
እየታየ ያለው ለውጥ፤ የቅርጽ ወይስ የይዘት?
ብርሃኑ አበጋዝ (ዶ/ር)
***
ጭብጥ
***
የጽሑፌ ጭብጥ፣ አሁን በአገራችን እየታየ ያለው ለውጥ የቅርጽ እንጂ የይዘት አይደለም የሚል ነው፡፡
መግቢያ
***
አንድ፣ ተርታው (ordinary) ዜጋ ሳይቀር እተገነዘበው የመጣ ሐቅ አለ፡፡ ይህም ሐቅ ገዥውን ግንባር የተመለከተ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ደንብሿል፤ አርጧል፤ አዲስ ሐሳብ ማመንጨት አይችልም፡፡ ይኽ እውነት ነው፡፡ ገዥው ግንባር ዘመኑን የዋጀ ሐሳብ የሚያፈልቅ አዲስ ኀይል ማፍራት የማይችል ድርጅት ሆኗል፡፡ አሁንም የድርጅቱ ከፍተኛም ይኹን ዝቅተኛ አመራሮች አቶ መለስ ባዘጋጇቸው መጻሕፍት ነው ስልጠና እየወሰዱ የሚገኙት፡፡ አዲስ ራዕይ የተባለው የድርጅቱ የንድፈ-ሐሳብ መጽሔት ሳይቀር አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ጊዜ ያዘጋጇቸውን ጽሑፎች እንደገና እየቀባባ ማወጣት ጀምሯል፡፡ ጥልቅ ተሐድሶ የሚለው “አዲሱ” የኢሕአዴግ መርሐ ግብርም በአቶ መለስ አስተምህሮዎች ላይ የተንጠለጠለ እና የእሳቸውን ጽሑፎች መሠረት ያደረገ ነው፡፡
የሚገርመው የገዥው ግንባር መሪዎች ለስልጠና ሳይቀር አቶ መለስ የተናገሯቸውን ንግግሮች (ቪዲዮዎች) በመጠቀም ላይ ናቸው፡፡ አሁንም የሐሳቡ አምንጭም አሰልጣኙም አቶ መለስ ናቸው፡፡ አንዳንዴም በብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያው ሳይቀር የአቶ መለስ ንግግሮች ይቀርባሉ፡፡
ጥልቅ ተሐድሶ በሚባለው መርሐ ግብር ከቀረቡት ነጥቦች ውስጥ “መስመር መሳት” የሚል ይገኝበታል፡፡ መስመር መሳት የተባለውም በአቶ መለስ የተዘጋጁትን ፖሊሲዎችና ፕሮግራሞች መተው ማለት ነው፡፡ አዲስ ሐሳብ፣ ከዘመኑ ጋር ሊሄድ የሚችል አቀራረብ ከድርጅቱ መስመር እንደመውጣት ይቆጠራል፤ ያስገመግማል፡፡ “ዴሞክራሲያዊ ልማታዊነት እና/ወይም አብዮታዊ ዴሞክራሲ” ከሚባለው መስመር ውጭ የሚታሰብ ነገር የለም፡፡
የግንባሩ ከፍተኛ አመራሮችም ሆኑ አፈ ጮሌ (እና አድርባይ) ካድሬዎች የሚናገሩት ሁሉ የዛገና አዲስ ነገር ጠብ የማይለው እየሆነ፣ እንኳን ለሕዝቡ ለራሳቸው ለአባላቱም እጅ እጅ እያላቸው ምጥቷል፡፡ አሁንም እንደትናንቱ በጠላትነት የሚቀመጡት የፈረደባቸው ኪራይሰብሳቢነት፣ ትምክህት፣ ጥበት፣ ኒዮሊብራሊዝም የሚባሉት ጉዶች ናቸው፡፡ በዘመነ ደርግ የጥበቃና የቤት ሠራተኞች ሳይቀሩ ስለጭቁኑና ስለበዝባዡ “የፊውዶ ቡርዧ መደብ” እየተንደቀደቁ ይናገሩ እንደነበረው ሁሉ፣ የኢሕአዴግ ካድሬዎችም ምንነቱን ስለማያውቁት ኒዮሊብራሊዝም አንገታቸውን እየሰበቁ ይናገራሉ፤ ምንነቱን ስለማያውቁት ልማታዊ መንግሥት በፍፁም ልበ-ሙሉነት “ይተነትናሉ”፡፡ የፈረደባቸው እነ ፍራንሲስ ፉኩያማም የስድብና የውግዘት መዓት ይወርድባቸዋል! ለአብነት ያህል የሚዲያ ዳሰሳ በሚባለው ፕሮግራም ላይ የሚቀርቡትን “ድንቅ የምሁራን ትንታኔዎች” ማየት ነው፡፡
