April 25, 2018
ከዲ/ን አባይነህ ካሴ
እኒህ አባት ደጋግመው ይናገራሉ፡፡ የከንፈራቸውን ሳይኾን የአንጀታቸውን፡፡ ለበጎቻቸው ወግነው መንግሥትን ከእነወታደሩ ሲገስጹ ዐይተናል ሰምተናል፡፡ እውነትን ለመከላከል ብቁ መንፈሳዊ ትጥቃቸውን እንደታጠቁ ያሉ አንደበተ ርቱዕ! ፍሬ ከናፍራቸው ስንቱን እንደፈወሰ ጊዜው አልራቀምና ከዐይናችን ሥር ይገኛል፡፡ አቡነ አብርሃም በባሕር ዳር መስቀል አደባባይ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር በድቅድቅ ጨለማ ውስጥ እንደፈነጠቀ ብርሃን ታይቶናል፡፡ የምንኩስና ግብሩን አስመልክተውናል፡፡ ያን ጊዜ የብዙዎች ልብ እረፍት እንዲያገኝ መድኃኒት ኾነው በሽታችንን ሽረውልናል፡፡ ከአድማስ አድማስ የሚሰማ ቃላቸው የሰማዩን አድማስ ከድኖት ነበረ፡፡ ተስፋ ሊቆርጥ ለነበረው ኦርቶዶክሳዊ የተስፋ ገመዱ የመነመነች ስትመስል ፈጽሞ የማትበጠስ መኾኗን አብሥረውልናል፡፡ በዚያ የተስፋ በር እየተመላለስን ስንኮራ አቡነ ኤርምያስ የተባሉ ጀግና ተወልደው ወልዲያ ላይ የአንበሳ ጣሕር አሰሙን፡፡ እነዚህ ኹለት አባቶች እንደ ተራራ የገዘፈውን በወታደር ያጌጠውን የጊዜውን መንግሥት ሲገስጹ በእጃቸው ያለው መስቀላቸው ብቻ ነው፡፡
ከመስቀል በላይ ተራራ የለምና እነርሱ ተራራው ላይ ናቸው፡፡ አሁንም ከተራራው ራስ እንዳልወረዱ የሚያረጋግጥ ቃል በአዲሱ ሹም ጠቅላይ ሚንስትር ፊት እንደ ሱራፊ ሰይፍ የሚንበለበል ቃላቸውን አዝንበውታል፡፡ ተጽፎ የተሰጣቸውን አይደለም፡፡ መንፈስ ቅዱስ ያቀበላቸውን አሰምተውናል፡፡ በወጉ በሥርዓቱ ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድንም በአቡናዊ ሥልጣን እግዚአብሔር ይባርክልኝ ብለውታል፡፡ የእርሳቸው ቃል ብዙ ሰበዞች እንደሚቀልሱት የሣር ክዳን ነው፡፡ እያንዳንዷ ሰበዝ ተስተካክላ ሥፍራዋን ስትይዝ ጣራው ቅርጽም፣ መልክም፣ ግርማም፣ ክዳንም ይኖረዋል፡፡ ንግግራቸው እንደዚያ የተሳካ፣ በስፍራ በስፍራው የተሰደሩ ቃላት እንደ ነቅዐ ማይ ፉል ፉል እያሉ ከአንደበታቸው ሲወጡ ሰምተናል፡፡ ከውኃ ምንጭ ግሩም ሰላማዊ እንጅ ለጆሮ የሚቆረቁር ድምጽ አይሰማም፡፡ ዐይንን ከድኖ የውኃ ምንጭ ሥር ጆሮን ቀስሮ ድምጹን የመስማት ዕድል ቢያጋጥም የሚሰማው ሰላም እንዴት ግሩም መሰላችሁ! መገፋፋት፣ መፋተግ፣ መታመስ፣ መተራመስ የሌለበት ሁሉም ተራውን ጠብቆ ባማረ ሰልፍ የሚወጣበት ሥርዓት አለ፡፡
