የውብሸት ታዬ (ጋዜጠኛ)፣ የትናንት የዝዋይ ገጠመኝ …
—–
በትናንትናው ዕለት በዝዋይ እስር ቤት ያሉ ጓደኞቼን ለመጠየቅ ወደ ስምጥ ሸለቆዋ መዲና አቅንቼ ነበር። የጉዞዬ መቋጫ ጉዳይ ለጊዜው ይቆየንና (የባሰም አለና)ስመለስ በዚያው አንድ ዘመዴን ለመጠየቅ ደብረ ዘይት/Bishooftu/ ላይ ወረድኩ። እናም ቀበሌ 01 (መከላከያ አጠገብ) ወዳለው መኖርያው ሳዘግም አንድ አሳዛኝ ሁነት ትኩረቴን ሳበው። በዚህ ምስል ላይ እንደምትመለከቱት የአንዲት ዜጋ ሙሉ የቤት ዕቃ ጎዳና ላይ ተጥሎ ዝናብ ይደበድበዋል። አንዳንድ ቀማኞች ከንብረቱ መንትፈው ለመሮጥ ዳር ዳር ይላሉ።
ስለሁኔታው በአከባቢው ያገኘሁዋቸውን አንዳንድ ሰዎች መጠያየቅ ጀመርኩ። ንብረቷ 27 ዓመት ከኖረችበት ቤት በ”ሕግ አስከባሪዎች” ወጥቶ ጎዳና ላይ የተበተነባት ኢትዮጵያዊት የከተማው ውሃና ፍሳሽ አገልግሎት መ/ቤት ባልደረባ ስትሆን ስሟ ፍፁም ለገሰ ይባላል። ይህችን እህት ለማነጋገር ብሞክርም በጣም ተረብሻ ስለነበር ሊሳካልኝ አልቻለም። የደረሰባት ሁኔታ ግን ተምሳሌታዊና “ከፈለግን ይህንንም ማድረግ እንችላለን” የሚል መልዕክት ማስተላለፍ መሆኑ በገሀድ ይስተዋላል።
ይህ አላፊ አግዳሚውን በቁጭትና በነግ በኔ ተምኔት ያስደመመና የዜግነትን ክብር የነካ ጉዳይ የተከሰተው መሰረታዊ የሕግ ሂደት (Due process of law) ባልተፈፀመበት ሁኔታ እንደሆነ አረጋገጥኩ። ማንም የፈለገውን የሃይማኖት፣ የአስተሳሰብ ወይም የፖለቲካ አመለካከት መያዝ ይችላል። ይህ ተጨባጭ እውነታ ማንንም ለጥቃት ሊያጋልጥ አይገባም ነበር።
ሁኔታው ብዙ ጥያቄ የሚያጭርና ሰብአዊ ስሜትን ጠልቆ የሚነካ ነበርና የነገሩን መጨረሻ ለማጣራት ዛሬ እኩለ ቀን ላይ በቦታው ተገኘሁ። ለውጥ የለም። የዚህ ዓይነት ብዙ የፍትሕ መዛባቶችና የዜግነት ጥያቄ የሚያስነሱ ጉዳዮች የተለየ ባህሪ ይዘው እየተከሰቱ ነው። ለምን? የት ያደርሰናል? ስንት ዜጎች ከሞቀ ቤታቸው ጎዳና ላይ ቢወጡ የግፉ ፅዋ ይሞላ ይሆን? …እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ።