~”በእስር ቤት አንድም ቀን አሳልፈው ስለማያውቁ የእስር ቤት ሕይወት ይገባዎታል ብለን አንደፍርም። በማንነታቸው………በማያምኑበትና ባልፈፀሙት ታስረው፣ በምርመራ ወቅት አሰቃቂ ግፍ ደርሶባቸው፣ አካላቸው ጎድሎ፣ የዘር ፍረያቸውን እየተኮላሸ መሃን የሆኑ፣ ወገባቸው፣ እጅና እግራቸው ተሰብሮ፣ አካለ ስንኩል የተደረጉ ያለ ማስረጃ በሀሰት ምስክር እየቀረበባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ። አይጥ፣ ትኋንና ቁንጫ ጋር ተገደው ዝምድና ፈጥረው በእስር አስከፊ ሕይወት ይመራሉ።

~”ይህ የተማረረ ሕዝብ በንግግር እና “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል” ስለተባለ የሚሸነገል ከመሰለዎት ከፍተኛ ስህተት ውስጥ እየተዘፈቁ እንደሆነ ግልፅ ነው። በአንፃሩ በአስቸኳይ ወደ ተግባር ከገቡ ተስፋ ያደረገብዎት ሕዝብ ከጎንዎት እንደሚቆም አያጠራጥርም።”

~”………በአንድ ወር ውስጥ መፍታት አለመቻልዎት ለምን ይሆን? የጥያቄዎቹን አንጋብጋቢነት አልተረዱትም ይሆን? እየዞሩ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ምክንያት ጊዜ አጡ? እርስዎ ሳይሆኑ፣ የድሮዎቹ አሳሪና ፈችዎች አሁንም አሳሪና ፈችዎች ናቸው? አሁንም እርስዎ ሳይሆኑ አዛዦቹ እነ ጌታቸው አሰፋ ናቸው?”

(ከህሊና እስረኞች የተላከ)

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ሆይ!

የእርስዎም ሆነ በአካባቢዎ ያሉ ግለሰቦችን ሚና ባይናቅም አሁን ለተቀመጡበት ወንበር ያበቃዎት ሕይወታቸውንና አካላቸውን ያጡ፣ በእስር ላይ የሚገኙ፣ ለሀገራቸው ሲሉ በሰው ሀገር የሚንከራተቱት ኢትዮጵያውያን የከፈሉት መስዋዕትነት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ያደረጓቸው አንዳንዶቹ ንግግሮች ሕዝብ ተስፋ እንዲጥልብዎ አድርገዋል። ነገር ግን ትዝብት ውስጥ የሚከትቱ ጉዳዮችም አሉ። ለምሳሌ:-

1) የኢህአዴግ መንግስት ስለ ዲሞክራሲ ሲያወራ 27 አመቱ በጣም ጥቂት ጊዜ ስለሆነ ገና ታዳጊና እየተለማመድን ስለሆንን በትግስት ተጠባበቁ የሚባለው

2) 10 የስኳር ፋብሪካዎች እና ሌሎች ትልልቅ ፕሮጀክቶች ለብረታብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖረሽን (ሜቴክ) ተሰጥቶት ነበር። ብዙ ሚሊዮን ዶላር ከስሯል። ነገር ግን ማንም ተጠያቂ አይደለም ብለው በፓርላማ ተናግረዋል።
3) ደረቅ ሕግ ያለ ፍትሕ ሊሰራ እንደማይችል ደጋግመው ተናግረዋል። በፍትህ እጦት ሕዝብ ተቸግሯል። አስቸኳይ ፍትሕ ያስፈልጋል ብለዋል። ሆኖም የብዙ ሀገራት መሪዎች ለውጥ ሲያደርጉ አስቸኳይ ውሳኔዎችን ያስተላልፋሉ።

እርስዎ በእስር ቤት አንድም ቀን አሳልፈው ስለማያውቁ የእስር ቤት ሕይወት ይገባዎታል ብለን አንደፍርም። ዛሬ በማንነታቸው፣ በአመኑበት ሕጋዊ የፖለቲካ አቋም፣ በማያምኑበትና ባልፈፀሙት ታስረው፣ በምርመራ ወቅት አሰቃቂ ግፍ ደርሶባቸው፣ አካላቸው ጎድሎ፣ የዘር ፍረያቸውን እየተኮላሸ መሃን የሆኑ፣ ወገባቸው፣ እጅና እግራቸው ተሰብሮ፣ አካለ ስንኩል የተደረጉ ያለ ማስረጃ በሀሰት ምስክር እየቀረበባቸው በእስር ላይ ይገኛሉ። አይጥ፣ ትኋንና ቁንጫ ጋር ተገደው ዝምድና ፈጥረው በእስር አስከፊ ሕይወት ይመራሉ።

