April 28, 2018
ባለፉት አመታት… ኢትዮጵያችን በዘረኞች የመርዝ ጦር ተወግታ፤ ኢትዮጵያዊነትም እንደገደል አፈር እየተፍረከረከ ሲፈራርስ አይተን፤ “ምነው አምላክ ኢትዮጵያን ዘነጋሃት?” ብለን ነበር። ዜጎች ሃሳባቸውን ስለገለጹ ብቻ፤ “አሸባሪዎች!” ተብለው በህግ ሽፋን እስር ቤት ሲወረወሩ አዝነን፤ “የህሊና እስረኞች ይፈቱ!” ብለን ድምጻችንን ከፍ አድርገን ጮኸን ነበር። ኢትዮጵያንና ሃብቷን በግል እና በቡድን ተደራጅተው ሲቦጠቡጧት ውስጣችን በንዴት ቆስሎ፤
“ኢትዮጵያ አገሬ፣ ሞኝ ነሽ ተላላ፤
የሞተልሽ ቀርቶ፣ የበደለሽ በላ!” ማለታችን አልቀረም።
እንደውም ግፍ ከመብዛቱ የተነሳ፤ በሁኔታው ክፉኛ አዝነን “ግፍ የደረሰባቸው ብቻ ሳይሆን፤ ግፈኞችም ነጻ መውጣት አለባቸው” እስከማለት ደርሰን ነበር። ከዚያም ነገሮች በገደምዳሜ አለፉና… ዶ/ር አብይ አህመድ ዘመን ላይ ደረስን። እስካሁን ባለው ሁኔታ… የዶ/ር አብይ አህመድ ኢትዮጵያዊ በትር ሌባ ሌባውን ለመምታት ሲሰነዘር አይተን ተደምመናል፤ “ይህ ማለት ግን ኢህአዴግ ያደረሰብንን ግፍ እና በደል፤ የሚክስ ወይም የሚያስረሳ ሊሆን አይችልም – በጭራሽ!!”። ሆኖም እንደሰለጠነ ህብረተሰብ ነገሩን በጥሞና ካየነው… ግለሰብን ሳይሆን፤ ሃሳቡን ለመጥላት ወይም ለመጣላት በቂ ምክንያት እንደሚያስፈልገን አበክረን እናምናለን። ስለዚህ ነገሮችን በሰለጠነና ጥሞናዊ በሆነ መንገድ ለማየት እንዘጋጅ!
ጎበዝ! ዶ/ር አብይን እንጥላው ወይስ እንጣላው?
(ዳዊት ከበደ ወየሳ)
ልክ የዛሬ አመት ነው፤ ይሄንን ቀልድ የሰማነው።
ሴትዮዋ ቤታቸውን ለማከራየት ፈልገው፤ በደላላ አማካኝነት በወር 5ሺህ የሚከፍል የህወሃት አባል ይመጣላቸዋል። ክፍያው ጥሩ ቢሆንም፤ አከራይዋ “እምቢ” ይላሉ።
ደላላው ተከራይ አፈላልጎ አጣና በመጨረሻ፤ በወር አንድ ሺህ ብር የሚከፍል ሰይጣን ያገኝላቸዋል። ሴትዮዋም፤ “ግዴለም ሰይጣኑን በአንድ ሺህ ብር ባከራየው ይሻለኛል።” ብለው ውል ለመፈጸም ይዘጋጃሉ። በሁኔታው የተገረመው ደላላም እንዲህ አለ።
“እማማ!”
“አቤት?”
