April 30, 2018 – Konjit Sitotaw

ዴሞክራሲን የማስፈን ሒደት፤
(ፓርቲ ወይስ ንቅናቄ?)
***
አሸናፊ ሞላ
***
በአገራችን የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ተፈቅዷል ከተባለበት ከ1984 ዓ.ም. ጊዜ ጀምሮ በርካታ የፖለቲካ ድርጅቶች ተቋቁመዋል፤ ከተቋቋሙት ድርጅቶች መካከል በርካቶች ይህ ነው የሚባል ተግባር ሳይፈፅሙ፣ ሕዝብም ከነመኖራቸው ሳያውቃቸው ሞተዋል፤ የቀሩት በየጊዜው እየተሰነጣጠቁ በከፍተኛ ደረጃ ተዳክመዋል፡፡ ይኹን እንጂ አሁንም አዳዲስ የፖለቲካ ድርጅቶች እየተቋቋሙ ነው፡፡ ለመሆኑ በአገራችን ተጨባጭ የፖለቲካ ሁኔታ የሚያስፈልጉን የፖለቲካ ፓርቲዎች ናቸው ወይስ ንቅናቄዎች?
በዚህ ጽሑፍ አሁን ከምንገኝበት እጅግ አሳሳቢ ሁኔታ እንድንወጣ እና የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንድንገነባ ካስፈለገ በተለመደውና በኖርንበት መንገድ መቀጠል እንደማንችል፤ የሚያስፈልገን ከላይ ከማዕከል ወደታች የሚንቆረቆር ሳይሆን ከታች ወደላይ እየተገነባ የሚሄድ የፖለቲካ ዘይቤ እንደሆነ፣ ይህን ለማድረግ የሚያስችለን አደረጃጀት ደግሞ ፓርቲ ሳይሆን ንቅናቄ ስለመሆኑ ለማብራራት እሞክራለሁ፡፡ በጽሑፉ የመጀመሪያ ክፍል የፖለቲካ ፓርቲና የንቅናቄን ምንነት በአጭሩ ካስታወስኩ በኋላ፣ ለጠቅ አድርጌ ለምን ንቅናቄ እንደሚያስፈልገን እና ንቅናቄዎቹ በምን መልኩ ሊደራጁ እንደሚችሉ (እንደሚገባ) የተወሰኑ ነጥቦችን እሰነዝራለሁ፡፡
የፖለቲካ ፓርቲንና የንቅናቄን ልዩነትና ተመሳሳይነት በሚመለከት አንድ ሁሉን የሚስማማ ብያኔ መስጠት ባይቻልም፣ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል “የፖለቲካ ፓርቲ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚታገል፣ በሕግ የተመዘገበ እና ከሞላ ጎደል ተቀራራቢ የፖለቲካ አስተሳሰብና ዓላማ ያላቸው ዜጎች ስብስብ ነው” የሚለውን ብያኔ እንደመነሻ እንጠቀም፡፡ ማንኛውም ፖለቲካ ፓርቲ ለፖለቲካ ሥልጣን ከመወዳደሩ በፊት ይብዛም ይነስም የራሱ የሆነ፣ ብመረጥ አስፈጽመዋለሁ የሚለው ፕሮግራም ይኖረዋል፡፡ ፓርቲው ይህን የፖለቲካ ፕሮግራሙን ለሕዝብ በማስተዋወቅና ሕዝብ እንዲቀበለው በማድረግ፣ ይልቁንም ከሌሎች ተቀናቃኝ ፓርቲዎች ጋር ሲወዳደር የእሱ ፕሮግራም የተሻለ እንደሆነ በማሳመን ለፖለቲካ ሥልጣን ይታገላል፡፡ አብላጫ ድምጽ አግኝቶ የመንግሥት ሥልጣን ከተረከበም ያቀረባቸውን የፖሊሲ አጀንዳዎች ያስፈጽማል፡፡
ንቅናቄ በአንጻሩ ከፖለቲካ ፓርቲ በብዙ መልኩ የተለየ ነው፡፡ ሁለት አብነቶችን ብጠቅስ፡-
