April 25, 2018
(ጌታቸው ሺፈራው)
በተደጋጋሚ በግንቦት 7 የሚከሰሱት እስረኞች የሚገጥማቸውን ችግር እንፅፋለን! 90 በመቶ የሚሆኑት የአማራ ተወላጆች ናቸው። እነዚህ እስረኞች “በኢትዮጵያዊ” አቋማቸው ነው የታሰሩት የሚሉ እና በ”አማራነታቸው ነው።”የታሰሩት የሚል አካልም አለ። ከሁለቱም አካል ዘወር ብሎ የሚያያቸው ጥቂት ነው። በተለይ በስማቸው፣ ፎቷቸው እየሸጠ የተጠቀመበት ደግሞ እንዳለ ሲሰማ ይበልጡን አሳዛኝ ያደርገዋል።
በቅርቡ በኦነግ ተከስሰው ከተፈቱት መካከል ደስ የሚል እውቅና የተደረገላቸው አሉ። ከችሎት ጀምሮ አስደማሚ አጋርነት ያገኘው የሙስሊሙ ኮሚቴ አባላትም ተሸልመዋል። በእስር ቤት እያለ የሚገባውን ባያገኝም አንዱዓለም አራጌ በቅርቡ ተሸልሟል። ይበል የሚያሰኝ ነው! ግሎባል አሊያንስ በቅርቡ ለተፈቱት፣ እንዲያውም ማንም ለማያቋጥራቸው ይበል የሚያሰኝ ስራ ጀምሯል።
እውነቱን ለመናገር በእስር ቤት ታጉረው የቆዩት የትግሉ ምልክት ናቸው። የተሸለሙት ቢያንስባቸው እንጅ አይበዛባቸውም። የተሸለሙት እጅግ በጣም ቢያንሱ ነው እንጅ ብዙዎች አይደሉም። ከምንም በላይ የትግሉ ዋና ምልክት ከተባሉት መካከል የተረሱ መኖራቸው ነው። 9 አመት ታስረው የተፈቱት እነ ጀኔራል ተፈራ ማሞ ይህ ነው የሚባል ነገር ተደረገላቸው ሲባል አልሰማሁም። በእርግጥ ሲታሰሩ ይደረግልናል ብለው አይደለም። ነገር ግን በእስሩ ወቅት ቤተሰባቸው ችግር ውስጥ ወድቋል። የሚገባቸውን ያህል ትኩረት አላገኙም። ከተደረገላቸው ለተጎዳው ቤተሰባቸው ብቻ አይደለም። ታስረው እያለም የትግሉ አንድ መዘውር እንደነበሩ ሁሉ ወደፊትም የበኩላቸውን ያደርጉ ዘንድ ስለሚቀጥለው ወር ኪራይ፣ ስለ ቤተሰብ ቀጣይ የኑሮ ሁኔታ በማሰብ መጠመድ አይገባቸው። እነሱ ትግሉን ሲይዙ፣ ትግሉ ያለው፣ የሌለውም የበኩሉን ሲያደርግ እንደ ስራ ክፍፍል እንጅ ችሎታ አይደለም። የስራ ክፍፍል ተደርጎ መታየት አለበት።
በተለይ አሁን ላለው ትግል ትልቅ ምሳሌ የሆኑት ሳይቀር ትኩረት አጥተዋል። በእነሱ ስም እየታገለ፣ ከዛም ሲያልፍ ፎቷቸውን እየሸጠ ያለ አካል ግን ምንም አይነት ትኩረት የለውም። እነዚህ ሰዎች ገቢ የላቸውም። የቆዩት በእስር ቤት ነው። ተዘዋውረው አይሰሩም። ከአደጋው ባሻገር ስራቸው ትግል ሆኗል። የቤት ኪራያቸውን፣ የልጆቻቸው ትምህርት፣ የቤተሰቡን ኑሮ ወጭ ማን እየሸፈነላቸው ይኖር ይሆን ብሎ የሚጨነቅ ይኖር ይሆናል። ተጨንቆ የሚገባውን የሚያደርግ ግን እጅግ በጣም ጥቂት ነው። ያውም በሌለ አቅሙ። አቅም ያለው፣ እገዛ ሊያደርግ የሚገባው አካል እገዛ አደረገ ሲባል አይሰማም።