“በወር 5 ሺህ ብር ለሚከፍለው ወያኔ ‘እምቢ’ ብለው፤ አንድ ሺህ ብር ብቻ የሚከፍለውን ሰይጣን ‘እሺ’ ያሉበት ምክንያት ምንድነው?” ብሎ መገረም እና መናደድን ቀላቅሎ ይጠይቃቸዋል።
ሴትዮዋም፤ “አየህ ልጄ… ሰይጣኑ ከቤቴ አልወጣ ቢለኝ፤ በፀበል ልቡን አጥፍቼ አስወጣዋለሁ። ወያኔው ሰውዬ አልወጣም ቢለኝ ግን ምን አደርጋለሁ?!” በማለት ሲመልሱ፤ ደላላው ጭምር ስቆ ሃሳባቸውን የሚቃወምበት ቃላት አጣ።
ይህ ለቀልድ ያህል እናንሳው እንጂ፤ ውስጡ ግን ቁምነገር አዝሏል። አንድም የወያኔ አባላትን ህገወጥነት እናያለን። ሲቀጥልም ህብረተሰብ በነሱ ላይ ያለው እምነት መሟጠጡን እናስተውላለን። ዛሬ ዶ/ር አብት አህመድን አጥብቀው የሚጠሉትና የሚቃወሙት ሰዎች፤ አንድም ጥቅም እና ገዢነት የቀረባቸው ወያኔዎችና ተከታዮቻቸው ናቸው። ሌላኛዎቹ ደግሞ… ወያኔን ከሰይጣን አብልጠው የሚፈሩትና የሚጠሉት፤ ብሎም ለህወሃት ግፍ የበላይነት የተንበረከኩ ሰዎች ናቸው።
ወደድንም ጠላን፣ የህወሃት ደጋፊም ሆንን ነቃፊ ከአንድ እውነት ጋር መጣካት አንችልም። እስከቅርብ ግዜ ድረስ ህወሃት እራሱን ከህግ በላይ አድርጎ፤ የሁሉ ነገር አድራጊና ፈጣሪ ሆኖ ቆይቷል። ይህ የህወሃት መንገድ የራሱን ሰዎች በትእቢት እያሳበጠ፣ ሌላውን ደግሞ በፍርሃት እያንቀጠቀጠ ቆይቷል። ሆኖም የማያልፍ ይመስል የነበረው ዘመን እያለፈ ቢሆንም፤ ህወሃትን ከሚገባው በላይ አተልቀውና አግዝፈው የሚያዩት ሰዎች፤ “ከያንዳንዱ ለውጥ ጀርባ ህወሃት አለበት” ሲሉ ሊሞግቱን ይሻሉ። ችግሩ የእነዚህ ሰዎች አስተያየት የሚመነጨው… ከነባራዊው እውነት ሳሆን ሳይሆን፤ ህወሃትን ካለማመን ወይም ክፉኛ ከመፍራት የመጣ መሆኑ ነው።
አሁንም ድረስ እየመጣ ባለው ለውጥ ውስጥ፤ ሊገኝ የሚችለው የፖለቲካ ጥቅም ከማስላት ይልቅ፤ ባሉበት ሆነው እያንዳንዱን ለውጥ በጥርጣሬ እና በፍራቻ የሚያዩ ሰዎች ብዙ አሉ። እነዚህን ሰዎች እንደብዛታቸው በብዙ ፈርጅ ልናስቀምጣቸው እንችላለን። ለምሳሌ ወያኔ ተሽቀንጥሮ ወድቆልን፤ እኛ የምንፈልገው የፖለቲካ ፓርቲ ስልጣን ስላልያዘ ቅር የተሰኘን ሰዎች አለን። የህወሃት ገዳዮችና አስገዳዮች ለፍርድ እንዲቀርቡ የምንፈልግ ሰዎች አለን። በምንም መልኩ ኢህአዴግ እድል አግኝቶ አገር እንዲመራ የማንፈልግ ብዙ ነን። እናም ህወሃት/ኢህአዴግ ካደረሰብን ግፍ በመነሳት፤ ፈርጀ-ብዙ የተቃውሞ አጀንዳ ያለን ሰዎች አለን። እኛ እና የኛ አይነቶቹ… ከህወሃት/ኢህአዴግ ጋር ገና ያላወራረድነው የእንባ እና የደም ሂሳብ ስላለ ወደ አንድ ጎን ልንመደብ እንችላለን። ሆኖም ዛሬ ቅድሚያ መስጠት ያለብን አገርን የማዳን ተግባር ላይ ስለሆነ፤ ፍላጎታችንን ዋጥ አድርገን ቅድሚያውን ስፍራ ለአገራችን መስጠት እንዳለብን እናምናለን።
