AFP
ሜይ ዴይ – ዓለምአቀፍ የሠራተኞች፣ የወዝአደሮች ወይም የላብአደሮች ቀንን ትናንትና በዓለም ዙሪያ ተከበሯል፡፡ ይህ በአል ሲከበር እንደወትሮው ሁሉ የኢትዓዮጵያ ሰራተኞም ስለመብታቸው መከበር መውተወቱን ቀጥለዋል።
በኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ ሕግ ላይ አንገብጋቢ ከሆኑ ጉዳዮች መካከል ቀዳሚው የመደራጀት ጥያቄ መሆኑ አያጠያይቅም። የአሰሪና ሰራተኛ አዋጁም ሆነ ሕገ መንግስቱ መደራጀትን ፈቅደዋል፤ ኢትዮጵያም የዓለም ስራ ድርጅት ኮንቬንሽን 87ን ፈርማለች።
ነገር ግን በተግባር መደራጀት ላይ ትልቅ ችግር አለ ይላሉ የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ካለው ሰራተኛ የተደራጀው ትንሹ ነው የሚሉት የኢትዮጵያ ሰራተኛ ማህበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት መንግስት ያሉትን አዋጆች የማስፈፀም ችግር አለበት ሲሉ ይወቅሳሉ።
በተለይ ደግሞ አዲስ በተፈጠሩ የኢንደስትሪ ፓርኮች፣ በውጭ ድርጅቶች ውስጥ በሚሰሩ ሰራተኞች ላይ የመደራጀት መብታቸው እጅጉን የተገፋ እንደሆነ ብዙ ጊዜ ሲነገር ይደመጣል።
“የኢትዮጵያ አሰሪና ሰራተኛ አዋጅ መደራጀትን የሚፈቅደው ለመንግስት የልማት ድርጅት ሰራተኞችና ለግል ድርጅቶች መሆኑን ልብ ይኋል” የሚሉት አቶ ካሳሁን ነገር ግን በህገመንግስቱ ላይ የሰዎች የመደራጀት መብት ስለተፈቀደ ይህ መብት ለመንግስት ሰራተኞችም ሊነፈግ እንደማይገባ አፅንኦት ይሰጣሉ።
ይህ የመደራጀት ጥያቄ በኮንፌዴሬሽኑ አመራሮች ለዘመናት በተደጋጋሚ መጠየቁን ያስታወሱት አቶ ካሳሁን በነበሩት መንግሥታት ሁሉ በአጠቃላይ አለመከበሩን በማስታወስ የሰራተኛው መብት እንዲከበር እንደሚታገሉ ይናገራሉ።
ሌሎች ተግዳሮቶች. . .
የኢትዮጵያ ሰራተኞች ችግር ተቆጥሮ የሚያልቅ አይመስልም። የሙያ ደህንነትና ጤንነትም አሳሳቢ እንደሆነ ፕሬዝዳንቱ ይገልፃሉ።” ሰራተኞች በስራ ቦታቸው ላይ ጉዳት ደርሶባቸው አካላቸው ጎድሎ አንዳንድ አሰሪዎች በቂ ህክምና እንዲያገኙ አያደርጉም” ሲሉ ቅሬታቸውን ይገልጻሉ።
ይህ ብቻም ሳይሆን ሰራተኛው በራሴ ወጭ ልታከም ብሎ ፈቃድ ሲጠይቅም የሚከለከልበት አጋጣሚ እንዳለ ፕሬዝዳንቱ በቁጭት ያስታውሳሉ።
በኢትዮጵያ ውስጥ ሌላው የሰራተኞችን መብት መከበር ፈታኝ ያደረጉት ጉዳይ ደግሞ የአሰሪና ሰራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች ናቸው።