ዘፈን ሲዘፈን እጅ ለእጅ ከሸኪው ጋር ተያይዞ በዘፈን ስሜት ሲመሩ ላየናቸው ፓትርያርክ ከዚህ በላይ አስተማሪ ነገር አይኖርም፡፡ ለዘፈን የሚነሣ ፓትርያርክ ከወዴት እንዳመጣን እንጃ፡፡ ሰው ሁሉ ያደረገውን ማድረግ የመሪ ተግባር አይደለም፡፡ መሪ የራሱን ተግባር በመፈጸም ሌላው እንዲከተለው ያደርጋል እንጅ፡፡ እርሱን ዐይተንና ሰምተን ቅጭም ብለን ሳለን ያንን የሚያስረሳ ደገኛ ሥራ ከአባ አብርሃም አገኘን፡፡ ኹለቱም በጠቅላይ ሚንስትሩ ፊት የተደረጉ ናቸው፡፡ ይሁን እንጅ ዝቅ ያለውን አነውረን የሚበልጠውን ይዘን እንቀጥላለን፡፡
የአቡኑን ንግግር በአምስት መድበን ልንመለከታቸው እንችላለን፡፡ በየራሳቸው ብዙ እምቅ መልእክት ናቸው፡፡ ግን ደግሞ ይያያዛሉ፡፡ ተደጋጋፊነታቸው ለጠቅላይ ሚንስትሩ አንድ ወጥ እና ሙሉ መልእክት እንዳስተላለፉ ያሳያል፡፡ ቀና እንድንል ቀና ብሎ የሚሔድ የተናገረውን በማስተዋል ማየት ይገባል፡፡ አንድ በአንድ እንመልከታቸው፡፡
፩. የደግና የክፉ መሪዎች አነሣስ በቅድመ እግዚአብሔር
“እግዚአብሔር ሲሾም ኹለት ዓይነት ነው” ብለው ክፉውን መቼ ደጉንም መቼ እንደሚያስነሣው ለጠቅላይ ሚንስትሩ ይነግሩታል፡፡ ሕዝብ ሲበድል ከአምልኮተ እግዚአብሔር ፈቀቅ ሲል በእርሳቸው ቃል “ለጅራፍነት፣ ለአለንጋነት” ይሾማል ብለዋል፡፡ ሕዝብ ለፈጣሪው ሲገዛ ደግሞ “የሚቆረቆርለትን፣ አለሁ የሚለውን ይሾማል” በማለት ኹለቱን አጥናፍ ያገናዝባሉ፡፡ ይህ አባባል ሦስት አካላትን ያስተሳሥራል፡፡ ሕዝብን፣ መሪን እና እግዚአብሔርን፡፡ በዚህ ቃለው ብቻ አቡኑ ኹለት መልእክታትን ለጠቅላይ ሚንስትሩ አስተላልፈዋል ብዬ አምናለሁ፡፡
ሀ. የሕዝቡ ውጤት ነዎት ማለታቸው ነው
ጠቅላይ ሚንስትሩ በብቃቴ፣ በዕውቀቴ፣ በሀብቴ፣ በቁመናዬ ወዘተ ብለው ሌላ ምድራዊ አስተሳሰብን እንዳይከተሉ የገደቡበት ቃል ነው ብሎ ማሰብ ይቻላል፡፡ ደግም ቢኾኑ ክፉ ስለ ሕዝቡ እግዚአብሔር የሾመዎት እንጅ በራስዎ የመጡ አይደሉም፡፡ የእርስዎ ምክንያተ ሲመት የትኛው እንደኾነ የሚታወቀው በሕዝቡ ምግባርና ገጽታ ነው፡፡ ስለዚህ ሕዝቡን ሲያዩ ራስዎን ያያሉ ማለታቸው እንደኾነ መገመት አያዳግትም፡፡ በሌላ ቃል ሕዝቡ ለጠቅላይ ሚንስትሩ መስታወታቸው መኾኑን ያመላክታል፡፡ እርግጠኛ መኾን የሚቻልበት አንድ ነገር ቢኖር ጠቅላይ ሚንስትሩ ሕዝቡን እንደገና ማየት እንዲጀምሩ የሚገፋ ቃል መናገራቸው ነው፡፡ ብልኅ መሪ ከኾኑ መላልሰው ያጤኑታል፡፡ ጊዜ ወይም ፋታ ሲኖራቸው ጠቅላይ ሚንስትሩ የአቡኑን ቃል ደጋግመው ቢያዳምጡት ብዙ ያሻግራቸዋል፡፡
ለ. ለየትኛው ነው የተሾምሁት ብለው እንዲጠይቁ ያስገድዳቸዋል