(1.) ንቅናቄ ከፖለቲካ ሥልጣኑ ይልቅ ለፖለቲካ ሂደቱ ከፍተኛ ትኩረት ይሰጣል፡፡ የንቅናቄ ዓላማ በአምስት ወይም በስድስት ዓመት በሚመጣ ምርጫ አማካይነት ተወዳድሮ የፖለቲካ ሥልጣን መያዝ ሳይሆን ያልተቋረጠ ቅስቀሳ ማድረግ፣ ኅብረተሰብን ማንቃት፣ ሰፊ መሠረት ያለው ሕዝባዊ ንቅናቄ መፍጠር፣ በመንግሥት ላይ ተጽዕኖ ማሳደር ወዘተ. ነው፡፡
(2.) ንቅናቄ በውስጡ ለፖለቲካ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን ለሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች (ለምሳሌ ለሴቶች፣ ለሕፃናት፣ ለአረጋዊያን፣ ለአካባቢ ጥበቃ፣ ለሕግ የበላይነት፣ ለፕሬስ ነጻነት፣ ለሠራተኞች ወዘተ.) የሚታገሉ ልዩ ልዩ ንዑሳን ንቅናቄዎችን በሥሩ ወይም በአጋርነት ስለሚይዝ ንቅናቄ ከፖለቲካ ፓርቲ የተለየ እና ሰፋ ያለ ሕዝባዊ መሠረት ያለው ነው፡፡
ንቅናቄና ፖለቲካ ፓርቲ በኢትዮጵያ
***
በአገራችን “ንቅናቄ” የሚለው ቃል ሲነሳ በሁሉም ሰው አእምሮ ውስጥ የሚመጣው የኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ ይመስለኛል፡፡ በእርግጥም ከኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄ በፊት ሆነ በኋላ በአገራችን ንቅናቄ ነበር ወይም አለ ማለት አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ንቅናቄ ታሪክ የሚጀምረውም የሚያቆመውም እዚያ ላይ ቢባል ስህተት አይመሰለኝም፡፡
የመሬት ላራሹ ትውልድ ኢትዮጵያ ውስጥ ጭሰኝነትን ለማስወገድ እና በማኅበረሰቦች መካከል ዕኩልነትን ለማስፈን የታገለውን ያህል ስለ አፍሪካ ነፃነት፣ ስለ ኢምፔርያሊዝም፣ ስለ ቬትናም ወረራ፣ ስለ “ሮዴዥያ” (የዛሬይቱ ዚምባብዌ)፣ ስለአፓርታይድ ወዘተ. እያነሳ ይጽፍ፣ ይናገር፣ ሰላማዊ ሰልፍ ይወጣ እንደነበር አይዘነጋም፡፡
ይኹን እንጂ ያ ንቅናቄ የቱንም ያህል ስለሕዝብ መብት ቢጽፍና ቢታገልም ያው እንደስሙ የተማሪ ንቅናቄ ስለነበር በወቅቱ በጣም ውሱን ቁጥር ያላቸውን የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ያቀፈ፣ ብዙሃኑን የኅብረተሰብ ክፍል ያላሳተፈ እና ከታች ወደላይ የተገነባ ሳይሆን ከላይ (ከልሂቃኑ/ተማሪዎች) ወደታችን የሚያማትር ንቅናቄ ስለነበር ለአገራችን የፖለቲካ ባህል ዕድገት ያደረገው አስተዋጽዖ አሉታዊ ነው፡፡ ዕድሜውም በጣም አጭር ነበር፡፡
ከየካቲት 66 በኋላ የንቅናቄው አባላት ወደተለያዩ ቡድኖችና ፓርቲዎች በይፋ ተከፋፍሉ፡፡ የተወሰነው ወገን ከደርግ ጋር እስከተለያዩ ደረጃዎች ተጓዘ፡፡ ከደረግ ጋር የዘለቀውም ዘለቀ፡፡ ጫካ ከገባው መካከል ኹለቱ፣ ኹለት አገርና ኹለት መንግሥት ለማቋቋም በቅቷል፡፡
