
ኪም ጆንግ ኡን የኮሪያን ምድር ለሁለት የከፈለው ጦርነት ካበቃ በኋላ ድንበር ተሻግረው የደቡብ ኮሪያን መሬት የረገጡ የመጀመሪያው የሰሜን ኮሪያ መሪ ሆኑ።
ልዩ ትርጓሜ በሚሰጠው ተምሳሌታዊው ክስተት የደቡብ ኮሪያው መሪ ሙን ጃኢ-ኢን እና ኪም ጆንግ ኡን ድንበር ላይ ተገናኝተው ተጨባብጠዋል።
በዚህ ሞቅ ያለ ሥነ-ሥርዓት ጅማሬ ላይ ኪም ጆንግ ኡን “ግልፅ” ውይይት ይደረጋል ብለው ተስፋ እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።
ከጥቂት ወራት በፊት ከሰሜን ኮሪያ ይደመጥ የነበረው ከጦርነት ጋር የሚመሳሰል የነበረ ሲሆን፤ አሁን ግን ሁለቱ ወገኖች ስለሰላምና ስለኒውክሌር ጦር መሳሪያዎች ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በሁለቱ መሪዎች ውይይት ወቅት ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች ቀደም ተብሎ ከስምምነት የተደረሰባቸው ናቸው። ነገር ግን በርካታ ተንታኞች ሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራዋን ለማቆም ያላት አቋም ላይ ከፍተና ጥርጣሬ አላቸው።
ያልታሰቡ ቅፅበቶች
ሁለቱን ሀገራት በሚያካልለው ድንበርና ወታደራዊ ባልሆነው ቀጠና ሁለቱ መሪዎች ሲጨባበጡ ለመመልከት ኮሪያውያን ቆመው ነበር።
ተከትሎም ኪም የደቡ ኮሪያ አቻቸውን ድንበሩን አልፈው ወደ ሰሜን ኮሪያ ግዛት እንዲሻገሩ ሲጋብዟቸው ብዙዎች ሁኔታውን በመደመም ነው ያዩት።
በመቀጠልም ሁለቱ መሪዎች እጅ ለእጅ እንደተያያዙ ወደ ደቡብ ኮሪያ ግዛት ተመለሱ።
የሁለቱ መሪዎች ግንኙነት በደንብ ተጠንቶ ከመቀናበሩ አንፃር ይህ ሁኔታ ያልታሰበ ቅፅበት ነው ተብሏል።
የመጀመሪያው ክፍለ-ጊዜ ውይይት የተጠናቀቀ ሲሆን ፕሬዚዳንቶቹ ምሳ ለመብላት ተለያይተዋል።
ኪም በጠባቂዎቻቸው ታጅበው በጥቁር ሊሞዚን ወደ ሰሜን ኮሪያ ያመሩ ሲሆን ከሰዓት በኋላም ውይይቱን ለመቀጠል ድንበሩን ተሻግረው ወደ ደቡብ ኮሪያ ያመራሉ።
የአዲስ ታሪክ ጅማሮ
መሪዎቹን የተቀበሏቸው በደቡብ ኮሪያ ባህል ልብስ የታጀቡ የክብር ዘበኛ አባላት ናቸው።
መሪዎቹም ፓንሙንጆም ግዛት ውስጥ በሚገኝ ‘ፒስ ሀውስ’ ተብሎ በሚጠራው ወታደራዊ ባልሆነው ቀጠና ቦታ አምርተዋል ።
” አሁን አዲስ ታሪክ ይጀምራል። ይህ የታሪክ ጅማሮና የሰላም ዘመን መጀመሪያ ነው” በማለት ኪም በ’ፒስ ሀውስ’ ለእንግዶች በተዘጋጀ ማስታወሻ ደብተር ላይ ፅፈዋል።
ከአስርት ዓመታት በኋላ የተገናኙት ሁለቱ መሪዎች ንግግርም በቀልድም የታጀበ ነበር።
ኪም ታዋቂ የሆነውን የሰሚን ኮሪያ ቀዝቃዛ ‘ኑድልስ’ ምግብ ለስብሰባው ላምጣ ብለው ቀልደዋል።
የዋይት ሀውስ ባለስልጣናት በበኩላቸው እንዲህ አይነት ውይይቶች ለወደፊቱ ሰላምና ብልፅግናን ለማምጣት ጥሩ ጅምር ናቸው ብለዋል።
የሁለቱ መሪዎች ውይይትም በቀጣዩ ለታቀደው የኪምና የትራምፕ ውይይት በር ከፋች ነው የተባለ ሲሆን፤ የአሜሪካ ፕሬዚዳንትም ከሰሜን ኮሪያ መሪ ጋር ሲገናኙ የመጀመሪያው ይሆናል ተብሏል።
የውይይት ነጥቦች
የሁለቱ መሪዎች ዋናው የመነጋገሪያ ነጥብ አወዛጋቢ የሚባለውን የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር የጦር መሳሪያ ፕሮግራም ነው።
ከዚህ ቀደምም የደቡብ ኮሪያ ባለስልጣናት ሰሜን ኮሪያን የኒውክሌር ፕሮግራሟን ለማቋረጥ ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ ነው በማለት ማስጠንቀቂያ ሰጥተው ነበር።
ባለፈው ሳምንት ኪም የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ሙከራቸውን ለመሰረዝ ተስማምተዋል።
ይህ ውሳኔያቸው በደቡብ ኮሪያና በአሜሪካ ሲወደስ፤ ቻይናውያን ተመራማሪዎች በበኩላቸው የሰሜን ኮሪያ የኒውክሌር ሙከራ ማዕከል ድንጋይ ስለወደቀበት ከጥቅም ውጭ በመሆኑ እንዳቆሙ ጠቁመዋል።
ከኒውክሌር ፕሮግራሟ በተጨማሪ ሁለቱ መሪዎች ስለ ሰላም፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ጉዳዮችን ይወያያሉ።
ዛሬ ምን ይፈጠራል?
እያንዳንዱ ፕሮግራም ከስብሰባ ጀምሮ አስከ እራት ድረስ በዝርዝር ተቀምጧል።
ከሰዓት በኋላም በተያዘው ዝግጅትም ሁለቱ መሪዎች ከሁለቱም ሀገራት በተውጣጣ አፈርና ውሃን በመጠቀም ዝግባን የሚተክሉ ሲሆን ይህም ሰላምንና ብልፅግናን የሚያመላክት ነው ተብሏል።
SOURCE – BBC/AMHARIC