አቶ መለስ በሕይወት በነበሩበት ወቅት ተጀምሯል የተባለው የመተካካት ሂደት ውኃ በልቶታል፡፡ ዛሬ ኢሕአዴግ ውስጥ ስለዚህ አጀንዳ የሚያነሳ አንድም ሰው የለም፡፡ ሌላም ብዙ የድርጅቱን ቆሞ-ቀርነት ሊያስረዱ የሚችሉ አብነቶችን ማንሳት ይቻላል፡፡
የሆነ ሆኖ፣ ነገሮች ሁሉ እንዲህ ባሉበት እየረገጡም ቢሆን ኢሕአዴግ ሃያም ሠላሳም ዓመት ሊገዛ የሚችልበት ዕድል አለ፡፡
“ያረጀው ሥርዓት እየሞተ ነው፤ አዲሱ ሥርዓት ግን ገና አልተወለደም”
***
ዝነኛው ጣሊያናዊ ፈላስፋና የፖለቲካ መሪ አንቶኒዮ ግራምሺ “ያረጀው ሥርዓት እየሞተ ነው፤ አዲሱ ሥርዓት ግን ገና አልተወለደም” የሚል ዘመን አይሽሬ አባባል አለው፡፡ አንድ ገዥ ፓርቲ ሐሳብ የደረቀበት፣ ያረጠ ድርጅትም ቢሆን እንዲሁ በቀላሉ ይንኮታኮታል ማለት አይቻልም፡፡ ለበርካታ ዓመታት በሥልጣን ላይ በመኖሩ ምክንያት የገነባቸው ልዩ ልዩ ኀይሎች እስካሉ ድረስ ያውን፣ እጅ እጅ የሚለውን ሐሳቡን እንደያዘ ሕዝብ እያስለቀሰም ቢሆን ይኖራል፡፡
በእርግጥ አንድ ድርጅት አዲስ ሐሳብ ማፍለቅ አለመቻሉ፣ ይልቁንም ትኩስ የፖለቲካ ትውልድ መፍጠር አለመቻሉ ለድርጅቱ ትልቅ ጉዳት መሆኑ አያጠራጥርም፡፡ ይሁን እንጂ ድርጅቱ አዲስ ሐሳብ ማፍለቅ አልቻለም ማለት ነገሩ አለቀ ደቀቀ ማለት አይደለም፡፡ በፍፁም! እንዲያ ቢሆን ኖሮ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት ገዥ ፓርቲዎች መንግሥታዊ ሥልጣንን ርስት ባላደረጉትም ነበር፡፡ የዙምባቡዌው አምባገነን ሮበርት ሙጋቤና ድርጅታቸው ዛኑ ፒኤፍ ለዚህ ትልቅ አብነት አይደሉምን? የዩጋንዳው አምባገነን ዩዌሪ ሙሴቬኒና ድርጅታቸውስ? የሱዳኑ ጀኔራል አልበሽርስ? ፈላጭ ቆራጩ ኢሳያስ አፈወርቂስና ድርጅታቸው ሕግዴፍስ? ኧረ ስንቱ! አፍሪካማ በዚህ በኩል ሀብታም ነች፡፡
ቁም ነገሩ፣ ግራምሺ እንዳለው በሥልጣን ላይ ያለው የፖለቲካ ኀይል እያረጀና እያፈጀ ያለ ቢሆንም የብዙሃኑን ሕዝብ ቀልብ ሊገዛ የሚችል፣ አዲስና ዘመኑን የዋጀ ጠንካራ (ተቀናቃኝ) የፖለቲካ ኀይል እስካልተፈጠረ ድረስ ነገሩ ሁሉ ባለበት ይቀጥላል፡፡
በእኔ እይታ የወቅቱ የአገራችን እውነታ ይኽን የመሰለ ነው፡፡ ኢሕአዴግ ያለጥርጥር አርጧል፡፡ በዚህ ላይ መከራከር አይቻልም፡፡ የኢሕአዴግ ከፍተኛ አመራሮች በአልሞት ባይ ተጋዳይነት ስሜት (ውስጣቸው እውነታውን እያወቀው) ሊነገሩን እንደሚሞክሩት ሳይሆን ገዥው ግንባር ራሱን ሊያድስ ከማይችልበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ሆኖም የአገራችንን ሕዝብ (ብዙሃኑን) ከጎኑ ሊያሰልፍ የሚችል የጠራ የፖለቲካ ፕሮግራም እና ጠንካራ ድርጅታዊ ቁመና ያለው የፖለቲካ ኀይል ስለሌለ ላልተወሰኑ ዓመታት በዚኸው ባረጠው ድርጅት እየቆሰልን መቀጠላችን የማይቀር ነው፡፡ አለመታደል!