የመሬት ላራሹ ትውልድ አባላት ወደተለያዩ ፓርቲዎች በመግባታቸው ምክንያት ንቅናቄው እየሰፋ፣ ሌሎችን ንዑሳን ንቅናቄዎችን እያካተተና እያደገ ከመሄድ ይልቅ በአጭር ጊዜ ውስጥ ነበር የተኮላሸ፡፡ ከንቅናቄው መክሰም በኋላ የተፈጠሩት ሌኒኒስታዊና ስታሊኒስታዊ የፖለቲካ ድርጅቶች በአንድ ግንባር ቀደም (vanguard) ፓርቲ አስተሳሰብና አሠራር በጽኑ የሚያምኑ ስለነበሩ ማንኛውንም የፖለቲካም ይኹን የሲቪክ ድርጅት ወይም የሠራተኛ ማኅበር ሰርገው እየገቡ መቆጣጠር የተለመደ ተግባራቸው ሆነ፡፡ ይህ ማንኛውንም የተደራጀ ስብስብ በዓይነ ቁራኛ የመቆጣጠርና ሰርጎ የመግባት (infiltration) አደገኛ አካሄድ ለነጻ ንቅናቄ መፈጠርና ማበብ ከፍተኛ መሰናክል ሆኖ ቆይቷል፡፡ አደገኛው ስታሊኒስታዊ የሴራ ፖለቲካ እስካሁንም ድረስ በአገራችን ማዕከላዊ ቦታ እንደያዘ ይገኛል፡፡
ብዙ አገር ወዳዶች ደጋግመው እንደሚያስገነዝቡትና እኔም እንደምስማማበት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ሁኔታ በመሠረታዊነት እንዲቀየርና እንዲሻሻል ካስፈለገ ይህ “የጎርዲያን ቋጠሮ” (Gordian Knot) መፈታት ይኖርበታል፡፡ የጎርዲያን ቋጠሮው ሊፈታ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከጎጥና ከቀበሌ ጀምሮ የራሱንና የአገሩን ጉዳይ ለጥቂት አፈ ጮሌዎች አሳልፎ ሳይሰጥ በያገባኛል መንፈስ በልዩ ልዩ ሲቪክና ሲቪል ማኅበረሰቦች አማካይነት እየተደራጀ ሲታገል ብቻ ነው፡፡
ፓርቲ ወይስ ንቅናቄ?
***
እንደሚታወቀው በሌሎች አገሮች፣ በተለይ ደግሞ የዳበረ ዴሞክራሲ ባለቤት በሆኑ አገሮች ውስጥ በኢኮኖሚ፣ በፖለቲካና በሌሎች ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ወቅታዊና ዝርዝር ጥናት የሚያደርጉ የሐሳብ-ጎተራዎች (Think Tanks) አሉ፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻቸውና ልዩ ልዩ የጥናትና ምርምር ተቋሞቻቸውም በልዩ ልዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ሰፊ ሥራዎችን ይሠራሉ፡፡ የጥቅም (interest groups) እና የሞያ ማኅበራት (professional associations) የሚወክሉትን ሕዝብ መብት የሚመለከቱ ብዙ ተግባራትን ያከናውናሉ፤ መንግሥትን ይታገላሉ፡፡ መገናኛ ብዙሃንም እንዲሁ የመንግሥትን ያልተገባ ተግባር ያጋልጣሉ፤ በድፍረትና በመረጃ ይተቻሉ፡፡
በአገራችን ይህ ሁሉ የለም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ኢትዮጵያ ውስጥ ውስን ለሆነ ግብ (ለፖለቲካ ሥልጣን) የሚታገሉ ፓርቲዎች ሳይሆኑ ሰፊ መሠረት ያላቸው፣ ድርብርብ ተግባራትን ሊያከናውኑ የሚችሉ እና ቀጣይነት ባለው መልኩ የሚታገሉ ንቅናቄዎች የሚያስፈልጉት፡፡ ንቅናቄዎች በአንድ በኩል ፕሮግራም ያዘጋጃሉ፤ ያስተዋውቃሉ፤ አባላት ይመለምላሉ፤ ሌሎችን የአደረጃጀት ሥራዎች ያከናውናሉ፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ኅብረተሰቡ ለመብቱ እንዲታገል የማስተማርና የማንቃት ሥራ ይሠራሉ፤ ጥናት ያጠናሉ ወዘተ፡፡
