ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ኢህአዴግ ከሚባል ድርጅት መጣ እንጂ በህዝብ ምርጫ አልመጣም። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ህውአት ሲጨንቀው አነገሰው እንጂ ህዝብ ፈቅዶ አልሾመውም። ባልተለመደ መልኩ የሚፈልጉትን አውርደው የማይፈልጉትን የመሾሙ ምስጢር ለአገርና ለህዝብ ታስቦ ሳይሆን በአገርና በውጪ የተነሳባቸውን የለውጥ ማእበል በዚህ መልኩ እናልፋለን ከሚል እሳቤ ነው። ዶክተር አብይ ከህዝብና ከአገር ክብር የድርጅቱን ክብር አስበልጦ ድርጅቴን እታደጋለው የሚል ከሆነ ድርጅት ሆኖ ይቀራል አልያም ለአገርና ለህዝብ ከሰራ ግን ህዝብ በክብር ማማ ላይ ያስቀምጠዋል። ዋናው ቁምነገር ኢህአዴግ ሊያውቁት የሚገባው በጥገናዊ ለውጥ የሚመለጥበት ግዜ ማለፉን ነው።
ጠቅላይ ሚኒስተር አብይ በመጀመሪያ የሹመት ቀን ላይ በፓርላማው ንግግር አድርገዋል። ሲቀጥል በኦጋዴን፣ በአንቦ፣ በትግራይ፣ በጎንደር፣ በባህር ዳር፣ በአዋሳ እንዲሁም ከባለሃብቶች ጋርም ንግግር አድርጓል። አሁን የሚቀረው ከሙሁራን፣ ከሐይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ፣ ከውጪ ከሚኖሩ ኢትዮጵያኖች እና ከጋዜጠኞች ጋር ነው። ከነዚህ አካላት ጋር እንደሚወያይ ተስፋ አደርጋለው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከፓርላማው ጀምሮ በሁሉም አካባቢ የተለያየ ይዞታዎች ነበሩት። በፓርላማው የሰማነው ንግግር ድንቅ ንግግር ነበር። በኢህአዴግአዊ ተቋም በ27 አመት ውስጥ ሰምተነው የማናውቀውን ኢትዮጵያዊነትን የሰማንበት እና ኢህአዴግአዊ  መዋቅር የፈረሰበት ኢህአዴግአዊ ምሽግ የተጣሰበት እውነተኛ ለህዝብና ለአገር የሚያስብ መሪ መናገር ያለበትን ንግግር ነበር የሰማነው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በመቀጠል በኡጋዴን የተጣላን እንታረቅ እኛ ስንዋደድ ጠላት ይሸነፋል በሚል እሳቤ የሱማሌ፣ የአማራ ፣ የኦሮሞ እና ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እጅ ለእጅ በመያያዝ ፍቅራቸውን የገለጽበት።
በአንቦ የኦሮሞ ህዝብ ፍቅር እደሆነና የኢትዮጵያ ዋልታ እንደሆነ በመግለጽ ህዝቡ መሪውን ከቦ ፎቶ በመነሳት ለህዝብ ያለውን ፍቅር የገለጸበት እንደሆነ ተመልክተናል።
በትግራይ ያደረጉት ብስለት ያለው ንግግር ቢሆንም ትግራይን አመሰግናለው ብለው የአማራ ማህበረሰብን ያስቀየሙበት ህውአትን ለማስደሰት ብለው እውነትን የደፈጠጡበት በመሆኑ በትግራይ ያደረጉት ንግግር ሲጠቃለል ተለማማጭነትን ያሳዩበት አድር ባይነት የተንጸባረቀበት ክህውአቶች ውዳሴ ከንቱ የፈለጉበት ንግግር አድርገዋል።
በጎንደር ላጠፉት ጥፋት ይቅርታ ለመጠየቅ የሚችሉ መሪ መሆናቸውን እና ጥፋት ካለ ተቆንጥጠው አልያም ተመክረው መመለስ እንደሚችሉ ያሳዩበት ነበር።
በባህር ዳር ኢትዮጵያ ውስጥ መጠነ ሰፊ ችግር እንዳለ የተረዱበት እና ህዝቡ መከራው ከመብዛቱ የተነሳ ፍራቻን አስወግዶ ለመብቱ ፊለፊት በመጋፈጥ ሞትን እንኳን መፍራት ያቆበት ሰአት እንደሆነ የተረዱበት ሆኖ መጠነ ሰፊ ችግር እንዳለ አምነው ነገር ግን ችግሮቹ በአንዴ መፈታት ስለማይቻል ለመፍቴው ህዝቡ አብሮ እንዲሰራ ያመላከቱበ ነበር።
ከባለሃብቶች ጋር ያደረገው ንግግር ባለሃብቶቹ ወደስራ እንዲገቡና በውጭ ያሉትም መጥተው እንዲሰሩ የተናገሩ ሲሆን ከአገር ውጭ የተቀመጡ ዶላሮች ወደ አገር በማስገባት ሊሰሩባቸው እንደሚገባ ጠቅሰዋል። በአገሪቱ የዶላር እጥረት በከፍተኛ መከሰቱንም ጠቅሰዋል።
በአዋሳ ከፖለቲካው አለም ወጣ በማለት ሰባኪ ሆነው የተገኙበትንም ክስተት አይተናል። ነገ ደግሞ ከሙሁራኑ ጋር፣ ውጭ ከሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ጋር፣ እንዲሁም ከሐይማኖት አባቶችና ከአገር ሽማግሌዎች ጋር እንደሚወያዩ ተስፋ አደርጋለው።