ኢሕአዴግ እንደማንኛውም የሐሳብ የበላይነት (hegemony) ድርቅ እንደመታው ድርጅት፣ ፕሮግራሙን ለሕዝብ አቅርቦ መሸጥ እንደማይችል ስለተረዳ፣ በአንድ በኩል የፖለቲካ አመራሩን ትቶ በጸጥታው ዘርፍ ላይ ከፍ ያለ ትኩረት አድርጓል፡፡ የፖለቲካ ምልሽ የሚያስፈልጋቸውን መሠረታዊ የሕዝብ ጥያቄዎች በሰለጠነ መልኩ ከመፍታት ይልቅ የጸጥታ ኃይሉን እየተጠቀመ ጥያቄ አቅራቢዎችን ዝም ለማሰኘት ሲሞክር በስፋት ይታያል፡፡
አሁን አሁን ደግሞ ሕዝበኛ (populist) አጀንዳዎችን የሚያራምዱ አመራሮችን ወደፊት በማምጣት የሕዝቡን መሠረታዊ ጥያቄ ለማስቀየስ ጥረት ሲያደርግ ይስተዋላል፡፡ የዜጎችን ሁለንተናዊ የኑሮ ሁኔታ የሚያሻሽል፣ ከጊዜው ጋር የሚሄድ የፖለቲካ ፕግራምና ከዘመኑ የሚዘምን ድርጅታዊ ቁመና ሳይኖር ሲቀር የሕዝብን ስሜት በሚኮረኩሩ አላፊ ጠፊ አጀንዳዎች ላይ ትኩረት ይደረጋል፡፡ ሕዝበኝነት የዚኽ ስሜታዊ አጀንዳ ዋናው መገለጫው ነው፡፡
የኢሕአዴግ መሪዎች ከዘመናት በኋላ የኢትዮጵያ ገናና ታሪክ የተገለጸላቸው እና ስለ ኢትዮጵያና ስለ ሕዝቧ ታላቅነት የሚዘምሩት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ የሰሞኑ የነአቶ ለማ መገርሳ የ“ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” ተረክ ምንጩም ይህ ሕዝበኛ አጀንዳ (populism) እንጂ ሌላ ምንም አዲስ ምክንያት የለውም፡፡
ከዚህ በኋላ ኢሕአዴግ ከተቻለ ይህን ሕዝበኛ አጀንዳ እነ መልግሥቱ ኀይለማርያምን በሚያስንቅ መልኩ ይገፋበትና የሕዝብን ስሜት ኮርኩሮ ድጋፍ ለማግኘት ይጥራል፡፡ ይህ ስትራቴጂ የማያዋጣ ከሆነ ደግሞ ያው የጽጥታ (security) አማራጩን እየተጠቀመ ያዘግማል፡፡ በእርግጥም እንደአስፈላጊነቱ ኹለቱን ስትራቴጂዎች እያፈራረቀ እየተጠቀመ ላልተወሰነ ዓመታት መግዛት (መምራት አላልኩም) ይችላል፡፡ በሙሰኞች ላይ እየተወሰደ ነው የሚባለው ሙስናን የመዋጋት ድራማም ሆነ የከፍተኛ ባለሥልጣናት ከኀላፊነት “መልቀቅ” ሁሉ ከዚህ ከመቀባባት እና ሕዝበኛ አጀንዳ ጋር የሚያያዙ ኩነቶች ናቸው፡፡
በነገራችን ላይ፣ ኢሕአዴግ የተቀናቃኝ (በግንባሩ የንደፈ-ሐሳብ ሰነዶች ላይ “ጠላት” ተብለው ነው የሚታወቁት) የፖለቲካ ኀይሎችን አጀንዳ ወይም ጩኸት በመቀማት የሚደርስበት ስለሌለ፣ ራሱ ሕዝበኛ አጀንዳ እያራመደ “ሕዝበኛነት በድርጅታችን ውስጥ ተቀባይነት የለውም፤ ስለሆነም አጥቀን እንታገለዋለን፤” ይላል፡፡ ሙስናን የሚቀፈቅፍ ፖሊሰ ባለቤት ሆኖ ሳለ፣ “ሙስናን እየተዋጋሁ ነው፤ ሙስና የእኔ መገለጫ አይደለም፤” እንደሚለው ማለት ነው፡፡
የቅርጽ ወይስ የይዘት ለውጥ?