እናም የኛን ጉዳይ በይደር አስቀምጠን፤ ወደሚቀጥለው ምእራፍ እንዳንሸጋገር እንቅፋት ስለሚሆኑብን ሁለት አይነት ቡድኖች እንነጋገር። ከላይ እንደገለጽነው… ከእነዚህ ሁለት ቡድኖች መካከል አንደኛው የህወሃት ደጋፊዎች እና አባላት ያሉበት ሲሆን፤ ከሰማይ በታች ህወሃትን እንደፈጣሪ የሚያመልኩ ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች ስልጣንን የግል እና የቡድን ጥቅም ማስጠበቂያ አድርገው ስለሚጠቀሙበት፤ በስልጣን ዘመናቸው የኢትዮጵያን ህዝብ መበደላቸው ሳያንስ፤ አሁን ስልጣን ከእጃቸው መውጣት ሲጀምር፤ ወባ እንደያዘው ሰው መንቀጥቀጥና መርበድበድ የጀመሩ ናቸው። እነዚህ የህወሃት አባላት ሌላው ብሄር እርስ በርሱ እየተጋጨ እነሱ ሁሌም አስታራቂ ሆነው፤ ስልጣን ላይ መቆየት የሚፈልጉ በመሆናቸው፤ አዲሱን ጠቅላይ ሚንስትር ብቻ ሳይሆን ወደፊት ተፎካካሪ ሆኖ የሚመጣን ድርጅት ወይም ኢትዮጵያዊነት የሚያቀነቅን ግለሰብ በምንም አይነት የሚደግፉ አይደሉም፤ ይደግፋሉ ብሎ መጠበቅም የዋህነት ነው።
እነዚህ ህወሃት እና ደጋፊዎቻቸው ሊያደርሱ የሚችሉት መከፋፈል እና እብሪት እንዳለ ሆኖ፤ ከነሱ ይልቅ ስጋት ላይ የሚጥለን በማወቅም ሆነ ባለማወቅ፤ ህወሃትን የሚፈሩና ሰማይ የሚያደርሱት ሰዎች ጉዳይ ነው። እነዚህኛዎቹ ከህወሃት የሚለዩት በኢትዮጵያዊነት የሚያምኑ በመሆናቸው እንጂ፤ በድርጊት እና በጥላቻ መጠናቸው ከህወሃቶች የማይተናነስ ሃይል ያላቸው ሰዎች ናቸው። እነዚህ ሰዎች… አብረውን ጮኸው ያመጣነውን የጋራ ለውጥ… መጠበቅ ተስኗቸው፤ ሁሉንም ነገር በጥርጣሬ እና በጥያቄ ምልክት ውስጥ ይጨምራሉ። ነገሩ “እባብ ያየ፣ በልጥ በራየ!“ ሆነና፤ በመግቢያችን ላይ በቀልድ መልክ እንደገለጽናቸው አይነት ሰዎች ቢኖሩ ልንገረም አይገባም።
የዚህ ሁሉ ጥርጣሬ ምንጩ ደግሞ ያለፍንበትን መጥፎ ዘመን ነው። በኢህአዴግ ዘመን ህብረተሰቡ ደግሞ ደጋግሞ የተማረው ነገር ቢኖር፤ ተንኮል ተንኮል እና ሌላ ተንኮል ነው። በዚህ ምክንያት አንደኛው ሌላኛውን በጥርጣሬና በጥላቻ ቢመለከት ልንፈርድበት አንችልም። ያለፍንበት መንገድ አስከፊና አሰቃቂ በመሆኑ ኢህአዴግን ለማመን ግዜ ያስፈልጋል። ሆኖም የዘረኝነትን ቡቱቶ አውልቆ፤ ከወደቀበት