በኢህአደግ ስራ አስፈላሚ ስብሰባ የህሊና እስረኞ እንዲፈቱ መስማማታችሁ ተገልፆ ነበር። በውሳኔው መሰረት ይህ ጉዳይ በሁለት ወር ውስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ነበር። እስካሁን ለምን ሁሉም የህሊና እስረኞች አልተፈቱም? የህሊና እስረኞችን ለመፍታት እና ጊዜያዊ አዋጁን ለማንሳት አንድ ቀጭን ትዕዛዝ በቂ መሆኑ ግልፅ ነው። ታዲያ ሕዝባችን አንገብጋቢ ብሎ ያስቀመጠውን ችግር በአንድ ወር ውስጥ መፍታት አለመቻልዎት ለምን ይሆን? የጥያቄዎቹን አንጋብጋቢነት አልተረዱትም ይሆን? እየዞሩ በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ምክንያት ጊዜ አጡ? እርስዎ ሳይሆኑ፣ የድሮዎቹ አሳሪና ፈችዎች አሁንም አሳሪና ፈችዎች ናቸው? አሁንም እርስዎ ሳይሆኑ አዛዦቹ እነ ጌታቸው አሰፋ ናቸው? ወይንስ እርስዎም ከሚናገሩት በተቃራኒ ያልተቀየረው ኢህአዴግ ነዎት?

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ ሆይ፣ ስርዓቱ እንዳልተቀየረና የመቀየር ምልክትም እንዳላሳየ አንዳንድ ማሳያዎችን እንጥቀስ:_
1ኛ ፍርድ ቤቶች አሁንም፣ አቃቤ ሕግ ምስክር አልመጣልኝም ስላለ ብቻ በተደጋጋሚ ቀጠሮ እየሰጡ የህሊና እስረኞችን እያመላለሱ ነው። አቃቤ ሕግ ምስክር አላገኘሁም እያለና በሌሎች ሰበቦች ፍርድ ቤት በ101 ጊዜ ቀጠሮ የሰጠውና እየተመላለሰ ያለ እስረኛ ቂሊንጦ ውስጥ ይገኛል። ከ15 እስከ 25 ጊዜ መቀጠር የተለመደ ነው።

2ኛ ተከሳሾች ፍርድ ቤት ሳይቀርቡ ለማረሚያ ቤት ተደውሎ “ተከሳሾችን ዛሬ እንዳታቀርቧቸው፣ ቀጠሯቸውን በጉዳይ አስፈፃሚ እንልካለን” ይባላል። ለአብነት ያህልም በቂሊንጦ ቃጠሎ ሰበብ የተከሰሱት 38ቱ ተከሳሾች ለመጨረሻ ጊዜ በሚል ለሚያዝያ 16 ቀጠሮ ተሰጥቶ ቤተሰቦቻቸውና ጠበቆቻቸው በፍርድ ቤት ተገኝተው ተከሳሾች አልተገኙም። ፍርድ ቤቱ ብይኑን ሰርተን አልጨረስንም በሚል ለሚያዝያ 30 ባልተገኙበት ቀጠሮ ሰጥቷል።

ዶ/ር አብይ ሆይ!

በአምቦ የተደረገው ሰልፍ፣ በጎንደር የተሰማው ጉምጉምታን በአንክሮ አይተው ትምህርት ካልወሰዱ ከእርስዎ ቀድመው የነበሩት ላይ የደረሰው እርስዎም ላይ ገና ወንበሩ ሳይደምቅ እንደሚደገም እንዳይጠራጠሩ። ይህ የተማረረ ሕዝብ በንግግር እና “ሰላማዊ የስልጣን ሽግግር ተደርጓል” ስለተባለ የሚሸነገል ከመሰለዎት ከፍተኛ ስህተት ውስጥ እየተዘፈቁ እንደሆነ ግልፅ ነው። በአንፃሩ በአስቸኳይ ወደ ተግባር ከገቡ ተስፋ ያደረገብዎት ሕዝብ ከጎንዎት እንደሚቆም አያጠራጥርም።