April 25, 2018
ከጌታቸው ሽፈራው
~”የጤናዬ ሁኔታ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ ህይወቴ አደጋ ላይ ወድቋል”
~” ወደ ሽንት ቤት ለመሄድ በጣም በመቸገሬ፣ ውሃና ምግብም በአግባቡ ባለማግኘቴ በስቃይ ውስጥ እገኛለሁ።”
(በማዕከላዊ ጉዳት ደርሶበት በሕመም ላይ የሚገኘው ዮናስ ጋሻው ለፍርድ ቤት ካቀረበው አቤቱታ የተወሰደ)
ለፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ
19ኛ ወንጀል ችሎት
አዲስ አበባ
ቀን 18/07/2010 ዓም
ተከሳሽ ዮናስ ጋሻው ደመቀ
ጉዳዩ:_ በቂ ሕክምና እንዳገኝ ስለመጠየቅ
ተከሳሽ ማዕከላዊ በደረሰብኝ ድብደባ እና የአካል ጉዳይ ምክንያት ለተደራራቢ ሕመም በመዳረጌ፣ ሕክምናውም ከማረሚያ ቤቱ አቅም በላይ በመሆኑ ቃሊቲ፣ ቪዥን፣ ጳውሎስ፣ በፖሊስ ሆስፒታል እና በዘውዲቱ ሆስፒታል ህክምና ባዳርግም የጤናዬ ሁኔታ ባለመሻሻሉ ወደ ውጭ ሀገር ሄጄ እንድታከም ቢነገረኝም ያለሁበት ሁኔታ አመች ባለመሆኑ በዘውዲቱ ሆስፒታል ሆኜ ህክምናዬን እንድከታተል ፍ/ቤቱ ለማረሚያ ቤቱ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር። ሆኖም ዘውዲቱ ሆስፒታል ሆኜ እንድታከም የተሰጠው ትዕዛዝ ተፈፃሚ አልሆነም።
ከዚህ በተጨማሪ በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል በቀን 27/04/2010 ዓም የተሰጠኝ MRI ውጤት በቀን 2/05/2010 ዓም ለማረሚያ ቤቱ አስረክቤያለሁ። ዘውዲቱ ሆስፒታል በቀን 18/05/2010 ዓም የተነሳሁትን የMRI ውጤት እንዲላክልኝ፣ ይህ ካልሆነ ግን የህክምና አገልግሎት ለመስጠት እንደማይችል በተደጋጋሚ ቢጠይቅም ማረሚያ ቤቱ ውጤቱን ለሆስፒታል ሊልክልኝ ባለመቻሉ ሕክምና ማግኘት አልቻልኩም።
የዓለም ቀይ መስቀል ማህበር ማረሚያ ቤቱ ውስጥ ክትትልና ድጋፍ በሚያደርግበት ወቅት የጤናዬን ሁኔታ ካየ በኋላ ውጭ ሀገር ሄጄ መታከም እንዳለብኝ ነግረውኛል። ማረሚያ ቤቱ አንዳንድ ነገሮችን ማለትም ክራንች፣ ዊልቸር፣ የሽንት ቤትና ቤት ውስጥ የምቀመጥባቸው ወንበሮች እንዲያሟላልኝ ትዕዛዝ የሰጠ ቢሆንም ማረሚያ ቤቱ በፍርድ ቤት ትዕዛዝ መሰረት አላሟላልኝም። ዘውዲቱ ሆስፒታል የሚፈልገው የMRI ውጤት ባለመላኩም የጤናዬ ሁኔታ ከዕለት ዕለት እየተባባሰ ህይወቴ አደጋ ላይ ወድቋል። ከዚህ በተጨማሪ ወደ ሽንት ቤት ለመሄድ በጣም በመቸገሬ፣ ውሃና ምግብም በአግባቡ ባለማግኘቴ በስቃይ ውስጥ እገኛለሁ።
በመሆኑም ፍርድ ቤቱ ያለሁበትን ሁኔታ ተረድቶ የMRI ውጤቱ ከማረሚያ ቤቱ ወደ ዘውዲቱ ሆስፒታል በአስቸኳይ እንዲላክልኝ፣ ከህመሜ እድን ዘንድም ፍርድ ቤቱ ከአሁን ቀደም ማረሚያ ቤቱ እንዲያሟላልኝ ያዘዘልኝ ዊልቸር፣ ሽንት ቤትና ቤት ውስጥ የምቀመጥባቸው ወንበሮች እንዲሟሉልኝ በድጋሜ እና አፋጣኝ ጥብቅ ትዕዛዝ እንዲሰጥልኝ እጠይቃለሁ!
(የመጀመርያው ፎቶ ከመታሰሩ በፊት የተነሳ ሲሆን ሁለተኛው ማዕከላዊ በድብደባ ከተጎዳ በኋላ ወደ ፍርድ ቤት ሲሄድ የተነሳ ነው። በመጀመርያው ፎቶ ያነሳው እግሩ ማዕከላዊ ከገባ በኋላ በድብደባ ተጎድቷል)