ተነስቶ ወደፊት መገስገስ የሚፈልገው ህዝብ መሪ ያስፈልገዋል። አዲሶቹ መሪዎች ዶ/ር አብይን በግል ከመጥላት ይልቅ ከሃሳቡ ጋር በመጣላት፤ አዲስ እና አሸናፊ ሃሳብ በማቅረብ ብዙ ተከታዮችን ሊያፈሩ የሚችሉበት ጥሩ አጋጣሚ ሊያመልጣቸው አይገባም። በአጭሩ ለኢትዮጵያ እና ለኢትዮጵያዊነት የሚሰራ… ተፎካካሪ ሃይል ሊወለድና ሊመነደግ የሚገባበት ወቅት ላይ ነው ያለነው።
ወደድንም ጠላን… ህወሃት በዘራፊነት፣ በዘረኝነት፣ በጸረ ኢትዮጵያዊነት አቋሙ ሊቀጥል ይችላል። ይህ አቋሙም ከነዶ/ር አህመድ ጋር እሳትና ጭድ አደጎ፤ ህወሃትና የነዶ/ር አብይ ቡድን እርስ በርስ ነደውና ተንደው ማለቃቸው አይቀርም። ጥያቄው “በወደፊቱ የኢህአዴግ ውድቀት ላይ የሚገነባ አዲስ ጃይል አለ ወይ?” የሚለው ይሆናል። በመሆኑም ተቃዋሚዎች ራሳቸውን በፍጥነት ወደተፎካካሪነት መለወጥ ካልቻሉ፤ ተቃዋሚ ብቻ ሆነው በአሉታ እና በኡኡታ ብቻ እድሜያቸውን ይገፋሉ። ተቃዋሚዎች ራሳቸውን ወደተፎካካሪነት የሚቀይሩበትን ይህን ወርቃማ አጋጣሚ ካልተጠቀሙበት፤ ዶ/ር አብይ እየተዳከመ… ህወሃት ደግሞ እንደገና እንዲያንሰራራ አቅም ይሰጡታል። በመሆኑም ግዜው ሳኡመሽ… ልዩነት እና አንድነታችንን አጥርተን እና አበጥረን ማውጣት የግድ ይለናል።
ሁላችንም እንደምናውቀው… ዶ/ር አብይ አህመድ፤ ዘረኝነትን ከሚያራምድ የፖለቲካ ድርጅት ውስጥ ወጥቶ፤ ኢትዮጵያዊነትን መስበክ ከቻለ፤ በኢትዮጵያዊነት ተደራጅተን… ለኢትዮጵያ ህዝብ እንሰራለን የምንል ሰዎች፤ ከዚህ ልቀን አንድ እርምጃ ቀድመን መገኘት አለብን። ይህ ካልሆነም በተመጣጣኝ ሃይልና ጉልበት ወደፊት መራመድ አለብን እንጂ፤ አሁን ዶ/ር አብይ አህመድ እየሄደበት ያለውን መንገድ በመርገምና በመቃወም የምናገኘው የፖለቲካ ትርፍ ኢምንት ነው። ስለሆነም ጥያቄያችን ህጋዊ፣ ተቃውሟችንም ምክንያታዊ ሊሆን ይገባዋል።
ሌሎችም ይህን አጋጣሚ በመጠቀም ህዝባዊ አቋም ያለው የብሄራዊ እርቅ ተቋም እንዲቋቋም ግፊት ማድረግ አለባቸው። ይህ ተቋም ያለአንዳች አድልዎ በህዝብ ላይ የደረሰው በደል እንደገና እንዳይደርስ ትምህርት የሚሰጥ፤ በኢህአዴግ ምክንያት አስከፊ በደል የደረሰባቸው ሰዎች እና ድርጅቶች ለጋራ አገራዊ አጀንዳ አብረው የሚቆሙበት ብቻ ሳይሆን የሚካሱበትን ሁኔታ የሚያመቻች መሆን አለበት። “ጥሩ ቀን፣ ጥሩ ሳይባል ያልፋል” እንደሚባለው፤ ይህ አጋጣሚው እንደዋዛ ሊያልፍ አይገባም። የስርአት ብቻ ሳይሆን የህብረተሰብ ለውጥ የሚያመጣ ኃይል ለመፍጠር መትጋት ይኖርብናል።
