scan0061

  • የተቀበለበት፣ የዳሽን ባንክ አካውንቱ የገቢ ማዘዣ ሰነድ ለፓትርያርኩ በማስረጃነት ተሰጠ
  • “ትክክለኛ ከኾነ አላውለውም፤ አላሳድረውም” ያሉት ፓትርያርኩ ተጨማሪ ማጣራት አዘዙ
  • በሌሎች ባንኮች ባሉት አካውንቶቹ፣ የሚታዩት ከፍተኛ ተቀማጮች ምንጭ እያነጋገረ ነው
  • ቅጥሩን የደለለው፣ የደብረ ገሊላ ቅ/ዐማኑኤል ካቴድራል አለቃ አባ ናትናኤል መላኩ ነው
  • ለራሱና ለጎይትኦም ሲደልልየወደቀውን የካቴድራሉን ጉልላት መስቀል የሚያሠራ ጠፋ!

†††

(አዲስ አድማስ፤ ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም.)

Mmr Goitom

“በሀገረ ስብከቱ የሙስና አዝማሚያ እንጅ ሙስናው የለም፤” ያለው ተመጻዳቂው ሥራ አስኪያጅ ጎይትኦም ያይኑ

በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል፣ የትሩፋት(ነፃ) አገልጋይ የኾኑ ዲያቆን፣ በቢሮ ሥራ ለመመደብ በሚል ለሥራ አስኪያጁ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ፣ 100ሺሕ ብር ጉቦ መስጠታቸውን ከግለሰቡ የተገኘው ማስረጃ አጋለጠ፡፡

ፈቀደ ተስፍዬ የተባሉት አገልጋዩ፣ በዳሽን ባንክ በተከፈተ የሥራ አስኪያጁ የቁጠባ ሒሳብ ልደታ ቅርንጫፍ፣ ባለፈው ዓመት ሐምሌ 4 ቀን 2009 ዓ.ም. የጉቦ ገንዘቡን እንዳስገቡ፣ የገቢ ማዘዣ ሰነዱ(Cash Deposit Voucher) ያረጋግጣል፡፡

በአካውንቲንግ ሞያ በወረዳ ብድርና ቁጠባ ተቋም እንደሠሩና በካቴድራሉ ከ15 ዓመታት ያላነሰ በደጀ ጠኚነት በዲቁና እንዳገለገሉ የሚናገሩት ግለሰቡ፤ ምደባ የጠየቁበት የቢሮ ሥራ፣ ሒሳብ ሹምነት እንደኾነ ተጠቁሟል፡፡ ኾኖም እጅ መንሻ የሰጡበትና በካቴድራሉ አስተዳዳሪ ደላላነት ለማስፈጸም የሞከሩትን ምደባ፣ ከድለላው ክፍያ ጋራ ተያይዞ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት ምክንያት ባለማግኘታቸው፣ ገንዘባቸውን ባለፈው ማክሰኞ ማስመለሳቸው ታውቋል፡፡

Goitom Yaynu Sequar Dashen Bank Saving Acct

በአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት፣ የሠራተኞች ቅጥር የሚፈጸመው፣ ጥያቄው በአድባራት ሲቀርብ በሀገረ ስብከቱ እንደኾነና አሠራሩም የቅጥር ኮሚቴ በማዋቀርና ማስታወቂያ በማውጣት በውድድር እንደሚፈጸም፣ ባለፈው መጋቢት አጋማሽ ከአዲስ አድማስ ጋር ቃለ ምልልስ ያደረገው ሥራ አስኪያጁ መ/ር ጎይትኦም ያይኑ መግለጹ ይታወሳል፡፡ ከአሠራሩ ውጭ የሠራተኛ ቅጥር “አልፎ አልፎ የሚፈጸመው” በአድባራቱ እንደኾነና አለመግባባት የሚፈጠርበት አንዱ መንሥኤ እንደኾነም መናገሩ አይዘነጋም፡፡

ሥራ አስኪያጁ ይህን ይበል እንጅ፣ ከደብረ ገሊላ ቅዱስ ዐማኑኤል ካቴድራል ነፃ አገልጋይ ቅጥር ጋራ በተያያዘ የተጋለጠው ጉቦኛነቱ፣ በሀገረ ስብከቱ የለም እያለ የሚክደው ሙስና ተንሰራፍቶ እንዳለ የተረጋገጠበት አነስተኛው ማሳያና ግብዝነቱን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ ሀገረ ስብከቱ ጽ/ቤት ድረስ በተለይ በሰው ኃይል ቅጥርና ዝውውር የተዘረጋውን የሙስና ሰንሰለትና ሓላፊዎቹ የሚያካብቱትን ሕገ ወጥ ሀብት የሚያጋልጥ ነው፡፡

የማስረጃ ሰነዱ፣ ለብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርኩ መድረሱን ያመለከቱት ምንጮቹ፣ በሥራ አስኪያጁ ድርጊት ከመበሳጨታቸው ይኹን ከመደንገጣቸው የተነሣ፣ “እንደማልቀስ ቃጥቷቸው ነበር፤” ብለዋል፡፡ በሰነዱ ትክክለኛነትና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተጨማሪ ማጣራት እንዲደረግ ያዘዙ ሲኾን፣ እንደተጠናቀቀ አስተዳደራዊና ሕጋዊ ርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ጠቁመዋል፡፡

‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡‡

ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ምንጮች እንደተናገሩት፤

ጉቦውን በማስረጃ ያጋለጠው ፈቀደ ተስፍዬ፣ ከ12 ዓመቱ ጀምሮ በዲቁና በማገልገል ይታወቃል፡፡ የአካውንቲንግ ተማሪ ሲኾን ወረዳ 01 በብድርና ቁጠባ ተቋም ውስጥ ለ5 ዓመታት ሠርቷል፡፡ በሞያው የ8 ዓመት ልምድ አለው፡፡ በዲቁናው ከ20 ዓመት ያላነሰ ካቴድራሉን አገልግሏል፡፡ የድለላ ገንዘብ ከአስተዳዳሪው አባ ናትናኤል መላኩ እየተቀበለ በእርሳቸውም በጎይትኦምም አካውንት በማስገባት ይላላካቸው ነበር፡፡ አባ ናትናኤል የጎይትኦም ደላላ ሲኾኑ፣ ባንክ ቤት ወስዶ በጎይትኦም አካውንት የሚያስገባላቸው ልጁ ነበር፡፡

በዚህም ተስፋ አድርጎ ለካቴድራሉ ሒሳብ ሹምነት ምደባ ሲጠይቅ፣ አስተዳዳሪው ከእርሱ ጋራ በደርዘን የሚቆጠሩ ሰዎችን የቅጥር ጥያቄ በአንድነት አድርገው ለጎይትኦም አቅርበዋል፡፡ አሁን እንኳን አባ ውሂበ የሚባሉ የቤተ መቅደሱ ቁልፍ ያዥ ዐርፈው አስከሬናቸው ወደ ደብረ ሊባኖስ ሳይሔድ በቦታቸው ለመቀጠር ከዐሥር በላይ ሰዎች ናቸው፣ “ብር አስገቡ” እየተባሉ በአባ ናትናኤል እየተጠየቁ ያሉት፡፡

scan0063

ልጁ የጠየቀውን ምደባ እንዲያገኝ ጎይትኦም ደብዳቤ ጽፎለት ነበር፡፡ አባ ናትናኤል ግን፣ ለእኔ ያልከፈልከኝ ቀሪ ብር አለብህ፤ በማለታቸው ተጣልተውት አስቀደዱበት፡፡ እርሳቸው ለደለሉበት 40ሺሕ ብር ነው የጠየቁት፡፡ ሁለት ጊዜ 10ሺሕ ብር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አካውንታቸው እንዳስገባላቸው፣ የገቢ ማድረጊያ ቅጹ ያሳያል፡፡

scan0062

ኃሙስ፣ ሚያዝያ 18 ቀን፣ “ብርህን መልሼልሃለሁ” ብለው አስተዳዳሪው አባ ናትናኤል መላኩ በሞባይል ስልክ መልእክት አስታውቀውታል፡፡ ልጁ፣ 100ሺሕ ብሩን፣ በጎይትኦም የዳሽን ባንክ አካውንት ልደታ ቅርንጫፍ ያስገባበትን ሰነድ ኮፒውን ለራሱ አስቀርቶ ስለነበር ሊክዱት አልቻሉም፡፡“የእኔ ዐይነ ጥላ ይኹን ያንተ ባይታወቅም ሊሳካ አልቻለም፤” ሲሉም አፊዘውበታል፡፡

ከአባ ናትናኤል መላኩ(በቀድሞ ስማቸው መዝገቡ) ጋራ አንድ ቤት ተከራይተው ለረጅም ጊዜ አብሯቸው ይኖር ነበር፡፡ አስተዳዳሪው አሁን ከሴት ሠራተኛቸው ጋራ ነው የሚኖሩት፤ መንጃ ፈቃድም አውጥተውላታል፡፡ ከሐዋሳው የ“ሦስቱ ወፎች” ታሪክ እስከ ዐማኑኤል ካቴድራል እልቅና ድረስ ብዙ ጉድ አለባቸው፡፡ ዛሬም ቤታቸውን የሞላው የእነበጋሻው ስብከት ነው፤ በተሐድሶ ኑፋቄ ከሚጠረጠሩት ጋራ የጠበቀ ወዳጅነት አላቸው፡፡ ክብረ ታቦትን፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ደፍሮ የማስደፈር ዝንባሌ ይታይባቸዋል፡፡ ሥራ ሳይሠሩ የልማት ዐርበኛ መባል ይፈልጋሉ፡፡ ለራሳቸውና ለጎይትኦም የድለላ ብር ሲያካብቱ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ጉልላት ላይ ያለው መስቀል ግን ወድቋል፤ መስጊድ ነው የሚመስለው፤ ሦስት፣ አራት ቀናትን ቢያስቆጥርም ምንም የተሠራ ሥራ የለም፡፡

አባ ናትናኤል መላኩ አሁን ካራ አካባቢ ነው የሚኖሩት፡፡ በዚያው አካባቢ ባለ ሆቴልና ቤት ውስጥም ረቡዕና ዓርብ ቡና እያስፈሉና ዕጣን እያጫጫሱ እንደ ጠንቋይም ያደርጋቸዋል፡፡ ብሥራተ ገብርኤል አካባቢ እርሳቸው ብቻ የሚገቡበትና ወይዛዝርት የሚሰበሰቡበት ቤትም ያዘወትራሉ፡፡