አንድ ንቅናቄ ዓላማውን ለሕዝብ በሚያስተዋውቅበትና በሚያስረዳበት ወቅት እግረ መንገዱን የኅብረተሰቡን የፖለቲካ ንቃተ ኅሊናም እያሳደገ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ጠንካራ የጥቅም፣ የሠራተኛና የሞያ ማኅበራት እና ጠንካራ መገናኛ ብዙሃን በሌለባቸው አገሮች እንዲያውም የንቅናቄዎች የማስተማርና የማንቃት ሥራ ከሌላው ተግባራቸው በእጅጉ ጎልቶ መውጣት ይኖርበታል፡፡
አሌክሲ ደ. ቶኮቪል (Alexis De Tocqueville) የተባለው ዝነኛ ፈረንሳያዊ ምሁርና የፖለቲካ ሰው Democracy in America በሚለው ዘመን አይሽሬ ሥራው እንዳስገነዘበው፣ የአሜሪካ ሕዝብ የተፈጥሮም ይኹን ሰው ሠራሽ አደጋ ሲገጥመው፣ ከላይ ከማዕከላዊ መንግሥት እርዳታና ድጋፍ ከመጠበቅ ይልቅ ራሱን በየአካባቢው፣ በየሞያ መስኩ ወዘተ. እያደራጀ ችግሩን የሚፈታ ሕዝብ ነው፡፡ የዜጎችን መብት በየደረጃው ለማስከበርም የሴቶች መብት ንቅናቄ፣ የጥቁሮች መብት ንቅናቄ፣ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ፣ የፀረ ቬትናም ጦርነት ንቅናቄ፣ የመናገር ነጻነት ንቅናቄ፣ የሕገ መንግሥት እንክብካቤ ንቅናቄ ወዘተ. እያለ እየተደራጀ ይታገላል፡፡ አንዳንዶች የአሜሪካንን ዴሞክራሲ “የንቅናቄ ዴሞክራሲ” የሚሉት በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በቅርቡ በጥቁር አሜሪካውያን የተመሠረተው #Black Lives Matter! የተባለው እና በቅርቡ ደግሞ #MeToo የተሰኘው ንቅናቄ ምን ያህል ትልቅ ሥራ እየሠሩ እንደሆነ ማየትም ይቻላል፡፡
በአገራችን ሊለመድና ሊኮተኮት የሚገባው የዚህ ዓይነቱ የፖለቲካ ባህል ነው፡፡ ከፍ ብየ እንደጠቀስኩት በአገራችን የፖለቲካ ፓርቲም ይሁን የንቅናቄ ታሪካችን በጣም አጭር ብቻ ሳይሆን አፈጣጠሩም የተበላሸ ነው፡፡ አፈጣጠሩ የተበላሸ ነው ከምልባቸው በርካታ ምክንያቶች ውስጥ የተወሰኑትን ብቻ ብጠቅስ፡-
(1.) ፖለቲካ በመሠረታዊነት አካባቢያዊ (local) ሆኖ የአካባቢውን ችግር ከመፍታት (ወይም ለመፍታት ከመታገል) የሚጀምርና እያደገ የሚሄድ ቢሆንም፣ የአገራችን ፖለቲካ የሚነሳው ከላይ ከማዕከል (ከአዲስ አበባ) ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ብዙሃኑ የአገራችን ሕዝብ በራሱ፣ በአካባቢውና በአገሩ ጉዳይ ላይ የማይሳተፍ ባይተዋር ሆኖ ነው የኖረው፡፡ ሰፊ መሠረት ያላቸው፣ ከታች ከቀበሌ ጀምረው ሕዝብ እያደራጁና እያሳተፉ የሚያታግሉና የሚታገሉ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄዎች መፍጠር ያልቻልነው በዚህ ምክንያት ነው፡፡ በአጠቃላይ ፖለቲካችን ከትናንት እስከ ዛሬ ብዙሃኑን ኢትዮጵያዊ ያላማከለ እና አየር ላይ ተንሳፈፈ መሆኑ በእጅጉ ጎድቶናል፡፡
