የሐዋሳ ዩኒቨርሲቲ ኦርቶዶክሳውያን ሰሞኑን ያደረጉት ተጋድሎ በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ኦርቶዶክሳውያን ወቅታዊ ትእምርት እንጅ፡፡ ከዩኒቨርሲቲው ቅጽር አልፈው ወደ እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን የሚሔዱበትን የአጥር በር “ክፋት የተሞሉ ሰዎች” ያለምንም ማስጠንቀቂያ ዘጉባቸው፡፡ በዚህም ምክንያት ለመሳለም የወጡት ተመልሰው ለመግባት አልቻሉም፡፡ ዞረን በሌላ በር እንገባለን ሲሉ እንደ ወንጀለኛ አንዳንዶችን ለእስራት ሌሎችንም መታወቂያ በመቀማት አጣደፏቸው፡፡ በዚህ ተነሣ ተማሪዎች ምስካዬ ኅዙናን (ላዘኑ መጠጊያ) ወደ ኾነችው ቤተ ክርስቲያኖቸው ቀጥ ብለው ግቢያቸውን ለቅቀው ወጡ፡፡
የሐዋሳ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም እስከ ፪ሺ፭፻ የሚደርስ ቁጥር ያላቸውን ተማሪዎች በእናትነት ፍቅር ተቀበላቸው፡፡ ምእመናን፣ ሀገረ ስብከቱ፣ እና ገዳሙ በፈጣን እንቅስቃሴ ፍሪዳ ጥለው አስተናገዷቸው፣ አጽናኗቸው፡፡ ተማሪዎቹ ጥያቄአቸውን ለዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት አቅርበው ያገኙት ምላሽ ከአንድ የዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የማይጠበቅ ዝቅ በጣም ዝቅ ያለ ኾነባቸው፡፡ የእርሱን እምነት ያልተከተለ የማይኖርበት ወይም የማይማርበት ዩኒቨርሲቲ ለማድረግ ዕቅድ ያለው መኾኑን አካሔዱ አሳብቆበታል፡፡
ተማሪዎቹ ተስፋ ባለ መቁረጥ በሊቀ ጳጳሳቸው እየተመሩ ጉዳዩን ወደ ክልሉ ይዘውት ይሔዳሉ፡፡ አቡነ ገብርኤልና ሊቀ ጉባኤ አባ ገብረ ማርያም ሠናይ ሥራ ሠሩ፡፡ በዚያም ከክልል ባለሥልጣናት አንስቶ የዩኒቨርሲቲው አመራሮች ፕሬዝዳንቱን ጨምሮ በተገኙበት ተማሪዎች ሦስት መሠረታዊ ጥያቄዎችን በብስለት ጠየቁ፡፡
፩. የተዘጋባቸው በር እንዲከፈትላቸው
፪. ኾን ተብሎ በፍስክ ቀን ሊበሉ የሚገባቸውን ምግቦች በጦም ቀን ማቅረብ እንዲቀር
፫. ተማሪዎች በጦም ቀንም ኾነ በፈለጉ ጊዜ ዳቧቸውን ወደ ማደሪያ ክፍላቸው ይዘው ለመሔድ እንዲፈቀድላቸው
የማንንም መብት ሳይነኩ የራሳቸውን ለማስከበር ተጋደሉ፡፡ የክልሉ የሥነ ምግባር መኮንን በመሩት ስብሰባ ሦቱም ጥያቄዎች በአዎንታ ተቀባይነት አግኝተው ድሉ ለኦርቶዶክሳውያን ኾነ፡፡ ጥቂት መገፋት ለብዙ ሹመት ያደርሳል፡፡ አንዳንድ ጊዜ እንደዚህ ባለው ሁኔታ እግዚአብሔር የራሱን ሥራ ይሠራል፡፡ በበር መዝጋት ሰይጣን ትግሉን ሲጀምረው፣ በር በማስከፈት ብቻ ሳይኾን በተጨማሪ ሽልማት እግዚአብሔር ድል ያደርጋል፡፡
የሐዋሳ ሀገረ ስብከት በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ወሳኝ ሥራ እየሠራ የሚገኝ ድንቅ ሀገረ ስብከት ነው፡፡ ዕቅበተ እምነት ላይ በጠንካራዎቹ ኦርቶዶክሳውያን ልጆቹ እየታጋዘ ለሀገር በሚበቃ መልክ የሠራው ሥራ ግሩም ነው፡፡ ሀገረ ስብከቱ ከምእመናን ጋር ለመሥራት ምንጊዜም ዝግጁ ነው፡፡ በዚህ እንደዚህ ያለውን ሀገረ ስብከት እናያለን፤ በዚያ ደግሞ እንደ ምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት ያለ የቤቱን የሚያስወጣ እኩይ ተግባር በማድረግ የተካነ እናያለን፡፡ በዚህ ተማሪዎቹን አቅፎ ደግፎ መብት የሚያስከብር በዚያ ደግሞ ሒዱ ጥፉ አልያችሁ የሚል፡፡ ተማሪዎቹን ብቻ ሳይኾን አሁንማ ምእመኑንም አልያችሁ እያለ ነው አሉ፡፡ ይኸው ስድስት ዓመት ሞላው፡፡ በጎቹን አሳልፎ ለመስጠት የሚተጋ እንዲሀም ያለ እረኛ አናውቅ፡፡
ኹለት ዓይነት ሀገረ ስብከት ይዛ ቤተ ክርስቲያን እስከማዕዜኑ?