***
በዘውግ ላይ የተመሠረተው ፌደራላዊ ሥርዓት ይቀጥላል፡፡ ኢሕአዴግ የሚያራምደው መሠረታዊ ንድፈ-ሐሳብ አሁንም “አብዮታዊ ዴሞክራሲ” እና/ወይም “ዴሞክራሲያዊ ልማታዊነት” ነው፡፡ አብዮታዊ ዴሞክራሲ ደግሞ ኅብረተሰብን በወዳጅ-ጠላት ትንታኔ መነጽር የሚተነትን ንድፈ-ሐሳብ ነው፡፡ ስለ መድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ፣ ስለ ሕግ የበላይነት፣ ስለ ፍትሕ ወዘተ. ቢሰበክም፣ እነዚህ አጀንዳዎች ተፈጻሚነት የሚኖራቸው የኢሕአዴግ መሥመር አደጋ ላይ እስካልወደቀ ጊዜ ድረስ ብቻ ነው፡፡ ድሮም ኢሕአዴግ “ዴሞክራሲ የህልውና ጉዳይ ነው” ይል ነበር፡፡ ዴሞክራሲያዊ ድርጅት እንዳልነበረ ግን አሳምረን እናውቃለን፡፡ ድሮም ኢሕአዴግ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስለማክበርና ማስከበር ይናገር ነበር፡፡ የዜጎችን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች አክብሮና አስከብሮ እንደማያውቅ ግን አሳምረን እናውቃለን፡፡ ሌላም ሌላም፡፡
ስለሆነም ድርጅቱ የሚመራበት መሠረታዊ ንደፈ-ሐሳብ (አብዮታዊ ዴሞክራሲ/ዴሞክራሲያዊ ልማታዊነት) ባልተቀየረበት ሁኔታ አሁን የሚታየው ለውጥ የቅርጽ እንጂ የይዘት ሊሆን አይችልም፡፡ ስለ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይህን ያህል ጮህ ተደርጎ የሚነገረውም ቢሆን ከይዘት ለውጥ ጋር የሚያገናኘውም ምንም ዓይነት ነገር የለም፡፡ በአሁኑ ሕገ መንግሥት መሠረት ስለ ኢትዮጵያዊነትና ስለ አንድነት የሚነገረው “አንድነት በልዩነት” (unity in diversity) ከሚለው መርሆ በመነሳት ነው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ ስለ አንድነት ሲያወሩ፣ “አንድነት በልዩነት” ማለታቸው እንጂ “ልዩነት በአንድነት” (Diversity in unity) ማለታቸው እንዳልሆነ ሊሰመርበት ይገባል፡፡ ኹለቱ አስተሳሰቦች በጣም የተራራቁና መሠረታዊ ልዩነት ያላቸው አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ እነ ዶ/ር ዐቢይ ከአንድነት ይልቅ ለልዩነት ከፍ ያለ ቦታ ስለሚሰጠው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ነው የሚነግሩን፡፡ በዚህ መርሆ መሠረት አንድነት ከልዩነት ቅድሚያ ወይም እኩል ቦታ አያገኝም፡፡
የኢሕአዴግ ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ካለፈው ታኅሣሥ 3 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ለ17 ቀናት ባደረገው ስብሰባ፣ ግንባሩ የኢትዮጵያ አንድነትን በማቀንቀን ረገድ በርካታ ጉድለቶች እንዳሉበት ግልጾ፣ ይኸው አጀንዳ የድርጅቱ ቀጣይ የቤት ሥራ እንዲሆን አጽንዖት ሰጥቶ መወያየቱ ተገልጿል፡፡ ስለሆነም ከዚህ በኋላ ስለ ኢትዮጵያ አንድነት እና ስለ ኢትዮጵያዊነት በስፋት እንሰማለን፡፡ ምን ዓይነት አንድነት? ምን ዓይነት ኢትዮጵያዊነት? የሚለው ነው መሠረታዊው አጀንዳ፡፡ ምን ዓይነት ዴሞክራሲ? ምን ዓይነት ብሔራዊ መግባባት? …
ኢሕአዴግ የሚመራበት ንድፈ-ሐሳብ ሳይቀየር የይዘት ለውጥ ሊመጣ የሚችልበት ምንም ዓይነት ዕድል የለም፡፡ ንድፈ-ሐሳቡን ሕዝቡ በአዲስ መንፈስ እንዲቀርበውና እንዲቀበለው ማድረግ ግን ይቻላል፡፡ የሚቀርበውን ምርት ወይም አገልግሎት ሳይሆን አቀራረቡን፣ የሚታሸገውን ሳይሆን አስተሻሸጉን መቀየር/ማሻሻል አንዱ የገበያ (marketing) ስትራቴጂ ነው፡፡
የቅርጽ እንጂ የይዘት ለውጥ የለም፤ አይኖርምም፡፡
………………..
ምን ትላላችሁ?
መወያየት መልካም ነው፡፡ እስኪ እንወያይ …