(2.) በኢትዮጵያ ተማሪዎች ንቅናቄም ይሁን በንቅናቄው አባላት መሪነት በተፈጠሩት የፖለቲካ ድርጅቶች ውስጥ በጣት የሚቆጠሩ አፈ ጮሌዎችና የሥልጣን ጥመኞች በሌኒኒስታና ስታሊኒስታዊ የሴራ ፖለቲካ ብዙሃኑን የድርጅት አባል የሚጋልቡበት አሠራር በአገራችን ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ባህል መሠረት እንዳይኖረው ደንቀራ ሆኖ ቀይቷል፤ አሁንም ከዚህ በአንድ ወይም በጥቂት ግለሰቦች የሚዘወር አደገኛ የፖለቲካ አስተሳሰብና አሠራር አልተላቀቅንም፡፡
ይህ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ምሥረታና ለዜጎች መብት መጠበቅ ደንቀራ የሆነ የተበላሸ የፖለተካ ባህል ከሥረ መሠረቱ መቀየር ይኖርበታል፡፡ ለዚህ መድሃኒቱ ደግሞ ከታች ወደላይ እያደገና እየጎለመሰ የሚሄድ የዜጎች ንቅናቄ ነው፡፡ ሕዝብ መብቱን እንዲጠይቅ፣ ለሲቪልና ለፖለቲካ መብቱ እንዲታገልና በሂደት ዴሞክራሲን እየተለማመደ የሰለጠነ የፖለቲካ ባህል እንዲገነባ የሚያስችለው በየደረጃው በንቅናቄ መልክ ሲደራጅና ሲታገል ነው፡፡ ይህን አደገኛ የፖለቲካ ባህል ዛሬ ታግለን ካልቀየርነውና ካላሻሻልነው በስተቀር የትኛውም የተደራጀ አላፊ አግዳሚ ኃይል ረግጦ እንደገዛን ይኖራል፡፡
ንቅናቄ፤ እንዴት?
***
ንቅናቄዎች በበርካታ መንገዶች ሊደራጁ ይችላሉ፡፡ በበኩሌ የደቡብ ኮሪያ የዴሞክራታይዜሽን ሒደት ለአገራችን እንደትልቅ አብነት ሊወሰድ ይገባዋል የሚል እምነት አለኝ፡፡ ደቡብ ኮሪያ ውስጥ በተለይ ጀኔራል ፓርክ ጁንግ ሂ (Park Chung Hee) በመፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን ከያዙበት ጊዜ ጀምሮ በተማሪዎች፣ መምህራን (ምሁራን)፣ ታዋቂ ሰዎችና የሃይማኖት መሪዎች፣ ጋዜጠኞችና የሰብአዊ መብት ተንከባካቢ አክቲቪስቶች ወዘተ. የተጀመረው ንቅናቄ ለበርካታ ዓመታት ከፍና ዝቅ እያለ (እና ከውድቀቱ እየተማረ) ያለማቋረጥ ያደረገው እንቅስቃሴና ትግል ለደቡብ ኮሪያ የዴሞክራሲ ግንባታና ሁለንተናዊ ልማት በጣም ከፍተኛ ሚና ተጫውቷል፡፡
ከጀኔራል ፓርክ አስተዳደር ጊዜ ጀምሮ በተደረገው የመብትና የዴሞክራሲ ትግል በርካቶች ታስረዋል፣ አገራቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ተደርገዋል፤ የሞቱትም ብዙ ናቸው፡፡ ሆኖም ንቅናቄው የተለያየ መልክና ቅርጽ እየያዘ ሳያቋርጥ ስለቀጠለ በርካታ ሰዎች መስዋዕትነት ቢከፍሉም ደቡብ ኮሪያ ዛሬ ለዜጎቿ የምትመችና በብዙ ረገድ የበለፀገች አገር ለመሆን በቅታለች፡፡
