(ቢቢኤን) ኢትዮጵያ እና ሱዳን የአባይን ግድብ ከጥቃት ለመጠበቅ የጋራ ወታደራዊ ጦር ለማቋቋም መስማማታቸው ተገለጸ፡፡ የሁለቱ ሀገራት ወታደራዊ አዛዦች ያደረጉትን ውይይት ዋቢ ያደረገው የሚድል ኢስት ሞኒተር ዘገባ፣ ሱዳን እና ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ ላይ እየተገነባ ያለውን ግድብ ከጥቃት ለመከላከል ጨምሮ በሌሎች ወታደራዊ ጉዳዮች ላይ ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ጠቁሟል፡፡ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሳሞራ የኑስ እና የሱዳን አቻቸው ከማል አብዱል ማሩፍ አል ማሂ ባለፈው አርብ አዲስ አበባ ላይ ተገናኝተው በወታደራዊ እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ የተለያዩ ወታደራዊ ተልዕኮዎችን ለመወጣት የጋራ ጦር ለማቋቋም እንደተስማሙም ያስረዳል፡፡ ሁለቱ ሀገራት የሚያቋቁሙት የጋራ ጦር፣ ከሱዳን ድንበር 20 ኪሎ ሜትሮች ብቻ የሚርቀውን የአባይ ግድብ ከጥቃት መከላከልን ጨምሮ በሌሎች ድንበር ዘለል እንቅስቃሴዎች ላይ ይሰማራል ተብሏል፡፡

 

የጋራ ጦሩ ግድቡን ከጥቃት ከመከላከል ጨምሮ ድንበር ዘለል በሆኑ የወንጀል ድርጊቶችን፣ በህገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን፣ በጦር መሳሪያ ንግድን እና በሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ተልዕኮውን እንደሚወጣ በሁለቱ ሀገራት መካከል የተደረሰው ስምምነት ያስረዳል፡፡ ኢትዮጵያ እና ሱዳን በወታደራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመንቀሳቀስ ስምምነት ላይ የደረሱት፣ ግብጽ በአባይ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር አለመግባባት ውስጥ በገባችበት በዚህ ሰዓት ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ግድቡን ከጥቃት ለመከላከል የሚያቋቁሙት የጋራ ወታደራዊ ጦር፣ በግብጽ ዘንድ ትልቅ የፖለቲካ ትርጉም እንደሚፈጥር የፖለቲካ ተንታኞች ይገልጻሉ፡፡ የግብጽ መንግስት ግድቡን በተመለከተ በተደጋጋሚ የሚያቀርባቸው የመደራደሪያ ነጥቦች፤ በኢትዮጵያ ዘንድ ውድቅ ሲደረጉበት መቆየታቸው ይታወቃል፡፡

ሱዳን ግድቡን በተመለከተ የራሷ አቋም ቢኖራትም፤ የግብጽን ያህል ግትር የሚባል ደረጃ ላይ አልደረሰችም ይላሉ ተንታኞቹ፡፡ ሱዳን ግድቡን በተመለከተ የያዘችው አቋም ለዘብተኛ የሚባል እንደሆነ የሚናገሩት ተንታኞቹ፤ አንዳንዴም ኢትዮጵያ ከያዘችው አቋም ጋር የሚጣጣም እንደሆነም ተንታኞቹ ያክላሉ፡፡ ሱዳን ግድቡን ከጥቃት ለመከላከል የጋራ ወታደራዊ ኃይል ለማቋቋም ከኢትዮጵያ ጋር መስማማቷ፤ ሱዳን ግድቡ በውሃ ድርሻዋ እና በሌሎች ነገሮች ላይ ተፅዕኖ እንደማያሳድር ያመላክታል ሲሉም ተንታኞቹ ያስረዳሉ፡፡ ሱዳን እና ኢትዮጵያ የጋራ ወታደራዊ ጦር ለማቋቋም መስማማታቸውን ተከትሎ፣ ይህ ዜና እስከተጠናቀረበት ሰዓት ድረስ ግብጽ የሰጠችው ምላሽ የለም፡፡