**መነሻ ጭብጥ- ይህ ጽሁፍ የተጠናቀረው ሰሞኑን ከ “ህዳሴ ኢትዮጵያ” በሚል ጸሃፊ ስም በአይጋ ፎረም ላይ ለወጣው መጣጥፋቸው መልስ ታስቦ ሲሆን ጸሃፊው 25ገጽ የፈጀውን የጽሁፋቸውን ርእስ «አብዮታዊ ዲሞክራሲ እየተሸረሸረ ነው» በሚል ዋና አርእስት ስር «አብዮታዊ ዲሞክራሲን ማዳን ማለት ኢትዮጵያን ማዳን ማለት ነው» በሚል ለጻፉት እኔ ደግሞ «አብዮታዊ ዲሞክራሲን መቅበር ኢትዮጵያን ማዳን ማለት ነው» በሚል መልስ አቅርቤያለሁ፡፡
ጸሃፊው ህዳሴ ኢትዮጵያ 25ገጽ በፈጀው ጽሁፋቸው ደግመው ደጋግመው በመግለጽ አንባቢን ለማስረዳት የጣሩት የዘርፈ ብዙው የሀገራችን ፖለቲካዊ፣ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች መንስኤን የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ በአመራሩ መተግበር አለመቸል መሆኑን ያሰምሩበትና ለመፍትሄውም ብቸኛው መንገድ ይህን እየተሸረሸረ ነው ያሉትን አይዲኦሎጂ ሙሉ በሙሉ በመተግበር ብቻ ነው ሲሉ ይደመጣሉ፡፡
እንደጸሃፊው አባባል ላለፉት 2-3ዓመታቶች ውስጥ የተጋፈጥናቸው ሀገር አቀፍ ችግሮች አራቱ የኢህአዴግ ድርጅቶች በተዘፈቁበት ውስጣዊ ዝቅጠት የተነሳ አብዮታዊ ዲሞክራሲ ተሸርሽሮ ተሸርሽሮ እጥቅም ላይ ባለመዋሉ ምክንያት የተፈጠረ ችግር እንጂ (ያ ማለት በአፈጻጸም ብቃትና አቅም ማነስ የተነሳ ማለታቸው ነው)በራሱ በአብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ የሀገሪቷን ችግር መፍታት አለመቻል የተነሳ የተፈጠረ ችግር አይደለም ብለው ያምናሉ፡፡
ይህ እምነታቸውም ተጠናክሮ በመቀጠል አዲሱ ጠ/ምኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የኢህአዴግ መስመር በሆነው አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ በመመለስና ብሎም በመጠቀም የሀገሪቱን ችግር መፍታት አለባቸው በማለት የአብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ አይዲኦሎጂን ዘመን አይሽሬ አስፈላጊነትን ይገልጹና ይህንንም ጽሁፍ ለማዘጋጀት የተገደዱት «ዋና አላማዬ ለሀገር የሚበጅ ነገር አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው» ሲሉ አላማቸውን ገልጸዋል፡፡
በእርግጥ ጸሃፊው እንዳሉት አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ (መስመር) ለሀገራችን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች መፍትሄ ነውን ወይንስ አባባሽ ፈንጂ ነው የሚለውን ክፍል ከማቅረቤ በፊት «…ለሀገር የሚበጅ ነገር አስተዋጽኦ ለማድረግ ነው» ባሉት ጉዳይ ላይ ማሳወቅ ያለብኝን እውነታ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