ጠቅላይ ሚንስትሩ በተወሰኑ የኢትዮጵያ ክፍሎች በመዘዋወር ያደረጉት ንግግር ከህዝብ ጋር ለመቀራረብ ይጥቅማቸዋል እንጂ በራሱ የመፍቴ ሃሳብ ሊሆን ግን ከቶውን አይችልም። ኢትዮጵያውስጥ ያለው ችግር እንዲህ በቀላሉ የሚፈታ አይደለም ህውአት ስልጣኑን ለማቆየት ብለው የሰሩት ስህተት እራሳቸውን ጨምሮ በአገር ላይ ከፍተኛ አደጋ ጋርጠዋል። ስለዚህ በኢትዮጵያ በሁሉም አካባቢ አፋጣኝ የፖለቲካ መልሶች የሚሹ ወሳኝና አፋጣኝ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው።
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በጣም የተጣበበ እና ግዜ የማይሰጥበት የመጨረሻው ምእራፍ ላይ ቢመጡም ቆራጥና ጀግና ከሆኑ ትልቅ የታሪክ እድል አግኝተዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአገርና ለህዝብ ታማኝ በመሆን እውነተኛ መሪነታቸውን ካሳዩ 100 ሚሊዮን ህዝብ ከጎኖ የሚያሰልፉበት በተገላቢጦሽ በመቆም አገርንና ህዝብን ክደው ህውአትን አገለግላለው የሚሉ ከሆነ 100 ሚሊዮን ህዝብን በእርሶላይ የሚያምጽበት ግዜ ነውና በሚወስዱት ፈጣንና ወሳኝ እርምጃዎች ህዝብና እገርን የመታደጉ ስራን በመስራት የሚፈተኑበት የመጨረሻው ግዜ ላይ ኖት። ግዜ የማይሰጣቸው ግን ደግሞ በጣም ወሳኝ የሚባሉትን ውሳኔዎችን ጠቆም አድርጌ ልለፍ። ውሳኔዋችን በአፋጣኝ ባለመውሰዶ ህዝብ ውስጥ የተዳፈነው እሳት ከፈነዳ ያኔ የእርሶም ታሪክ የመስሪያ ግዜ ያበቃለታል በጥልቀት ማሰብና በፍጥነት የሚሰራበት ሰአት ለይ ነው። አፋጣኝ ውሳኔዎች ከሚያስፈልጋቸ የመጀመሪያዎቹ እና ግዜ የማይሰጣቸው…….
1. ኢትዮጵያ ውስጥ ከጠቅላይ ሚንስትሩ ትእዛዝ ውጪ ማንም እየተነሳ ህዝብን የሚያስርና ህዝብን የሚገድሉ አካላቶችን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በአዋጅ በማስቆም በግለሰብ ደረጃ ወታደርና እስር ቤት ያላቸውን አካላቶች ምንም አይነት በህዝብና በአገር የሚያደርሱትን ጥፋት በማስቆም ለህዝባችን ዋስትና መስጠት። ወንጀል የሰሩት በሙሉ በህግ እንዲጠየቁ ማድረግ።
2. ኮማንድ ፖስት የሚባለው አካል የህዝብንና የአገር ደንነት ለመጠበቅ የተቋቋመ ሳይሆን በስልጣን ላይ ያሉትን ግለሰብን እና ፖርቲያቸውን ለመታደግ የታለመ ስለሆነ ለአገር ደህንነትና ለህዝብ ሰላም የሚያስቡ ከሆነ በአዋጅ እንደጸደቀው በአዋጅ መሻር አለበት። ከእንግዲህም በኋላ ህዝብንና አገርን ለአደጋ የሚያጋልጡ የሞት አዎጆች እንደማይታወጁ ለህዝብ ዋስትና መስጠት።
3. በኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ባንኮች በሙሉ ላልተወሰነ ግዜ ብድር እንዳይሰጡ በአዋጅ መከልከል። ገቢና ወጪአቸውን በማስላት ለመንግስት እንዲያሳውቁ ማድረግ። በአገር ቤት የታተሙ ሃሰተኛ ብሮችን ከትክክለኛው በመለየት እንዲሰበሰቡ ማድረግ። ህዝቡምን በሃሰተኛ የብር ኖቶች ንብረቱን ተታሎ እንዳይሸጥ መግለጫ በማውጣት የተበላሸውን የባንክ አሰራር በማጥራት ወደትክክለኛው የባንክ አሰራር በመመለስ አስተማማኝ የባንክ አሰራር እንዲኖር ማድረግ።
4. ደንነቱን፣ መከላከያውን ፣ የመገናኛ አውታኖችን፣ የእገር ውስጥና የውጭ ንግድ እንቅስቃሴን፣ ከዝቅተኛ እስከ ከፍተኛ የመንግስ ተቋማት የመሳሰሉት በሙሉ ለቦታው የሚመጥንና ለአገርና ለህዝ አሳቢ የሆኑትን በአፋጣኝ መሾም ያስፈልጋል። ይህ ትክክለኛ ሹመት ከሆነ የህዝብን  ቁጣ ሊያስታግስ ይችላል። ካለበለዛ ግን ግዜው ያበቃና መቀልበሻው ያጥሮታል።
ሳጠቃልለው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ እየተዘዋወሩ ንግግር ማድረግና የህዝቡን ሃሳብ መስማት ጥሩ ቢሆንም ይሄ ግን የመፍቴው አካል አይደለም። መፍቴ ሊሆን የሚችለው ችግሮችን በፍጥነት መፍታት ብቻ ነው። ስለዚህ ለኢአዴግ የሚሰጥ ግዜ የለም።
ከተማ ዋቅጅራ
29.04.2018
Email- waqjirak@yahoo.com