በዚህ የደግ እና ክፉ መሪዎች አነሣስ አቡነ አብርሃም ለጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንን ኹለተኛ ቃል አስተላልፈዋል፡፡ እርሱም ሁል ጊዜ “እኔ የተሾምሁት ለየትኛው ነው” እያሉ እንዲጠይቁ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህንን መጠየቅ ለማረምም ኾነ ለማዳበር ይዳርጋል፡፡ ሕዝቡን ጠጋ ብሎ መጠየቅን፣ ማወቅን፣ ማገናዘብን ያስከትላል፡፡ እንደ አብዛኞቹ መሪዎቻችን እና ባለሥልጣኖቻችን ከሕዝብ ተነጥለው እንዳይኖሩ ያስወድዳል፡፡
መሪ ባሕታዊ አይደለም፡፡ ከመንጋው ተለይቶ የሚጠብቅ እረኛም የለም፡፡ ውሎውና አዳሩ ከሕዝቡ ጋር መኾን አለበት፡፡ እስከዛሬ በሕዝቡና በመሪዎች መካከል ከባድ ገደል ሲቆፈር ኖሯል፡፡ ስለዚህም መሪዎች በስማ በለው እንጅ ከሕዝቡ ጋር የመኖር ዕድል አልገጠማቸውም፡፡ እንደተነጠሉ ኖረው ይሔዳሉ፡፡ እምዬ ምኒልክ “እምዬ” እስከመባል የደረሱት ከሕዝቡ ጋር ለመኖር ባደረጉት ረቂቅ የጥበብ አመራራቸው መኾኑን ልብ ይሏል፡፡ በሕዝብ ልብ ውስጥ ለመኖር፣ ከሕዝብ አለመነጠል ብቸኛው መንገድ ሳይኾ አይቀርም፡፡ አቀባባዮች በሕዝብና በመሪ መካከል ሲገቡ ግን ገደሉ እየሰፋ መቀራረብ ቀርቶ ጠላትነት “ይበለጽጋል”፡፡ አባታችን ይህ እንዳይመጣ አስቀድመው መምከራቸውን እንገነዘባለን፡፡
፪. ኢትዮጵያዊነታቸውን አሞግሰዋል
ጠቅላይ ሚንስትሩ ኢትዮጵያዊነትን የሰበኩባቸውን መንገዶች ሊቀ ጳጳሱ አሞግሰው አድንቀውላቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን በወርቃማ ቃላት፣ ኅብረ ቀለማትን በተላበሱ ቃላት፣ እንደ ሠንሰለት ተሳሥረው እንደ ሐረግ ተመዝዘው፣ አንዳቸው በአንዳቸው ላይ የቆሙ ቃላትን እና ዐረፍተ ነገሮችን እየተጠቀሙ መስበካቸውን መስክረውላቸዋል፡፡ እንዲያውም አባባላቸውን ውብ ብለው አሞካሽተውቸዋል፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ከፍ አድርገው ገልጸዋል በማለትም ያደንቋቸዋል፡፡ ይህም ስለኾነ “እግዚአብሔርን አመሰግነዋለሁ” በማለት ፈጣሪያቸውን ተመልከተዋል፡፡
ኢትዮጵያዊነትን ተጸይፎ የኢትዮጵያ መሪ የኾኑ ባየንባት ምድር ኢትዮጵያዊነትን እየሰበኩ የኢትዮጵያ መሪ ማየት በጣም ደስ ይላል፡፡ ኢትዮጵያ ፍልስፍና እንጅ አንዲት ተራ ምድር አይደለችም፡፡ ቅዱሳት መጻሕፍት ሁሉ በልዩ ዐይን ይመለከቷታል፡፡ በጎቹን እየጠላ የበጎች እረኛ እንዴት መኾን ይቻላል? በጎቹን የሚጠላ በበጎቹ ላይ አዛዥ ናዛዥ ይኾናል እንጅ እረኛ አይኾናቸውም፡፡ የጠበቀ መስሎ አስሯቸው ይኖራል፡፡ እነርሱ የፈለጉትን ሣር ሳይኾን የራሱን ገለባ ይመግባቸዋል፡፡ ሳይወድዱ ይገዙለታል እንጅ እረኛቸው አይደለም፡፡ አዎ እንደዚህ የሚመስሉ መሪዎች ነበሩን፡፡ እኒህኛው ከእነዚያ ተለይተው ቴዎድሮስነትን ከጠፋበት ፈልገው አግኝተውታል፡፡ የመይሳው ሕልም የኢትዮጵያ አንድነትን እና ልዕልና ነበርና፡፡ ዮሐንስነትም አላቸው በመተማ በኩል የጠፋብንን ድንበር ለማስከበር ቃል ገብተዋልና፡፡