የደቡብ ኮሪያ የዴሞክራሲ ንቅናቄ ጥቂቶች ሳይሆኑ ብዙሃኑ ተሳታፊ የሆኑበት፣ ከላይ ወደታች ሳይሆን ከታች ከቀበሌ ጀምሮ ወደላይ የተገነባ፣ ተማሪዎችን፣ መምህራንን፣ ታዋቂ ሰዎችን፣ የአገር ሽማግሌዎችንና የሃይማኖት መሪዎችን፣ የሲቪልና ማኅበረሰብ አባላትንና መሪዎችን፣ የመንግሥትና የግል ሠራተኞች፣ ጋዜጠኞችንና አክቲቪስቶችን ያሳተፈ ነበር፡፡ ንቅናቄው በአንድ ቡድን ግንባር ቀደም መሪነት የሚዘወር ሳይሆን ብዙሃኑን ባሳተፈ መልኩ የሚካሄድ ስላልነበረ በሂደት እያደገና እየሰፋ ሊሄድ ችሏል፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብም ከየትኛውም የእናውቅልሃለን ፖለቲካ አራማጅ ቡድን ምንም ነገር ሳይጠብቅ ከታች ከቀበሌ ጀምሮ ለራሱ፣ ለአካባቢውና ለአገሩ በያገባኛል ስሜት እንዲታገል ያስፈልጋል፡፡ በእርግጥ በንቅናቄ ውስጥ መሳተፍና ለመብት መታገል ጊዜ፣ ገንዘብና ሌላም ብዙ መስዋዕትነትን ያስከፍላል፡፡ ሆኖም በዚህ መንገድ ነው ዘላቂና አስተማማኝ የሆነ የፖለቲካ ሥርዓት ሊመሠረት የሚችለው፡፡ ስለሆነም ሕዝባችን ከታችን ከቀበሌ ጀምሮ በየደረጃው (በወረዳ፣ በክፍለ አገርና በአገር ደረጃ) እየተደራጀ ልዩ ልዩ ንቅናቄዎችን መፍጠር እና ለሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶቹ መከበር፣ ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት መመሥረት፣ ለሕግ የበላይነት መጠበቅ ወዘተ. እንዲታገል ያስፈልጋል፡፡
ኢትዮጵያ ምንም በአመራር ችግር ምክንያት ወደኋላ የቀረች አገር ብትሆንም፣ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን የሚጋሯውና የሚኮሩባቸው ድንቅ እሴቶች ያሏት አገር መሆኗን መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያን ልንወድና ልናፈቅር የምንችልባቸው በጣም በርካታ ምክንያቶች አሉን፡፡ እነዚህን ድንቅ ዕሴቶች በአርበኝነት ስሜት መንከባከብ፣ ሌሎችን አዳዲስ ዕሴቶች በነባሮቹ ላይ እየገነቡ መሄድ፣ የማንኛውም ዜጋ መብት እንዳይነካ ለሕግ የበላይነት በጋራ መቆም፣ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ እሴቶችን መንከባከብና ማሳደግ ወዘተ. ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጵያዊያን በደንብ እንድንገነዘበው የሚያስፈልገው አንድ መሠረታዊ ቁም ነገር፣ መንግሥትም ይኹን ሌላ የተደራጀ ኀይል የዜጎችን መብት ይወስዳል (ይነጥቃል) እንጂ መብት አይሰጥም፡፡ መብትን መጠበቅ የእኛ የእያንዳንዳችን የባለመብቶቹ ኀላፊነት መሆኑን አውቀን ሁላችንም በያገባኛል ስሜት መታገል፣ የጭቆናን ቀንበር መስበር እና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን ማስፈን ይኖርብናል፡፡