“እነዚህ ኤጀንሲዎች ሰራተኛንና አሰሪን ካገናኙ በኋላ ገንዘባቸውን ተቀብለው ከመሃል መውጣት ሲኖርባቸው እነርሱ ግን በየወሩ ከሰራተኛው በሚቆረጥ ደመወዝ የሚኖሩ አሉ” ሲሉ ይከሳሉ፤ እነዚህ ድርጅቶች አንድን ስራ ኮንትራት ከወሰዱ በኋላ ሰራተኞችን ቀጥረው ሲያሰሩ ለሰራተኞቹ የሚከፍሉት ከኮንትራት ሰጭው መስሪያ ቤት ከሚያገኙት እጅጉን ያነሰ እንደሆነ በማስረዳት።
በዚህ ሳያበቃ የአሰሪና ሰራተኛ ድርጅቶች ቢሯቸው በሌላ ስፍራ ተቀምጦ የሚያስፈልግ የሰው ሃይል ሲቀርብ ከሰራተኞቹ ጋር የቅጥር ውል የሚፈፅመው ኤጀንሲው ሆኖ ሰራተኞቹ በሌላ አካባቢ ሄደው ይሰራሉ። በኋላ በሰራተኞች እና በድርጅቱ መካከል ለሚነሳ ማንኛውም ጥያቄ አሰሪው ድርጅት ምንም አይነት ሃላፊነት ሳይወስድ እንደሚቀር ያስረዳሉ።
ይህም ሰራተኞቹ ስለ መብታቸው፣ ስለመደራጀት እና ስለ አንዳንድ ጥቅማ ጥቅሞቻቸው መጠየቅ እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል ሲሉ የችግሩን ግዝፈት ያስረዳሉ። ኤጀንሲውም የሰራተኞቹን መብት ለማክበር ስለማይፈለግ በመካከል ተጎጂ የሚሆኑት ሰራተኞቹ መሆናቸውን ያነሳሉ።
አነስተኛ የሰራተኞች ደመወዝን የመወሰን አስፈላጊነት
ለአቶ ካሳሁን ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል በአዲሱ የአሰሪና ሰራተኛ አዋጅ ላይ ያላቸው ትልቁ ጥያቄ ነው፤ “ሰራተኛው ዝቅተኛ የሰራተኛ የደመወዝ ወለል ሊኖር እንደሚገባ ደጋግሞ ቢጠይቅም እሰከዛሬ ድረስ ግን መንግሥት ጥያቄውን ሳይቀበል ቀርቷል” ሲሉ አቶ ካሳሁን ያነሳሉ።
በርግጥ ይህ ጥያቄ ላለፉት አስር አመታት ሲጠየቅ የቆየ ቢሆንም መንግስት ግን ጥያቄውን ለመቀበል ዳተኛ ሆኖ ቆይቷል የሚሉት አቶ ካሳሁን በአዲሱ የሰራተኛና አሰሪ አዋጅ ላይ እንዲካተት ጥያቄ ቀርቦ መንግስት በእንቢተኝነቱ መፅናቱን ያስታውሳሉ።
በቀጣይ ውይይቶች አዲስ ነገር ካልመጣ በስተቀር በዚህ የደመወዝ ጣሪያ አለመወሰን ምክንያት በኢንድስትሪ ፓርክም ሆነ በሌሎች በውጭ ድርጅቶች የሚሰሩ ሰራተኞች ስራ ያላቸው ግን በጣም ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ያላቸው ሰዎች እንደሆኑ ይናገራሉ።
እነዚህ ሰራተኞች ይላሉ አቶ ካሳሁን “እነዚህ ሰራተኞች በሚያገኙት ደመወዝ የዕለት ጉርሳቸውን ለመሸፈን እንኳ ፈተና የሆነባቸው ዜጎች ናቸው።”
እንደ አቶ ካሳሁን ከሆነ ይህንን አነስተኛ የደመወዝ ወለል ለመወሰን ጥናቶች ተደርገዋል። በቅርቡም በዓለም የስራ ድርጅት የተሰራው ጥናት ይፋ ይሆናል ብለው የሚጠብቁ ሲሆን ኮንፌዴሬሽኑ ከዚህ ቀደም ያስጠናው ጊዜ ስላለፈበት እንደ አዲስ ማስጠናት መጀመራቸውን ይናገራሉ።