ጊዜው ልፍስፍስ ኦርቶዶክስ የሚንጋጋበት አይደለም፡፡ ቆራጥነት ከብስለት ጋር ያስፈልጋል፡፡ መብትን መጠየቅ ግድ ኾኗል፡፡ በብዙ ነገር ወደኋላ ስለቀረን የቀደሙን ሊጫኑን የብረት ክንዳቸውን እያሳረፉብን ናቸው፡፡ ያለንበትን ሁኔታ መካድ ከየትኛውም አደጋ አያድነንም፡፡ የአደጋውን ህላዌ ስንቀበለው መፍትሔው ላይ መሥራት ይቻለናል፡፡ ብዙ ነን፣ ምን እንኾናለን፣ በጸሎት ነው ብሎ ነገር ከኦርቶዶክሳውያን የሚሰሙ መኾን የለባቸውም፡፡ ሥራ የሌለው ጸሎት በሌሎች እንጅ በኦርቶዶክስ ዘንድ የለም፡፡ ስለዚህ ጸሎት ብቻ ሳይኾን እየጸለዩ መጋደል ነው፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ እየጸለየ ተጋደለ እንጅ “ጸሎት ብቻ” ብሎ አልቆመም፡፡ ሰባቱ አክሊላት የተጋድሎ ውጤቶች ናቸው፡፡
ሐዋሳዎች ተጋደሉ፣ እግዚአብሔር መልስ ሰጣቸው፡፡ ትእምርትነታቸው (ምልክትነታቸው) በዚህ ነው፡፡ ዩኒቨርሲቲዎቻችን ኦርቶዶክስን ማሰሪያ ወኅኒዎች እንደኾኑ የተፈረደውን እኩይ ፍርድ ሰባብረውታል፡፡ በተለይም እንደ ጅማ ዩኒቨርሲቲ ያሉት ከእንግዲህ በቸልታ እንደማይታዩ ማሳያዎቻችን ናችሁ፡፡ ከእንግዲህ መብቱን የማይጠይቅ፣ በቤተ ክርስቲያን የሚታይን አጓጉል አሠራር ችላ የሚል፣ ነገረ ሐራጥቃን ወደ ጎን የሚያደርግ፣ ዘረኛን የሚታገስ፣ ፖለቲካን በዐውደ ምሕረት በሉት በቤተ ክህነት የሚቀላውጥን፣ ነቢይ ነኝ አጠምቃለሁ ራእይ ዐይቻለሁ ባይ ጆቢራዎችን ዝም ማለት ማብቃት አለበት፡፡ ቤተ ክርስቲያንን ማስከበር እግዚአብሔራዊነት ነው፡፡
እንደ ኤፌሶኑ አለቃ እንኾን ዘንድ ያስፈልጋል፡- “ክፉዎችንም ልትታገስ እንዳትችል፥ እንዲሁም ሳይኾኑ፦ ሐዋርያት ነን የሚሉቱን መርምረህ ሐሰተኞች ኾነው እንዳገኘሃቸው ዐውቃለሁ” ተብሏልና፡፡ ራእይ ፪፥፪። አሁን ሐራጥቃውያንን ድል ለመንሣት መዘጋጀት አለብን፡፡ ሁል ጊዜ “ወንጌል” እየጠቀሱ ይመጣሉ ብለን መሞኘት ሳይኖርብን እንዲህ እንደ ሐዋሳ እንመክት፡፡ እና ስንነሣ እግዚአብሔር ያሰምረዋል፡፡ ነህምያ እንዳለው “እኛ እንነሣ ሰማይም አምላክ ያከናውንልንል፡፡” ቁጭ ብሎ ጽድቅ ድሮም ዘንድሮም የለም፡፡
ክፉ ሠሪዎችን ችላ ማለት ደግሞ በአንጻሩ ያስወቅሳል፡፡ የትያጥሮኑ አለቃ የተወቀሰው በዚህ ነው፡- “ነቢይ ነኝ የምትለውን ባሪያዎቼንም እንዲሴስኑና ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉ የምታስተምረውንና የምታስተውን ያችን ሴት ኤልዛቤልን ስለምትተዋት የምነቅፍብህ ነገር አለኝ” እንዲል፡፡ ራእይ ፪፥፳። ከሴት እስከ ወንዱ ነቢይ ነኝ የማይል የለም፡፡ ይህ ክፉ መንፈስ በዓለም ላይ ተዘርቷል፡፡ እነዚህን ዝም ማለት ያስነቅፋል፡፡ ከታች ብቻ ሳይኾን ከላይ ጭምር፡፡