ከዚህ በኋላ… እንደኢሰመጉ አይነት የሰብአዊ ድርጅቶች ዳግም በኢትዮጵያ ምድር ሊጠናከሩ፤ የነጻ-ፕሬስ ውጤቶች ሊያብቡ፣ ተቃዋሚ እና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ከነሙሉ ጥንካሬያቸው የፖለቲካውን መድረክ ሊጠቀሙበት ይገባል። ይህ ሲሆን ነው፤ የምርጫ ቦርዱ እንዲስተካከል መሟገት የሚቻለው። ነጻ-ፕሬሱ ዳግም ሲያንሰራራ ነው ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብትን የምንጎናጸፈው፤ እንደኢሰመጉ አይነት ድርጅት መጠናከር ሲችል ነው መንግስትን ተጠያቂ አድርገን መሞገት የምንችለው። ሌላው ቀርቶ… ትክክለኛ ፍርድ ለማግኘት፤ የፍትህ አካሉን መፈተሽ ያለብን አሁን ላይ ሆነን ነው።
የዶ/ር አብይ አህመድን የፖለቲካ መስመር ከመቃወም አልፈን፤ ኃይል ሆነን መውጣት የምንችለው ከላይ የተገለጹትን ተቋማት፤ ዳግም በመፍጠርና በማጠናከር እንጂ ከዳር ሆነን በመመልከት ሊሆን አይገባም። ዛሬ ዶ/ር አብይ አህመድ የሚለውና የሚናገረውን ኢትዮያዊነት፤ ከኛ እንጂ ከህወሃት አልተማረውም። ይህ ለውጥ የመጣውም በ’ኛው ጩኸት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። እንዲህ ወድቀን እና ተነስተን የፈጠርነውን የለውጥ መንገድ መልሰን ጥላሸት ከመቀባት ይልቅ፤ ራሳችንን የድሉ ባለቤት ልናደርግ ይገባናል።
በአጠቃላይ… ሰላማዊ ትግላችን ሲያብብ፤ የታሰሩት ወገኖቻችን ሲፈቱ… አዲስ የለውጥ ማዕበል የኢህአዴግን መርከብ ሲንጠው አይተናል። አሁን ሁሉም ነገር ‘አልጋ ባልጋ ሆኗል’ ማለት ባንችልም…በዘረኝነት ሸምቀቆ ውስጥ ታንቆ የነበረው ኢትዮጵያዊነት፤ ዳግም ነፍስ መዝራት ጀምሯል። በአንጻሩ ዘረኝነት ወደ ከርሰ መቃብር ሊወርድ ፍታት ሲደረግለት አይተን… እኛ እልል ብለናል፤ ጠባብ ብሄረተኝነትን የሚያዜሙና ዘረኝነት እየከሰመ በመምጣቱ የከፋቸው ሰዎች ደግሞ፤ ሃዘናቸው ቅጥ አጥቶ አሁንም ቤታቸውን ዘግተው ሃዘን ላይ ናቸው። በዚያም ተባለ በዚህ… ይህ የምናየው ለውጥ የትላንት ጩኸታችን ውጤት ነው። ዶ/ር አብይም ቢሆን፣ ለማ መገርሳም ቢሆን… የህወሃት ሳይሆን የኛ ጩኸት ውጤቶች ናቸው። እኛ ግን እንላለን… ጩኸታችን ጠቅላይ ሚንስትሩን ለመጥላት ብቻ መሆን የለበትም። ግለሰብን በመጥላት ሳይሆን፤ ሃሳቡን በመጣላት የተሻለ ነጻነት፣ ፍትህ እና ዲሞክራሲ በኢትዮጵያ እስከሚሰፍን ድረስ፦ የምናደርገው ፍልሚያ መቀጠል አለበት… አዎ ትግሉ ይቀጥላል፠