ብዙ ጊዜ “ኢትዮጵያዊነት” ተቀብሮ እንዲቆፈር ሙከራ ተደርጓል፡፡ ኢትዮጵያ በዚህ በዘመነ ትንሣኤ ስትነሣ እንዴት ያስደስታል፡፡ አቡኑ ይህንን የቆየ ሽምቅ ሥራ ያውቃሉ፡፡ ስላወቁም የጠቅላይ ሚንስትሩን “የኢትዮጵያዊነት” መዝሙር በቀላሉ ሊያልፉት አልፈለጉም፡፡ ይቀጥሉበት ብለው ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ ለኢትዮጵያችን ቃል ቢያጥረንም ቃል ፈጥረን እንናገር ዘንድ ይገባል፡፡ ኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና ነው፡፡ ከድንበር አልፎ መንፈስ ከኾነ ውሎ አድሯል፡፡ የዓለምን የጭቆና አገዛዝ ገርስሶ፣ ገዝግዞ የእኩልነትን ሥልጣን ያጎናጸፈ፣ እኔ ልብለጥ የማይል የመከባበር አፍላጋት ምንጭ ነው፡፡ ዓለም ከዚህ ምንጭ ጠጥቶ ከተጣባው በሽታ ቢወድድም ባይወድድም ተፈውሷል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያዊነትን ለሚዘምር ሙገሳ ሲያንሰው ነው፡፡
የአፋሩን አሊ ሚራ ንግግር ጠቅሰዋል፡፡ አቡን ነኝ ብለው በኾነ አጥር ውስጥ ሳይከለሉ ሙስሊሙን መሪ በኢትዮጵያዊነት ጉዳይ ሲጠቅሱ አላነቀፋቸውም፡፡ ኢትዮጵያ የሁላችንም ናት ማለታቸው በዚህ ይታወቃል፡፡ እናም እኒያ ታላቅ መሪ “ኢትዮጵያን እንኳን እኛ ግመሎቻችንም ያውቋታል ከእነ ባንዲራዋ” ብለዋል አሉ፡፡ አዎ እኒያ መሪ ግመሎቹ ድንበራቸው ቀይ ባሕር መኾኑን ያውቃሉ ሲሉ እኛም ሰምተናል፡፡ አቡነ ይህን ማስታወሳችው ይኾን? ቀይ ባሕር ስሙን ኢትዮጵያዊ እንዳደረገ ርቆን እንዳይቀር አሰብን አስበዋታል አቡኑ፡፡
ኢትዮጵያዊነትን የማያውቅ ትውልድ አሁን እየተፈጠረ ነው ሲሉም ያክላሉ፡፡ በዚህ ትውልድ መካካል ብቅ ያሉት እርስዎ እንዲህ ኢትዮጵያዊነትን እየሰበኩ ትውልዱ እንዲፈወስ ያድርጉ ማለታቸው ነው፡፡ ኢትዮጵያ ለማለት ኢትዮፕያ የሚል ትውልድም በዝቶብናል፡፡ ሀገሩን በአግባቡ የማይጠራ ትውልድ መጥቶብናል፡፡ የተፀውዖ ስም አይቀየርም፣ አይለወጥም፡፡ ኢትዮጵያ ማለትን ከማለማመድ የምንጀመርበት የትውልድ ቀረጻ ያስፈልጋል ሲሉ አቡኑ መናገራቸው ሳይኾን እንዳልቀረ መገመት አያስቸግርም፡፡