የጸሃፊውን ባለ25ገጽ ጽሁፍ ሲያነቡ እጅግ ጎልቶና ገዝፎ የሚያገኙት ጸሃፊው ለድርጅታቸው ኢህአዴግ በተለይም የድርጅቱ መስመር ላሉት አብዮታዊ ዲሞክራሲ ብቻ እንደሆነ በማያሻማ ሁኔታ መረዳት ይችላሉ፡፡ እውነተኛ ለሀገር ያሰበ ሰው ላሰበለት ሀገር ውስጥ ለተፈጠረው ችግር እውነተኛ የሆነን ፍቱን መድሃኒት(መፍትሄ)ያግኝለት ዘንድ ያቅሙን ሲጥር ይታያል፡፡ ያንንም ፍቱን መድሃኒት ለማግኘት የሚቀድመው የችግሩን አይነትና መንስኤን ሳይሸሽጉ በይፋ
በመቀበልና በማሳወቅ ቢሆንም በ«በህዳሴ ኢትዮጵያ» ጽሁፍ ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ችግር የአብዮታዊ ዲሞክራሲን አፈጻጸም ጉድለት የወለደው የስራ አጥነት፤ኪራይ ሰብሳቢነት፤ የቢሮክራሲያዊ ችግር ብቻ ነው ብለው ነው የሚያብራሩት፡፡ እንደ እሳቸው አመለካከት የህዝባችን ቀንደኛ ጠላት ድህነት ሲሆን የህዝቡም ጥያቄ የልማት ጥያቄ ነው ብለው ሲገልጹ ሳይ እኚህን ሰውዬ እንቅልፍ ነስቶ 25ገጽ ያስቸከቸካቸው ጉዳይ የሀገራችን ችግር ሳይሆን የድርጅታቸው ኢህአዴግ በተለይም የህወሃት እንደሆነ በግልጽ ማየት እንችላለን ማለት ነው፡፡
ድህነት በእርግጥም እሳቸው እንዳሉት የህዝባችን ጠላት ነው ነገር ግን የድህነታችን ምንጭና መንስኤው የአብዮታዊው ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ ውጤት መሆኑን በመግለጽ የህዝቡም ሁለንተናዊ ጥያቄ ከልማት ባሻገር የዴሞክራሲያዊ እሴቶቹ መከበር ጥያቄ እንደሆነ ለምን ሊያምኑ አልፈለጉም ብለን ስንጠይቅ የሰውዬውን ጭንቀት ለማን እንደሆነ ቁልጭ አድርገን ማየት ይችለናል ማለት ነው፡፡
ጸሃፊው በመግቢያቸው ላይ «የኢትዮጵያ ሕዝብ ኢ ከሌሎች የፖለቲካ ፓርቲዎች አወዳድሮ ኢህአዴግን ሲመርጥ በመስመሩ /አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ልማታዊ ዲሞክራሲ/ ነው የመረጠው» በማለት የ27ዓመቱን አሰልቺ ፕሮፖጋንዳ በመግለጽ ለሀገር በማሰብ ነው በሚል ሽንገላ ተጃጅለው ሊያጃጅሉ ሲውተረተሩ ታይተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህዝብ አይደለም በዘመነ ኢህአዴጉ አብዮታዊ ዲሞክራሲ አገዛዝ ይቅርና በታሪኩም አንድም ግዜ ይመራኛል ብሎ ያመነበትን ፓርቲና እጩ መርጦና ለስልጣንም አብቅቶ የማያውቅ ህዝብ ሆኖ ሳለ እኚህ ጸሃፊ (ምናልባትም አቶ በረከት ሳይሆኑ አይቀሩም) ግን አይናቸውን በጨው አጥበው እኛንም ጨፍኑና ላሞኟችሁ በሚል እሳቤ ጉልበተኛው ድርጅታቸው ኢህአዴግ በህዝብ የተመረጠ ድርጅት ነው ሲሉን በእርግጥ እሳቸውና ጽሁፋቸው ለሀገራችን ዘርፈ ብዙ ችግሮች የመፍትሄ አካል የሆኑ ሳይሆን የችግሩ አካል የሆኑ መሆናቸውን እንድንረዳ ያደርገናል፡፡
