ገዢው ፓርቲና መሪዎቹ በተቃዋሚዎቻቸው ከሚተቹባቸው ጉዳዮች መካከል የኤርትራን ጉዳይ የያዙበት መንገድ አንዱ ነው። ይህ ጉዳይም አሁን ድረስ በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ላይ ዋነኛ አወዛጋቢ ርዕስ ሆኖ ዘልቋል።
SOURXE – BBC/AMHARIC