ሌላው ይቅር ኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ይኖርበት የነበረው ቤት በሕዝብ ላይ ለሚፈፀም በደል ትልቅ ምልክት ነው። ይህ ቤት በሕዝብ ላይ ለተፈፀመው ብቻ ሳይሆን ሕዝብ ከገዥዎች ጋር ላደረገው ትንቅንቅም ጭምር ትልቅ ምልክት ነው። ይህ ቤት በሙዝዬምነት መቀመጥ የነበረበት ቤት ነው። ይህ ቤት በአንድ ስብሰባ ከተሸጠ የኮ/ል ደመቀ ፎቶ ያነሰ እንጅ የሚበዛ ዋጋ አያወጣም። ነገር ግን እስካሁን የተሰራ ስራ የለም። ከኮ/ል ደመቀ ዘውዱ ባሻገር በዛ ተጋድሎ ወቅት የተሰዋው የሲሳይ ታከለ ቤት ለሽያጭ ሊቀርብ ነው። ማን ሊገዛው እንደሚችል ግን ግልፅ ነው። በአካባቢው ሕዝብ ስም የተቋቋመ ድትጅትና ማህበር ሳይቀር አንድ ጥይት ተተኮሰ ሲባል ፌስቡክ ላይ “ጎንደር ቆርጦ ተነሳ!” እያለ ፌስ ቡክ ላይ ከመለጠፍ፣ በፎቷቸው በመቶ ሺህ ዶላሮች ሲሰበስብባቸው የነበሩት እስረኞች ሲፈቱ “የእኛ ጀግኖች” ከማለት ውጭ ለጀግኖቹ የረባ ነገር አድርጎ አያውቅም። እንዲያውም ነገደባቸው ማለት ይቀላል።
በሌላ በኩል ሀገር ውስጥ ያለው ባለሀብትም ሆነ አቅም ያለው ድል የምትባል ስትገኝ ፊት አውራሪ ከመምሰል ውጭ በሚያስፈልግበት ጊዜ እየተገኘ አይደለም።
ይህን የምለው የትግሉ ቀንዲል የሆኑት በቅርቡ የተፈቱ ሰዎች ጥቃቅን ወጭዎች እንኳ በእነዚህ ሰዎች ስም ብዙ የተጠቀሙ፣ ወይንም አቅም ያላቸው እያሉ የራሳቸውን ህይወት ጎድተው ትልቅ ሸክም የወደቀባቸውን የተወሰኑ ሰዎች በማየቴ ነው። እንዲያው አንድ ቀን ኃፍረቱ በተግባር፣ በአባባይ ከመገለፁ በፊት ሀፍረት የሚሰማው ከተገኘም በሚል ነው።
ከዚህ ሲያልፍ ግን በእነዚህ ጀግኖች ስም የነገዱ አካላት የሰበሰቡት ለእነሱ ባይደርስም በጀግኖቹ ስም ገንዘብ የከፈለው ሕዝብ እንዲጠይቃቸውም ጭምር ነው! ምን አልባት ተፈችዎቹ በስብዕና በመግነናቸው ምንም የማያጡ የሚመስለው የየአካባቢያቸው ሕዝብም የበኩሉን አድርጎ ትግሉ እያለ ሊብከነከኑበት ስለማይገናው የኑሮ ሁኔታ እገዛ ሊያደርግ ስለሚገባ ነው።
በመጨረሻም የሚጠበቀውና አደርጋለሁ የሚለው ሁሉ ፍሬ ቢስ ከሆነ ሀገር ውስጥ ያለው ሕዝብ የሚችለውን አዋጥቶ የኮ/ል ደመቀ ዘውዱን ቤት ምልክት ሆኖ እንዲቆይ ማድረግ ያለበት ይመስለኛል። ሁሌ ሲያፍር ከመኖር ቢያንስ አንድ ቀን፣ አንድ ሳምንት፣ አንድ ወር ቢቸገር ነው!
(ፎቶው የጎንደር ነዋሪ የሆነ የቀን ሰራተኛ ያለችውን 50 ሳንቲም ሲያበረክት የሚያሳይ ነው። ይህን አይቶ እንኳ የማያፍር ይኖራል። ከኮ/ል ደመቀ ፎቶ ሽያጭ ካገኘው ባሻገር ይህን የመሰሉ የቀን ሰራተኞችም 50 ቢለቅም ደስ የሚለው ይኖራል። ለእነዚህ ሁሉ ማፈር ሊኖርብን ነው!)