አቻምየለህ ታምሩ

ከታች በፎቶው የሚታዩት ገበሬዎች ከጎጃም መተከል አማራ በመሆናቸው ብቻ ከተፈቀሉት 500 አርሷደሮች መካከል ከፊሎቹ ናቸው። እነዚህ ባገራቸው የተፈናቀሉት የአማራ ገበሬዎች ባህር ዳር አካባቢ በሚገኝው የዐባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያን ቅጥር ግቢ ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ።

አርሷደሮቹ አገርና መንግሥት ያላቸው መስሏቸው አንዳች መፍትሔ ይሰጣቸው ዘንድ ስምንት ተወካዮቻቸውን ወደ ብአዴን ልከው ነበር። ነብር ዥንጉርጉርነቱን ብአዴን ነውረኛነቱን ሊለውጥ ከቶ አይቻለውምና «የአማራው ወኪል» ነውረኛው ብአዴን የተፈናቀሉ የአማራ ገበሬዎችን ወኪሎች ለምን ለአቤቱታ መጣችሁ ብሎ ባህር ዳር በሚገኘው ሁለተኛ ፓሊስ ጣቢያ አስሮ አሳድሮ ዛሬ ባህር ዳርን ለቀው እንዲወጡ በማዘዝ በጊዜ ገደብ ለቋቸዋል።

ነውረኛው ብአዴን በተፈናቃይ የአማራ ገበሬዎች ላይ የፈጸመው ግፍ ይህ ብቻ አይደለም፤ ተፈናቃዮቹ በቶሎ ባህር ዳርን ለቀው ካልወጡና ተጠልለው የሚገኙበትን ቤተ ክርስቲያን ካልለቀቁ በወያኔው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መሰረት ሁሉም ተፈናቃዮች ለስድስት ወር እንደሚታሰሩ አስጠንቅቋቸዋል። ያስጠለላቸው የዐባይ ማዶ ቅዱስ ገብርኤል ቤተ ክርስቲያንም ካሁን በኋላ ተፈናቃዮችን ካስጠለለ እንደሚጠየቅ ተነግሮታል። ነውረኛው ብአዴን ለሀያ ሰባት አመታት አማራን የወከለው በዚህ መልኩ ነበር።