ራሳቸው አቡኑ ስለ ኢትዮጵያ እንዲህ በማለት ያክላሉ፡፡ የትናንትናዋ ንጽሕት ኢትዮጵያ ቅድስት ኢትዮጵያ እንደነበረች እንደትቀጥል አሳስበዋል፡፡ ንጽሕት ቅድስት በሚለው ቃላቸው ውስጥ አቤት ያለው እውነት ብዛት! ይህች ሀገር ጠልቀው የሚጠጧት እንጅ ጨልፈው የሚቀምሷት አይደለችም፡፡ በመጭለፍ ዐወቅናት የሚሉቱ ሁሉ የስሕተት ጉዳት ያገኛቸዋል፡፡ ኢትዮጵያን ለመረዳት ከጥልቀቷ መጥለቅ ያስፈልጋል፡፡ ላይ ላዩን በመላስ ጣዕሟን ማጣጣም፣ መቅኔዋን መቅመስ፣ ምስጢሯን መዳሰስ አይቻልም፡፡ ኢትዮጵያ ንጽሕት ስትባል አንድምታው ብዙ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቅድስት ስትባል ብዙ ያስተነትናል፡፡ በአጭር ቃል እግዚአብሔር የሚወድዳት ሀገረ እግዚአብሔር ናት፡፡ በዚህ ቃል ስትገለጽ መስማት በሐሴት ይሞላል፡፡
፫. ንግግሮቹ ወደ ተግባር እንዲለወጡ አሳስበዋል
አዎ “መናገር ቀላል ነው ማድረግ ግን ከባድ ነው” ብለዋል፡፡ ንጽጽሩን ማለታቸው እንጅ መናገር በራሱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ መናገር ማማጥን ይጠይቃል፡፡ መናገር ደጋግሞ ማሰብን ያስገድዳል፡፡ መናገር ቃላት መምረጥን ያስወድዳል፡፡ መናገር አድማጩን መለየትን ይፈልጋል፡፡ የታዳሚውን ሥልጣኔውን፣ ታሪኩን፣ ወጉን፣ ባሕሉን፣ ዕውቀቱን እና ፍላጎቱን ቀድሞ ማወቅ አማራጭ አይደለም፡፡ መናገር የጊዜን ቁጥብነት ግምት ውስጥ ያስገባል፡፡ እናም መናገር በራሱ ቀላል የሚባል አይደለም፡፡
ነገር ግን የመሥራትን ያኸል ክብደት አለው ማለት ደግሞ አይቻልም፡፡ ገቢርን (ሥራን) ኀልዮ (ማሰብ) ይወልደዋል፡፡ መናገርንም እንዲሁ፡፡ ገቢርና ነቢብ የማሰብ የኀልዮ ውጤቶች ናቸው፡፡ በዚህ በኩል ገቢርና ነቢብ ወንድማማቾች (እኅትማማቾች) ናቸው፡፡ ግን ደግሞ አፈጻጸማቸው ለየቅል መኾኑ አይካድም፡፡ ነቢብ የተናጋሪውን የግል ውሣኑ ብቻ ይጠይቃል፡፡ ተናጋሪው እስከወሠነ ድረስ በየትም ይሁን በየት ያሰበውን መናገር ይችላል፡፡ ለመናገር አግዙኝ አይባልም፡፡ ለተግባር ግን አጋዥ ያስፈልጋል፡፡
ጥቂት ገቢራት አሉ ብቻን እንደታሰቡ ለብቻ ሊሠሩ የሚችሉ፡፡ አሁን የሚያነጋግረን ገቢር ግን አገርን ሠርቶ የማሠራት ጉዳይ ነውና ብዙ አጋሮች ብቻ ሳይኾን የዜጎችን ሁሉ ሱታፌ ይፈልጋል፡፡ ዜጎችን በአንድ ዓላማ ለማስተባበር ብዙ ውጣ ውረድ አለበት፡፡ የሚጀምረው ግን ከነቢብ ነውና ጅምሩ ታይቷል፡፡ ገናም ብዚ ሲነገሩ ልንሰማቸው የምንፈልጋቸው አሉ፡፡ ተነግረው አላላቁም፡፡ ነቢብ የራሱን ፈውስ መስጠት መጀመሩም አይካድም፡፡ አንዱ ከሌላው እንዳይጋጭ በጥንቃቄ ማስሔድም ይፈልጋልና ነቢብ በራሱ ቀላል አይደለም፡፡ ማሰቡ ላይ ብዙ አጋሮች ሊሳተፉ ይችላሉ፡፡ የገቢሩን ያኸል ግን ከዳር እስከ ዳር አያሳትፍም፡፡ ስለዚህ ገቢር መክበዱ አይቀርም፡፡ በተለይም ደግሞ ያሰቡትን ሳይኾ የተናገሩትን መሥራት!