የመፍትሄዎች ሁሉ መጀመሪያው ችግሮቹንና መንስኤውን ሳይደብቁ ማወቅና መቀበል ነውና እኚህ ጸሃፊ የመፍትሄያችን አካል አይደሉም፡፡
**ለሀገራዊ ችግሮቻችን መፍትሄው የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ ሙሉ በሙሉ መተግበር ነው ወይንስ ሙሉ በሙሉ መወገድ ነው የሚሆነው ?
በአቶ መለስ ዜናዊ ፍላጎት፤ራእይና ወርድ ቁመና ልክ ተለክቶና ተመጥኖ የተፈጠረው አብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ ገጽታና ማንነት፡፡
ከሁሉ በፊት ይህ አብዮታዊ ዲሞክራሲና ኢህአዴግ ያጸደቀው ህግ መንግስት በዲ ኤን ኤ እማይገናኙና እንዲያውም አንደኛው ለሌላኛው ህልውና ጸር የሆኑ ተቃርኖዎች መሆናቸውን ቀድሜ ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
ምእርባዊያኑን ለማታለል ታስበው በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት የይስሙላ መብቶችና ህግጋቶች በይዘታቸውና በአተረጓጎማቸው መቼም ቢሆን ከአብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ ጋር ሊጣጣሙ ይቅርና ሊተዋወቁ እንኳን እማይችሉ ባላንጣዎች መሆናቸውን የምንስተው አይደለም፡፡
የአቶ መለሱ አብዮታዊ ዲሞክራሲ በይዘቱና አቀራረቡ የአንድ ፓርቲ አገዛዝን አስፍነው ኢኮኖሚያዊ እድገትን ካስመዘገቡት የሩቅ ምስራቅ እስያ ሀገራትን ልምድና አይዲኦሎጂ ቅጂ የሆነው አብዮታዊ ዲሞክራሲ እራሱን በልማታዊ መንግስት በይበልጥ የሚያስተዋውቅ
አይዲኦሎጂ ሲሆን የፖለቲካውንና ኢኮኖሚውን በመንግስታዊ ሞኖፖል ስር መሆንን የሚደነግግ ስርዓት ነው፡፡
አይዲኦሎጂው ለዜጎች በተናጥልም ይሁን በወል ተፈጥሮአዊ መብቶች መከበር ቅንጣት ስፍራንና እውቅናን በመንፈግ በአንጻሩም በገዢው ድርጅት ውስጥ ማእከላዊነትን ያጠበቀ ዲሞክራሲያዊ ባህል እንዲዳብር በመጣር በውጪኛው ክፍል ላይ ማለትም በሚገዛው ህዝብ ላይ በውስጥ ድርጅታዊ ዲሞክራሲ የሚመረጥንና የሚወሰንን ያለአማራጭ ተቀባይነትን በኋይል አስፍኖ ሀገሪቷን መግዛት የሚል አይዲኦሎጂ ሆኖ ሳለ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት የይስሙላ መብቶችና ዲሞክራሲያዊ እሴቶች መኖር ከዚህ አይዲኦሎጂ ጋር እሳትና ጭድ እንዲሆኑ አድርጓቸዋል ማለት ይቻለናል፡፡
ዛሬ በሀገራችን ውስጥ ያለው ዘርፈ ብዙ ፖለቲካዊ፣ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች ዋና መንስኤ በህገ መንግስቱ ላይ የሰፈሩት አናሳ መብቶችና ህግጋቶች ባለመከበር የተነሳ ሀገሪቷ በአንድ አምባገነናዊ አገዛዝ ስር በመውደቋ የተፈጠረ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ የውድቀት ውጤት ሆኖ ሳለ እኚህ «ህዳሴ ኢትዮጵያ» የተባሉ ጸሃፊ ለችግሮቻችን መፍትሄ የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አይዲኦሎጂ ሙሉ በሙሉ መተግበር ነው ማለታቸው በእርግጥም ያላቸው ከፍተኛ ፍቅርና ስጋት ለድርጅታቸው እንጂ ለሀገራችን እንዳልሆነ በግልጽ የሚያሳይ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡
የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አይዲኦሎጂ እራሱን በልማታዊ ዲሞክራሲና በልማታዊ መንግስት ስም የቀረበለት የኢትዮጵያ ህዝብ ላለፉት 27ዓመታት የተጋፈጣቸውን ችግሮች መሸከም ከሚቻለው በላይ በመድረሳቸው ከጫንቃው ላይ አሸቀንጥሮ ለመጣል ከዳር እስክ ዳር ሆ ብሎ የተነሳው ይህው አይዲኦሎጂ በፈጠረው ችግር ተማሮ እንጂ ጸሃፊው እንዳሉት በአፈጻጸም ጉድለት በተፈጠረ ችግር ተበሳጭቶ እንዳልሆነ መስዋእትነቱን የከፈለው ሰፊው ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል፡፡
ህዝብ ለአስተዳደራዊ ችግሮች ነው እንዴ ይህን ያህል መስዋእትነት እየከፈለ ለመታገል የተገደደው ብለው እኚህን ጸሀፊ ቢጠይቁ መልሱ ባይገጥምም የሚመልሱትን እንደማያጡ እያወቅኩ በኦሮሚያ ከ6400 በላይ በአማራ ከ2600በላይ ንጹሃን የተሰውበት ህዝባዊ ጥያቄ 1ኛ-የስርዓት ለውጥ 2ኛ-አጠቃላይ የፖለቲካ እስረኞች መፈታት 3ኛ-የህግ የበላይነት መስፈንና በመሬታችን ወሳኝና አዛዥ እራሳችን እንሁን…የሚሉ ወዘተ ጥያቄዎች ሆነው ሳለ ጸሃፊው ግን የህዝቡን ጥያቄ አውርዶ አውርዶ በአስተዳደራዊ ጉደለት ደረጃ መመደቡ ድርጅቱ ውስጥ አሁንም እማይለወጡ ኋይሎች እንዳሉን አመላካች ሆኖኗል ለማለት አስችሎኛል፡፡
የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አይዲኦሎጂ መሸርሸር ብለው ጸሃፊው ለአብነት ካቀረቧቸው ናሙናዎች ውስጥ ጥቂቱን ለመጥቀስ ያህል –
**የአስቸኳይ ግዜ አዋጁን በፓርላማ እንዳያልፍ የተቃወመውን ኦህዴድን እንደ ጸረ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እርምጃ በመቁጠር
**የዶ/ር አቢይ ወደ ኢህአዴግ ሊ/ነት የመጡበት የምርጫ ሂደትና ውጤትን ኢ-አብዮታዊ ዲሞክራሲ ነው ማለታቸው
**የአቶ ደመቀ መኮንን እና የብአዴንን ከኦህዴድ ጋር ያደረገውን መደጋገፍ በመርሃ አልባ ግንኙነት ስር መመደባቸው
**የፖለቲካ እስረኞች መፍታትን እንደ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ መሸርሸሪያ ተግባሮች አድርገው መግለጻቸው
**በእነ አቶ ለማ መገርሳ የተሰበከውን ኢትዮጵያዊ አንድነትንና የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ስራን እንደ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ተጻራሪ አድርጎ ማቅረብ
**የፌዴራሉን ባለኮከብማ ባንዲራን በየክልሎቹ አለመከበርን
**በባህር ዳር የትምክህተኞች ጎራ አንሰራርቶ ጠ/ም ዶ/ር አቢይን የተለየ ጥያቄ ማቅረብን
**በኦሮሚያና አምሃራ በተነሳው ህዝባዊ እምቢተኝነት የተነሳ የሁለቱ ክልል መሪ ድርጅቶች ኦህዴድና ብአዴን የተጫወቱትን ህዝባዊ ወገንተኝነትን
**የቋንቋና ባህልና መሬት ጥያቄን እና የመሳስሉትን እንደ ጸረ አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊነት በማቅረብ አዲሱ የዶ/ር አቢይ መራሹ አመራር ወደ መስመሩ አብዮታዊ ዲሞክራሲ መመለስ አለበት ሲል ይሞግታል፡፡
በአጠቃላይ የጸሃፊውን ዋና መልእክት ስናይ ሀገሪቱን እያረጋጋ ያለውን እርምጃዎች ሁሉ በጸረ አብዮታዊ ዲሞክራሲነት በመፈረጅ የአይዲኦሎጂው መሸርሸር ሲል ይገልጸዋል፡፡፡