ያንን መሰረት አድርጎ አነስተኛ የደመወዝ ወለልን የመወሰን ከመንግስት፣ ከሰራተኛ፣ ከአሰሪ የተውጣጣ አማካሪ ቦርድ መቋቋም እንደሚያስፈልግም ያነሳሉ። ይህንንም በየአመቱ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት እያቀረበ የሚያፀድቅ እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ መንግስት ይህ የዝቅተኛ የደመወዝ መጠን በህግ እንዲቀመጥ የማይፈልግበት ምክንያት ከውጭ እየገቡ ያሉ ባለሃብቶች ላይመቱ ይችላሉ ከሚልና ከፍተኛ የስራ አጥ ቁጥር ባለበት ሃገር ይህንን ማስቀመጥ ይከብዳል ከሚል መሆኑን የሚያነሱት አቶ ካሳሁን “ይህ ትውልድ መስዋዕትነት መክፈል አለበት” የሚል እምነት ያላቸው ባለስልጣናት መኖራቸውንም ተናግረዋል።
ይህ ግን ስህተት እንደሆነ የሚያስረዱት አቶ ካሳሁን የስራ አጥ ቁጥር ከፍተኛ መሆን የትኛውንም ባለሃብት ከሚፈልገው የሰው ሃብት በላይ እንዲቀጥር አድርጎ እንደማያውቅ አስረጅ ይጠቅሳሉ። ሌላው ይላሉ አቶ ካሳሁን ኢትዮጵያ ውስጥ የውጭ ባለሃብቶችን ለማበረታታት በርካታ ነገሮች መደረጋቸውን ያስታውሳሉ። ይህ ደግሞ መሬትን፣ መሰረተ ልማትን አሟልቶ እስከማቅረብ የሄደ እንደሆነ ሊታወስ እንደሚገባም ይጠቅሳሉ።
ጥያቄዎቻቸው ባይመለሱ. . .?
አቶ ካሳሁን በአዲሱ ረቂቅ የአሰሪና የሰራተኛ አዋጅ በርካታ ሰራተኛው የነበሩትን መብቶች የሚያሳጡ አንቀፆች መግባታቸውን በማስታወስ በእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከመንግስት ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ነው የሚናገሩት።
ይህ ረቂቅ አዋጅ አንድ ሰራተኛ ስራውን በፈቃዱ ከለቀቀ የስራ ስንብት ክፍያ መብቱን አንዳያገኝ፣ የዓመት እረፍቱ በየዓመቱ ሳይሆን በየአምስት ዓመቱ እንዲጨምርና ሌሎች መሰረታዊ መብቶችን የሚጥስ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ካሳሁን ይህ አዋጅ እንዳይወጣ በውይይት ላይ እንዳሉ ገልፀዋል።
ይህ ጉዳይ በውይይት የማይፈታ ከሆነ አገር አቀፍ ሰላማዊ ሰልፍ እና አገር አቀፍ የስራ ማቆም አድማ ለማድረግ በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 1674 መሰረታዊ ሰራተኛ ማህበራት ጋር ስምምነት ላይ ተደርሷል ብለዋል።
የኢሰማኮ ጠቅላይ ምክር ቤትም በዚህ ጉዳይ ላይ ተመሳሳይ አቋም እንዳለው ያስታወሱት አቶ ካሳሁን መንግሥትም ይህንን ተረድቶ አዋጁ ከመፅደቁ በፊት ለውይይት እንደተቀመጠ አንስተዋል። ካልሆነ ግን መብታቸውን ለማስከበር እነዚህን እርምጃዎች ተግባራዊ ከማድረግ ወደኋላ እንደማይሉም ይገልፃሉ።