አቡኑ እነዚህን በጥልቀት ስለተመለከቱ መናገር ቀላል ነው መሥራት ግን ከባድ ነው ብለዋል፡፡ መናገሩን አልናቁትም፣ አላቃለሉትም፡፡ ግን ከአፍ ከወጣ አፋፍ ነውና ጥንቃቄ እንዲታከልብት ማሳሰባቸው ክፉ አይደለም፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ እንዲህ ይመለከቱታል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ አባትነት ምክር ነውና የተናገሯቸውን እንዳይረሱ በግል ማስታወሻ እነዲያሰፍሯቸው አሳስበዋቸዋል፡፡ ከተነገሯቸው ውስጥ የትኞቹን ተግባራዊ እንዳደረጉ እና የትኞቹ እንደሚቀሩ የሚለዩበት ዝክረ ነቢብ እንዲኖራቸው አመላክተዋል፡፡
“ስምን ፈረሰኛ አይቀድመውም እና ልጄ ተጠንቀቅ” የሚለውን ብኂለ አበው ጠቅሰው ጠቅላይ ሚንስትሩ በጀመሩት በጎ ሥራ እንዲጸኑበት መክረዋል፡፡ ወጉ ማዕርጉ እንዲህ ነው፡፡ አባት ልጁን ይመክራል፡፡ ልጅም በአባቱ ይመከራል፡፡ ጠቅላይ ሚንስትሩ “ካጠፋሁ ቆኝጥጡኝ” የሚል አትሕቶ ርእስ ያላቸው ከመኾናቸው ጋር አብሮ የሚሔድ ቃል፡፡
፬. የጎጣ ጎጡ ጉዳይ
ቋንቋ ፌደራሊዝም እንዲኾንባት የተጫነባት እርሱም ቢኾን ብዙ ውጥንቅጥ የበዛበት ሥርዓት የተተከለባት ምስኪን ምድር የእኛዋ ኢትዮጵያ ናት፡፡ ከጋምቤላ፣ ከደቡብ፣ ከድሬዳዋና ከአዲስ አባባ በስተቀር ሌሎች ክልሎች የቋንቋ መሠረት ይዘው የተሰየሙ ናቸው፡፡ እነዚህም ቢኾኑ አዲስ አበባን ይጭነቃት እንጅ የውስጥ አደረጃጀታቸው ቋንቋን እንደ ድንጋይ ተንተርሰውታል፡፡
ይህን አደረጃጀት ሕዝብ አልወደደውም፡፡ አንቅሮ ተፍቶታል፡፡ ወዳጅ እንደዚህ ያለውን አይፈልገውም፡፡ ነባር ጠላቶቻችን ግን እንዲህ እንድኾን ይፈልጋሉ፡፡ እናም ጠፍጥፈው የሠሯቸው አሻንጉሊቶች አምጥተው ጫኑብን፡፡ ፳፯ ዓመታቱ የባከኑት ኢትዮጵያን በሚያቃውስ አሠራር ለመኾኑ ነጋሪ አያሻም፡፡ ይህንን አቡኑ አምርረው ተጸይፈውታል፡፡ ሕዝቡም በጭብጨባ ተከትሏቸዋል፡፡
አንዱ ሲሽር ሌላ እየተወለደ ዘለዓለም በቋንቋ አጥር ታጥረን እንድንኖር የቤት ሥራ የሰጡን ሌሎች ናቸው፡፡ በቅርቡ የሚታየው አዳዲስ መንገድ አስደንጋጭነቱ ያይላል፡፡ ችግሩ ችግር ሲወልድ እንደዚህ ነው፡፡ አባ አብርሃም የተወለደው ችግር እንዲከስም ጥሪ አስተላልፈዋል፡፡ በዘር መቧደኑ በሀገር ወደ መቧደን ከፍ እንዲል አሳስበዋል፡፡
ከእኛ የመነጨ አስተሳሰብ ሳይኾን “ወዳጆቻችን የሰጡን የቤት ሥራ” እንደኾነ አቡኑ ጠቁመዋል፡፡ ሊሠመርበት የሚገባው ነገር አስተሳሰቡ ሀገር ያበቀለው ሳይኾን ተሰድዶ የመጣ ካላገሩ ሊበቅል የተመኘ አረም መኾኑን ያሳያል፡፡ “ሠርገኛ ጤፍ” የምትለው የተወደደች ቃል ሀገርኛ ስትኾን ዳቦ (ቀይ ዌም ጥቁር) ጤፍን ከነጭ ጤፍ ያዋደደች እንጅ አረምን ከጤፍ የቀላቀለች አይደለችም፡፡ ስለዚህ ጤፍነታችን ላይ እናትኩር የምትለው የአቶ ለማ እና የዶ/ር ዐቢይ ንግግር በጣም ቀዳሚዋ ሀገሪቱን በአንድ ማሠሪያ አንድ ነዶ የምታደርግ ናት፡፡ ቋንቋ መልክ እንጅ ክልል መኾን የለበትም፡፡ ይህንን ጭነት እናራግፈው ነው የአባታችን መልእክት እና አደራ፡፡