አስማተኞች በርከት በርከትከት እያሉ በሚሔዱባት ዓለም መኖራችንን አንካድ፡፡ መኖራቸውን ዐውቀን ግን እንጋደል፡፡ እነርሱን እግዚአብሔር ይጠላቸዋልና፡፡ እግዚአብሔር የጠላውን የሚወድድ ደግሞ ክርስቲያን አይባልም፡፡ “እኔ ደግሞ የምጠላውን የኒቆላውያንን ሥራ ጠልተሃልና” እንዲል፡፡ ራእይ ፪፥፮። ኒቆላውያን አስማተኞች ናቸው፡፡ እዚህም እዚያም ተሰንቅረው ቤተ ክርስቲያንን ሲያውኩ ዝም አይባሉም፡፡
በልዓማውያንንም እንዲሁ እንጋፈጣቸው ዘንድ መጽሐፍ ያስተምረናል፡፡ አለመጋፈጥና እንዳላዩ ኾኖ ማለፍ ደግሞ በቅድመ እግዚአብሔር ያስወቅሳል፡፡ “ዳሩ ግን ለጣዖት የታረደውን እንዲበሉና እንዲሴስኑ በእስራኤል ልጆች ፊት ማሰናከያን ሊያኖርባቸው ባላቅን ያስተማረ የበልዓምን ትምህርት የሚጠብቁ በዚያ ከአንተ ጋር ስላሉ፥ የምነቅፍብህ ጥቂት ነገር አለኝ።” እንዲል፡፡ ራእይ ፪፥፲፬።
በክርስትና ማውገርገር አይቻልም፡፡ ክርስትና መቀላወጥን አይፈቅድም፡፡ ክርስትና እዚህም እዚያም አለሁበት ማለትን ይቃወማል፡፡ ክርስትና አቋም አለው፡፡ ያውም የማይገለባበጥ፡፡ በጊዜውም አለጊዜውም ጽና እንዲል መጽሐፈ ኢያሱ፡፡ “በራድ ወይም ትኩስ እንዳይደለህ ሥራህን ዐውቃለሁ። በራድ ወይም ትኩስ ብትኾንስ መልካም በኾነ ነበር። እንዲሁ ለብ ስላልህ በራድም ወይም ትኩስ ስላልኾንህ ከአፌ ልተፋህ ነው።” ያለውም ያንኑ ያጠይቃል፡፡ ፫፥፲፭-፲፮። በተለይም የደረስንበት ጊዜ ለብታን ይደግፋልና ከመተፋት ለመትረፍ ወይ በራድ ወይ ትኩስ መኾን ይገባል፡፡ ለብታ ከኹለቱም አለሁበት ለማለት ትመቻለች፡፡ ወላዋይነት ናት፡፡ እርሷ ፈጽማ አትወደድም፡፡
በራድነት የያዘውን አያበላሽም፣ እንደነበረ ይጠብቃል፡፡ ለሚረከበውም በነበረበት ሁኔታ ያስረክባል፡፡ በማቀዝቀዣ ውስጥ የገባ ምግብ ራሱን ጠብቆ ሳይበላሽ እስከተፈለገው ጊዜ እንደሚቆይ ማለት ነው፡፡ በራድ የተባሉት ሊቃውንት፣ መምህራን፣ አበው፣ አረጋውያን ነባሩን እምነት ጠብቀው አስጠብቀው ሳይሸራረፍ ለትውልድ ያስረክባሉ፡፡ አያጎድሉም፣ አይጨምሩምም፡፡ ትኩሶቹ ደግሞ ሐዋርያት (መምህራነ ወንጌል)፣ ሰማዕታት፣ መናንያን፣ ባሕታውያን ናቸው፡፡ ይሔዳሉ፣ ይጋደላሉ፡፡ ኑፋቄን፣ ጣዖት አምልኮን፣ ግፍን ይቃወማሉ፣ የጠፋውን ይመልሳሉ፣ ከአጋንንት ጋር ይፋለማሉ፣ ከሥጋቸው ፍላጎት ይታገላሉ፣ ከአላውያን ፈተና ይጋፈጣሉ፡፡ እየሞቱ ያኖራሉ፡፡ እየሔዱ ይመልሳሉ፡፡ ትኩስ ነገር የነካውን እንዲያቃጥል እነዚህም የነፍስ የሥጋ ጸሮችን በተጋድሎ ጽናት ያጠፋሉ፡፡