እንደጸሃፊው አባባል የሀገሪቱን ችግር ለመፍታት በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር ብቻ መጠቀም እንደሚገባ ያሰምርበትና ይህንን ለማድረግም ቢሆን ዛሬም በአዘቅጥ ውስጥ ቢሆንም ገና አላከተመም ሲል ተስፋ ያደርጋል፡፡
የሀገራችንን ችግር በአብዮታዊ ዲሞክራሲ መስመር መፍታት ማለት የተፈቱት የፖለቲካ እስረኞች በሙሉ ወንጀለኛ ስለሆነ ወደ እስር ቤት ተመልሰው በመታሰር መንግስት የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት ቃል የገባውን በሙሉ እርግፍ አድርጎ በመተው ባለው ወታደራዊ ኋይል ተጠቅሞ ህዝባዊ ጥያቄውን በጉልበት መመለስ ማለት ነው እንደጸሃፊው አባባል፡፡
ጸሃፊው ስለ ኢህአዴግ ወቅታዊ ሁኔታ ከገለጹት ልቀንጭብ ..«…በአሁኑ ሰዓት ኢህአዴግ ከመቸውም በበለጠ ከመበስበስና ከዝቅጠት አዘቅት የሚያወጣው የውስጥ ሓይል ይፈልጋል፡፡ የኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶች በአሁኑ ደረጃ አፍን ሞልቶ ታድሷል ለማለት አያስደፍርም፡፡ በተለይ አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስተር ክቡር ዶ/ር አብዪ የሚመሩት ድርጅት ጨምሮ ሌሎች የኢህአዴግ ኣባል ድርጅቶችም ከአብዮታዊ ዴሞክራሲ እሴቶችና መርሆዎች ውጭ ሲንቀሳቀሱና በዝቅጠ አዘቅት ተዘፍቆ የለውጡ/የተሃድሶው ሻምፒዮን መስሎ ለመታየት…»እያሉ ለአዲሱ ጠ/ምኒስትር ዶ/ር አቢይ የአብዮታዊ ዲሞክራሲን አስፈላጊነት ሊግቱ ሲውተረተሩ ይታያሉ፡፡
ሀገራችን በታላቅ ፖለቲካዊ፤ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግሮች አረንቋ ውስጥ ተዘፍቃ ህልውናዋ በአደጋ ላይ የወደቀ ሀገር ናት፡፡
የችግሮቻችን አስኳልም የዲሞክራሲያዊ እሴቶች መጥፋት እንጂ የአብዮታዊ ዲሞክራሲ ስርዓት አለመተግበር አይደለም፡፡ በእርግጥም አብዮታዊ ዲሞክራሲ የአስኳሉ ችግራችን ፈልፋይና
አፍላቂ ኋይል ሆኖ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ህልውና ለከፍተኛ አደጋ የዳረገ ኮሚኒስታዊ ርእዮት እንደመሆኑ መጠን ዛሬ እየተንኮታኮተ ያለውን ይህንን ራእይና አይዲኦሎጂ መታደግና ማዳን ማለት ለመዳን ተስፋ የሰነቀችውን ሀገራችንን መልሶ ማጥፋትና ብሎም መግደል ስለሆነ አንድን ትናንት የተፈጠረን ጨፍጫፊና ዘረኛን ፋሽስታዊ ድርጅትን ለማዳን ሲባል ከአራት ሺህ በላይ እድሜ ያላትንና ከመቶ ሚሊዮን በላይ ህዝብ መኖሪያ የሆነችውን ሀገራችንን ህልውና ለአደጋ የሚያጋልጥ መሪ ከህወሃቶ አቶ መለስ በስተቀር ያለ አይደለምና ከእንግዲህ ጨቋኙን አይዲኦሎጂ ለማዳን መፍጨርጨር ግዜ ያለፈበት ከንቱነት ነው በማለት ጽሁፌን እደመድማለሁ
አስተያየትና ጥያቄያችሁን teklu7@gmail.com ጻፉልኝ እመልሳለሁ