ጠላት ዲዛይን ባደረገልን የጥፋት መንገድ እየነጎድን አለማን ማለት አይቻልም፡፡ ሀገራዊነት ለምልሞ ዘውጌያዊነት ሲከስም ተጠቃን ብለው የሚሞግቱት አካላትም በጠቅላዩ ቃል ይደመራሉ፡፡ ችሎ ችሎ ሲበዛበት ጥያቄ የሚያነሣውን ብረድ ማለት ይቻላል፡፡ ለደቡብ ክልል የሠራው ከዐርባ ዘጠኝ በላይ ቋንቋ ያለበትን ክለላ በአንድ ማደራጀት በሀገር ደረጃ ለምን አልኾነም ብልን መጠየቅ ይኖርብናል፡፡ ስለዚህ አስቀድመው የጀመሩትን በብርታት እንዲገፉበት አባታዊ ጉልበት ጨምረውበታል፡፡
፭. ቤተ ክርስቲያናቸውን ስለመከላከል
አቡነ አብርሃም ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከድንበር በላይ መኾኗን መሥክረውላታል፡፡ ይህንንም በሥራዋ ማረጋገጫነት ይገልጧታል፡፡ “እገሌ ወእገሌ ሳትል፣ ሁሉንም በየእምነቱ ፊደል ያስቆጠረች፣ ለሀገር መሪነትም ያበቃች” በማለት ተናግረውላታል፡፡ አዎ ማነበብና መጻፍ የሚችል ኢትዮጵያ መሪ ካለ አስተማሪዋ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ፊደል ቀርጻ የጽሑፍ ቋንቋን የመሠረተች ባለሀብት፡፡ እምነቱ ምንም ይሁን ምን በቤተ ክርስቲያን ፊደል ያልጻፈ፣ ትምህርቱን ያልተማረ ማን ነው? ቢያንስ የላቲን ፊደል ከመጣብን ወዲህ የመጣ መሪ ስለሌለ፡፡
የእምነታችን ተከታይ ያልኾኑ ሰዎችን እናከብራቸዋለን በማለትም መተናኮል የሌለበት ሥርዓትን እንደምታራምድ ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው ቁመና ገልጠዋል፡፡ በአንጻሩ ደግሞ ሌሎች እንዲያከብሩንም እንፈልጋለን በማለት ቅርጽ ያለው አቋማቸውን አሰምተውላታል፡፡ በምሥራቁ በደቡቡ በሌላውም ቤተ ክርስቲያን ጣጣው እየበዛባት ነው በማለት አሳስበዋል፡፡ እምነትም ከኾነ በትምህርት ላይ የተመሠረተ እንጂ በሰይፍና በጦርነት ያልተመሠረተ ይኾን ዘንድ እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
አባ አብርሃም ባሉበት ሀገረ ስብከት እንደዚህ ያለ ፈተና ስለገጠማቸው የተናገሩት አይደለም፡፡ አጠቃላይ እናት ቤተ ክርስቲያንን ወክለው እንጅ፡፡ እየፈለግነው ያጣነውን ኖላዊነት ልናገኘው ይኾን? ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ልትናገር እንዲህ ልትደመጥ ይገባታል፡፡ ደረጃዋ ይህና ከዚህም በላይ ነውና፡፡
የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን በመንግሥት ባለሥልጣናት የሚደርስባትን ጣልቃ ገብነት ስለማስቆምም ማሳሰቢያ ሰጥተዋል፡፡ በአንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ባለሥልጣናት የተሸሙበትን ትተው የሃይማኖት መሪዎች ኾነው ቤተ ክርስቲያንን እየተጋፉ እንደኾነ ጠበቅ አድርገው አቅርበዋል፡፡ በአንዳንድ ቦታዎችም ባደረችበት እንዳትውል፣ በዋለችበት እንዳታድር በሮማውያን ዘመን የደረሰባትን ግፍና መከራ የሚስታውስ ድርጊት መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ አዎ የቤተ ክርስቲያን አንደበት መኾን እንደዚህ ነው፡፡ ያለምንም ምክንያት ስንት አብያተ ክርስቲያናት እንደተቃጠሉና፣ ስንት ምእመናን እንደታረዱ፣ እንደተሰደዱ ምሥክሮች ነን፡፡