በእነዚህ መካካል ገብቶ መኻል ሰፋሪ መኾን መልክ ያሳጣል፡፡ ለብ ያለ ውኃ ሲጠጡት የረጋውን ምግብ ያውካል፣ ይረብሻል ብሎም ያስመልሳል፡፡ እንደዚሁም ሁሉ ለብ ያሉ ሰዎች የያዙትን ያስለቅቃሉ፡፡ ከዓለምም ከቤተ ክርስቲያንም ይቀላውጣሉ፡፡ መረጋጋትን ያጠፋሉ፡፡ ለብ ያለውን እግዚአብሔርም ልተፋህ ነው እንዳለው እኛም ልንተፋቸው ይገባል፡፡ ከእግዚአብሔር በላይ ቸር መኾን አይቻልም፡፡ እርሱ የሚተፋውን እኛ እናዝንለት ዘንድ አንጀት የለንም፡፡ አንጀት አለን ካልን እግዚአብሔርን ክደነዋል ማለት ነው፡፡ የእግዚአብሔርን የርኅራኄ ወሰን ስናውቅ መቼ እንደሚተፋ ይገባናል፡፡ እርሱ ለሚተፋው እናዝናለን የምንል ከኾነ ከእርሱ የርኅራኄ አድማስ (ወሰን) የሚልቅ ርኅሩኅነት አለን እያልን ነው፡፡ ይህ ደግሞ ክሕደት ይኾናል፡፡
እንደ ይሁዳ ለማያሳዝነው እያዘንን ከኾነ ሌብነታችን ይጋለጣል፡፡ ስለዚህ ለብታችንን አውልቀን ጥለን ወደ በራድነት ወይም ወደ ትኩስነት እንግባ! ቤተ ክርስቲን ላይ ምንም ሲቀልድባት የሩቅ ተመልካች ከመኾን እንውጣ፡፡ የሰውን መብት እናክብር የእኛንም እናስጠብቅ፡፡ ያለበለዚያ በገዛ ዳቦዬ ልብ ልቡን አጣሁት እንዲሉ በገዛ ሀገሯ ቤተ ክርስቲያንን መጻተኛ እናደርጋታለን፡፡ ያቃተን ካለንም ቦታ እንልቀቅ፡፡ ለትንታጎቹ የቤተ ክርስቲያን ልጆች መንገድ እንክፈት፡፡ እነ እገሌ አሉ እየተባልን ሳንኖር ቦታ አናጣብብ፡፡
ሐዋሳዎች አሁን የሚያስፈልጉን ክርስቲያኖች ምሳሌዎች ናቸው፡፡ ሰዓሊተ ምሕረቶችም እንደዚሁ፡፡ ዑራኤሎች እንዳደረጉት እያደረጉ ነውና፡፡ ምሥራቅ ጎጃሞች ተስፋ እትቁረጡ፡፡ ክፉውን ሳታስወጡ እንቅልፍ የለም፡፡ የምንታገሰውን ከማንታገሰው መለየት የአሁኑ ፈተናችን ነው፡፡ ሰዎችን እንጅ ሰይጣንን አንታገሰውም፡፡ ሰይጣንን በመታገስ የተገኘ አክሊል የለም፡፡ ፈተናውን በትዕግስት መጋደል ማለት ራሱን ሰይጣንን መታገስ ማለት አይደለም፡፡ ትዕግስት የሰይጣንን ልብ ራስ መውጊያ ጦር የሚኾንበት የፈተና ዓይነት አለ፡፡ ለዚያ ተነገረ እንጅ ሰይጣንንማ መቸም መች አንታገሰውም፡፡
ኦርቶዶክሳውያን እንደ ትዕማር አንገት ደፍተን የምንኖርበት ጊዜ ይበቃል፡፡ ከአጥቢያ ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ወዲህም ደግሞ በቤተ መንግሥትና ጥጋ ጥጎቹ ተጠልለው የሚመጡብንን ፈተና እንጋፈጥ ዘንድ እንወቅበት፡፡ እንደ ንስር ዓይኖቻችን ጥቃቅን የሚመስሉትን ሁሉ ለመመርመር የተገለጡ ይኹኑ፡፡ ባቄላዋ በማደሯ ወዳለመቆርጠም ከመለወጧ በፊት መከካት አለባት፡፡ ብዙ የብዙ ብዙ ጥጋ ጥጉን እና ሥር ሥሩን የሚሔዱ የወዳጅ ጠላቶች በዝተውባታልና በንቃት እንኑር፡፡ ተኝቶ ከመማረክ ነቅቶ መጠበቅን እናስቀድም፡፡ ሐዋሳዎችን እንምሰላቸው፡፡