መንግሥት ባለሥልጣናቱ ወሰን እያለፉ የሚያደርሱባትን በደል ማቆም አለበት፡፡ ፍትሕ ርትዕ ካለ ለሁሉም እንጅ ባለሥልጣናቱ በሰፈሩት ቁና ልክ አይወሰንም፡፡ ይህንን የቤት ሥራ ዶ/ር ዐቢይ ከአጋሮ የሚመዘዝ ትውልድ እንዳለው ኢትዮጵያዊ በደንብ ያውቁታል ተብሎ ግምት ቢወሰድ መደምደሚያው ስሕተት አይኾንም፡፡ ወደኋላ ተመልሶ ለመካሰስ ጊዜው የለንም፡፡ የወደፊቱን ለመከላከል ግን ከዛሬ የተሻለ ቀን አንጠብቅም፡፡
በእነዚህ አምስት ቃላት ሊመደቡ የሚችሉትን መልእክታት አባ አብርሃም የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን የወከለ ድምጽ አሰምተዋል፡፡ አበጁ አባታችን፡፡ ቡራኬዎ ይድረሰን! በነገዋ ኢትዮጵያ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ስለሚኖራት ሚና ቀድመን እናስብ፡፡ የግንቦቱ ርክበ ካህናትን መሠረት ያደረገው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ስለ ቤተ ክርስቲያን ሀገራዊ ሚና የሚያቅድ እና የሚያስፈጽም አካል ሳይሰይም ማለፍ የለበትም፡፡ የዳር ተመልካችነቱ ዘመን ሊበቃን ይገባል፡፡ መንግሥት እና ሃይማኖት የተለያዩ ናቸው የሚለው ቃል ሸውራራ ትርጉም እየተሰጠው ያለው በእኛ ቤት ብቻ ሳይኾ አይቀርም፡፡ ቃሉን ከመፈተሽ ጀምሮ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል፡፡ ከቤታችን ያሉትን ደባል ሱሰኞችም ወደ ማስወገድ መሸጋገር አለብን፡፡ ለመንግሥትም ለቤተ ክህነትም እንጫወታለን የሚሉ ባለ ኹለት መታወቂያዎች እስካላራቅን ድረስ ቤተ ክርስቲያንን መታደግ አንችልም፡፡ መንግሥት “ቡራኬ” የሚሠጣት ቤተ ክርስቲያን እንደትኾን ስንት ክፉ ሥራ ተሠርቶባታል፡፡ ቦታውን ለማቀያየር ያልተደከመ ድካም የለም፡፡ ቡራኬው ወደ መንበሩ መመለስ አለበት፡፡ ባራኪዋ ተባራኪ አትኾንም፡፡
በዚህም ጠቅላይ ሚንስትሩ “አባታችን የመከሩኝን እፈጽማለሁ፣ ስለ ሀገር አንድነትና ኢትዮጵያዊነትን ስለመገንባት እርስዎም በጸሎት ያግዙኝ” በማለት አጠፌታውን በአክብሮት ገልጸዋል፡፡ ልጅ አባቱን ሲሰማ እንዲህ ነው፡፡ ቤት ለእንግዳ ብለው ኢትዮጵያን በቤት የዶ/ር ዐቢይን ሲመት ብለው አቡነ አብርሃም እንደተቀበሏቸው በአጠፌታው ጠቅላይ ሚንስትሩ ጸሎትና ቡራኬያቸውን ለምነዋል፡፡ ከብሮ ማስከበር እንዲህ እንጅ!
አቡነ አብርሃምም ንግግራቸውን ሲደመድሙ ቡራኬ ሰጥተዋል፡፡ “እግዚአብሔር ይባርክልኝ” በማለት ጠቅላይ ሚንስትሩን ባርከዋል፡፡ አዲሱን ስናመሰግን የቅርባችንን እንዳንረሳ ብለውም የክልሉን ፕሬዝዳንት አቶ ገዱንና እና የከተማውን ከንቲባ አመስግነዋል፡፡ አባቶች ደረጃቸው ይህ ነው፡፡ ባራኪ እንጂ ጭብጦ እንደተወረወረለት መንገደኛ አመስጋኝ አይደሉም፡፡ ልዩነቱን ስለሳዩን ደስ ብሎናል፡፡ እነ አባ ገዳ ሰንበቶ የሚሊንየም አዳራሽ እስኪናወጥ ድረስ የተቀበሉትን የሙገሳ ጩኸት የእኛ አባቶች ለምን ቢያንስ ዝምታውን እንኳ እንዳላገኙት (ዝርዝሩ ይቅር) የምናሰላስልበት ሠዓት ላይ ደርሰናልና ለመለወጥ እንዘጋጅ፡፡